ዳታን በመቆጠብ ጽሑፍ ብቻ ለማንበብ

እስራኤል በኢራን የፈጸመችው ጥቃት

13 ሰኔ 2025

እስራኤል የኢራን የኒውክሌር ፕሮግራም ማዕከል ላይ ያነጣጠረ ነው ያለችውን ጥቃት ሐሙስ ለአርብ አጥቢያ በመላው ኢራን በከፍተኛ ሁኔታ ፈጽማለች።

በዚህ ጥቃት የአገሪቱ ጦር ኃይሎች አንደኛው ኃያል ቅርንጫፍ የሆነውን የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ ዋና አዛዥ ሆሴይን ሳላሚ፣ ከፍተኛ ወታደራዊ ባለስልጣናት እንዲሁም ስድስት የኒውክሌር ሳይንቲስቶች መገደላቸውን የኢራን መንግሥታዊ ሚዲያ ዘግቧል።

ህጻናትን ጨምሮ ሰላማዊ ዜጎችም በዚህ የእስራኤል ጥቃት መገደላቸው ተገልጿል።

ቢቢሲ እነዚህን ዘገባዎች በገለልተኝነት ማረጋገጥ አልቻለም።

ኢራን በምላሹ 100 ያህል ድሮኖችን ወደ እስራኤል ማስወንጨፏን እና ሁሉም መክሸፋቸውን የእስራኤል ሚዲያዎች ዘግበዋል።

በእስራኤል ስጋት አይሎ የአስቸኳይ ጊዜ ታውጇል።

አሜሪካ በዚህ የእስራኤል ጥቃት ምንም አይነት ተሳትፎ የለኝም ብላለች። የኢራን ዋነኛ የኒውክሌር ማበልጸጊያ ተቋምን ጨምሮ በርካታ ማዕከላት ጥቃት ተፈጽሞባቸዋል።

ጥቃቶቹ መቼ እና የት ተፈጸሙ?

በኢራን መዲና ቴህራን ፍንዳታዎች የተሰሙት በአገሬው ሰዓት አቆጣጠር ሐሙስ ለአርብ አጥቢያ ሌሊት 9፡30 ገደማ ነው።

የኢራን መንግሥታዊ ቴሌቪዥን በቴህራን የሚገኙ የመኖሪያ ስፍራዎች ጥቃት እንደደረሰባቸው እና ከዋና ከተማዋ በስተሰሜን ምስራቅ ፍንዳታዎች መሰማታቸውን ዘግበዋል።

በእስራኤል ነዋሪዎች በተመሳሳይ ሰዓት የአደጋ ጊዜ የስልክ ማስጠንቂያዎች ደርሷቸዋል።

የእስራኤል ጦር በኢራን የተለያዩ አካባቢዎች የኒውክሌር ይዞታዎችን ጨምሮ በርካታ ወታደራዊ ኢላማዎች ላይ ጥቃት መፈጸሙን አስታውቋል።

የመጀመሪያው ጥቃት ከተፈጸመ ከሰዓታት በኋላ ከዋና ከተማዋ በስተደቡብ 225 ኪሎሜትር ርቀት ላይ በሚገኛው ናታንዝ የኒውክሌር ጣቢያ ፍንዳታ መሰማቱን የኢራን መንግሥታዊ ሚዲያ ዘግቧል።

የአለም አቀፉ የኒውክሌር ተቆጣጣሪ፣ አለም አቀፍ የአቶሚክ ኤነርጂ ኤጀንሲ (IAEA) የናታንዝ የኒውክሌር ማዕከል ጥቃት እንደተፈጸመበት አረጋግጧል።

ኤጀንሲው ከጥቃቱ ጋር ተያይዞ በናታንዝ ጣቢያ የጨረር መጠን እንዳልጨመረ የኢራን ባለስልጣናት እንዳሳወቁት ገልጿል።

የኤጀንሲው ኃላፊ ራፋኤል ግሮሲ የኒውክሌር ተቋማት “በፍጹም ጥቃት ሊፈጸምባቸው አይገባም። እንደነዚህ አይነት ጥቃቶች በኒውክሌር ደህንነት፣ በጸጥታ እንዲሁም በዓለም አቀፍ ሰላም እና ደህንነት ላይ ከፍተኛ አንድምታ አላቸው” ብለዋል።

ኃላፊው ለቦርድ አባላት በሰጡት መግለጫ “የኒውክሌር ተቋማትን ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥል ማንኛውም ወታደራዊ እርምጃ በኢራን፣ በቀጣናው እና በሌሎች አካባቢዎች ከባድ መዘዝን የሚያስከትል ነው” ብለዋል።

አክለውም ነገሮች የበለጠ እንዳይባባሱ ሁለቱም ወገኖች እንዲቆጠቡ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

በቴህራን የተፈጸመው ጥቃት

እስራኤል ጀመርኩት የምትለው ዘመቻ ምንድን ነው?

የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ አገራቸው የጀመረችው ‘ኦፐሬሽን ራይዚንግ ላየን’ [ የሚያንሰራራ አንበሳ ዘመቻ] ሲሉ የጠሩት ጥቃት ኢራን በእስራኤል ላይ የደቀነችውን የህልውና አደጋ ለመቀልበስ ያለመ ነው ብለዋል።

ዘመቻ ሲሉ የጠሩት ይህ በኢራን ላይ የሚፈጸመው ጥቃት ለቀናት እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

“ካላስቆምናት ኢራን በአጭር ጊዜ ውስጥ የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ማምረት ትችላለች። አንድ ዓመት ሊሆን ይችላል። በጥቂት ወራቶች ወይም ከአንድ ዓመተ ባነሰ ጊዜ ሊሆን ይችላል። ይህ ለእስራኤል ህልውና ግልጽ እና ወቅታዊ አደጋ ነው” ብለዋል።

ኔታንያሁ በተጨማሪም የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ “የኢራንን የኒውክሌር መሳሪያ ፕሮግራም በግልጽ በመጋፈጣቸው” ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

የኢራን ታላቁ መንፈሳዊ መሪ አሊ ኻሜኒ

ኢራን “ሉዓላዊነቷን” ለመከላከል ቃል ገብታለች

ኢራን አርብ ማለዳ ላይ ወደ 100 የሚጠጉ ሰው አልባ አውሮፕላኖችን ወደ እስራኤል ልካለች። ሁሉም ድሮኖች መክሸፋቸውን የእስራኤል ጦር አስታውቋል።

የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የኢራን ኃይሎች “የኢራንን ሉዓላዊነት በሙሉ ጥንካሬ እና ተገቢ ነው ብለው ባሰቡት መንገድ ከመከላከል ወደ ኋላ አይሉም” ብሏል።

ሚኒስቴሩ ባወጣው መግለጫ የእስራኤልን ተግባር “ወረራ” ሲል የፈረጀው ሲሆን “የአሜሪካ መንግሥት የዚህ አገዛዝ ዋነኛ ጠባቂ እንደመሆኑ መጠን ኃላፊነቱን ይወስዳል” ብሏል።

የኢራን ታላቁ መንፈሳዊ መሪ አሊ ኻሜኒ ጥቃቱን ተከትሎ እስራኤል “መራራ እና የከፋ ህመም ” እጣ እንደሚገጥማት አስጠንቅቀዋል።

“በአምላክ ፈቃድ እንዲሁም በእስላሚክ ሪፐብሊክ ጦር ኃይሎች ኃያል እጅ እስራኤል ቅጣት ሳይፈጸምባት አይቀርም” ብለዋል።

የአሜሪካ እና የሌሎች አገራት ምላሽ

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሩቢዮ አገራቸው በጥቃቱ እንዳልተሳተፈች እና ምንም አይነት እርዳታ ለእስራኤል እንዳልሰጠች ተናግረዋል።

የአሜሪካ ዋነኛ ትኩረት በቀጣናው የሚገኙ የአሜሪካ ኃይሎችን መጠበቅ ነው ብለዋል።

የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በበኩላቸው ጥቃቶቹ እንደሚፈጸሙ እንደሚያውቁ፤ ነገር ግን አገራቸው እንዳልተሳተፈች ለፎክስ ኒውስ ገልጸዋል።

በኢራን እና አሜሪካ ያለውን የኒውክሌር ድርድር ስታሸማግል የነበረችው ኦማን “ለዚህ መባባስ እና መዘዝ” እስራኤልን ተጠያቂ አድርጋለች።

የዩናይትድ ኪንግደሙ ጠቅላይ ሚኒስትር ኬይር ስታርመር ጥቃቶቹ ” አሳሳቢ” እንደሆኑ ገልጸው ነገሮች እንዲረግቡም ጥሪ አድርገዋል።

ጃፓን፣ ቱርክ፣ ኢንዶኔዥያ እና ሳዑዲ አረቢያ ጥቃቱን አውግዘዋል። ቻይና በበኩሏ ጥቃቶቹ ሊያስከትሉ የሚችሏቸው አስከፊ መዘዞች ስጋት ላይ እንደጣላት ገልጻለች።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ እስራኤል በኢራን ነውክሌር ይዞታዎች ላይ ያደረሰችውን ጥቃት አውግዘው ሁለቱም ወገኖች ቀጠናው ወደ ከፋ ጦርነት እንዳይገባ እንዲቆጠቡ ጥሪ አድርገዋል።

እስራኤል በፈጸመችው ጥቃት የገደለቻቸው የኢራን አብዮታዊ ዘብ ኃላፊ ሆሴይን ሳላሚ እና የአገሪቱ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም መሐመድ ባግሄሪ
የምስሉ መግለጫ,እስራኤል በፈጸመችው ጥቃት የገደለቻቸው የኢራን አብዮታዊ ዘብ ኃላፊ ሆሴይን ሳላሚ እና የአገሪቱ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም መሐመድ ባግሄሪ

እስራኤል በፈጸመችው ጥቃት እነማን ተገደሉ?

የኢራን አብዮታዊ ዘብ አዛዥ ሆሴይን ሳላሚ ምናልባትም በዚህ የእስራኤል ጥቃት ከተገደሉ ከፍተኛ አዛዦች መካከል ዋነኛው ሳይሆኑ አይቀሩም ተብሏል።

ሆሴይን የአብዮታዊ ዘብን የተቀላቀሉት የኢራን ኢራቅ ጦርነት መፈንዳቱን ተከትሎ በአውሮፓውያኑ 1980 ነው።

በወታደራዊ ማዕረግ ከፍ እያሉ ሲመጡም በአሜሪካ እና በምዕራባውያን አጋሮቿ ላይ በሚናገሩት ጠንካራ ትርክቶች ዝናን አተረፉ።

በኢራን ኒውክሌር እና ወታደራዊ ፕሮግራሞች ተሳትፏቸው የተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት እና አሜሪካ ከአውሮፓውያኑ 2000 ጀምሮ በኃላፊው ላይ ማዕቀብ ጥለውባቸዋል።

ኢራን 300 ድሮኖች እና ሚሳኤሎችን ያሳተፈ የመጀመሪያውን የቀጥታ ጥቃት በእስራኤል ላይ ስትፈጽም እሳቸው የአብዮታዊ ዘብ ኃላፊ ነበሩ።

ከቅርብ ቀናት ወዲህ ከእስራኤል ጋር ያለው ውጥረት መጋጋሉን ተከትሎ ሆሴይን አገራቸው “ለማንኛውም ሁኔታ፣ ክስተት እና አጋጣሚዎች” ዝግጁ መሆኗን ሐሙስ ዕለት ተናግረው ነበር።

የኢራን ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም መሐመድ ባግሄሪ በዚህ ጥቃት ከተገደሉት መካከል አንዱ ናቸው።

ጠቅላይ ኤታማዦር ሹሙ በአውሮፓውያኑ 1980 አብዮታዊ ዘቡን የተቀላቀሉ ሲሆን በሃገሪቱ ከፍተኛ ወታደራዊ መሪዎች አንዱ ናቸው።

የአገሪቱ የአቶሚክ ኢነርጂ ድርጅት ኃላፊ የነበሩት የኒውክሌር ሳይንቲስቱ ፍሬይዱን አባሲ ሌላኛው በዚህ ጥቃት የተገደሉ ናቸው።

ፍሬይዱን አባሲ ለኢራን የኒውክሌር ማበልጸግ የአንበሳውን ድርሻ እንደተጫወቱ ይነገርላቸዋል።

ሳይንቲስቱ ከዚህ ቀደም በአውሮፓውያኑ 2010 በቴህራን ጎዳና ላይ ከተቃጣባቸው የግድያ ሙከራ ተርፈው ነበር።

ሌላኛው በዚህ ጥቃት የተገደሉት የኒውክሌር ሳይንቲስት እና በቴህራን የሚገኘው የእስላሚክ አዛድ ዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንት መህዲ ቴህራንቺ ናቸው።

እስራኤል በዚህ ጥቃት የገደለቻቸው ስድስት የኒውክሌር ሳይንቲስቶች መሆናቸውን ኢራን ገልጻለች።

የኒውክሌር ሳይንቲስቱ እና በሻሂድ ቡህሽቲ ዩኒቨርስቲ የኒውክሌር ኢንጂነሪንግ ኃላፊ የሆኑት አብዶልሃሚድ ሚኖሸር፣ በዚሁ ዩኒቨርስቲ የኒውክሌር ኢንጂነርግ ፕሮፌሰር የሆኑት አህመድ ረዛ ዞልፋጋሪ እንዲሁም በተመሳሳይ ዩኒቨርስቲ የኒውክሌር ፕሮፌሰር የሆኑት አሚርሆሴን ፈቂ እስራኤል በፈጸመችው ጥቃት የተገደሉ ናቸው።

በተጨማሪም ሞታልቢዛዴህ የተሰኘ የኒውክሌር ሳይንቲስት መገደሉ ተገልጿል።

በተጨማሪም የኢራን ጦር ምክትል አዛዥ እና የካህታም አል አንቢያ የተሰኘው ማዕከላዊ ዋና መስሪያ ቤት ኃላፊ ጎላማሊ ራሺድ ተገድለዋል።

የኢራኑ ታላቁ መሪ አያቶላህ አሊ ኻሜኒ አማካሪ አሊ ኻምካኒ የከፋ ጉዳት እንደደረሰባቸው የኢራን ዘገባዎች አመልክተዋል።

እስራኤል ኢላማ ያደረግኩት ወታደራዊ ይዞታዎችን ነው ብትልም፤ የኢራን መገናኛ ብዙኃን በበኩላቸው በቴህራን የመኖሪያ ቤቶች ጥቃት እንደተፈጸመባቸው እና ከተገደሉትም መካከል ህጻናትን ጨምሮ ሰላማዊ ዜጎች መገደላቸውን ዘግቧል።

የኢራን የኒውክሌር መርሃ ግብር ምንድን ነው?

ኢራን ለረጅም ጊዜ የኒውክሌር መርሃ ግብሯ ለሲቪል ዓላማ ብቻ እንደምትገለገልበት ስትገልጽ ቆይታለች። በአገሪቱ ዙሪያ የኒውክሌር ማዕከላት ያሏት ሲሆን የተወሰኑት እስራኤል ጥቃት የፈጸመችባቸው ናቸው።

አለም አቀፍ የአቶሚክ ኤነርጂ ኤጀንሲ (IAEA)ን ጨምሮ በርካታ አገራት የኢራን የኒውክሌር ፕሮግራም ለሲቪል ዓላማ ብቻ ስለመዋሉ እርግጠኛ አይደሉም።

በዚህ ሳምንት የኤጀንሲው የገዥዎች ቦርድ ኢራን የተጣለባትን “ከማስፋፋት የመቆጠብ” ግዴታዋን ከ20 ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥሳለች ብሏል።

ቦርዱ ኢራን ከዚህ ቀደም ያልገለጸቻቸው የኒውክሌር ቁሶች እንዲሁም የበለጸገ የዩራኒየም ክምችትን በተመለከተ ምላሽ መስጠት አለመቻሏን ጠቅሶ ጥሰት ያላቸውን አስቀምጧል

ቀደም ሲል ኤጀንሲው ያወጣው ሪፖርት ኢራን ዩራኒየምን 60 በመቶ በጠራ መልኩ ማበልጸጓን ነው፤ ይህም መሳሪያ ማምረት የሚያስችል መሆኑን እና ዘጠኝ የኒውሌር ቦምቦች ለመስራት በቂ ነው ብሏል።