26/12/2017

“አባቴ ሙስሊም ነው እናቴ ክርስቲያን ነች፡፡ ሀምሳ አመት በጋብቻ ሲኖሩ እኔን ጨምሮ ዘጠኝ ልጆች ወልደው አሳድገዋል” ሲሉ ስለትውልዳቸው ይናገራሉ፡፡ “Social Capital and Inter-Religious Conflict in Jimma Zone” በተሰኘ ርእሰ ጉዳይ ለዶክትሬት ማሟያ ፅሁፍ ንድፈ ሀሳብ ባቀረቡበት ቪዲዮ፡፡ የትውልድ ቦታቸው ጥናታቸውን በሰሩበት በዚሁ በኦሮሚያ ክልል ጂማ ዞን አጋሮ አካባቢ ከመሆኑ ያለፈ ስለትውልድና እድገታቸው መረጃ ማግኘት አልቻልኩም፡፡

የመንግስት ስራ የትና መቸ እንደጀመሩ የሚገልጥ መረጃ ለማግኘት ባደረግሁት ፍለጋ እውነትነታቸውን ማረጋገጥ ያልቻልኩት ሌላ መረጃ እንደሚገልፀው ከደርግ መውደቅ በኋላ የሀገር መከላከያ ሰራዊት እንደተቀላቀሉና በምዕራብ ወለጋ አሰፋ ብርጌድ በሚባል እዝ ወታደራዊ ስልጠና ወስደው በመቀጠልም የስራ ዘርፋቸው የወታደራዊ መገናኛ ቴክኖሎጅ ስራ ላይ ስለነበር ወደማዕከል ተዘዋውረው (በወታደራዊ መረጃና ደህንነት ይመስለኛል) መስራታቸውን የሚገልፅ ፍንጮችን ከኢንተርኔት ማግኘት ችያለሁ፡፡ አጫጭር ስልጠናወችን ከወሰዱ በኋላ በብሄራዊ መረጃና ደህንነት መስራያ ቤት የኦሮሚያ ክልል የመረጃ ጉዳይ ሃላፊ ሆነው እንደሰሩም በተጨማሪ ይገልፃል፡፡

የመረጃ ደህንነት ኤጀንሲ
የዶ/ር አብይ የከፍተኛ ስልጣን ጉዞ የሚጀምረው ሀዳር 15 ቀን 1999 የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ለመመስረት የወጣ የሚኒስተሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 130/1999 ጋር ነው፡፡ የኤጀንሲው መመስረቻ ደንብ እነደሚያትተው የሀገሪቱን ቁልፍ የመገናኛ አውታሮችን ከአደጋ ለመከላከልና ለማሳደግ እንዲችል ሰፋ ያለ ስልጣን እንዲኖረውና ተቋሙ በኤጀንሲ ደረጃ ይጠራ እንጅ የኤጀንሲው ዳሬክተር ተጠሪነታቸው በቀጥታ ለጠቅላይ ሚኒስተሩ እንዲሆን ያደርጋል፡፡
ይህ ኤጀንሲ የሀገሪቱን ሁነኛ ተቋማት ማለትም የደህንነት፤ የፋይናንስ፤ ወታደራዊና ፖለቲካዊ ተቋማት የሚጠቀሙባቸውን የስልክ፣ የኢንተርነትና ሌሎች የመገናኛ አውታሮች ለመከላከል ሲባል ያለምንም ገደብ እነዲያስስና እየተነተነ እንዲያቀርብ በወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስተር መለስ ዜናዊ በተፈረመ በዚሁ ደንብ ስልጣን ተሰጥቶታል፡፡

አቶ አብይ ይህን ኤጀንሲ በበላይነት የመሩ ግለሰብ እንደመሆናቸው በመገናኛ ብዙሀንም ይሁን በሌላ መንገድ ስማቸው ጎልተው የሚታዩ ሰው ግን አልነበሩም፡፡ ስለዚህ በወቅቱ የነበራቸው ሚና በቅርብ ከሚያቋቸው ሰወች ባገኘሁት መረጃ የተመሰረተ ነው፡፡

በደህንነት መስሪ ቤቱ ያሳዩት ለውጥ
አብይ አህመድ የኢትዮጵያ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ዳይሬክተር በነበሩበት ወቅት የሚመሩትን የዚሁን የደህንነት መዋቅር (ኢንሳ) ከፖለቲካ ማለትም ከህወሀት ወገንተኝነት ለማላቀቅ እንደሞከሩ መረጃወች ያሳያሉ፡፡ ለዚህም በመጀመሪያ የሚጠቀሰው የደህንነት መስሪያ ቤቱ የምልመላ ሂደት የከፍተኛ ትምህርት ተመራቂወችን በውጤታቸውና ለሀገር ባላቸው ቀና አመለካከት ብቻ እንዲሆን ለማድረግ መሞከራቸው ነው።
መስሪያ ቤቱ የተቋቋመበት ዘመን ምርጫ 97 ተከትሎ በመጣው የኢህአዴግ ሁሉን አቀፍ ተቃውሞ የማጥፋት ዘመቻ ላይ እንደመሆኑ ከቀበሌ እስከ ዩኒቨርሲቲ በየትኛውም የመንግስት ቢሮክራሲ ያለምንም ውድድር ሰራተኞች በየዩኒቨርሲቲው በተቋቋሙ የኢህአዲግ የህዋስ አደረጃጀቶች ብቻ የሚመለመሉበት ጊዜ እንደነበር በወቅቱ የዩኒቨርሲቲ ተማሪ የነበሩ ሁሉ የሚያስታውሱት ነው፡፡

አብይ የሚመሩት መስሪያ ቤት ግን በተለየ ሁኔታ ይሰራ ነበር፡፡ ለዚህም በጊዜው በዩኒቨርሲቲወችና የትምህርተ ዘርፎች የላቀ ቸሎታ ያላቸውን ተማሪወች እንዲመለመሉ ያደርጉ ነበር፡፡ አቅም አላቸው የተባለ ማንም ሁን ማን በስልክ በመደወል ስራ እንዲያመለክቱ ከመወትወት በተጨማሪ ሰራተኞቻቸው በመሰናዶ ትምህርተ ቤቶች ሳይቀር የላቀ ችሎታ ያላቸውን ሰወች በመሰሪያ ቤቱን እንዲቀላቀሉ እንዲያደርጉ ለሰራተኞቻቸው የቤት ስራ ይሰጡ ነበር፡፡
የደህንነት መስሪያ ቤቱ የሚጠብቀው የኢህአዴግን ስልጣን ወይም የፖለቲካ ቡድኖችን ፍላጎት ሳይሆን የኢትዮጵያን ሀገራዊ ጥቅም ብቻ አስበው አንዲሰሩ በግልፅ እንደሚናገሩ ሰራተኞቻቸው ይመሰክሩላቸዋል። በወቅቱ INSA ውስጥ ኢህአዴግን መቃወም ቀርቶ የተቃዋሚ ፓርቲ አባል መሆን እንኳን ከምንም እንደማያግድ በቅርብ የሚያውቋቸው ይናገራሉ። በአጠቃላይ ለኢትዮጵያ አንድነትም ሆነ በዴሞክራሲ እንዲሁም በብቃት ላይ የተመሰረተ አስተዳደር እንዲኖር ያላቸው እምነት በእጅጉ ቀናና የማያወላዳ እንደነበር ይመሰክሩላቸዋል።

ይህ አመለካከታቸው የኋላ ኋላ በህወሀት የደህንነትና መከላከያ ሰወች ጥርስ እንዲነከስባቸው ማድረጉንና አሁን የኤጀንሲው ዳይሬክተር የሆኑት ሜጀር ጀኔራል ተክለ ብርሀን እንዲተኩ ተደርገው እንደተነሱና አዲሱ የህወሀት ሹመኛም ያደረጉት የመጀመሪያ ርምጃ አብይ በየዪኒቨርሲቲው የመለመላቸውን ሰራተኞች በተለመደው ፖለቲካ እየገመገሙ በጅምላ ማባረር ነበር። በጊዜው ስለመስሪያ ቤቱ አውርተው የማይጠግቡት ሰራተኞችም ብዙወቹ የአብይን መልቀቅ ተከትሎ ሀገር ለቀው በስደት እንደሚኖሩ መረዳት ችያለሁ፡፡
በኢንተርኔት ያገኘሁት የአንድ ፀሀፊ ምልከታም ይህንኑ ያጠናክራል፡፡ እንደተረዳሁት ከሆነ አቶ አብይ ኢንሳ የሚባለውን የመረጃ መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ከምንም ተነስቶ አቋቋመው፡፡ ተቋሙ በደንብ መሰረት እስኪይዝም ጠበቁት፡፡ በኋላም ከሱ በኩል ተቋሙ ጠንካራ የመረጃና የቴክኖሎጂ ስራ የሚሰራ መሆን አለበት በሚል፣ ከህወሓት ሰዎች በኩል ደግሞ የለም የስለላ ተቋም እናድርገው የሚለውን የውዝግብ ነጠብ ተከትሎ ጊዜ ጠብቀው አባረሩትና ህወሐቶች እራሳቸው ለስለላ ሲሉ ተቆጣጠሩት፡፡

የፓርላማ ተሳትፎ
በየትኛውና ለምን ያህል የፓርላማ ዘመን የህዝብ ተወካይ ሆነው እንደሰሩ ባይገልፅም የአብይ አህመድ ስም ከፓርላማ ጋርም እንደሚያያዝ ቀደም ብሎ በአዲስ አበባው ሸገር ሬድዮ ጣቢያ፣ በአሁን ሰዓት ደግሞ በስደት ላይ ባሉ ጋዜጠኞች በሚሰናዳው ዋዜማ ሬድዮ ላይ የምትሰራው ሀኒ ሰለሞን ፓርላማ ለመዘገብ በሄደችበት ወቅት የነበራትን ትዝብት አስመልክቶ በብሎግ የሰፈረ አንድ ፅሁፍ የሀኒን ምልከታ እንደሚከተለው አስቀምጦታል፡፡

“ሀኒ በፌስቡክ ገጽዋ ላይም በገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ ላይ ተደጋጋሚ ትችቶች በመሰንዘር ትታወቃለች፡፡ ነገር ግን ልክ የዛሬ ዓመት አከባቢ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አዳዲስ ሚኒስትሮቻቸውን ይፋ ባደረጉበት ወቅት ለየት ያለ አስተያየት አሰፈረች፡፡ ሀኒ ወደእንቅልፋሙ ፓርላማ ስታመራ ቀልቧን የሚስቡ አንድ ሞጋች የፓርላማ አባል ነበሩ፡፡ ብዙ ጊዜ ባለስልጣናት እንዲጸድቅላቸው አንጠልጥለው የሚመጡትን ያልተደራጀ ሰነድ የሚያብጠለጥሉትና በነጻነት እንደልባቸው የሚናገሩት እኚህ ሰው ብቻ እንደሆኑ ሀኒ በጽሁፏ ላይ ትጠቅሳለች፡፡ ታዲያ በእለቱ በሚኒስትርነት ከተሾሙት ዝርዝር ውስጥ የእኚህን ሰው ስም ትሰማለች፡፡ እናም በኢህአዴግ እድሉ ከተሰጣቸው ለውጥ ሊያመጡ እንደሚችሉና ተስፋ ብናደርግ እንደማይከፋ ትነግረናለች፡፡”

በሳይንስና ቴክኖሎጅ
ወደ ሳይንስና ቴክኖሎጅ ሚኒስተርነት ሲመጡ እንደማንኛውም ሚኒስተር ከፓርላማ ወንበር ተነስቶ በፖለቲካ ብቻ የተመደቡ ሰው አልነበሩም፡፡ ከኢንሳ ከተነሱ በኋላ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ስር እንደ አዲስ ገና በመቋቋም ላይ የነበረ የመረጃ ማዕከል ሀላፊ ሆነው እንደሰሩ ይገልፃል፡፡ ከሁለት ዓመት በኋላ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ሆነው ሲሾሙ ጸሀፊው ከዚህ በኋላ ስለነበራቸው የሚከተለውን አስቀምጧል፡፡

በሌላ ጊዜ የሰሩትንና የሚሰሩበትን ቢሮ ከወዳጆቼ ጋር በመሆን ጎበኘሁ፡፡ የቀየሩት የተቋሙ ቅርጽ፣በሁለቱ ዩኒቨርሲቲዎች ላይ የሰሩት የልህቀት ማዕከልነት ስራ፣ ለብዙ ጊዜ ሳይሳካ ቆይቶ እሳቸው ከመጡ በኋላ አሳማኝ ጥናት በማቅረብ ያቋቋሟቸው የባዮ ቴከኖሎጂና የስፔስ ሳይንስ ሁለት ግዙፍ ተቋማትን ጨምሮ በአንድ ዓመት ውስጥ የሰሯቸው ስራዎች የሰውዬውን ፍጥረት በብዙው ተጠራጠርኩት፡፡

የኢትዮጵያ ደራስያን

አብይን ከደራሲን ጋር ያገናኘው በዚሁ ሚኒስተርነት ላይ እያሉ ለሁለተኛ ጊዜ የተካሄደው ንባብ ለህይወት የተሰኘው የመጽሀፍት ኤግዚቢሽን ነው፡፡ ከላይ የጠቀስኩት ተመልካች በወቅቱ የነበረውን ሁኔታ እንደሚከተለው አስፍሮታል፡፡
“…እሳቸው በክብር እንግድነት፣ እኔ ደግሞ ለዘገባ ተገኝተን ነበር፡፡ የሳቸው ተራ ደርሶ መድረኩን ከያዙት በኋላ ግን የምሰማውን ተጠራጠርኩኝ፡፡ የኛ ባለስልጣን መሆናቸውን ተጠራጠርኩኝ፡፡ ደራሲዎቻችንን ሁሉ አፍ አስከፈቱ፡፡ በአጭር ሰዓት ብዙ እውቀትን አፍስሰውብን ወረዱ፡፡ ይህንኑ ንግግራቸውን ከሰሞኑም በዩትዩብ ላይ ደግሜ አየሁት፡፡ ድጋሚ እንደ አዲስ ተደመምኩባቸው፡፡”

በርግጥም አደረጉት የተባለውን ንግግር በዩትዩብ ላይ ማግኘት በመቻሌ የተመልካቹ ገለፃ እውነታነት ከማረጋገጥ አልፎ በንግግራቸው ውስጥ ከዚህም ያለፉ መልእክቶችን ማግኘት ችያለሁ፡፡ በንግግራቸው አፅንኦት ሰጥተው ከተናገሯቸው ጉዳዮች ውስጥ የሚከተለው ይገኝበታል፡፡
“ተፈጥሮ አድሎ የሰጠንን ሀገር ተጠቅመን መቀየር ያልቻልነው እውቀትን የመፈለግ ዝንባሌያችን ሽርፍራፊ ፍራንክ ለመለቃቀም ከምናደርገው ጥረት በእጅጉ የተለያየ መሆኑ ነው፡፡… ኢተዮጵያ ትልቅ ሀገር ነች፡፡ ከማንም የተሻለ የማድረግ አቅም እኛ ውስጥ አለ፡፡ እኛ ያጣነው ዊዝደም ነው፡፡”
የ2007 ምርጫን ተከትሎ የሳይንስና ቴክኖሎጅ ምንስተር ሆነው ከተሾሙ በኋላ በሳንስና ክኖሎጅ ሚኒስተር ያላቸው ቆይታ የዘለቀው እስከ ጥቅምት 2009 ለሁለት አመት ብቻ ነበር፡፡

የመለስ ሌጋሲ ግልበጣ
የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ጋር ተያይዞ በተነሳው የኦሮሚያ አመፅ ከአንድ አመት በፊት ማለትም በመስከረም 2009 ኦህዴድ ለአስቸኳይ ጊዜ ስብሰባ ይቀመጣል፡፡ ድርጅቱም ባልተለመደ ሁኔታ የህወሀት አሽከር ናቸው ተብለው የሚታሙትና ህዝባዊ ተቃዉሞው የበረታባቸውን የድርጅቱ ሊቀመንበርና ምክትል ሙክታር ከድርና አስቴር ማሞን ታሪካዊ በተባለለት መንገድ አንድ ጊዜ በማንሳት ለማ መገርሳንና ወርቅነህ ገበየሁን በመተካት ተጠናቀቀ፡፡
ድርጊቱ በወቅቱ የምክትል ጠቅላይ ሚኒስተርነት ስልጣን እስከ ክልል አስተዳዳሪነት በስልጣን ላይ ስልጣን የነበራቸው እነ አስቴር በአንድ ቀን ደራሻቸው ሲጠፋ በህወሀት ሰፈር መደናበርን ፈጥሮ እንደነበር አይዘነጋም፡፡ በብዙ ሰወች ዘንድ በኦሮሚያ የተደረገ መፈንቅለ መንግስት ተደርጎ ተወስዷል፡፡ በኢንግለዝኛ የሚታተመው አዲስ ፎርቹን በመለስ ሌጋሲ ላይ የተደረገ መፈንቅለ መንግስት ሲል ገልጦት ነበር፡፡

በወቅቱ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል የነበሩት አቶ አብይ አህመድ ግን አዲስ ምዕራፍ ከፍቶላቸዋል፡፡ ስማቸው ከፖሊቲካ ጋር መነሳት የጀመረውም ከዚህ እለት ጀምሮ ነው፡፡ ቀድሞውንም በአባልነት የነበሩበት የኦሮሞ ህዝብ ዲሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦህዴድ) ይሁን እንጅ ፓርቲውም ሆነ ክልሉ ላይ ውስጥ የሚታይ የፖሊቲካ ልምድም ሆነ የስራ ድርሻ አልነበራቸውም፡፡ ከስራቸው ሙያዊነት አንፃር የፖለቲካ ስራ ላይዋጣላቸው ስለሚችል ለመገመት አስቸጋሪ ነበር፡፡
በጥቅምት 2009 ለማ መገርሳ አዲስ ያቋቋሙትን ካቢኔ ይፋ ሲያደርጉ የፌደራል ሚኒስተር የነበሩት አብይ አህመድ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የከተማ ልማትና የቤቶች ቢሮ ሐላፊ ሆነው ተሾሙ፡፡ የክልል ስልጣን ወደታች እንደመውረድ ሊቆጠር ቢችልም የኦህዴድ ቁልፍ ሰው ለመሆን እንደሚበቁ ለማስመስከር ግን ጊዜ አልፈጀባቸውም፡፡

ባለፈው አመት ረብሻውን ተከትሎ በነበረው የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ጉባኤ በኢትዮጵያ የዘር የበላይነት መስፈኑንና ሀገሪቱ በሙስና እየዘቀጠች መሄዷን፤ እዚህ የምትገኙ ባለስልጣኖች ውጭ ሀገር ባንክ አካውንት የሌለው ማነው በማለት ለአንድ ሰዓት ባደረጉት ንግግር የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚን መወረፋቸው ፎርቹን በድጋሜ ዘግቦ ነበር።

የኦሮሚያ ቴሌቪዥን በለገጣፎ መሬታቸውን በቀድሞው የአብይ መስሪያ ቤት ስለተቀሙ ግለሰቦች ጉዳይ ሳይቀር በኦሮሚያ ቴሌቪዥን ሲብጠለጠል እርሳቸው የቴሌቪዥን ድርጅቱ ቦርድ ሀላፊ ነበሩ። በወቅቱም በኢንሳ ሃላፊ ማስጠንቀቂ በመመስል መንገድ ማስተባበያ እንዲደረግ ደብዳቤ መፃፉንና ደብዳቤውም ፌስቡክ ላይ ሲዘዋወር እንደነበር ይታወሳል፡፡

የኦህዴድ ቁልፍ ሰው
በፖለቲካ ፓርቲ አደረጃጀት የፓርቲው ዋና ፀሀፊ (ሴክሬተሪ) የፓርቲው ሊቀመንበር እንደ አቻ የሚቆጠር ከፍተኛ ቦታ ነው። የትናንቱ የመከላከያና የደህንነት ሰው ተሀድሶ በተባለው አዲሱ የጨፌ ካቤኔ የክልሉ ከተማ ልማት ሀላፊና ም/ፕሬዘዳንት ሆነው ብዙ ሳይቆዩ የፓርቲውን ከፍተኛ ስልጣን (secretary general) ይዘዋል። ይህ ማለት በሚሊዮን የሚቆጠር የድረጅቱ አባላትና የኢትዮጵያ ሰፊ ክልል የቀን ተቀን ጉዞና ስብሰባ አጀንዳ የሚመሩት አብይ አሁን ያለጥርጥር የኢትዮጵያም ቁልፍ ሰው ሆነዋል፡፡ ሁለት አመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ሲሆን ከዚህ ጎን ለጎን አቶ አብይ በPhD ከአ/አ/ዩኒቨርሲቲ የሰላምና ደህንነት ተቋም ከላይ በተገለፀው ጥናታቸውን አጠናቀው ዶ/ር ተብለዋል።

ፅሁፉን የማጠናቅቀው በዘንድሮው የአዲስ አመት አቀባበል የክልሉን ፕሬዝዳንት ለማ መገርሳን በመወከል ካደረጉት ንግግር ላይ በመውሰድ ነው፡፡

“…ይህ የጭለማ ዘመን ሊነጋ ነው የሰፊው የኦሮሞ ህዝብ ድል ቅረብ ነው። አንድነታችንን አጠናክረን… ልናወራ ሳይሆን ልናሸንፍና ህዛብችንን ለማሸጋገር እውነታኛ ዲሞክራሲን እውነተኛ ሰላምን እውነተኛ አንድነትን በዚህ አገር ውስጥ ለማምጣት እንሰራለን፡፡ …ትንሹም ትልቁም ኦሮሞንና ኦሮሚያን ይጠራጠራል፡፡ ኦሮሞና ኦሮሚያ የኢትዮጲያ ዋልታ ምሰሶ ነው፡፡ ኢትዮጲያን እናጠናክራልን እናሳድጋለን፡ በደስታም እንኖራለን ከኢትዮጲያ ግራና ቀኝ መሄድን አናስብም፡ ኢትዮጲያ ውስጥ ዲሞክራሲያዊነት ሰላምና ልማት ተስተካክሎ እንዲኖር ደግሞ ትግላችንን እንቀጥላለን።”

አምባገነን መዋቅራዊ ነው። ከአምባገናዊነት ወደ ዲሞክራሲ የሚደረግ ለውጥም መዋቅራዊ ነው፡፡ በሂደቱ ግን ለውጡ የሚጠነሰሰው አምባገነንን መገዳደር የሚችል ራእይና ስትራቴጅ ባላቸው ግለሰቦች ማህጸን ውስጥ ነው። ይህ የአብይ ጉዞ ለራሳቸው ብቻ ሳይሆን ለሀገሪቱም ወሳኝ ነው፡፡ ኢትዮጵያን ህዝባዊ ተቀባይነት ያለውና ብቃት ያለው አስተዳደር ገንብቶ ለመምራት በአንድ ቀን ሌሊት የሚጠናቀቅ ስራ አይደለም፤ እውቀትና አመራር፤ ተከታታይ የህዝብ ጥያቄወችና ድጋፍ እንዲሁም ጠንካራ የሲቪል ማህረሰብ የሚዲያ ስራ ይፈልጋል፡፡ አስተዳደራቸው በሰፊ የዲሞክራሲና የአንድነት ጥያቄ ከመናጥ አሁንም አልቦዘነም፡ ወደፊትም የሚቆም አይደለም፡፡ ቢሆንም የሚፈልጉትን ያህል ድጋፍም እያገኙ ያሉት ከዚሁ ተመሳሳይ ቡድን ነው፡፡ ይህ ለአስተዳደራቸው ተጨማሪ ጉልበት ነው፡፡ ከኋላ ታሪካቸው መረዳት እንደምንችለው አብይ ፈቃዱም ችሎታውም አላቸው፡፡ አብይን ወደፊት ከመጓዝ የሚያግዳቸው ነገር አይኖርም፡፡

** የዚህ ፅሁፍ አዘጋጅ ኢትዮጵያ በጠንካራ አንድነት ላይ የተመሰረተ ዲሞክራሲያዊ መንግስትና የህዝቦቿ መሰረታዊ ፍላጎቶችና ነፃነቶች የተከበሩባት ሀገር እንድትሆን በፅኑ አምናለሁ፡፡ ፅሁፉን ለማሰናዳት የድህረገፅ መረጃወችን እስከቻልኩት ድረስ በማገላበጥና በስምንት አመት የስራ ቆይታ ከታዘብኩት ጋር በመጨመር የተዘጋጀ እንጅ ለድርጅታቸውም ሆነ አስተዳደራቸው ለሚከተለው ርዕዮተ አለም ያለኝን ድጋፍ አያመለክትም፡፡ ፀሀፊውን fikriesintayehu@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡”