ዳታን በመቆጠብ ጽሑፍ ብቻ ለማንበብ

የኮንጎ ጤና ባለሙያ የአንዲት ሴትን ሙቀት እየለካ

ታትሟልከ 9 ሰአት በፊት

የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የተከሰተው ኢቦላ ኢትዮጵያን ጨምሮ ወደ አስር የአፍሪካ አገራት ሊስፋፋ ይችላል የሚል “ስጋት” መኖሩን የአፍሪካ በሽታ መቆጣጠርያ እና መከላከያ ማዕከል (አፍሪካ ሲዲሲ) አስጠነቀቀ።

የአፍሪካ ሲዲሲ ኃላፊ ዣን ካሴያ ቅዳሜ ዕለት በሰጡት መግለጫ “ስጋት ላይ የሆኑ አስር አገራት አሉን” በማለት ኢትዮጵያ፣ ሩዋንዳ፣ ኬንያ፣ ታንዛኒያ፣ አንጎላ፣ ብሩንዲ፣ ማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ፣ ኮንጎ ሪፐብሊክ፣ ደቡብ ሱዳን እና ዛምቢያ ቫይረሱ ይሰረጭባቸዋል ተብለው ከተሰጉት አገራት ውስጥ መሆናቸውን ዘርዝረዋል።

ኃላፊው በመግለጫቸው አሁን የተከሰተው የኢቦላ ቫይረስ ስርጭት ከአስር ዓመት በፊት በምዕራብ አፍሪካ ከታየው በጣም ግዙፉ ነው ብለዋል።

ካሴያ በኢቦላ ወረርሽኝ ላይ በኦንላይን በሰጡት መግለጫ ወቅት ከኢትዮጵያ ውጭ የዘረዘሯቸው አገራት በአጠቃላይ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች የተገኘባቸው የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ወይንም ኡጋንዳ ጎረቤቶች ናቸው።

የአፍሪካ ሲዲሲ ኃላፊ በካምፓላ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ እስካሁን ድረስ 200 ያህል በቫይረሱ ተይዘው መሞታቸው የተጠረጠሩ መሆኑን ገልጸው በኮንጎ የተከሰተው የኢቦላ የቫይረሱ ስርጭት ሰፊ ነው ብለዋል።

ቫይረሱ ከዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ባሻገር እንዲሁም በቀጣናው አገራት ሊስፋፋ እንደሚችል አስጠንቅቀዋል።

የዓለም የጤና ድርጅት በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የተከሰተው የኢቦላ ወረርሽኝ በማኅበረሰብ ጤና ላይ የፈጠረውን ስጋት ደረጃ ከነበረበት “ከፍተኛ” ወደ “እጅግ ከፍተኛ” ከፍ ያደረገው አርብ ዕለት ነው።

አፍሪካ ሲዲሲ እና የዓለም ጤና ድርጅት የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት የሚደረገውን ዘመቻ ለማገዝ ከ314 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገንዘብ እንደሚያስፍለግ አስታውቀዋል።

አብዛኛው ገንዘብ በኮንጎ እና ኡጋንዳ ለሚሰጠው ሕክምና፣ ቅኝት እና መከላከል የሚውል ሲሆን 54 ሚሊዮን ዶላሩ ስጋት ላለባቸው አገራት እንደሚከፋፈል ተገልጿል።

የሚገኘው ገንዘብ አገራት ብሔራዊ በሽታውን የመከላከል እና የመቆጣጠር ስርዓትን እንዲዘረጉ፣ በቀጣናው ያሉ አገራት ድንበር ተሻጋሪ ትብብርን እንዲያጠናክሩ፣ በቡንዲብግዩ ዝርያ ክትባት ላይ የሚደረገውን ምርምር ለማፋጠን፣ ተጨማሪ ባለሙያዎችን ለማሰማራት፣ በሽታው ከሰው ወደ ሰው የመተላላፍ መጠኑ ሳይጨምር የአደጋ ዝግጅት በበቂ ለማድረግ ይውላል ተብሏል።

በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ኢቱሪ ግዛት ግንቦት 7 2018 ዓ.ም. ኢቦላ መከሰቱ ከታወቀ ወዲህ ቁጥሩ በከፍተኛ ፍጥነት እየጨመረ ነው።

በሽታው በሰሜናዊ እና ደብባዊ ኪቪ አካባቢዎች ተስፋፍቷል።

እስካሁን ድረስ 750 በቫይረሱ እንደተያዙ የተጠረጠሩ ሰዎች የተገኙ ሲሆን 177 ደግሞ በዚሁ በሽታ እንደሞቱ እንደሚገመት የዓለም ጤና ድርጅት ይፋ አድርጓል።

በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ብቻ ቢያንስ 82 ሰዎች በኢቦላ ተይዘው መሞታቸው ተረጋግጧል።

ቅዳሜ ዕለት በኡጋንዳ ሦስት አዲስ ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው የታወቀ ሲሆን ይህም በሽታው ወደ አገሪቱ መግባቱ ከተለየ ወዲህ የተያዙ ሰዎችን ቁጥርን አምስት እንደሚያደርሰው የአገሪቱ ጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።

የኮንጎ ባለሥልጣናት ቫይረሱ በቅድሚያ በተከሰተበት ኢቱሪ ወረርሽኙን ለመከላከል ስፖርትን ጨምሮ ማንኛውንም ማኅበራዊ እንቅስቃሴዎችን አግደዋል።

ኢቱሪን የሚያስተዳድሩት ጄነራል ጆኒ ሉቦያ ባወጡት መግለጫ በቡኒያ፣ ራዋምፓራ፣ ሙንግዋሉ እና ኒያኩንዴ ከ50 ሰዎች በላይ ሆኖ መሰብሰብ መከልከሉን በመግለጫቸው ላይ ተናግረዋል።

የዓለም ጤና ድርጅት የስጋት ደረጃውን “በጣም ከፍተኛ” ወደሚል ከፍ ያደረገ ሲሆን በርካታ የጎረቤት አገራትም ቫይረሱ እንዳይሰራጭ ለማድረግ ከዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የሚመጡ ሰዎችን ከመከልከል ጀምሮ የተለያዩ የመከላከያ እርምጃዎችን እየወሰዱ ነው።