

16 January 2022
በእንግሊዝ አገር በሰላም ጥናት በሚታወቀው ብራድፎርድ ዩኒቨርሲቲ ሦስተኛ ዲግሪያቸውን ሠርተዋል፡፡ የከፍተኛ ትምህርት ሕይወትን የጀመሩት በእንግሊዝኛ ቋንቋና በሥነ ጽሑፍ የመጀመሪያ ዲግሪቸውን በመሥራት ነበር፡፡ በሥነ ቋንቋ ዘርፍ በመግፋት ደግሞ በአፕላይድ ሊንጉስቲክስ ሁለተኛ ዲግሪ ይዘዋል፡፡ ትምህርታቸውን ወደ ሌሎች መስኮች በማሳደግ በፖለቲካና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ትምህርት ሦስተኛ ዲግሪ ሠርተዋል፡፡ በድኅረ ምረቃ ጥናቶች በተለይ በደኅንነትና በሰላም ብዙ ሠርተዋል፡፡ በዚህ ዘርፍ የበለጠ በመግፋትም ወደ እንግሊዝ አገር በማቅናት የሰላም ጥናት ትምህርታቸውን በፒኤችዲ ዲግሪ ተከታትለዋል፡፡ በምርምሩ ረገድም በዓለም አቀፍና አኅጉራዊ የሰላምና ደኅንነት ጉዳዮች የተለያዩ የምርምር ሥራዎችን አሳትመዋል፣ ለማሳተምም በዝግጅት ላይ ይገኛሉ፡፡ ለረዥም ዓመታት ባገለገሉበት በሰላምና ደኅንነት ጥናት ለተባባሪ ፕሮፌሰርነት የበቁ መሆናቸውን ይናገራሉ፡፡ የዛሬው የቆይታ እንግዳ ዮናስ አዳዬ (ዶ/ር) በትምህርት ካሳለፉትና በምርምር ካገኙት ብቻ ሳይሆን፣ ኖረው ካዩት ልምድና ዕውቀትም በመነሳት ሰላም እንዴት እንደሚገነባና ስለዘላቂ ሰላም ግንባታ ሒደት በሰፊው አብራርተዋል፡፡ ዮናስ (ዶ/ር) የምርምር ሥራዎቻቸው በዋናነት በአፍሪካ፣ በተለይም ኢትዮጵያ በምትገኝበት የምሥራቅ አፍሪካ ቀንድ ላይ ያተኮሩ ሲሆን ከዮናስ አማረ ጋር ያደረጉት ቆይታ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡
ሪፖርተር፡- የምሥራቅ አፍሪካ ቀንድ ፖለቲካን እንዴት ይገነዘቡታል? ኢትዮጵያስ የምትገኝበት ሁኔታ ምን ይመስላል?
ዮናስ (ዶ/ር)፡- በሰላም ጥናት ውስጥ አንድ አገር ብቻውን አይተነተንም፡፡ በሰላም ጥናት አንድ አገር የሚገኝበት ሁኔታ/ዓውድ መታየት አለበት፡፡ የውስጥ ብቻ ሳይሆን የውጭ ተፅዕኖዎችም መታየት አለባቸው፡፡ ከባቢያዊ ወይም አኅጉራዊ፣ ግሎባል ወይም ሉዓላዊ ተፅዕኖዎች አሉ፡፡ አሜሪካና አውሮፓ ጭምር የሚወሰኑ ውሳኔዎች እኛ ላይ እንዴት ተፅዕኖ እያሳደሩ እንደመጡ ሁሉም እያየው ይገኛል፡፡ በሰላም ጥናት የምንጠቀምበት ‹‹ኮምፕሌክሲቲ ቲዮሪ›› አፍጋኒስታን ውስጥ አንድ ታዳጊ ያለ ምግብ ማደሩ አሜሪካ ውስጥ የአስተዳደር ቀውስ ይፈጥራል፣ ህንድ አገር አንዲት ቢራቢሮ ክንፏን ብታርገበግብ ሳንፍራንሲስኮ ተፅዕኖው ይታያል በሚሉ አስገራሚ ምሳሌዎች የሚቀርብ የዓለም ሰላም አጠናን አለ፡፡ ይህ ሁሉ ዓለማችን ምን ያህል የተያያዘች እንደሆነች ለማሳየት የሚቀመጥ ነው፡፡ በዓረብ አገሮችና በአፍጋኒስታን ዜጎች ዳቦ አጥተው ማደራቸውና በድህነት መዘፈቃቸው ለሽብርተኝነት ተመልማይ አደረጋቸው፡፡ ይህ ደግሞ በሃይማኖት መገፋፋትና በፖለቲካ ተፅዕኖ መስፋት ቁርሾና ቁጣ ወልዶ በአሜሪካ ላይ የመስከረም 11 ጥቃትን የዓረብ ወጣቶች እንዲፈጽሙ አደረገ፡፡ የ9/11 የሽብር ጥቃት ደግሞ ሌላ ዙር ቀውስና ግጭቶችን በአፍጋኒስታንና በመካከለኛው ምሥራቅ ወለደ፡፡ የዓለም ሰላምም ሆነ የሰላም ሥጋት ልክ እንዲህ የተሳሰረ ግንኙነት ያለው ነው፡፡javascript:””
ሁላችንም የተያያዝን ስለሆነ የኢትዮጵያ ሰላም ተብሎ ብቻውን የቆመ ሰላም የለም፡፡ የአፍሪካ ሰላም የሚባል ብቻውን የቆመ ሰላም የለም፡፡ የአፍሪካ ሰላም የአውሮፓ ሰላም ነው፡፡ አፍሪካ ሰላም ከሌላት አውሮፓም ሆነ አሜሪካ ሰላም አያገኙም፣ በብዙ ምክንያቶች፡፡ አንደኛው ምክንያት በአፍሪካ ሰላም ከሌለ ወደ አውሮፓና አሜሪካ የሚፈልሰው ዜጋ ይበዛል፡፡ እነሱም ቢሆኑ ለሸቀጦቻቸው ገበያ ያጣሉ፣ ከዚያም አልፎ የጥሬ እቃ አቅርቦት ምንጮቻቸው ይደርቃሉ፡፡ የምሥራቅ አፍሪካን ቀንድም የምንረዳው በዚሁ መንገድ ነው፡፡ በሱዳን ሰላም ከሌለ በኢትዮጵያ፣ በኤርትራ፣ በሶማሊያ፣ በጂቡቲ፣ በኬንያ፣ በሶማሊያም ሆነ በደቡብ ሱዳን ሰላም ሊኖር እንደማይችል ማስቀመጥ ይቻላል፡፡ የኢትዮጵያን ተጨባጭ ሁኔታ እንይ ካልን ደግሞ በምሥራቅ አፍሪካ ቀንድ መካከል የምትገኝ የቀጣናው ዕምብርት የሆነች አገር ናት፡፡ በአቀማመጧ ብቻም አይደል በስፋቷ፣ በተፅዕኖዋና በሕዝብ ብዛቷም የቀጣናው የልብ ትርታ ናት፡፡ የኢትዮጵያ ሰላም ማጣት ማለት ደግሞ በዙሪያዋ ያሉ አገሮችን እስከ ቀይ ባህር ያለውን ቀጣና የሚያናጋ ጭምር ነው፡፡
ኢትዮጵያ የምትገኝበት ቀጣና ውስብስብ የፖለቲካ ገጽታ የሚስተዋልበት አካባቢ ነው፡፡ ይህ የሆነው ደግሞ አንድም በአገር ውስጥ ለ27 ዓመታት በሰፈነው የዘር/የጎሳ ፖለቲካ የተነሳ ከባድ ቀውስ በኢትዮጵያ ተፈጥሯል፡፡ ይህ ደግሞ በዋናነት እኔ ብቻ ካልገዛሁና የፖለቲካ ሥልጣኑን ካልጠቀለልኩ ኢትዮጵያ የምትባል አገርን ጨርሶ አጠፋለሁ ብሎ የተነሳ ኃይል በመኖሩ የተፈጠረም ነው፡፡ ይህ መላው አገራችንን እየፈተነ ያለ ችግር ደግሞ ለጂቡቲም፣ ለሶማሊያም ሆነ ለመላው ዓለም የሚተርፍ ነው፡፡ በዚህ የተነሳ ይህን ዓይነት ነውጠኛ የብሔር ፖለቲካ ኃይልን መላው ዓለም ከኢትዮጵያ ጋር ተባብሮ መታገል ካልቻለ፣ ለእነሱም የሚተርፍ የሰላም ችግር መፈጠሩ አይቀርም ተብሎ ነው የሚታመነው፡፡ ይህን ኃይል መታገልና ማስወገድ ያለባቸው ለራሳቸው ሰላም ሲሉ ነው፡፡ የሰላም ጥናት አብሮነት ላይ ያተኮረ ነው፡፡ ዓውድ ቁልፍ ነው፡፡ የአፍሪካን ቀንድ መመልከት ያለብንም አንድን ነገር ነጥለን ሳይሆን፣ የተወሳሰበ ገጽታውን በመፈተሽ ጭምር ነው፡፡ ቀጣናዊ ፖለቲካው ከውስጣዊ፣ ውስጣዊና ቀጣናዊ ፖለቲካው ከዓለም አቀፋዊ ሰላም ጋር ተሳስረው ሲታዩ ነው የቀጣናውን ገጽታ የምንረዳው፡፡
ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያን ፖለቲካ የሚያወሳስቡ ጉዳዮች ምንድን ናቸው?
ዮናስ (ዶ/ር)፡– ኢትዮጵያ ውስጥ በደርግ፣ በኃይለ ሥላሴ፣ በምኒልክ፣ በዮሐንስና በቴዎድሮስ ዘመን የነበረው ፖለቲካ የዘር ጭቆና የሰፈነበት ነበር ተብሎ ተደመደመ፡፡ ለብሔር ጭቆና መልስ የሚሆነው ደግሞ የብሔር ፖለቲካ ነው ተብሎ መጣ፡፡ ይህ ከመነሻው ጀምሮ ስህተት የሆነ አረዳድና ድምዳሜ ነው፡፡ በማኅበረሰብ ሳይንስ የመንስዔና የውጤት አመክንዮ ሁልጊዜ አይሠራም፡፡ ለአንድ ችግር ብዙ ምክንያቶችና ውጤቶች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ በኅብረተሰብ ሳይንስ አንድ ምክንያትና አንድ ውጤት ብቻ የለም፡፡ በኢትዮጵያ የነበረውን የፖለቲካ ችግር የፈጠረው ብዙ ምክንያት እንዳለ እየታወቀ የዘር መድልኦን ብቻ አመክንዮ አድርጎ ማቅረቡ ከመነሻው ስህተት ነበር፡፡ ለምሳሌ አንድ ሰው ስንት ማንነቶች አሉት? አንተ ለምሳሌ ወንድ መሆንህ፣ ጋዜጠኛ መሆንህ፣ ክርስቲያን/ሙስሊም መሆንህና ሌላም ብዙ ማንነቶች አሉህ፡፡ ከእነዚህ ሁሉ ብዙ ማንነቶች ውስጥ ግን አንዱን የጎሳ ማንነት ብቻ ማዕከል በማድረግ የፖለቲካ ሥርዓት መፍጠር እጅግ አደገኛ ሆኖ ነው የምናገኘው፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ ኢትዮጵያ የምትከተለውን ዓይነት የዘር ፖለቲካ ሥርዓት የሚከተል አገር የለም፡፡ በዚህ ባለንበት ዘመን ከ193 የተባበሩት መንግሥታት አባል አገሮች ውስጥ የዘር ፖለቲካን በሕገ መንግሥት ደንግጋ የምትመራ አገር ኢትዮጵያና ኢትዮጵያ ብቻ ናት፡፡ በሩዋንዳ የዘር ፖለቲካ ማራመድና ማደራጀት ከባድ የአገር ክህደት ወንጀል ተደርጓል፡፡ ኬንያ፣ ናይጄሪያ፣ ጋናም ሆነ 55 የአፍሪካ አገሮች ብንዞር የጎሳና የዘር መሥፈርት ለፖለቲካ መሠረት ሲሆን አናገኝም፡፡ ያንን የሚያደርጉ አካላት ከተገኙ ሕገወጥና ተቀጪም ናቸው፡፡ ሆኖም ወደ ኢትዮጵያ ስትመጣ ይህ ተቃራኒ ሆኖ ነው የምናገኘው፡፡ እዚህ በዘርና በጎሳ ካልተደራጀ የፖለቲካ ፓርቲ ይፈርሳል ወይም ስኬታማ አይሆንም፡፡
ለአገር ውስጥ ግጭቶቻችን ዋነኛ ምክንያት እየሆነ ያለውና ችግሮቻችንን ያወሳሰበው በዋናነት የምንከተለው የጎሳ/የዘር ፖለቲካ ነው፡፡ ይህን የማንነት ፖለቲካ መዋቅራዊና ተቋማዊ በማድረጋችን በመካከላችን መጠራጠር፣ መከፋፈልና ግጭት እንዳያባራ አድርጎታል፡፡ እኔ አንተን እጠራጠራለሁ፣ አማራው የኦሮሞ፣ ኦሮሞውም የአማራው፣ ትግሬው የአማራው፣ አማራው የትግሬው ጠላት ሆኖ እንዲተያይ ሆኗል፡፡ እርስ በእርስ ከመጠራጠርና ከመጠላላት በስተቀር መተማመንና አንድነት በአገራችን መስፈን አልቻለም፡፡ ከፋፍለህ ግዛ ስለሆነ የፖለቲካችን አካሄድ፣ ገዥዎቻችንም ካልከፋፈሉ መግዛት ስለማይችሉ፣ በዚህ የተነሳ የውስጥ ፖለቲካችን ተበላሽቷል፡፡ የውስጥ ፖለቲካችን መበላሸት ደግሞ በቀጣናችንም ቢሆን የተበላሸ ፖለቲካ ውስጥ ከተተን፡፡ ይህ ደግሞ ቀደም ብዬ እንዳነሳሁት በውጭ ፖለቲካችንን አወሳስቦታል፡፡ ታሪካዊ የኢትዮጵያ ጠላቶችና እኛን ማዳከም የሚፈልጉ ኃይሎች በሙሉ ሊያጠቁን የሚያሰፈስፉት ያለ ምክንያት አይደለም፡፡ ይህ ሁሉ እሳትና ውስብስብ ችግር በሙሉ የተፈጠረው በውስጥ ፖለቲካችን ችግር መነሾነት ነው፡፡ እግዚአብሔር ይመሥገን አሁን ላይ ግን ይህን ሁሉ ችግር ተገንዝበን እሳቱን ለማጥፋት ጥረት ጀምረናል ማለት እችላለሁ፡፡
ሪፖርተር፡- ኢትዮጵያን ለቀውስ ተጋላጭ የሚያደርጋት የውስጥ ፖለቲካ ችግር ብቻ ነው ወይ? ኢትዮጵያንም ሆነ የምሥራቅ አፍሪካ ቀንድ አገሮችን ተጋላጭ የሚያደርጓቸው የቀውስ ሌሎች ምክንያቶች ምንድን ናቸው?
ዮናስ (ዶ/ር)፡- የተጋላጭነታችን መነሻ ምክንያት አንዱ የፖለቲካ ባህላችን ነው፡፡ ይህን በግልጽ መነጋገር አለብን፡፡ የተለየ እርግማን ወይም የፈጣሪ ቁጣ በእኛ ላይ ደርሶ አይደለም፡፡ ፖለቲካችን በንግግር ሳይሆን በጉልበት የሚያምን ነው፡፡ የዜሮ ድምር ጨዋታችንና አጥፍቶ የመጥፋት አካሄዳችን የዚህ የፖለቲካ ባህላችን ብልሽት ማሳያ ነው፡፡ ሌላው ራስን አለመቻል፣ በርትቶ አለመሥራትና ስንፍናችን ተጋላጭ ያደረገን ምክንያት ነው፡፡ የኢኮኖሚ ደካማነታችን የቀውስ ምንጫችን ነው፡፡ ሆኖም የኢኮኖሚ ደካማነት ከላይ ከፖለቲካችን አናት የሚነሳ ነው፡፡ ከፖለቲካ አወቃቀራችን የሚነሳ ነው የኢኮኖሚ ድክመታችን፡፡ እርግጥ ነው ለድህነትና ለድንቁርና የተዳረግንበት ምክንያት ፖለቲካችን ብቻ ሳይሆን ምንጩ ብዙ ነው፡፡ አንዳንዴ ይህ ጉዳይ ከዓለም አቀፍ ሁኔታ ጋር ተጋምዶም መታየት ያለበት ነው፡፡
ለአብነት ያህል ዋልተር ሩድኒ የተባለው ጸሐፊ አውሮፓዎች አፍሪካን እንዴት እንዳቆረቆዙ ባሳየበት ‹‹How Europe Underdeveloped Africa›› በሚል ባቀረበው ርዕስ መጽሐፍ፣ ስሜታዊ በሆነ መንገድ ሲሞግት ታየዋለህ፡፡ ያደጉት የበለጠ እያደጉ፣ ያላደጉት ግን ጭራሽ ወደኋላ እያሽቆለቆሉ እንዲሄዱ ዓለም አቀፉ የፖለቲካዊ ኢኮኖሚ ሥርዓት በእኛ ላይ ከረዥም ጊዜ በፊት ነው የበየነብን፡፡ ስለአፍሪካ እኮ እ.ኤ.አ. በ1884 በርሊን ላይ ባደረጉት ጉባዔ ነበር አውሮፓዎቹ የወሰኑት፡፡ ማንም አፍሪካዊ በሌለበት አፍሪካን ቅርጫ አድርገው ሊከፋፈሉ ተሰብስበው ዶልተዋል፡፡ ዛሬም ቢሆን በተባበሩት መንግሥታት ድርጅትና በአውሮፓ ኅብረት ሸንጎዎች ሲደረግ የምናየው የዚህ ግልባጭ ነው፡፡ የአፍሪካ ዕጣ ፈንታ ከራሱ ከአፍሪካዊው እጅ ወጥቷል፡፡ ስለአፍሪካ ያለ አፍሪካ ነው የሚወሰነው፡፡ ይህን ደግሞ ያስከተለው የፖለቲካ ባህል ብልሽት ብቻ ሳይሆን፣ በኢኮኖሚ ነፃ ወጥቶ ራስን በራስ ያለ መቻል ችግር ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ምዕራባዊያኑም ሆነ ሌሎች የውጭ ኃይሎች ኢትዮጵያን እግር በእግር እየተከተሉ ሰላም የሚነሱን ለምንድነው?
ዮናስ (ዶ/ር)፡– የውጭ ኃይሎች ጣልቃ ገብነት እየጎላ የመጣው ለምንድነው የሚለውን ጉዳይን በተመለከተ ግልጽ አመክንዮዎች ማቅረብ ይቻላል፡፡ ከእኛ ምንድነው የሚፈልጉት የሚለው መልሱ ቀላል ነው፡፡ በዋናነት ጥሬ ዕቃችንን ወይም የተፈጥሮ ሀብታችንን ይፈልጋሉ፡፡ ኢትዮጵያ የውኃ ሀብት አላት፡፡ ኢትዮጵያ በፍፁም ራሷን እንዳትችልና ቀና እንዳትል በማድረግ የተፈጥሮ ሀብቷን ለራሳቸው በሚፈልጉት መንገድ ለማዋል ነው፡፡ በመካከለኛው ምሥራቅ ጥሩ ባሪያ እኔ ነኝ ወይም ሁል ጊዜ የተሻልኩ አገልጋይ ነኝ ብለው ለምዕራባዊያን ራሳቸውን ለማሳየት የሚፎካከሩ ኃይሎች አሉ፡፡ የናይል (ዓባይ) ምንጭ የሆነችውን አገር ለመቆጣጠርና ለማስጎንበስ ረዥም ዘመን የተሻገረ ፍላጎትም በእነዚህ ኃይሎች ዘንድ አለ፡፡ አውሮፓዎችም ሆነ አሜሪካ የናይልን ምንጭ በመቆጣጠር እነሱ ለሚፈልጉት አገልጋይ አገር የውኃ ሀብቱን መስጠት ዋና ፍላጎታቸው እየሆነ መጥቷል፡፡ በዚህ የተነሳ ኢትዮጵያን ማዳከምና ማደህየት የዚህ ግዙፍ ሴራ ዋና ዓላማ ሆኖ ነው የተገኘው፡፡
ሌላው የውጭ ተፅዕኖ መነሻ ምክንያት ደግሞ ኢትዮጵያ የነጭ ዘር የበላይነት ርዕዮተ ዓለምን አለመቀበሏ የወለደው የፖለቲካ በቀል ነው፡፡ እ.ኤ.አ በ1896 ኢትዮጵያ የነጮች የበላይነትን ለማረጋገጥ የተደረገባትን ዘመቻ በአሸናፊነት መክታዋለች፡፡ ይህን ለመበቀል ለረዥም ዓመታት የተደገሰ ሴራ መኖሩን ብዙ ማስረጃዎችን የሚያቀርቡ መጻሕፍት አሉ፡፡ ኢትዮጵያ በዓድዋ ላይ ያሸነፈችውን የነጭ የበላይነት ትርክት ለመበቀል፣ ታሪክን መሠረት አድርጎ የሚሠራ ፖለቲካዊ አሻጥር አለ፡፡ ኢትዮጵያ በምሥራቅ አፍሪካ አካባቢ ነጥራ እንዳትወጣ ይፈለጋል፡፡ ከህንድ፣ ከሩሲያና ከቻይና ጋር ያላት ግንኙነት እየሰፋ መምጣቱም አይወደድም፡፡ ኢትዮጵያን ሳተላይት (ተከታይ አገር) ለማድረግ ስለሚፈለግ አገሪቱ ሚዛኗን ጠብቃ ከሁሉም ጋር በእኩል ደረጃ ግንኙነት መሥርታ እንድትኖር አይፈቀድላትም፡፡ እነዚህ ሁሉ ናቸው የውጭ ጣልቃ ገብነትን በኢትዮጵያ ላይ የጨመሩት፡፡
ሪፖርተር፡- ከምዕራባዊያን የሚሰጥ የሰላም አገነባብ መፍትሔ አይበጀንም፣ ከእነሱ የሚሠፈረው ከላይ ወደታች የሆነ (ሊበራል ፒስ ቢዩልዲንግ) መፍትሔ አያመጣም የሚሉ አሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በሁሉም መስክ ራስን ከቅኝ ተገዢነት ማላቀቅ (ዲኮሎናይዜሽን) አስፈላጊ መሆኑንም ያስቀምጣሉ፡፡ ይህ የዲኮሎናይዜሽን ጽንሰ ሐሳብ ምንድነው? የፓን አፍሪካዊነት ንቅናቄስ ምንድነው? ይህንን ቢያብራሩት?
ዮናስ (ዶ/ር)፡- በዚህ ጉዳይ ላይ ብዙ ሰዎች ጽፈዋል፡፡ አልጄሪያዊው ጸሐፊ አልበርት ካሙን ብዙ ጽፎበታል፡፡ ከእሱ በላይ ደግሞ ፍራንዝ ፋኖን ‹‹The Wretched of the Earth›› (የምድር እርግማኖች) ብሎ ባስነበበው መጽሐፍ ስለቅኝ ግዛት አስከፊነት ብዙ ጽፏል፡፡ ቅኝ ገዥነት (ኮሎኒያሊዝም) ራስህን እንድትጠላ ማድረግ ነው በዋናነት፡፡ በራስህ እንዳትተማመን ማድረግ፡፡ አንተነትህ የሚረጋገጠው እኔ በምሰጥህ ማስረጃ ነው ብሎ መደምደም፡፡ አንተ እንዲህ ነህ ብዬ የምበይነው እኔ ነኝ ማለት ነው፡፡ እኔ ነኝ የማሠለጥንህ ብሎ የሚነሳ ነው የምዕራባዊያን አካሄድ፡፡ አሜሪካ ወይም ምዕራባዊያን ለጥቁር ሰው ዘር ያላቸው አመለካከት ከእንስሳ ያልተሻለ ነው፡፡ ያልሠለጠኑ፣ ራሳቸውን የማይችሉና ከዝንጀሮና ከጦጣ ጋር የሚመሳሰሉ ብሎ እስከ መፈረጅ ይደርሳል፡፡ ይህን አመለካከት ስንረዳ ነው የኮሎናይዜሽንን ምንነት በተጨባጭ የምነገነዘበው፡፡ እነሱ በሚፈልጉት ቋንቋ መናገር፣ እነሱ ያሉትን ሃይማኖት መከተል፣ እንደ እነሱ መልበስ፣ ኮካ ኮላቸውንና በርገራቸውን ትክክል ነው ብሎ መቀበል፣ እነሱ ያሉት፣ የሚያሳዩትና የሚያስተምሩትን ሳያላምጡ መዋጥ፡፡ ከዚያ ውጭ በሌላ መንገድ ልሂድ ማለት ግን ልክ እንደ ሥልጣኔ ግጭት (Clash of Civilization) አድርጎ መበየንን የሚያመጣ ነው ቅኝ ተገዥነት፡፡ ይህ ደግሞ በሒደት ባርነትን እንደ ፀጋ እስከመቀበል የሚደርስ የአዕምሮ ቅኝ ተገዥነትን የሚያስከትል ነው፡፡
ዋናው ቅኝ የመገዛት ተፅዕኖ የአዕምሮ መገዛት ሲሆን፣ ከምዕራባዊያን የሚሰጠው ትክክል ነው ብሎ መቀበልን ያመጣል፡፡ ማሰብ የሚገባንን እንደ ሰው ከማሰብ ይልቅ እነሱ ያሉትንና የሰጡንን መቀበል ነው ኮሎናይዜሽን፡፡ ዲኮሎናይዜሽን ወይም ራስን ከተገዥነት ማላቀቅ ደግሞ ተቃራኒ ነው፡፡ ዲኮሎናይዜሽን እኔም እኮ እንደ እናንተው ፈጣሪ እኩል አድርጎ የፈጠረኝ ሰው ነኝ ብሎ ከማሰብ ይጀምራል፡፡ ምዕራባዊያኑ በመጽሐፍ ቅዱስ እንደሚሰብኩት አምላክ ሰውን የፈጠረው፣ እኩል አድርጎ በራሱ አምሳል መሆኑን መጀመሪያ ራሳቸው እንዲቀበሉት ማድረግ ይጠይቃል፡፡ እኛም ሰዎች ነን፣ እንችላለን ብሎ ማሰብና ሁሉም ራሱን ችሎ እንደሚቆም ማሳየት ነው፡፡ ዲኮሎናይዜሽን ከፓን አፍሪካዊ ፍልስፍና የተለየ አይደለም፡፡ ‹‹ኡቡምቱ›› የሚባለውን አብሮነትን የሚቀበል አፍሪካዊ እሴትንም ያቀፈ ነው ዲኮሎናይዜሽን፡፡ መጀመሪያ ምዕራባዊያኑን ከመሆን ተላቆ ራስን መሆን ነው ዲኮሎናይዜሽን የሚጠይቀው፡፡ ቅኝ ገዥዎች ግን ይህን ባልተከተለ መንገድ ነው አገር ወይም ሰላም እንገንባ የሚሉት፡፡ እኔ አውቅልሃለሁ ባይነት አሁንም አልቀረም፡፡ ምዕራባዊያኑ በአፍጋኒስታን፣ በሊቢያም ሆነ በእኛ ላይ ሊጭኑ የሚፈልጉት ይህንኑ ነው፡፡ ይህን ካላደረጋችሁ እያሉ የሰላም ቅድመ ሁኔታ ያስቀምጣሉ፡፡ ይህንን የቅኝ ገዥነት መንፈስ የተጫነው የሰላም ግንባታ ካላሸነፍንና በራሳችን አገር በቀል ዕውቀት መመርኮዝ ካልቻልን ዘላቂ ሰላም ለመገንባት ይከብደናል፡፡ በዚህ የተነሳ ነው የሰላም ግንባታችንም ሆነ በሁሉም የአገር ግንባታ መስክ ዲኮሎናይዜሽን (ራስን ከውጭ ተፅዕኖ ተገዥነት ነፃ ማውጣት) ያስፈልገናል በሚል ሐሳቡን ለማብራራት የሞከርኩት፡፡
ሪፖርተር፡- እኔ አውቅልሃለሁ ባይነቱ ከውጭ ብቻ አይደለም በውስጣችንም ያለ ነው ይባላል፣ ይህንን እንዴት ያዩታል?
ዮናስ (ዶ/ር)፡– ‹‹ከሰው መርጦ ለሹመት፣ ከእንጨት መርጦ ለታቦት›› የሚለው ብሂል ከአማራው ክፍል ብቻ የመነጨ ነው ብሎ መደምደም ትክክል አይደለም፡፡ ለምሳሌ ግሪኮች ኅብረተሰቡን በሦስት ይከፍሉ ነበር፡፡ የተመረጠ ወይም ወርቅ ብለው የሚጠሩት ክፍል አለ፡፡ ሊቅም ገዥም እየተባለ በግሪክ የሚነግሠው ከዚህ ክፍል የሚመጣው ነበር፡፡ በሁለተኛው መደብ ላይ ያለው አራሹ ሲሆን፣ በሦስተኛው እርከን ደግሞ ወታደሩ ነው፡፡ በቻይና ውስጥ 74 በመቶ የሀን ማኅበረሰብ ነው፡፡ ቻይና ከ56 ያላነሱ ብሔረሰቦች ያሉባት አገር ስትሆን፣ በአገር ደረጃ የመሪነቱን ቦታ የያዘው 90 በመቶ የሀን ማኅበረሰብ ነው፡፡ ጃፓን ብንሄድ ይህን መሰል ማኅበራዊ መዋቅር እናገኛለን፡፡ በብዙ አገሮች ውስጥ አፍሪካን ጨምሮ ይኼው በአንድ ኃይል ተፅዕኖ ሥር የመውደቅና አውቅልሃለሁ ባይነት ያለ ነገር ነው፡፡
ይህ ማኅበራዊ መስተጋብር ግን በጊዜ ሒደትና በሥልጣኔ የሚሻሻልና እየተቀየረ የሚሄድ ነው፡፡ በአገዛዝና በአስተዳደር በኩል ይህ ነገር መከሰት አደገኛ ነገር ነው፡፡ የእኛ አገር ለረዥም ጊዜ ሳይቀየር በመቆየቱና ከዚህ አዙሪት አለመላቀቁ ችግር ፈጥሯል፡፡ በሌሎች አገሮች ቻይናና እንግሊዝ ጨምሮ ይህ እየተለወጠ ነው፡፡ በእኛም አገር ቢሆን አሁን ላይ ጅምር እየታየ ነው፡፡ እኔ በዕድሜ ዘመኔ በተሻለ ነፃነት በሕዝብ ተመርጦ መሪ ወደ ሥልጣን ሲወጣ ያየሁት በቅርብ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ተጠያቂነት ያለው ሥርዓት ለመፍጠር መልካም አጋጣሚ ነው፡፡ አውቅልሃለሁ ባይነት የፖለቲካ ባህልን በማስተካከል ተጠያቂነት ያለው ሥርዓት በመፍጠር ነው ማስወገድ የምንችለው፡፡ ዕውቀት መር የሆነ ማኅበረሰብ እየፈጠርን ስንሄድ የሚቀር ይመስለኛል፡፡ ከዚያ ውጭ ግን አውቅልሃለሁ ባይነት በመላው ዓለም ነበር፣ ኢትዮጵያ ውስጥም ነበር፡፡ በሒደት እየቀነሰና እየቀረ የሚሄድ ይሆናል፡፡
ሪፖርተር፡- በኢትዮጵያ ለብሔራዊ መግባባት ውይይት መነሻ ጥረቶች ተጀምረዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ለብሔራዊ መግባባት ይበጃል በሚል የሕወሓት አመራሮችን ጨምሮ የፖለቲካ ሰዎችን ከእስር የመልቀቅ ዕርምጃ ተወስዷል፡፡ ነገር ግን ለብሔራዊ ዕርቅና መግባባት ይበጃል ተብሎ የተወሰደው ውሳኔ ሌላ ውዝግብ ይዞ ብቅ ብሏል፡፡ ለብሔራዊ መግባባት ተብለው የሚወሰዱ ዕርምጃዎች ለምን የብሔራዊ አለመግባባት ምንጭ እንደሚሆኑ ቢያስረዱን?
ዮናስ (ዶ/ር)፡- ሰላምን ለመፈለግ ወደ ጫካ መሄድና ወደ መጋደል ሳይገባ፣ እንዴት ሰላምን በሰላማዊ መንገድ እንፍጠር ተብሎ በአገር ደረጃ ምክክር ለማድረግ ጥረት መጀመሩ ትልቅ ሥራ ነው፡፡ የጦርነት ባህልን በሰላም እንተካ ተብሎ መታሰቡና የምክክር መድረክ ለማቋቋም መሞከሩ በአጭሩ በጎና የሚወደስ ተግባር ነው እላለሁ፡፡ ለዚህ ይረዳል ተብሎ የሕወሓት አመራሮችን ጨምሮ በቅርቡ ብዙ የፖለቲካ አመራሮች ከእስር ሲፈቱ ዓይተናል፡፡ ሆኖም የሕወሓት አመራሮች መፈታታቸው ግራ መጋባትና መደናገጥን በኅብረተሰቡ ውስጥ ፈጥሯል፡፡ እኔ ግን የሕዝቡን ቁጣና ስሜት ሳይ አትገረምብኝ እንጂ እንዲያውም ደስ ነው ያለኝ፡፡ በዋናነት ሕዝቡ ጉዳቱንና ስሜቱን በዚህ ደረጃ መግለጹ ነው ያስደሰተኝ፡፡ በኃይለ ሥላሴ ጊዜ ያደግኩ ሰው እንደ መሆኔ ሥዩመ እግዚአብሔር የሆኑት ንጉሡ ውሳኔ ቢሰጡ ይህን ዓይነት ስሜት ከሕዝቡ ይንፀባረቅ ነበር ወይ ብዬ ተመልሼ እንዳስታውስ አድርጎኛል፡፡ በደርግ አገዛዝ ዘመንስ ውሳኔው ምን ያስከትላል? በኢሕአዴግ ዘመንስ ቢሆን ስንት በመቶ ሕዝብ ነበር የመንግሥትን ውሳኔ በዚህ መንገድ ሊቃወም የሚችለው የሚል ጥያቄ ተመላልሶብኛል፡፡ አሁን ሕዝቡ የመንግሥትን ውሳኔ እኔ የመረጥኩትን ሳያማክር፣ ሚዲያው ሳያውቅና ተቃዋሚዎች ሳይነጋገሩ ብሎ መንግሥትን ሲቆጣ እኔ ደስ ነው ያለኝ፡፡ ሕዝቡ መንግሥትን ራሱ ወጥቶ በመምረጡ ተጠያቂ ለማድረግ መሞከሩን ያየሁበት አጋጣሚ ነበር፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጭምር በግልጽ ሲናገሩ ማየት የበለጠ የሚያረካ ነበር፡፡ ተቃዋሚዎች ከመንግሥት ጋር አንድ ላይ ሆነው በሕግ ማስከበር ዘመቻ ሲሠለፉ ያየንበት የታሪክ አጋጣሚ ነው ያለው፡፡ አንድ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ የሚኒስትርነትን ሥልጣን ሲይዝ ያየነው አሁን ባለንበት ወቅት ነው፡፡ ይህ ሁሉ ለእኔ አዲስ ዓይነት የፖለቲካ ልምምድ ውስጥ መግባታችንን የሚያመለክት ነው፡፡
እንደ አንድ የሰላም ተመራማሪ ለእኔ ከምንም ነገር ትንሽ ሰላም ትሻለኛለች፡፡ የመንግሥትን ውሳኔ ለመቀበል የተቸገሩ ወገኖች ብዙ ነገሮችን ማስተዋል አለባቸው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሲመረጡ ለማመን ተቸግረው የነበሩትና ከኢትዮጵያ ጋር የሻከረ ግንኙነት የነበራቸው የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን፣ ከዚህ ውሳኔ በኋላ አቋማቸው ሲለዝብ ነው ያየነው፡፡ የኢትዮጵያና የአሜሪካ ግንኙነት የመስተካከል ፍንጭ የታየው የእስረኞቹ መፈታትን ተከትሎ በሁለቱ መሪዎች መካከል የስልክ ግንኙነት ከተደረገ ወዲህ ነው፡፡ የሚቃወሙ ሰዎች የዴሞክራሲ ባህል ነውና አሳማኝ ሆኖ ካላገኙት መቃወም መብታቸው ነው፡፡ ከእስር የተፈቱ ሰዎችን በተመለከተ እኔ ከሰላም ግንባታ አኳያ በበጎ ነው ያየሁት፡፡ ከሰላም ግንባታ ሒደት አንዱ ነው፡፡ በነገራችን ላይ የሰላም ግንባታ ምንነትን እስካሁን አልፈታነውም፡፡ የሰላም ግንባታ የተግባቦት ግንባታ ማለት ነው በአጭሩ ሲቀመጥ፡፡ በጠላትነት፣ በጥርጣሬና በፍራቻ የሚተያዩ ወገኖች አካሄዳቸውን ቆም ብለው ዓይተው ግንኙነታቸውን ዳግም ለማጠናከርና ወደ ተሻለ መንገድ ለመውሰድ የሚጥሩበት ነው፡፡ የሰላም ግንባታ በመሬት ላይ ሳይሆን፣ በአስተሳሰብ ላይ ነውና የሚጀምረው ሁለት ወገኖች አመለካከታቸውን ቀይረው ተነጋግረውና ተግባብተው ለመኖር ሲወስኑ ነው የሰላም ግንባታ በተጨባጭ ተጀመረ የምንለው፡፡ ምንጊዜም አዲስ ነገር ሲጀመር ጥያቄ ያስነሳል፡፡ ጥያቄ መቅረቡም ተገቢ ነው፡፡ አዲሱ የብሔራዊ ምክክር ኮሚሽን የማዋቀር ሒደትም ሆነ እስረኞችን የመፍታት ሒደት፣ ከዚህ አንፃር ጥያቄ ቢያስነሳም ለሰላም ግንባታ ይበጃል እላለሁ፡፡
ሪፖርተር፡- ሰላምን በኢትዮጵያ ተቋማዊ ለማድረግ እንቅፋት ከሆኑ ነገሮች ሕገ መንግሥቱ አንዱ ነው ሲሉ ይደመጣሉ፡፡ ይህን ቢያብራሩልን?
ዮናስ (ዶ/ር)፡– ሰላም ተቋማዊ እንዳይሆን እጅግ አሳፋሪ በሆነ መንገድ ግጭትና ጦርነት በመቀስቀስ የሚተጉ ኃይሎች ተሠልፈዋል፡፡ ሁልጊዜ ረብሻ በመፍጠርና በጦርነት ለመኖር የሚተጉ ግለሰቦችም ሆነ ተቋማት አሉ፡፡ የተለያዩ ነገሮችን እንደ ምክንያት በመፍጠር ሁልጊዜ እነሱ ብቻ ግጭት እየፈጠሩና ደግሞ አስታራቂ ሆነው እየቀረቡ ለመኖር የሚፈልጉ ኃይሎች አሉ፡፡ ሰው ሲባላ እነሱ ግን የግጭት ነጋዴና አትራፊ ሆነው ለመኖር ይታትራሉ፡፡ ይህንን ስትራቴጂያቸውን ተቋማዊ ያደረጉት ደግሞ በሕገ መንግሥታችን ጭምር ነው፡፡ የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 39 ሕዝቦች ከአንድነት ይልቅ ልዩነትንና መከፋፈልን እንዲመርጡ ሆን ብሎ የሚገፋፋ ይዘት ያለው ነው፡፡ ለብዝኃነት መስፈን ያደረግነው ነው ቢሉም እንደ እነሱ ግን አሀዳዊና እኔ አውቅልሃለሁ ባይ የለም፡፡ በግጭት ለማትረፍ ሲሉ አንተ እንዲህ ነህ፣ እንዳትጨቆን ላደርግህ ነው በሚልና ሕዝብን በማደንቆር ለመበዝበዝ ነው ሲጠቀሙበት የኖሩት፡፡ ስለአገር አንድነት ስትናገር ነፍጠኛና አሀዳዊ እያሉ ይበይኑሃል፡፡ ጠባብ፣ ትምክህተኛና ብዝኃነት ጠል እያሉም ይፈርጃሉ፡፡
ይህ ልክ እንደ ቅኝ ገዥዎች ሌላውን ጥገኛ (ፓራሳይት) አድርጎ ለማኖር ያለመ፣ ቀውስን በመነገድ ለማትረፍ የሚተጋ ሥርዓት በሕገ መንግሥቱ ተቋማዊ መደረጉ ነው የሰላም ጠንቅ በኢትዮጵያ፡፡ ሕገ መንግሥቱ በውስጡ ብዙ ጠቃሚና ጥሩ ነገሮች ቢኖሩትም፣ ነገር ግን ጊዜ ጠብቆ የሚፈነዳ አቶሚክ ቦምብም የያዘ ነው፡፡ የሰላም ባህል እንዲያድግና ሰላም ተቋማዊ እንዲሆን ከተፈለገ ኅብረተሰቡ እነዚህን የሰላም ጠንቅ የሆኑ የሕገ መንግሥት አንቀጾች ሊመክርባቸውና አንድ መፍትሄ ሊወስድባቸው ይገባል፡፡ ለዘመናት የኖሩ ሕዝቦች ይህ ሕገ መንግሥት ከወጣ በኋላ ልዩነታቸው ሰፍቷል፡፡ ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ስላሉት ሳይሆን ይህ በይቅርታ እንኑር፣ እንደመር የሚለው የሰላም ጥሪ በበጎ መንገድ ካየነው ለአገራችን የሚበጅ ነው፡፡ ለኢትዮጵያ መሠረታዊ ችግር ኤርትራን ከኢትዮጵያ በመቀነስ ሳይሆን፣ በመደመርና ለሰላም አብሮ በመሆን ላይ ቢሠራ ለሰላም ይበጃል ነው የምለው፡፡ የብሔራዊ መግባባት ምክክሩ ይህን ሁሉ ነገር ከግምት ውስጥ ባስገባ መንገድ፣ ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና ልማት የሚበጅ ሕገ መንግሥት ስለመቅረፅ መወያየት አለበት ነው የምለው፡፡
