“#.. ፖለቲካ ምን ማለት እንደሆነ ሳይገባን በፖለቲካ መሳተፍ የምንፈልግ ሁሉ ቢቻል ንጉስ አለዚያ ራስ ወይንም ደጃዝማች ወይንም ከንቲባ መባል እንፈልጋለን ፡፡ ለእነዚህ ሹመቶች ወንበሮቹ አንዳንድ ናቸው፡፡” (ፕ/ር መስፍን ሥልጣን ባህልና አገዛዝ ፖለቲካና ምርጫ ፣ገጽ 12)

ከሚነገረውም ሆነ ከሚጻፈው በስተጀርባ  ያለውን ፍቅርና ሰላም፣ አንድነትና ተግባቦት አሳጥቶ የሚያባላውን ጉዳይ ወደ ጎን ብለን ካየነው የሁሉም የትግል ዓላማ የህዝብን የሥልጣን ባለቤትነት ማረጋገጥ የሚል  ነው፡፡ ይህም ማለት የኮሮጆ ድምጽ በትክክል ወደ መንግሥት ሥልጣንነት የሚቀየርበት ሥርዓት መፍጠር፣የህዝብ ለህዝብ በህዝብ ለሆነ ( እንደ አብርሀም ሊንከን አባባል) ዴሞክራሲያዊ አስተዳደር መብቃት ነው፡፡

የህዝብን የሥልጣን ባለቤትነት ማረጋገጥ በሚል ሽፋን ራስን ለምን- ይልህ ቤተ መንግሥት ለማብቃት አለያም ከዛ በመለስ ያሉ ግላዊ ጥቅሞችን ለማግኘት የሚካሄድ በዴሞክራሲ ዲስኩር የተለበጠ ትግል ተሳክቶ ለመንግሥትነት ቢያበቃ የሥልጣን ዘመን በህገ መነግሥት የተገደበ እንኳን ቢሆን እሱን እያሻሻሉ ይቀጥላሉ እንጂ ወደ ሥልጣን በመጡበት መንገድ ለመውረድ ፈቃደኛ ስለማይሆኑ እነርሱን ለሥልጣን ያበቃው የዴሞክራሲ ጅማሮ ይጨናገፍና ሌላ ትግል ሌላ እልቂት ሌላ ውድመት ይከተላል፡፡ዴሞክራሲን በማይናወጥ መሰረት ላይ ማቆም ከተቻለ ግን በምርጫ ወደ ሥልጣን ተወጥቶ በጉልበት ወንበር እስከመቃብር ከተባለ ዴሞክራሲን ይህን የሚያስተናግድበት ቀዳዳ የሚሸከምበት ጉልበት የለውምና በውርደት አሸቀንጥሮ ይጥላል፡፡ ፈጣ ለዛ እምንበቃ ይድርገን ፡፡

ከላይ እንደገለጽኩት የጀርባውን ትተን ከፊት ለፊት ከሚታይ ከሚሰማው ስንነሳ ሁሉም የሀገራችን ፖለቲከኞች በውስጥም በውጪም ያሉት ሥልጣን በህዝብ ይሁንታ በምርጫ ኮሮጆ ውጤት ብቻ የሚያዝ መሆን እንዳለበት ይናገራሉ፡፡ ይህ እውነት ከሆነ በዚህ ወቅት በድንገት ለተከሰቱት ጠቅላይ ምኒስትር መቅረብ ያለበት አብይ ጥያቄ ሁለት አመት የቀረው ምርጫ ፍጹም ነጻና ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን የሚያበቁ ተግባራት እንዲከናወኑ ይሄውም ውሎ ሳያድር ዛሬውኑ እንዲጀመር ነው፡፡ መጠየቅም ብቻ አይደለም ምን ምን ተግባራት እንዴት በምን ሁኔታና መቼ መከናወን እንዳለባቸው የሚገልጽ  በበቂ ጥናት ላይ የተመሰረተ ሀሳብ ማቅረብ ነው፡፡ ማገዝ ነው ፣ የሂደቱ አካል መሆን ነው የሚበጀው፡፡ ለዚህ የግድ የካቢኔ አባል መሆን አይጠይቅም ፣ወይንም ጠቅላይ ማኒስትሩ ቢሮአቸው ጠርተው እንዲያነጋግሩ  አይጠበቅም፡፡ ለነገሩ እየተመካከርን እየተረዳዳን ብለዋል ከዚህ በላይ አረንጓዴ መብራት የለም፡፡

ነገር ግን ዶ/ር አብይ ወደ ሥልጣን ከመጡ እለት አንስቶ በአንዳንድ ወገኖች የሚጠየቁ ጥያቄዎች፣ ማሳሰቢያዎች፣ ከዚህ አልፎ አንዳንዶች ከፍለ ጦር ሰራዊት ድንበር ላይ በተጠንቀቅ ያቆሙ በሚመስል ሁኔታ ግዜ መስጠት አያስፈልግም የሚለው ዛቻና ፉከራ ወዘተ ሲታይ ምን እንደሚሹ ግራ የሚያጋባ ነው፡፡

ዶ/ር አብይ አብዮታዊ ዴሞክራሲን አሽቀንጥረው እንዲጥሉ፣ኢህአዴግ የሚባል ድርጅትን እንዲያፈርሱ፣እነርሱ ወንጀለኛ የሚሉዋቸውን በአንድ ጀንበር ለቃቅመው ወህኒ እንዲያስገቡ፣ ባለሥልጣናቱን በሙሉ እንዲያሰናብቱ፣ተቀዋሚዎችን/ተፎካካሪዎችን ለሥልጣን እንዲያበቁ(ስንት ፓርቲ እንዳለ ግምት ውስጥ ያስገባ አይመስልም) ሀያ ሰባት አመት የደረጀ የተደራጀውን ሁሉ በአንድ ጀንበር ብትንትኑን እንዲያወጡ ወዘተ የሚከጅሉ የሚመስሉ ጥያቄዎችና ማሳሰቢያዎች እየሰማን እያነበብን ነው፡፡ የዚህ ምክንያቱ የተለያየ ቢሆንም አዎንታዊ ሊባል ግን አይቻልም፡፡ግንዱን ለመጣል ቅርንጫፉን መመልመል የሚለው የብልሆች ምክር በብዙዎች ዘንድ የሚታወቅ አይመስልም፡፡ የእነ አብይ ጉዞ ግን ይህን ያጤነ ይመስላል፡፡

ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያውያን የሚበጅ  የተሻለ  ራእይ፤ይህንንም ለመፈጸም አቅም አለን የሚሉ ፖለቲከኞች ዓላማቸውን ተፈጻሚ ለማድረግ ሥልጣን መያዝ ወይንም መጋራት ግድ ይላቸዋልና ዓላማቸውን ተፈጻሚ ለማድረግ ሥልጣን መያዝ ወይንም መጋራት ግድ ይላቸዋልና ለዚህ ደግሞ ነጻና ፍትሀዊ ምርጫ ማካሄድ የሚያስችሉ ሁኔታዎች ያስፈልጋሉና ዋንኛ ጥያቄአቸውም ሆነ ሥራቸው መሆን ያለበት ይሄው ተግባራዊ መጣር ነው፡፡ ሌላ ሌላውን ተሳክቶላቸው ለመመረጥ ከበቁ ሥልጣን ሲይዙ  የሚፈጽሙት ይሆናል፡፡

ሥልጣን በድርድር ሳይሆን በውድድር፡፡

ብቸኛው የሥልጣን መውጫ መንገድ የህዝብ ይሁንታ/ምርጫ/ መሆኑን ሁሉም የሚያምነበት ይመስለኛል፡፡ በምርጫ ለሥልጣን ለመብቃት ደግሞ የፖለቲካ ምህዳሩ ለነጻ ምርጫ የተመቸ መሆኑ ብቻውን በቂ አይደለም፡፡የህዝብን አመኔታ አግቶ፣ በውድድሩ በልጦ  ተገኝቶ ለማሸነፍ የሚያበቃ ድምጽ ለማግኘት ሰፊ ሥራ ይጠይቃል፡፡ ህዝብ ወያኔን ስለማይፈልግ ከወያኔ ውጪ የሚቀርብለትን ማንኛውንም ዕጩ ይመርጣል በሚል እምነት ምርጫ መወዳደር ግዜው ያለፈበት ይመስለኛል፡፡

አሁን በሚታየው አያያዝ ጠቅላይ ምኒስትሩ ቀጣዩን  ምርጫ ነጻ ለማድረግ ቆርጠው የተነሱ ብቻ ሳይሆን ድርጅታቸው ቢሸነፍ ሥልጣኑን በተረከቡበት መንገድ ለማስረከብ ራሳቸውን ያሳመኑም ያዘጋጁም ይመስላል፡፡ ይህ ቢሆን የእናቴ መቀነት አደናቀፈኝ እንዳይመጣ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ዛሬውኑ ሥራ መጀመር ይኖርባቸዋል፡፡ይሆናል የተባለው የማይሆንበት ኤሆንም የተባለው የሚሆንበት ብዙ አጋጣሚ አለና ቀድ ማሰቡ ቢጠቅም እንጂ አይጎዳም፡፡የለማ ቡድን የሚባል ለውጥ አቀንቃኝ አብይ የሚባል ኢትዮፕያን ጠርቶ የማይጠግብ መሪ ይመጣሉ ብሎ ማን ገምቶ ነበር፡፡

አስሩንም ጣታችንን ወደ ወያኔ እየቀሰርን ራሳችንን ለማየት ፍላጎቱም ድፍረቱም የለንም እንጂ፤ ለማየት ሲሞከርም ከየአቅጣጫው የስሜት ናዳ ይወርዳል፣ ፍረጃና ዘለፋ ይነጉዳል እንጂ ይሄ የእኛ  ሰፈር ብዙ ችግሮች ያሉበት ነው፡፡ በእያንዳንዱ ድርጅት ውስጥም ሆነ  በድርጅቶች መካከል ያሉ ችግሮች እልባት አግኝተው ጠንካራ የምርጫ ተወዳዳሪ/ዎች መፍጠር ካልተቻለ የቱንም ያህል ምቹ የምርጫ ሁኔታ ቢፈጠር ውጤት ላይገኝ ይችላል፡፡ ለዚህ ደግሞ ያለው ግዜ ሁለት አመት እጅግ በጣም አጭር ነው፡፡ ተሳታፊ ሳይሆን ተወዳዳሪ ሆኖ ለመቅረብ  አንድ የምርጫ ዘመን ( አምስት አመትም)  ያንሳል፡፡ መጪው ምርጫ ከቀሪው ግዜ ያለፈው የሚበልጥ ቢሆንም በተፎካካሪው ሰፈር ስለ ምርጫ ሲሰራ አይደለም ሲታሰብ ሲወራ  አልሰማንም፡፡

ዶ/ር አብይ የጸጥታ ሀይሉ ማለትም መከላከያ ፖሊስና ደህንነት ከፖለቲካ ወገንተኛነት በጸዳ መልኩ የሚሰራ መሆን እንዳለበት፣ የፍትህ አካሉ ለህግ የበላይነት መረጋገጥና ለፍትህ መስፈን ብቻ የሚሰራ እንዲሆን፣የመገናኛ ብዙኃን የፖለቲካው አፍና ጆሮ መሆናቸው እንዲያበቃ ወዘተ የሚሰሩ መሆናቸውን በዚህች አጭር ግዜ በተለያየ ቦታ ባደረጉት ንግግር በተለያየ መንገድ ገልጸዋል፡፡እነዚህ ተግባራዊ ከሆኑ ለነጻ ምርጫ አስፈላጊ የሆኑ ነገሮች ከግማሽ በላይ ተሳኩ ማለት ነው፡፡ ቀሪው ምርጫ አስፈጻሚው አካልና ህጉ፣ እንዲሁም መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ላይ የተጣለው በፖለቲካ ጉዳይ እጃቸውን እንዳያስገቡ የሚከለክለው ማዕቀብ መነሳት ይሆናል፡፡ ስለሆነም በመንግሥት በኩል ሁሉ ነገር በሚፈለገው መልክ ከተመቻቸ ለውጤት ለመወዳደር ሰርገኛ መጣ እንዳይሆንና ነገር ሁሉ ሱሪ በአንገት ሆኖ  የእናቴ መቀነት አደናቀፈኝ አይነት ሰበብ እንዳይበዛ  ከወዲሁ ስለ ምርጫ  ማሰብ፣ ማሰብ ብቻም  አይደል ግዜ ሳያጠፉ ዛሬውኑ ስራ መጀመር  ተገቢ ይመስለኛል፡፡ ይህን ማድረግ የሚያደርሰው ጉዳትም ሆነ ብክነት አይኖርም፡፡ ይልቁንም ነገሮች በሚፈለገው ሁኔታ ተስተካክለው ሁሉም እንደ አቅሙ የሚሮጥበት ሜዳ ከተመቻቸ ብቁ ተወዳዳሪ ለመሆን ፣ሳይሆን ቀርቶ መንግሥት ምቹ የምርጫ ሁኔታ መፍጠር ከተሳነው ለምርጫ የተፈጠረውን አቅም ለተቃውሞ ማዋል ይቻላል፡

እኛ ተቀዋሚ የለንም አማራጭ ሀሳብ ያላቸው በጋራ ሀገራችንን መለወጥ የምንችል ተፎካካሪዎች እንጂ የሚለው ንግግር ደንቃራ ካላገጠመው በስተቀር በውጪም በውስጥም ያላችሁ በማናቸውም የትግል መስክ የተሰማራችሁ በምርጫው መወዳደር ትችላላችሁ ወደሚል ሊያመራ እንደሚችል መገመት ተስፈኝነት አያሰኝም፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ እንኳን በውጪ ያለው ተጨምሮ ሀገር ቤት ያሉትም በተግባሩ ሳይሆን በቁጥሩ የበዙቱ በእንድ የምርጫ ክልል ከተመደበው ተወዳዳሪ ቁጥር በላይ እጩ እያቀረቡ በእጣ እስከ መለየት መደረሱን እናውቃለንና፣በዚህ ሁኔታ ምርጫ ማሸነፍ ቀርቶ የፓርላ ወንበር ማግኘትም ይገዳል እን  ወደ ራስ መለስ ብሎ ነጻ ምርጫ ቢመጣስ ብሎ ከወዲሁ አስቦ መላ መፈለጊያው ግዜ አሁን ይመስለኛል፡፡

በየምርጫው ወቅት የፖለቲከኞቹ  ቅድመ  ዝግጅት አለመኖር የሚያሳስባቸው ወገኖች ጥያቄ ሲያነሱ ነጻ የምርጫ መድረክ ከተፈጠረ ህዝቡ ወያኔን ስለማይፈልግ ማናቸውንም በተቃራኒ የቀረበ ተወዳዳሪን ይመርጣል የሚልና ቅንጅት ለአሸናፊነት በቅቶ የነበረው በስድስት ወራት ዝግጅት ነው የሚሉ ሁለት ተገቢ ያልሆኑ መልሶች ይሰጡ ነበር፡፡ መጀመሪያ ነገር ሁለቱም ትክክል አይደሉም፤ሲለጥቅ መወዳደር ከምንም በላይ በሌላው ድክመት ሳይሆን በራስ ጥንካሬ ቢሆን ነው ውጤታማ የሚያደርገው፡ ሲሰልስ ቅንጅት ከምርጫው በፊት የነበረው እድሜ ስድስት ወራት ቢሆንም መኢአድና ኢዴፓ በጣሉት መሰረት መቆሙ መዘንጋት የለበትም፡፡ ከዚህ ሁሉ በላይ ደግሞ ትናንት ዛሬ አይደለም፡፡በሌላ በኩል 200 የማይሞላ ዕጩ ለምርጫ አቅርበው ከውጤት በኋላ ወያኔ ያሸነፈን ምርጫ ቦርድንና ጠመንጃውን ይዞ ነው ማለት ከድርጊታቸው በላይ ንግግራቸውን አስገራሚ ያደርገዋል፡፡እጩ ማቅረብ ያልቻልነው በቻና ብዛት ነው እንኳን ቢሉ ያምራል፡፡አለበለዚያ ያቀረቡት ዕጩ በሙሉ እንኳን ቢያሸነፍ መንግሥት መመስረት አይደለም ሥልጣን መጋራት የማያስችላቸውመሆኑ እየታወቀ የማይስል ነገር ሲነግሩ እናም ስንሰማ አንዳንዶቻችንም ስናስተገባ ኖረናል፡፡ በመጪው ምርጫ መሰል ሁኔታ ተፈጥሮ  እነርሱ ለመናገር ቢደፍሩ ሰሚው ግን የሚቀበል አይመስለኝም፡፡ትናንት ዛሬ አይደለምና፡፡

ስለሆነም እኛ መንግሥት ብንሆን ከኢህአዴግ የተሻለ እንሰራለን  የሚሉ ወገኖች የሥልጣን ማግኛው ብቸኛ መንገድ ምርጫ ነውና  ለዚህ ምቹ ሁኔታ ይፈጠር፣ የመወዳደሪያው ሜዳ ይደልደል የሚሉ ጥያቄዎችን ማቅረብና ለምርጫ ራሳቸውን ማዘጋጀቱ ወቅቱ የሚፈልገው ቀዳሚ ሥራቸው መሆን በቻለ ነበር፡፡ ነገር ግን በተቃራኒው የብዙዎቹ ሥራ ዶ/ር አብይ የድርጅታው ርዕዮት የሆነውን አብዮታዊ ዴሞክራሲ ቀደው እንዲጥሉ፣ኢህዴግን እንዲያፈርሱ፣ለተቀዋሚዎች ሥልጣን እንዲያጋሩ መከጀል የሚመስሉ ጥያቄዎችን  ማንሳትና ቃል ሰልችቶናል ተግባር እንሻለን የሚለው ቀዳሚና ዋና ሥራ  መሆኑ ተገቢ አይመስለኝም፡፡ ኢህአዴግን ተወዳድሮ ለማሸነፍ መዘጋጀት እንጂ እራሱን በራሱ እንዲያጠፋ መተበቅ፣ወይንም ሥልጣን በድርድር እንዲያካፍል መመኘት ሊሆን የማይችል ነው፡፡

እናም በእኔ እምነት የዶ/ር አብይና መንግሥታቸው ዋና ተግባር መጪው ምርጫ ከምር እንከን የለሽ (አቶ መለስ በዚህ ቃል አፊዞበታል፣ዛሬ ግን የምር መሆን አለበት ) እንዲሆን የሚያስችሉ ተግባራትን ከወዲሁ መጀመር፣ ተፎካካሪዎችም ራሳቸውን ለምርጫ ከማዘጋጀት ጎን የመወዳደሪያ ሜዳውን ለማስተካከል አቅሙ ያላቸው የመጥረጊያና የመዳመጫ( የኮንስትራክሽን) መሳሪያ፣ አቅሙ የሌላቸው አካፋና ዶማ ይዘው መሰለፍ ነው፡፡

በጎ ነገሮችን ማየት አለመቻል ነጩንም ጥቁሩንም መቃወም አስር ጣትን ወደሌላው ለመቀሰር ካለው ድፍረት ትንሽ እንኳን  ራስን ለማይት አለማዋል፣ እኔ ምን ሰራሁ ምን መስራት ይጠበቅብኛል ሳይባል ጠያቂና ጠባቂ ብቻ መሆን፣ ወዘተ ትናንትም አልበጀ፣ ዛሬም እንዲሁ፣ አሁን አዲስ የለውጥ ነፋስ እየነፈሰ ነውና በዚህ ነፋስ ነገን የተሻለ ለማድረግ ከእውነት እንታረቅ ራሳችንን እንለውጥ፡፡ እናም ፖለቲከኞቻችን የድርጅቶቻችሁ ብዛት እንኳን ስማቸውን ቁጥራቸውን  ለመቁጠር የሚያታክት ደረጃ ደርሷልና ለውይይት ብትጋበዙ የምርጫ ሜዳው ተስተካክሎ ተወዳደሩ ብትባሉ ሊሆን ስለሚችለው ነገር አስባችሁበታል፡፡ አበቃሁ፡፡

በነገራችን ላይ ከነ ፕ/ር በየነ ጴጥሮስ ሰፈር የምትሰማውን “ሀቀኛ ተቀዋሚ” የምትል ነገር ልብ ብላችኋታል፡፡