Skip to content
አንብባችሁ ለወዳጀዎ ሸር ያድርጉ የስኳር በሽታ በሕክምና እንደሚድንና መድኃኒቱም ከሀገራችን ቡና እንደሚሠራ በምርምር የደረሱበትን ዶክተር ፋንታን አበበን በኩር ጋዜጣ እንግዳ አድርጋቸዋለችና እንድታነቡት እንደወረደ እንዲህ አቅርበነዋል፡፡
ሕዳር 20 ቀን 2009 ዓ.ም እንነጋገር፡-
“ቡና እግዚአብሔር እጃችን ላይ ያስቀመጠልን አልማዝ ነው”
ዶ/ር ፈንታሁን አበበ ትውልድና ዕድገታቸው በሰሜን ሸዋ መስተዳድር ዞን ሸዋሮቢት ከተማ ነው:: የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን እንዳጠናቀቁ በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በሒሳብ መዝገብ አያያዝ (አካውንቲንግ) ዲፕሎማ እና በአስተዳደር ጥበብ (ማኔጅመንት) በመጀመሪያ ዲግሪ ተከታትለዋል:: በመቀጠልም ወደ አዲስ አበባ አቅንተው የጥርስ ሕክምና ትምህርት (ዶክተር ኦፍ ዴንታል ሜዲስን) አጥንተዋል:: በአሁኑ ወቅትም አዲስ አበባ በሚገኘው የስኳር ሕሙማን ማዕከል ሕክምና ይሰጣሉ፤ በአፍሪካ ሜዲካል ኮሌጅ የጥርስ ሕክምና ትምህርት እና የጥናትና ምርምር ክፍሎች ኃላፊና መምህር ናቸው::
ዶክተር ፋንታሁን የሕክምና ትምህርታቸውን ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ ወደ ምርምር ሥራው በማዘንበል አስደናቂ የሆኑ ግኝቶችን ይፋ አድርገዋል፤ በሀገር አቀፍና ዓለም ዓቀፍ ደረጃም ዕውቅና ተችሯቸዋል:: የአየር ብክለትን ለመቆጣጠር የሚያስችል ግኝት አበርክተው ዓለም ዓቀፍ ዕውቅና አግኝተዋል:: ዝናብን በሰው ሰራሽ መንገድ በፈለጉት ቦታ ላይ ማዝነብ እንደሚቻልም በጥናት ደርሸበታለሁ ብለው በፈጠራ አስመዝግበዋል:: በተለይ የዓለማችን የጤና ችግር የሆነውን የስኳር በሽታም አክሞ ማዳን እንደሚቻል አረጋግጫለሁ ብለዋል:: ዶክተር ፋንታሁንን የበኲር እንግዳችን አድርገን በስኳር በሽታ መድኃኒት ዙሪያ “አዲስ ግኝት አለኝ” ባሉት ዙሪያ እንነጋገራለን፤ መልካም ንባብ!
ዶክተር ፋንታሁን ከመጀመሪያ የማኅበራዊ ሳይንስ ምሩቅ ሆነው እንዴት ወደ ጤናው ዘርፍ መሸጋገር ቻሉ?
ዝንባሌውና ቁርጠኝነቱ ካለ ይቻላል፤ የማይቻል ነገር አይደለም:: እንዳልከው ከመጀመሪያ ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም የገባሁት በማኅበራዊ ሳይንስ ዘርፍ ነው:: አንደኛው ምክንያት የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ማጠናቀቂያ ፈተናን ስሠራ “ሌሎችን ለማገዝ” በሚል የተሳሳተ አካሄድ ተረጋግቼ ባለመሥራቴ ውጤቴ ዝቅ በማለቱ የተነሳ ነው:: ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ የቤተሰብ ፍላጎትና የመንግሥት የተማሪ አመዳደብ ሁኔታ ነው፤ በእነዚህ ምክንያቶች የተነሳ የማኅበራዊ ሳይንስን ተቀላቀልኩ:: በዚያው ግን አልቀረሁም፤ በኋላ ላይ ዝንባሌዬ ወደሆነው የሕክምናው ዘርፍ በግሌ ገብቼ ተማርኩ::
ወደ ምርምር ሥራ የገቡት መቼ ነው? የሕክምና ትምህርቱን ከጨረሱ በኋላ ወይስ ሳይጨርሱ ነው?
የህክምና ትምህርቱን ገና በመማር ላይ እያለሁ ነው:: በትምህርት ላይ እያለን ለተግባር ልምምድ በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኙት ጳውሎስ፣ ምኒልክ፣ ዘውዲቱ፣ … ሆስፒታሎች እንሄድ ነበር:: በዚያን ጊዜ የተመለከትኳቸው አንዳንድ ነገሮች ገፋፉኝና ወደ ምርምሩ መግባት ጀመርኩ:: በተለይ የስኳር ታማሚዎች የሚያዩት ፈተና ከባድ ነው፤ ከሚወስዱት መድኃኒት ጋር ተያይዞም የሚያጋጥማቸው ውስብስብ ችግር አለ:: ከዚያ በመነሳት ነው የስኳር በሽታ መድኃኒት ላይ ምርምር ማድረግ የጀመርኩት::
የስኳር በሽታ በጣም አስቸጋሪ ነው፤ ታማሚዎቹ ሌላ በሽታ ሲያማቸው እንኳ ታክመው ለመዳን የሚገጥማቸው ችግር በጣም ከባድ ነው:: የታማሚዎቹ ቁጥር ደግሞ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ነው፤ በዓለም ላይ ከ400 ሚሊዮን በላይ ሰዎች የስኳር ታማሚ ናቸው:: በኢትዮጵያም ቁጥሩ በጣም እያሻቀበ ነው፤ በተለይ ደግሞ ታዳጊ ሕጻናት በበሽታው ክፉኛ እየተጠቁ ነው:: ወላጆች የልጆቻቸውን የስኳር መጠን በየቀኑ እየለኩ የሚከታተሉበት ደረጃ ላይ ደርሰዋል፤ በዚያ ላይ ልጃቸውን በሽታው እንዳይነጥቃቸው ወላጆች በስስት ሲመለከቷቸው ስታይ በጣም ያሳስብሃል:: በዚህ ተነስቼ ነው እንግዲህ ወደ ምርምሩ የገባሁት::
የስኳር በሽታ መድኃኒትን “ከቡና አግኝቻለሁ” እያሉ ነው፤ ቡናን ለምርምር እንዴት መረጡት?
ቡና ለኢትዮጵያውያን ምልክታችን ነው፤ እኔ ከልጅነቴም ሳድግ ቡና ሲጠጣና ዘመድ ሲሰባሰብ ከማዬት ባለፈ ጧት ጧት “የገቢ ምንጫችን ቡና ቡና፣ የኢኮኖሚ ዋልታ ቡና ቡና …” እየተባለ በራዲዮ ሲዘመር እየሰማሁ ነው ያደግሁት:: ይህ እንዳለ ሆኖ ደግሞ በተለይ ታዳጊ ሀገራት ባለን ሀብት እንዳንጠቀም የሚደረግብን ተፅዕኖ በጣም ይሰማኛል:: ከዚህም በላይ ከፍተኛ የመሬት ሽፋን የያዘው ቡና ነው፤ ከ25 ሚሊዮን በላይ የኢትዮጵያ ሕዝብም በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በቡና የሚተዳደር ነው:: በዚያ ላይ መንግሥት ባሉን የግብርና ምርቶች ላይ እሴት መጨመርን በእጅጉ ያበረታታል:: ከዚህ በመነሳት ‘ቡና ላይ ምን ዓይነት እሴት መጨመር አለብን?’ ብዬ ነው ቡና ላይ ለማጥናት የተነሳሁት::
ለረዥም ዓመታት ኢኮኖሚያችንን የደገፈውን ቡና እሴት መጨመር በጣም አስፈላጊ እንደሆነ በፅኑ ካመንኩበት በኋላ ደግሞ ይበልጥ ያነሳሳኝ ምክንያት አለ:: በበለፀጉ ሀገራት የሚኖሩ ድርጅቶች የኛን ቡና፡- ‘የይርጋ ጨፌ፣ የሲዳማ፣ … ቡና የኛ ነው’ ማለት መጀመራቸው በጣም አነሳሳኝ:: “ስታር ባክስ” ከእኛ ሀገር በላይ በኛ ቡና ላይ ተጠቃሚ ሲሆን ስመለከት በቡናችን እንደ ባለቤት በመጠበብ የሆነ ነገር መሥራት አለብን ብዬ ማጥናት ጀመርኩ::
ያጠኑት ቡናን ብቻ ነው ወይስ የለዩት ሌላ ዘርፍ ነበር?
ለማጥናት የለየኋቸው ዘርፎች ነበሩ፤ የጤና ባለሙያ ስለሆንኩ ጤናውንም ምጣኔ ሀብቱንም ታሳቢ አድርጌ ነው:: ከምጣኔ ሀብት አኳያ በተለይ ከድርቅ ጋር በተያያዘ የውኃ ማማ የሆነች ሀገር ይዘን በመጠማታችን ማጥናት ፈለግሁ:: ከጤና አኳያ ደግሞ ቀደም ሲል ያነሳሁትን የስኳር በሽታ መፍትሔ መፈለግ አሰብኩ:: ከምጣኔ ሀብት አኳያ ቡናን ለማጥናት እንቅስቃሴ ስጀምር የያዛቸውን ንጥረ ነገሮች አስቀድሜ ማወቅ ፈለግሁ:: የሚገርመው ነገር ቡና ለብዙ በሽታዎች ፈውስ የሚያገለግሉ መድኃኒቶች መቀመሚያ ንጥረ ነገሮችን ይዞ አገኘሁት::
በቡና ውስጥ ከ13 በላይ የመድኃኒት መሥሪያ ንጥረ ነገሮች ይገኛሉ:: ከእነዚህ ውስጥ አንዱ በሳይንሱ ‘ክሎሮጀኒክ’ የሚባለው ነው:: ክሎሮጄኒክ ደግሞ የሰውን የደም ውስጥ የስኳር መጠን የሚያመጣጥን ንጥረ ነገር ነው:: ስለዚህ “ከሀገራችን ቡና ይህ ንጥረ ነገር ከተገኘ ስኳርን ማከም ይቻላል” ብዬ ገመትኩና ወደ ጥናቱ ገባሁ:: ይህም እግረ መንገዴን የስኳር በሽታ መድኃኒትን ከቡና ስፈልግ በቡና ላይ እሴት ጨምሬ ከፍተኛ ገቢም እንድናገኝበት ለማድረግ ያግዘኛል ብዬ ወደ ጥናቱ በጥልቀት ገባሁበት::
ግኝቱን እንዴት አረጋገጡት?
መጀመሪያ በንድፈ ሀሳብ ደረጃ ከተጠናና ከታወቀ በኋላ መጀመሪያ በእንስሳት ላይ ነው የሚሞከረው:: በእንስሳት ላይም “እንዴት መሞከር አለበት?” የሚለውን ከኢትዮጵያ የመድኃኒትና ምግብ ቁጥጥር ባለስልጣን በሚገኘው ቤተ-ሙከራ (ላቦራቶሪ) ሄጄ “ክሎሮጀኒክ አለኝ፤ ለስኳር ታማሚዎች የስኳር መጠናቸውን የሚያስተካክልና ጣፊያ ‘ኢንሱሊን’ የተባለውን ሆርሞን ማመንጨት እንዲችል የሚደርግ ነው:: ሰዎች ዕድሜ ልክ ከሚወስዱት ክኒን ወይም መርፌ የሚገላግል፣ በሽታውን ማዳን የሚችል ነው” አልኳቸው::
እነሱም (የኢትዮጵያ የመድኃኒትና ምግብ ቁጥጥር ባለስልጣን ኃላፊዎች) ተቀብለውኝ በራሳቸው ቤተ ሙከራና በአይጦች ላይ ሞክረውት ከጎንዮሽ ጉዳትና ከመርዛማነት ነፃ መሆኑን አረጋግጠው ሰጡኝ:: በመቀጠልም ከአካባቢ ጤናና ቁጥጥርም በተመሳሳይ መልኩ ማረጋገጫ አሠራሁ:: በተጨማሪም ቡና ዘወትር የምንጠጣው ተፈጥሯዊ ፍሬ በመሆኑ የሚወሰደው መድኃኒትም ሌላ ባዕድ ነገር ሳይጨመርበት ከእርሱ በቀመር የሚወሰድ ንጥረ ነገር በመሆኑ ችግር የሌለበት ስለሆነ ምግብ እንደማለት ነው::
ስለዚህ በቀመር የወሰድኩትን ንጥረ ነገር ከሚመለከታቸው አካላት መረጋገጫ ካገኘሁ በኋላ ፈቃደኛ ለሆኑ የስኳር ታካሚዎች ሰጠኋቸው:: መድኃኒቱን የወሰዱት ሰዎችም የሚገርም ለውጥ አገኙ፤ አሁን ላይ በመዳናቸው ኢንሱሊን በመርፌ በየቀኑ ይወስዱ የነበሩ ሰዎች አቋርጠውታል::
ከቡና የስኳር መድኃኒት ከተገኘ ቡና በመጠጣት መፈወስ ያልተቻለው ለምንድን ነው?
ፈዋሹ ነገር ከቡና ተገኘ እንጅ ቡናው እንዳለ ሲወሰድ ፈዋሽ አይደለም:: ንጥረ ነገሩ በተለየ ቀመር ወጥቶ ነው ጥቅም ላይ የሚውለው:: ለዚህ ተግባር የሚውለውም የተቆላው ቡና ሳይሆን በጥሬው ያለው ነው:: እርሱም ቢሆን በተለየ ቀመር የሚፈለገው “ክሎሮጀኒክ” መውጣት አለበት:: ቡናው ሲቆላ በጣም እንዲያር ስለሚደረግ ብዙ ጠቃሚ ነገሮቹን ያጣል፤ ቡና ሲጠጣም ነጣ ብሎ መቆላት እንዳለበት በዚሁ አጋጣሚ ለመናገር እወዳለሁ::
በእርግጥ በቡና ውስጥ ብዙ ፈዋሽነት ያላቸው ንጥረ ነገሮች አሉ:: ለምሳሌ ያመረቀዘ ቁስል ላይ ቡናውን ደቀቅ አድርጎ ቢደመድሙበት ያድናል:: ካንሰር ያለበትን ሁሉ ቁስለቱን በቀላሉ ያድነዋል፤ የመድኃኒት መላመድ ችግር ለገጠማቸው ሰዎችም አጋዥ የሆኑ ንጥረ ነገሮችን የያዘ ነው:: በእርግጥ አንዳንዶች የጎንዮሽ ጉዳት እንዳለው ይናገራሉ፤ እኔ ግን “ምንም ነገር ቢሆን መጠኑን ካለፈ ስለሚጎዳ እንጅ ቡና ጎጂ ስለሆነ አይደለም” ብዬ ነው የማምነው:: ካልበዛ ለምግብ እንሽርሽሪት በጣም ጠቃሚ ነው፤ ችግሩ እኛ ቡናን አሳርረን ስለምንቆላው ወደ ካርቦንነት ይቀየርና በደም ውስጥ ከኦክስጅን ጋር ተዋሕዶ ካርቦን አንድ ኦክሳይድ (ካርቦንሞኖኦክሳይድ) ስለሚፈጥር የመተንፈስና የልብ መምታት ችግር ሊያመጣ ስለሚችል ነው::
ቡናን ለመድኃኒት መቀመሚያነት መጠቀሙ ምን ያህል ምጣኔ ሀብታዊ ጠቀሜታ አለው?
በእርግጥ ያደጉት ሀገራት ያለንን ሀብት እንድንጠቀም አይፈልጉም እንጅ ቡና እግዚአብሔር እጃችን ላይ ያስቀመጠልን አልማዝ ነው:: ቡና ለብዙ መድኃኒት መቀመሚያነት መዋል የሚችል ሳንቆፍር የምናገኘው ሀብታችን ነው:: አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ቡናን በጣም ርካሽ በሆነ ዋጋ ነው ለዓለም እያቀረብን ያለነው:: በእኔ ግኝት መሠረት ግን የአንዷ ቡና ፍሬ ግማሽ የአንድ ክኒን መስሪያ የሚሆን ንጥረ ነገር ይዛለች::
ይህ ማለት አንድ ሰው የሚወስደው ሙሉ ይዘት 21 ፍሬ ክኒን ቢሆን ለዚህ የሚያስፈልገው 11 ፍሬ ቡና ነው እንደማለት ነው:: በዚህ ስሌት መድኃኒቱን በሙሉ አቅም ወደማምረት ብንገባ አንድ ኩንታል ቡና በሚሊዮኖች የሚቆጠር ብር ያሳፍሰናል ማለት ነው:: ለአንዳንዶች ይህ የተጋነነ ይመስላቸዋል፤ ግን ሀቅ ነው:: አጥንተው ማረጋገጥ ይችላሉ::
ምን ያህል ታካሚዎችን መፈወስ ችለዋል?
በዚህ ወቅት (ሕዳር 2009ዓ.ም የመጀመሪያ ሳምንት) ከ500 በላይ ሰዎች መድኃኒቱን እየወሰዱ ናቸው፤ ከእነዚህ ውስጥ ከ400 በላዩ ከመርፌና ክኒን ተገላግለዋል::ይህን የማደርገው በራሴ ጥረት በግሌ አዲስ አበባ ስታዲዬም አካባቢ በተከራየሁት ቤት ፈቃድ አውጥቼ እየሠራሁ ነው::ይሁንና የመሥሪያ ቦታና የገንዘብ እገዛ ባለማግኘቴ በወረፋ ችግር በየቀኑ ከ60 በላይ ሰው ሳይስተናገድ ይመለሳል:: በቂ የሆነ የቤተ ሙከራና ሕክምና መስጫ ክፍል ስለሌለኝ::
የስኳር በሽታ የተለያየ ዓይነት ስለሆነ እርሶ ማዳን የቻሉት የትኛውን ነው?
እንዳልከው የስኳር በሽታ ዓይነት አንድ እና ዓይነት ሁለት የሚባል አለው:: እኔ ማዳን የቻልኩት ሁለቱንም ነው::
የተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን የስኳር በሽታ መድኃኒት ማግኘትዎን ሲያስተባብሉ ነበር፤ ምክንያቱ ምንድን ነው?
ይህንን የምርምር ይዘትና ውጤት ይዤ ስቀርብ በተደጋጋሚ የቀረቡብኝ አሉታዊ ትችቶች አሉ፤ አንዳንዶቹ “እንዴት ዓለም ዓቀፍ ችግር ለሆነና ፈረንጅ መፍትሔ ላጣለት የስኳር በሽታ ኢትዮጵያዊ ለዚያውም ከቡና መድኃኒት ሊያገኝ ይችላል?” ብለው በጭፍን ይወርዱብኛል:: በሙያው ውስጥ ያሉና አዋቂ የምላቸው ሰዎች ጭምር ስልክ እየደወሉ አጣጥለውኛል:: ግን ዓላማ ስላለኝና ፍንጭም ያየሁበት ስለሆነ ቀጥዬበት ከዚህ ደርሻለሁ:: ሌሎቹ “ለዚያውም ከኢትዮጵያ ቡና¡” ብለው በመሳለቅ በሕክምና መጽሔቶች ሳይቀር ጽፈውብኛል:: ግን ጠጋ ብለው በዕውቀት ዓይን ቡናችንን ቢያዩት ትልቅ ክብር የሚሰጡት ይመስለኛል:: በሩቁ ባንገዳደል ጥሩ ነበር፤ ማበረታታት ልምዳችን ቢሆን መልካም ነበር:: እንዲያውም ፈቃድ የሰጠኝ አካል ሁሉ ፈቃድ እንዳልሰጠኝ ተደርጎ ሁሉ ተዘግቧል:: በኋላ ሄጄ ምን እያላችሁ ነው? ስላቸው “እንዲያውም አንተን ማገዝና ማበረታታት ነው የምንፈልገው” ብለው ባለሙያዎችን ሁሉ መደቡልኝ፤ ድጋፍም እያደረጉልኝ ነው:: ግን በወቅቱ ሆን ብለው የዘመቱብኝ ሰዎች ክፉኛ ስሜቴን ጎድተውታል:: እንዲያውም ልዩ እገዛ ነበር የሚያስፈልገኝ:: የሚገርመው ግን ሙያዊ እና በዕውቀት ተመሥርቶ ተቃውሞ የሚያቀርቡ ሰዎች አለመኖራቸው ነው::
ቡናችን አካባቢያዊ የሆነ ስያሜና ዝርያ አለው፤ የስኳር ፈዋሽ ንጥረ ነገር ይዘቱ በዚያው ልክ ይለያያል?
ቡናዎቹ እንደ መልክአ ምድራቸው በጣዕምም በንጥረ ነገር ይዘትም ይለያያሉ፤ ቡና የሚያሰኛቸው መሠረታዊ ባሕሪ እንዳለ ሆኖ:: አንዳንዶቹ የቡና ዛፎች እንደ ሙጫ ሌሎቹ ደግሞ እንደ ወይን ያለ ፈሳሽ አላቸው:: ይህ ነገር በሚይዙት ንጥረ ነገር ላይም ስለሚንፀባረቅ ሁሉም ቡናዎቻችን የስኳር ፈዋሽ ንጥረ ነገሩን ይዘዋል፤ በመጠን ግን ይለያያሉ::
አሁን ላይ በዓለም እየተሰጠ ያለው የስኳር በሽታ መድኃኒት ዕድሜ ልክ የሚወሰድ ነው፤ የእርሶ ግኝትስ?
በዓለም ላይ ጥቅም እየሰጡ ያሉት የስኳር መድኃኒቶች እንዳልከው በመርፌ ወይም በክኒን መልክ ሆነው ዕድሜ ልክ የሚወሰዱ ናቸው:: ያ መሆኑ ደግሞ የምጣኔ ሀብት፣ የስነ-ልቦና፣ የጤና ችግር አለው፤ አማራጭ ስለሌለ የሚወሰድ መድኃኒት ነው ማለት ይቻላል:: በእኔ እምነትና ባገኘሁት ውጤት ግን የስኳር በሽታ ታክሞ መዳን የሚችል ነው፤ ዕድሜ ልክ መድኃኒት መውሰድ አያስፈልግም:: በእኔ ግኝት መሠረት ለተወሰነ ጊዜ መድኃኒቱን ወስደው ዘላቂ ፈውስ ያገኛሉ::
ከመንግሥት አካልስ ምን ያህል ድጋፍ እያገኙ ነው?
መጀመሪያ ላይ በዚያም አካባቢ ውዥንብሮች ነበሩ:: በተለይ የስኳር በሽታ መድኃኒት በየጊዜው የሚገዟቸው ሰዎች ህመምተኞች የእኔን መድኃኒት ወስደው ሲድኑና ሲያቋርጡ ይበሳጩ ነበር፤ በግልፅ “እንዴት ይድናሉ!” ብለው የተበሳጩ ሰዎች አጋጥመውኛል:: አሁን ላይ ግን “ምን እናግዝህ? ባለሙያዎችን አቋቁመን እንዲረዱህ ማድረግ እንፈልጋለን?” እያሉኝ ነው፤ በተለይ ከመድኃኒትና ምግብ ቁጥጥር ባለስልጣን ጥሩ ድጋፍ እያገኘሁ ነው::
ለነበረን ቆይታ አመሰግናለሁ
እኔም በጣም አመሠግናለሁ!
በኩር (አብርሃም በዕውቀት) ሕዳር 19 ቀን 2009 ዓ.ም ዕትም
Like this:
Like Loading...