ዳታን በመቆጠብ ጽሑፍ ብቻ ለማንበብ

ተኩስ ከተከፈተበት አካባቢ የሚሸሹ ሰዎች

ታትሟልከ 8 ሰአት በፊት

የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

ቅዳሜ ምሽት በዋይት ሐውስ አቅራቢያ የደህንነት አባላት ላይ ተኩስ የከፈተ ግለሰብ መገደሉን ባለሥልጣናት አስታወቁ።

በአሜሪካ የቢቢሲ የሚዲያ አጋር የሆነው ሲቢኤስ ተጠርጣሪው የ21 ዓመት ወጣት መሆኑን እና ናስር ቤስት እንደሚባል ገልጾ፤ የአእምሮ ጤና ችግር እንዳለበት እንዲሁም በደህንነት አባላት የሚታወቅ መሆኑን ዘግቧል።

ዶናልድ ትራምፕ በትሩዝ ሶሻል ገጻቸው ላይ የደህንነት አባላት “ፈጣን እና ሙያዊ እርምጃ” በመውሰዳቸው አመስግነዋል። አክለውም ተጠርጣሪው “ከዚህ ቀድምም የአመጽ ታሪክ እንደነበረው እና ምናልባት ወሳኝ በሆኑ ብሔራዊ ትዕምርቶች ፍቅር ወድቆ ይሆናል” ብለዋል።

ተጠርጣሪው ተኩስ የከፈተው በጋዜጠኞች የእራት ግብዣ ላይ ተኩስ ከተከፈተ ከአንድ ወር በኋላ ነው።

ቅዳሜ ዕለት የነበረው ተኩስ ላይ ምርመራ እየተደረገ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን በዋይት ሐውስ አቅራቢያ የሚገኙ መንገዶች ዝግ ተደርገዋል።

ግለሰቡ ቅዳሜ ምሽት 12 ሰዓት ላይ በዋይት ሐውስ 17ኛ ጎዳና እና ፔንሴልቫኒያ መንገድ ጠመንጃውን ከቦርሳው በማውታት “ተኩስ ጀመረ” ሲሉ ባለሥልጣናት ተናግረዋል።

የደህንነት አባላት ወዲያውኑ ተኩስ በመክፈት ምላሽ የሰጡ ሲሆን ግለሰቡ ከተመታ በኋላ ወደ ሆስፒታል ቢወሰድም መሞቱ ተረጋግጧል።

በተኩስ ልውውጡ መንገደኛ የተጎዳ ሲሆን ስለ ሁኔታው የደህንነት መሥሪያ ቤቱ ዝርዝር መረጃ አልሰጠም። በጥቃቱ የተጎዳ የፖሊስ ባልደረባ እንደሌለ ግን አስታውቋል።

ተጠርጣሪው ግለሰብ ተኩስ በከፈተበት ወቅት ትራምፕ በዋይት ሐውስ የነበሩ ሲሆን የደህንነት መስሪያ ቤቱ “ምንም የተጎዳ አባል ወይንም የተስተጓጎለ ሥራ የለም” ብሏል።

ሲቢኤስ እና ሌሎች የአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን ተጠርጣሪው ናስር ቤስት እንደሚባል ዘግበዋል።

ግለሰቡ በደህንነት መሥሪያ ቤቱ እንደሁም በፖሊስ አበላት የሚታወቅ መሆኑንም ሲቢኤስ የሕግ አስከባሪ አካላትን ጠቅሶ ዘግቧል።

እየተደረገ ያለውን ምርመራ የሚያውቁ አንድ ግለሰብ ቤስት ባለፈው ዓመት ሐምሌ ወር ላይ ወደ ዋይት ሐውስ ለመግባት ሙከራ አድርጎ እንደነበር ገልጸው፣ በደህንነት አባላት ቁጥጥር ስር ውሎ ወደ አእምሮ ጤና ሕክምና መስጫ ተቋም ተልኳል ብለዋል።

ግለሰቡ ላለፉት አስራ ስምንት ወራት በዋሺንግተን ዲሲ ይኖር እንደነበርም ጨምረው ገልጸዋል።

የጸጥታ አባላት ተኩስ ከተከፈተ በኋላ በአካባቢው ተሰማርተወል

ትራምፕ በትሩዝ ሶሻል ገጻቸው ላይ “ዛሬ ማምሻውን በዋይት ሐውስ አቅራቢያ ተኩስ በከፈተው ግለሰብ ላይ ለተወሰደው ፈጣን እና ሙያዊ እርምጃ የታላቁ የደህንነት አባላቶቻችን እና የሕግ አስከባሪዎቻችን አመሰግናለሁ” ብለዋል።

ትራምፕ ተጠርጣሪው ተኩስ የከፈተው የዋይት ሐውስ ዘጋቢዎች እራት ግብዣ ላይ ተኩስ ከተከፈተ ከአንድ ወር በኋላ መሆኑን አስታውሰው ለወደፊት የአሜሪካ ፕሬዚዳንቶች በደህንነት ዙሪያ ጠንካራ እርምጃ መውሰድ እንዳለባቸው የሚያስታውስ መሆኑን ተናግረዋል።