January 28, 2018 – ቆንጅት ስጦታው
የኢትዮጵያ ራዕይ ፓርቲ [ኢራፓ]
==================================
‘ኢራፓ’ ‘ኢሕአዴግ’ን የመገነዝ ሃላፊነት የለበትም !!
በምልዓተ ሕዝቡ እየተጋጋመ የመጣውን፣ ሠላማዊ ህጋዊ – ታላቅ ሕዝባዊ ትግል መደኋላ መቀልበስ ፈጽሞ አይቻልም !!
የኢትዮጵያ ራዕይ ፓርቲ [ኢራፓ]
YE ETHIOPIA RAEIE PARTY [ERaPa]
===============================
የአገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች ድርድርን አስመልክቶ፣
ከኢትዮጵያ ራዕይ ፓርቲ[ኢራፓ] የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ።
———————————————————–
‘ኢራፓ’ ‘ኢሕአዴግ’ን የመገነዝ ሃላፊነት የለበትም !!
———————————————————–
ራዕይ ፓርቲ ከምስረታው ማግሥት አንስቶ ለባለፉት ዓመታት፣ በኢትዮጵያችን እየተካሄደ ላለው የነፃነት፣ የሉዓላዊነትና የአንድነት፤ የሠላም፣ የዲሞክራሲና የብልፅግና እልህ አስጨራሽ ሕዝባዊ ትግል፣ የራሱን አዎንታዊ አስተዋጽኦ በሠላማዊና ህጋዊ መንገድ ሲያበረክት ቆይቷል። በእነዚህም ከፍተኛ መስዋዕትነትን በጠየቁ የትግል ዘመናት ኢራፓ አገራችን አሁን ወደ ተዘፈቀችበት የህልውና ሥጋት እያመራች መሆኗን፣ አርቆ ከመገንዘብና አስቀድሞ ከመጠቆም አልፎ፣ ከወዲሁ ወደ ‘ብሔራዊ መግባባት’ መምጣት እንደሚገባን ለዘመናት ወትውቷል። አሁንም ቢሆን የብሔራዊ መግባባት አይቀሬ አስፈላጊነትን ሠርክ ከማስተጋባቱ በተጨማሪ፣ ለስኬታማነቱ እንደ ፓርቲ የሚቻለውን መንገድ ሁሉ እየተጓዘ ይገኛል።
———————————————————–
ገዢው የኢህአዴግ መንግሥት ግን ከየትኛውም አካል የሚመጣን የድርድር፣ የመግባባትና የእርቅ ጥያቄን ለዘመናት ከማንኳሰስና ከማንቋሸሽ አልፎ፣ “ማን ከማን ተጣላ?” በሚል ሲዘባበትና ሲሳለቅ እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው። የኋላ የኋላ “መንገዱን ጨርቅ ያድርግላችሁ!!” “ብትፈልጉ ሊማሊሞን ማቋረጥ ትችላላችሁ !!” እያለ ፌዘኛ በተረተባቸው፣ ፅኑ ፓርቲዎች፣ ቆራጥ ሠላማዊ ታጋዮች ብሎም በሰፊው ሕዝብ የደረሰበትን ፍጹም ሽንፈት በፀጋ ላለመቀበል እየዳዳው፣ በሲቃ ሲያዝ “ከሠማይ በታች ባሉ ጉዳዮች ሁሉ ለመደራደር ዝግጁ ነኝ፤” እያለ ሲለፍፍ ቆይቷል። በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ ድርጅቱ ‘ከአናት የመበስበስ’ና ‘ከውስጥ የመንቀዝ’ አደጋዎች አላላውስ ሲሉት፣ እያጣጣረም ቢሆን በመጨረሻ ለአገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች የድርድር ጥሪ በማቅረቡ፣ እነሆ ድፍን አንድ ዓመት ያስቆጠረ ‘ድርድር’ ሲካሄድ ቆይቷል።
———————————————————–
ምንም እንኳ ኢሕአዴግን ወደ ድርድር እንዲመጣ ያስገደዱት ገፊ ምክንያቶች ለማናችንም ግልጽ ቢሆኑም፤ በሂደቱ ምንአልባት ኢሕአዴግን ወደ- ሕዝባዊነት፣ ሕዝቡን ደግሞ ወደ- ሥልጣን ባለቤትነት ሊቀይሩ የሚችሉ ዕድሎች እንደሚፈጠሩ ተስፋ በመሰነቅ፣ ራዕይ ፓርቲም ወደ ድርድሩ ሊገባ ችሏል። ሆኖም ግን አምባገነኑ ኢሕአዴግ በአሳዛኝ ሁኔታ ‘ድርድሩን’ ለሕዝባዊ ትግሉ ማዳፈኛ፣ ለውረድልን ጥያቄው ማስታገሻ፣ ለፖለቲካ ፓርቲዎች ማስተንፈሻ፣ ለራሱ ደግሞ የማጣጣሪያ ትንፋሽ መግዢያ፤ አድርጎ ሲጠቀምበት ከርሟል። ከዚህ አይነት ጭፍን እርምጃው ታቅቦ ‘ድርድሩ’ ለአገራችንና ለሕዝባችን ይህ ነው የሚባል ተጨባጭ ውጤት እንዲኖረው በሚያስችል መንገድ ብቻ እንዲጓዝ በኢራፓ በኩል ሲደረጉ የነበሩ ትጉህ ጥረቶችን ሁሉ ከመግፋት አልፎ፣ በአንዳንድ አሸርጋጅ ተደራዳሪዎች የግፋ በለው ሽለላና ቀረርቶ በመታጀብ፣ በኢራፓና በልዑካን ተደራዳሪዎቹ ላይ “አሸባሪዎች” በሚል ጥቀርሻ እስከማጥለም በዘለቀ ዛቻና ፉከራ መጠመድን ሥራዬ ብሎታል።
———————————————————–
የኢትዮጵያ ራዕይ ፓርቲ ‘የድርድሩ’ የዓመት ጉዞ ለአገራችንም ሆነ ለሕዝባችን ያበረከተው ቁንጽል ታህል ፋይዳ እንዳልነበረውና፣ ከእንግዲህም ሊኖረው እንደማይችል፣ በተጨባጭ በመድረኩ በመገኘት ከመገምገም በዘለለ፤ በዚህ ‘ድርድር’ ተብዬ የፓርቲዎች ከንቱ ‘ድር – ድር’ ላይ በዚህ መልኩ መቀጠልን፣ ክቡር የሕይወት መስዋዕትነት እየከፈለበት ባለው የአይበገሬው ሕዝብ ኃያል የህልውና ትግል ላይ እንደመረማመድ ቆጥሮታል። “ሞታችንም ሆነ ትንሳኤያችን ከሕዝባችን ጋር ነው!!” ከሚለው አቋማችን በመነሳትም፣ ከ‘ፀፀትና ከ‘ይቅርታ’ ኑዛዜው ማግሥት፣ አሁንም በአይቀሬው ሞቱ አፋፍ ላይ እንኳ ሆኖ፣ በማናለብኝነት ትምክህት፣ በንፁሃን ዜጎቻችን ላይ አረመኔያዊ ጭፍጨፋ እያፋፋመ ለሚገኘው ህወሓት መራሹ ኢሕአዴግ፣ እንደ ነፍስ መዝሪያነት እያገለገለ ከሚገኘው ‘ድርድር’ ኢራፓ ከጥር 16 ቀን፣ 2010 ዓ.ም ጀምሮ ራሱን ማግለሉን ያሳውቃል።
———————————————————–
ሌሎች ተደራዳሪ አካላትም፣ በዚህ ወሳኝ ወቅት፣ ለኢሕአዴግ ነፍስ የመዝራት ግዳጅም ሆነ የመገነዝ ሃላፊነት እንደለሌባቸው በመገንዘብ፣ ጉዳዩን በጥልቀት አጢነው የየራሳቸውን ወቅታዊና ሕዝባዊ አቋም እንዲወስዱ ጥሪ እያቀረብን፤ እግረመንገዳችሁንም፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከእንግዲህ ፈጽሞ ሊቀለበስ ወደ ማይችል ህጋዊና ሠላማዊ ትግል ማቄን ጨርቄን ሳይል መትመሙን ማመንና፣ የራበው ሕዝብ መንግሥቱን መብላቱ ባይቀርም፣ ማወራርጃም ሊያሰኘው እንደሚችል ከወዲሁ መገንዘብ እንደሚያሻ እናስታውሳለን።
———————————————————–
በመጨረሻም እኛ ኢትዮጵያዊን አሁን ካለንበት የጥፋት ቋፍ ተላቀን፣ ህልውናችን አስጠብቀን መጓዝ ወደ ሚያስችለን ‘ሁሉ አቀፍ ብሔራዊ መግባባት’ እንመጣ ዘንድ፣ “የሠላማዊ ትግል መንገዶች ሁሉ ተዘግተውብናል” በማለት፣ ነፍጥ አንግበው በትጥቅ ትግል ላይ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያንን ጨምሮ፣ ሁሉንም ባለድርሻ አካላትን፣ የማስተባበር ተነሳሽነቱንና ኃላፊነቱን ለመውሰድ ኢራፓ በሙሉ የሞራል አቅም ላይ እንደሚገኝና፣ እየተጋጋመ ለመጣው ህጋዊና ሠላማዊ ሕዝባዊ ትግል የዕርከንና የግለት እድገት፣ እንደ ሠላማዊ-ፓርቲ የራሱን አስተዋጽኦ ለማበርከት ከመቼውም ጊዜ በላቀ ሁኔታ ዝግጁ መሆኑን አስምሮ ይገልፃል።
———————————————————–
“እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ !!”
———————————————————–
———————————————————-