JULY 12, 2017

በየአገሮቹ የተከሰቱት ቀውሶች ከኢትዮጵያ የባሱ ናቸው ተብሏል

ሐምሌ 3 ቀን 2009 .. በተካሔደ የቴሌፎን ኮንፈረንስ ይፋ እንደተደረገው ከሆነ፣ አሜሪካ ለእነዚህ አገሮች ቅድሚያ በመስጠት ከሚገኙበት አስከፊ የሰብዓዊ ቀውስና የእርስ በርስ ግጭት እንዲወጡ ተብሎ የተመደበ ተጨማሪ ፈንድ ነው፡፡ ዓለም ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ ያላየችውን አሰቃቂ የሰብዓዊ ቀውስ እያስተናገደች እንደምትገኝ የገለጹት፣ በአሜሪካ የዓለም አቀፍ የልማት ቢሮ ለዴሞክራሲ፣ ለግጭትና ለሰብዓዊ ጉዳዮች ዕርዳታ ቢሮ ተጠባባቂ ምክትል አስተዳዳሪ የሆኑት ሮበርት ጀንኪንስ ናቸው፡፡

ምክትል አስተዳዳሪ ጀንኪንስ በቴሌ ኮንፈረንሱ ወቅት እንደገለጹት፣ ለአገሮቹ የተመደበው ገንዘብ እ... 2017 ለተያዘው የድጋፍ መጠን ተጨማሪ በመሆኑ ለአራቱ አገሮች የሚከፋፈለውን የገንዘብ መጠን በጠቅላላው 1.8 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያደርሰው ታውቋል፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎን ከ639 ሚሊዮን ዶላር ውስጥ ለደቡብ ሱዳን የሚሰጠው የገንዘብ መጠን ከ190 ሚሊዮን ዶላር እንደሆነና በ2017 ለአገሪቱ የሚሰጣት የዕርዳታ መጠን በጠቅላላው 650 ሚሊዮን ዶላር እንደሆነም ጀንኪንስ ገልጸዋል፡፡

በአንፃሩ በኢትዮጵያ ለምግብ እጥረት የተጋለጡና ተጨማሪ የአስቸኳይ ዕለት ደራሽ ዕርዳታ ለ7.8 ሚሊዮን ሕዝቦች እንደሚያስፈልግ ያስታወሱት ምክትል አስተዳዳሪው፣ የአሜሪካ መንግሥት በዚህ ዓመት ብቻ የ225 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ማደረጉን አብራርተዋል፡፡ ጀንኪንስ ይህን ያብራሩት ኢትዮጵያ ከ639 ሚሊዮን ዶላር የዕርዳታ ገንዘብ ተጠቃሚ መሆን ያልቻለችባቸው ምክንያቶችን እንዲያብራሩ በተጠየቁበት ወቅት ነበር፡፡ ‹‹ኢትዮጵያ የዚህ ዕርዳታ አካል አልሆነችም ማለት ተዘንግታለች ማለት አይደለም፡፡ ሆኖም በኢትዮጵያ ካለው ይልቅ በአራቱ አገሮች ውስጥ የተከሰቱት ቀውሶች እጅግ አሳሳቢ በመሆናቸው ቅድሚያ ስለተሰጣቸው ነው፤›› ብለዋል፡፡

የአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ትብብር ኤጀንሲ (ዩኤስኤኣይዲ) ባጠናቀረው መረጃ መሠረት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ለ7.8 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን የድርቅ ተጎጂዎች ያስፈልጋል ካለው ተጨማሪ 540 ሚሊዮን ዶላር ባሻገር፣ አስከፊ የተመጣጠነ የምግብ ዕጥረት ለታየባቸው ሦስት ሚሊዮን ሰዎች የሚውል የ55 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ያስፈልጋል፡፡ ከዚህም ባሻገር ከደቡብ ሱዳን፣ ከሶማሊያና ከኤርትራ አሁንም ድረስ እየመጡ የሚገኙ ከ800 ሺሕ በላይ ስደተኞች በኢትዮጵያ የተለያዩ መጠለያዎች ይገኛሉ፡፡ ስደተኞቹ በካምፕ ከመኖር ባሻገር ከአገሬው ሕዝብ ጋር ተሰባጥረው የሚኖሩበት፣ የሚማሩበትና ሥራ ሠርተው የሚውሉበት አሠራር ተግባራዊ እየተደረገ ይገኛል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት በአሁኑ ወቅት በድርቅ ለተጎዱትም ሆኑ ባለፈው ከሁለት ዓመት በፊትም በምግብ እጥረት ለተጎዱ 10.2 ሚሊዮን ሰዎች የሚውል ትርጉም ያለው የዕርዳታ ድጋፍ ከውጭ ለማግኘት መቸገሩን በተደጋጋሚ ሲያስታውቅ ቆይቷል፡፡ ከጥቂት ወራት በፊት ለፓርላማው የመንግሥታቸውን ሪፖርት ያቀረቡት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በአፍሪካ ቀንድ፣ በምዕራብ አፍሪካ እንዲሁም በመካከለኛው ምሥራቅ የተከሰቱ ቀውሶች ለኢትዮጵያ ችግሮች ድጋፍ የማግኘት ጥሪዎቿን ምላሽ አልባ እንዳደረጋቸው አስታውቀው እንደነበር ይታወሳል፡፡ፕሬዚዳንት ትራምፕ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላም ለዕርዳታ የሚውል ድጋፍ ላይ ቅናሽ መደረጉ ሲዘገብ ቆይቷል፡፡ ቅናሹ በእጅጉ ከሚመለከታቸው አገሮች መካከል ኢትዮጵያ በግንባር ቀደምትነት መቀመጧም ሲነገር ነበር፡፡

... 2017 ብቻ የ200 ሚሊዮን ዶላር ቅናሽ እንደሚደረግባት መረጃዎች መውጣታቸውን በማስመልከት ሪፖርተር መዘገቡ ይታወሳል፡፡ በአዲስ አበባ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ዘገባውን ያስተባበለው፣ በወቅቱ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት የበጀት ቀመራቸውን ይፋ ባላደረጉበት የወጣ ዘገባ መሆኑን በመጥቀስ፣ በጀቱ ይፋ ሲደረግ የሚታይ ነው በማለት ነበር፡፡አሜሪካ በየዓመቱ ከ60 ቢሊዮን ዶላር ያነሰ የዕርዳታ ድጋፍ ለመላው ዓለም የምትሰጥ ቢሆንም፣ በአንፃሩ ከግማሽ ትሪሊዮን ዶላር በላይ ለወታደራዊ ተልዕኮዎች የምትመድብ በመሆኗ ለሰብዓዊ ድጋፎች የምትሰጠው ድጋፍ እጅግ አነስተኛ መሆኑ እያስተቻት ይገኛል፡፡

ከዚሁ ከ60 ቢሊዮን ዶላሩም ቢሆን በአዲሱ የፕሬዚዳንት ትራምፕ በጀት እስከ 20 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ቅናሽ እንደሚታይ ከወዲሁ እየተነገረ ነው፡፡ ሆኖም በእረፍት ላይ የሚገኘው የአሜሪካ ኮንግረስ ለሰብዓዊ ዕርዳታ የሚመደበው ገንዘብ ላይ የቀረበውን የቅነሳ ዕቅድ በመመልከት ውሳኔ እንዲሰጥበት እየተጠበቀ ይገኛል፡፡ አብዛኛውን የሰብዓዊና የልማት ሥራዎች የሚያከናውነው ዩኤስኤኣይዲ ሲሆን፣ ይህ ተልዕኮ የአሜሪካን መልካም ገጽታ ጭምር አደጋ ውስጥ የሚከት አካሔድ መሆኑን በመግለጽ፣ ፕሬዚዳንቱ ያቀረቡትን የተቀናሽ በጀት ዕቅድ በርካታ የኮንግረስ አባላት ሲቃወሙ መቆየታቸውም ይታወቃል፡፡

ሪፖርተር አማርኛ – በብርሃኑ ፈቃዱ