
24 March 2019
በአሥራዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ እያለች ትዳር እንድትይዝ በሚጠብቅ፣ ስኬቷን በትዳር አጋሯ የገቢ ሁኔታ በሚመዝን፣ ዝምተኛና አንገት ደፊ መሆኗን ከጨዋነት በሚቆጥር ማኅበረሰብ ውስጥ ሴት ሆኖ መፈጠር ፈተናው ብዙ ነው፡፡ እንዲህ ባለ ማኅበረሰብ ውስጥ ሴቶች ስኬታማ የሚያደርጋቸውን የሴትነት ሚዛን ለመድፋት የሕይወት ዘመን ትግል ይጠበቅባቸዋል፡፡
ወንድ ሲወለድ እልል ብሎና ጥይት ተኩሶ፣ ሴት ስትሆን ደግሞ ትሁን በሚልና ፆተኝነት ሥር በሰደደበት ማኅበረሰብ ውስጥ ሴቶች ጥሩ የትዳር አጋር ሆነው እንዲወጡ ማድረግ ትልቅ ቦታ ይሰጠዋል፡፡
በትምህርቷ ወይም በሥራዋ ልታስመዘግብ የምትችለው ልህቀት ጥሩ ሚስት፣ እናት ከመሆን አይወዳደርም፡፡ በርካቶች የሴትን ስኬት በባሏ ገቢ፣ አልያም ለልጆቿ ጥሩ እናት ከመሆኗ አንፃር ይለኩታል፡፡ ቀጭን ፈታይ እመቤት መሆኗም በቂ የሆነበት ማኅበረሰብ አለ፡፡ እጅ የሚያስቆረጥም ቁሌት ማቁላላት በመቻሏ የነገው ሕይወቷ የሰመረ ሊሆንና ጥሩ ባል ልታገኝ እንደምትችል ማስተማመኛ ተደርጎ አሁንም ድረስ ይታሰባል፡፡ ቅልስልስና አንገት ደፊ፣ ነገሮችን ስታውቅ እንደማታውቅ መሆኗም ከብልህነት ይቆጠርላታል፡፡ ዓይነግቡ የምትባል ዓይነት ከሆነች ደግሞ ባትማርም ግድ የለም፡፡ ቆንጆ ሚስት መሆኗ በቂዋ ሊሆን ይችላል፡፡ ቆንደ ሚስት መሆኗ በቂዋ ሊሆን ይችላል፡፡ 12 የዶሮ ብልት አውጥታ ጥሩ ዶሮ ወጥ መሥራት ካልቻለች ደግሞ መዘባበቻ መሆኗ አይቀርም፡፡ ውርደቱም ለእሷ ብቻ ሳይሆን ለወላጆቿም ይተርፋል፡፡ ጥሩ ሚስት መሆን ካልቻለች ባሏ እንደተውሶ ዕቃ ሚስቱን ለቤተሰቦቿ ሊመልስላቸው የሚችልበት አጋጣሚ ለኢትዮጵያ ብርቅ አይደለም፡፡ ባል ሥራ ውሎ ሲመለስ ሚስት እጅ የሚያስቆረጥም ምግብ አዘገጃጅታ፣ እሷም ተቆነጃጅታ መጠበቅ አለባት ብሎ የሴትነት መመዘኛ መስፈርቱን በዚህ መልኩ በቃኘ ማኅበረሰብ ውስጥ የሕይወት ጥሪን ተከትሎ ስኬታማ መሆን ፈተና ነው፡፡
በተለይም ሴቶች ወደ አመራርና ሌሎች የፖለቲካ መዋቅሮች ውስጥ ለመግባት ዕውቀቱ ሳያንሳቸው ስኬታማ ለመሆን ግን ብዙ ውጣ ውረዶችን ማለፍ ይኖርባቸዋል፡፡
‹‹የፖለቲካ ጽሑፎችን ለወንዶች፣ የመዝናኛ ጽሑፎችን ለሴቶች ነው የሚሰጡት፤›› የምትለው የ30 ዓመቷ ወ/ሪት ከውሰር እድሪስ፣ ሴቶች እንደ ፖለቲካ ያሉ ጠንከር ያሉ አገራዊ ጉዳዮች እንደማይመለከታቸው ተደርጎ እንደሚታሰብ ትናገራለች፡፡ በማኅበረሰብ ውስጥ በከፍተኛ መጠን ሰርፆ የሚገኘው ፆታን መሠረት ያደረገ ኢፍትሐዊነትን ወንዶችም ሴቶችም እያወቁትና ሳያውቁት እያራመዱት ይገኛሉም ትላለች፡፡
ሴቶች ፖለቲካ ውስጥ ገብተው ለውጥ መፍጠር እንደሚችሉ የማይጠራጠሩ ሰዎች እንኳ ባህሉ ካሳደረባቸው የፆተኝነት ተፅዕኖ ነፃ ላይሆኑ ይችላሉ፡፡ ሆስፒታል ውስጥ ነጭ ገዋን የለበሱ ወንዶችን ‹‹ዶክተር››፣ ሴቶችን ደግም ‹‹ሲስተር›› ብሎ መጥራት አመራር ላይ የሚቀመጠውን ወንድ፣ ረዳቱን ደግሞ ሴት እንድትሆን መጠበቅም የተለመደ ነው፡፡ ሥር የሰደደው ፆታን መሠረት ያደረገ አድልዎ እኩልነትን ለመፍጠር በሚታገሉ አንዳንድ ግለሰቦችም ላይ ጭምር ሊንፀባረቅ ይችላል፡፡
ይኼንን የመሰለ መሠረታዊ ችግር ባለበት አገር ውስጥ ጥቂት የማይባሉ አመራር ላይ የሚታዩ ሴቶች ቢኖሩም፣ የፖለቲካ ጉዳይ የወንዶች ብቻ ተደርጎ ይታሰባል፡፡ በፀጉር ቤቶችና በሌሎች ሴቶች ሊገኙባቸው በየሚችሉባቸው ቦታዎች ሁሉ የመዝናኛና የፋሽን መጽሔቶች ብቻ ተመርጠው የመቅረባቸው ጉዳይ የዚህ እውነታ ማሳያ ነው፡፡ ‹‹ፖለቲካ ለወንዶች እንጂ ለሴቶች አይደለም፤ የሚለውንም አስተሳሰብ ሴቶችም ተቀብለውት እየኖሩ ነው፤›› የምትለው ከውሰር፣ የአርበኞች ግንቦት ሰባት አባል እንደሆነች ትናገራለች፡፡
የፖለቲካው ርዕዮት ማኅበራዊ ፍትሕ ማምጣት እንደሆነ፣ ሴቶችን አግልሎ ማኅበራዊ ፍትሕ ማምጣት እንደማይቻልና ሴቶች ወደ ፖለቲካው እንዲቀላቀሉ ፓርቲው የዘመቻ ሥራ እየሠራ እንደሚገኝ ትገልጻለች፡፡ ወንዶች የፓርቲው አባል ለመሆን በራሳቸው ተነሳሽነት ፎርም ሞልተው በሚመዘገቡበት የፖለቲካ ንቅናቄ ውስጥ ያሉት ሁለት ሴቶች ብቻ እንደሆኑም ታክላለች፡፡ ሴቶች ወደ ፖለቲካው እንዲገቡ ግን የጉትጎታና የማነሳሳት ሥራ መሥራት አስፈልጓል፡፡ ‹‹የምትርቂው ጉዳይ የአገር ጉዳይ ነው፡፡ አንቺ ተቀምጠሽ ሌላ ሰው እንዲወስንልሽ አታድርጊ ለአንቺም አገርሽ ነው ብለን ወትውተን፤ ፖለቲካ አልወድም፣ አሁን ያለው ነገር ይለይለትና እወስናለሁ ይሉናል፤›› የምትለው ከውሰር፣ ‹ከባለቤቴ ጋር ተገጋግረን እንወስናለን› የሚሉና ስልካቸውን አጥፍተው የሚደበቁ እንደሚያጋጥማት ትናገራለች፡፡ ከውሰርም ብትሆን ወደ ፖለቲካው ለመግባት የደፈረችው በፆታ እኩልነት የሚያምን፣ መሪ ትሆናለች እያለ ያሳደጋት አባት ስላላት እንጂ ዕድሉ ስለተመቻቸላት አለመሆኑን ታስረዳለች፡፡
‹‹አንድ ቀን መሪ ትሆኛለሽ›› እየተባለች ማደጓ ፖለቲካን እንድትደፍር አድርጓታል፡፡ ፖለቲካ ነክ የሆኑ ጽሑፎችን ማንበብ የጀመረችውም ገና በልጅነቷ ነበር፡፡ የመጀመርያ ዲግሪዋን የጨረሰችው በሕግ ሲሆን፣ በጆርናሊዝምና በሊደርሺፕ የትምህርት ዘርፍም ተመርቃለች፡፡ ወደ ፖለቲካ ያዘነበለው ፍላጎቷ የኢትዮጵያ የምርጫ ሒደት ፍትሐዊና ሰላማዊ እንዲሆን የበኩሏን እንድትሠራ ይገፋፋታል፡፡ አርበኞች ግንቦት ሰባትን የተቀላቀለችው ከወራት በፊት ሲሆን፣ ለጊዜው የሴቶች የፖለቲካ ተሳትፎ እንዲጨምር የዘመቻ ሥራ በመሥራት ላይ ትገኛለች፡፡ ሌሎችን ለማብቃት ስትጥር ግን ትዳር እንድትይዝ የሚጎተጉቷት ጓደኞቿና የሚያውቋት የሰፈር ሰዎች የሴት ልጅ ወግ ማዕረግ ብለው ወደሚያስቡት የሕይወት መስመር እንድትገባ ይገፋፏታል፡፡ ዝግጁ አለመሆኗን ስትነግራቸው ደግሞ ‹‹ሴት ልጅ ስትማር ችግሩ ይሄ ነው›› የሚል አስተያየት ይሰነዝራሉ፡፡
ፖለቲካ ላይ በሚኖራት ተሳትፎ የራሷን አሻራ ለማኖር ቅድሚያ እንደምትሰጥ የምትናገረው ከውሰር ሴቶች ዝግጁ ሳይሆኑ ወደ ትዳር እንዲገቡ ግፊት ሲደረግ ፍላጎታቸው እንኳ ከግምት ሳይገባ ነው ትላለች፡፡ ትኩረታቸውን በሥራቸው ላይ ባደረጉ መጠን ሳያገቡ መቆየታቸው የሚያሳስበው ማኅበረሰብ ሁሉን ትተው ወደ ትዳር እንዲገቡ ጫና ማሳደሩ የሴቶች ስኬት ከእናትነትና ሚስትነት የዘለለ እንዳይሆን የሚያደርገው አጋጣሚ ነው፡፡ እነዚህን እንቅፋቶች አልፈው ፖለቲካው መዋቅር ውስጥ አልፈው የአመራርነት ደረጃ ላይ የሚደርሱ ጥቂት የማይባሉ ቢኖሩም፣ ከፈተና ነፃ አይደሉም፡፡
በአንድ ወገን እናት ሆኖ ቤተሰብን መምራት፣ በሌላው ደግሞ በትልልቅ የአገር ጉዳዮች ላይ ውሳኔ ሰጪ ሆኖ ቦታው ላይ መቆየት ሊከብድ ይችላል፡፡ የፖለቲካ ምኅዳሩ በወንዶች ለወንዶች እንዲመች ተደርጎ መሠራቱ፣ የማኅበረሰቡ ተፅዕኖ ሴቶች የወንዶችን ያህል ስኬታማ እንዳይሆኑ ያደርገዋል የሚሉት ‹‹የኢትዮጵያ ሴቶች የፖለቲካ ትግል ትላንት እና ዛሬ›› በሚል ኢምፓወር አፍሪካ ባዘጋጀው መድረክ ላይ የመወያያ ጥናት ያቀረቡት ወ/ሮ የልፍኝ አበጋዝ ናቸው፡፡
እንደ እሳቸው ገለጻ፣ ሹኹቻና ተንኮል በሚበዛበት የፖለቲካ መድረክ ሥራው ከሚጠይቀው ልፋት ያልተናነስ ጨዋታውን ተጫውቶ ማለፉ ግድ ነው፡፡ ለዚህም ከሚኖራቸው የሙያ ዝግጅት ባሻገር ሴረኛ መሆን መቻል ያስፈልጋል፡፡ ይኼንንም ለማድረግ ከሥራ ሰዓት ውጪ ከሰዎች ጋር መገናኘት፣ መተዋወቅና ጓደኝነት ወይም ትስስር መፍጠር ያስፈልጋል፡፡
‹‹ከ11 ሰዓት በኋላ አምሽቶ ከሰዎች ጋር እየጠጡ ለመጫወት ጊዜ ያስፈልገናል፡፡ እኔ እስከ ምሽት አምስት ሰዓት ስጠጣ ቆይቼ ቤቴ ስገባ ከሰዎች ጋር ኔትወርክ ሳደርግ ነው የቆየሁት ብል ምን ሊፈጠር እንደሚችል አስቡት፡፡ ይህ ግን ለወንዶቹ ቀላል ነው፤›› የሚሉት ወ/ሮ የልፍኝ፣ እንዲህ ባሉት አጋጣሚዎች ከሰዎች ጋር መተዋወቅና ትስስር መፍጠር ካልተቻለ በአመራር ቦታዎች ላይ መቆየት ለሴቶች ችግር እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ከሰዎች ጋር መተዋወቅና ራስን መሸጥ ካልተቻለ መታወቅ እንደማይኖር፣ መታወቅ ካልቻሉ ደግሞ ለተሻለ ኃላፊነት መሾምም ሆነ በተሰጣቸው ቦታ ላይ መቆየት ከባድ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡
‹‹ራሳችንን መሸጥና ተወዳዳሪ መሆናችንንም ማሳየት አለብን፡፡ ብልጥ ሆኖ መደራደርና ማሳመን መቻል የግድ ነው፡፡ ለሙያው ከሚያስፈልገው ዕውቀት ያልተናነሰ ብስለት በተሞላበት ሁኔታ ራስን መሸጥ፤›› ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ የወንድን የበላይነት በሚሰብክ ማኅረሰብ ውስጥ ላሉ ሴቶች ደግሞ ፖለቲካው ውስጥ ስኬታማ ለመሆን ከወንዶች የበለጠ መልፋትን ይጠይቃል፡፡ በራስ መተማመን ትልቁ ሀብት መሆኑን ተረድቶም መሥራት እንደሚችሉ ማሳየትና ማሳመንም ወሳኝ ነው፡፡
በውይይቱ ላይ ዋና ተሳታፊ ሆነው የቀረቡት የቀድሞዋ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ዋና ዳይሬክተርና የመንግሥት ቃል አቀባይ ወ/ሮ ሰሎሜ ታደሰ ደግሞ በራስ ከመተማመን ይልቅ ቅድሚያ ሴቶች የተሰማቸውን ሳይሸማቀቁ መናገር እንዲችሉ ማድረግ ወይም ማስቻል ይገባል ብለዋል፡፡ ‹‹ሰዎች የሚያውቁትን ነገር በድፍረት ሲናገሩ እየሰማንና እውነታውን እያወቅን ዝም እንላለን፡፡ ሀቁን እያወቅን ብንናገር ሰው ምን ይለናል በሚል ተሸማቀን ሳንናገር የምንቀር ስንቶቻችን ነን?›› ሲሉ የሚጠይቁት ወይዘሮዋ በቅድሚያ ሰዎች የሚያውቁትን ሳይሸማቀቁ እንዲናገሩ፣ የማያውቁትን አናውቅም እንዲሉና የሚሰማቸውን በነፃነት እንዲናገሩ መሠራት አለበት ይላሉ፡፡
የኢትዮጵያ ባህል ሰዎች ሳይሸማቀቁ የተሰማቸውን እንዲገልጹ የሚደግፍ አለመሆኑ ዋናው ችግር እንደሆነም ይናገራሉ፡፡ መልካም የሚባሉት ሰዎች ድምፃቸው የማይሰማ አንገታቸውን የደፉ ናቸው ተብሎ በሚታሰብበት ዓለም ስሜትን መግለጽ ከጋጠወጥነት ሊያስቆጥር እንደሚችል የታዘቡትን ከገጠመኞቻቸው እያዋዙ አቅርበዋል፡፡ እንዲህ ያሉ ተፅዕኖዎች በሴቶች ላይ ደግሞ እንደሚበረቱና ሰብሮ መውጣትም ፈታኝ እንደሆነ አክለዋል፡፡
‹‹የተሰማቸውን ሳይፈሩ የሚናገሩ፣ ከባድ ጥያቄዎችን የሚያነሱና ሰው ምን ይለኛል ብለው የማይሸማቀቁ ሕፃናት ብቻ ናቸው፤›› የሚሉት ወ/ሮ ሰሎሜ፣ ሕፃናትን ለማስረዳት የሚከብዱ ጥያቄዎችን አዋቂዎች በቁጣና በማስፈራራት የማለፍ ልማድ የችግሩ መንስኤ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ስለፆታዊ ግንኙነት፣ ስለመራቢያ አካል፣ ስለሃይማኖትና ስለፈጣሪ በጠየቁ ቁጥር የሚወርድባቸው ቁጣና ተግሳጽ ከፍ እያሉ ሲሄዱ መጠየቅና የተሰማቸውን መናገር እንዳይደፍሩ ያደርጋቸዋል፡፡ በዚህ ላይ ደግሞ ሴት ልጅ ቅልስልስ፣ አንገት ደፊ እንድትሆን ይጠበቅባታልና ከወንዶች የበለጠ የተፅዕኖው ሰለባ ትሆናለች፡፡ በዚህ ሁሉ አልፈው ራሳቸውን ለመሆን የሚሞክሩ ደግሞ ዋጋ ይከፍላሉ ብለዋል፡፡
‹‹እኔ ኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ስገባ በአንድ እጇ ሲጋራ እያጨሰች በአንድ እጇ መኪና የምትነዳ ሴት መጣችላችሁ ጉድፈላ ተባለ፡፡ እኔ ደግሞ እልህ ይዞኝ እነሱ የሚሉትን አደርግ ነበር፣ ዋጋ ከፍዬበታለሁ፤›› ሲሉ ከራሳቸው ሕይወት ጋር አገናኝተው ራስን መግለጽን በማይደግፍ ማኅበረሰብ ውስጥ ራሳቸውን ለመሆን የሚሞክሩ ዋጋ እንደሚከፍሉ ያስረዳሉ፡፡
ስለዚህም ራስን መግለጽ ከሁኔታዎች ጋር ሚዛናዊ ሆኖ ተግባራዊ የሚደረግበትን መንገድ መፈለግ ግድ ነው ብለዋል፡፡ ከዚህ ባሻገርም ሴቶች በፖለቲካ ምኅዳሩ እኩል ተሳትፎ እንዲኖራቸው ዕድል መስጠት መለመድ እንዳለበት በውይይቱ ላይ ተነስቷል፡፡ ‹‹ወደ እዚህች ዓለም ሹክክ ብለው ገብተው ሹክክ ብለው የሚመለሱ ብዙ አሉ፤›› የሚሉት ወ/ሮ ሰሎሜ ሁሉም እንደ ችሎታው የሚሠራበትን ዕድል ማጨናገፍ ትክክል አይደለም ብለዋል፡፡
ወ/ሮ የልፍኝ ባቀረቡት ጥናት ኢትዮጵያውያት በፖለቲካ ላይ ያላቸውን ተሳትፎ በየአገዛዝ ዘመኑ ምን እንደሚመስል አሳይተዋል፡፡ ሴቶች ቤትና ንብረት በስማቸው ማፍራት በማይችሉበት ዘመን አመራር ላይ መጥተው ታሪክ መሥራት የቻሉ ሴት ነገሥታት ነበሩ፡፡ የንጉሥ ሚስትና ልጅ በመሆን በደም ሐረግ በሚተላለፍ የሥልጣን ተዋረድ ገብተው ታሪክ የሠሩ አንደ እቴጌ ጣይቱ፣ ንግሥተ ሳባ፣ እቴጌ ሰብለ ወንጌል የመሳሰሉ ሴት የአገር መሪዎች እንደነበሩ አስታውሰዋል፡፡ እንደ ዮዲትና ፉራ ያሉትም በደም ከሚተላለፍ የሥልጣን ተዋረድ ውጪ ሥልጣን ይዘው ታሪክ የሠሩ መሆናቸውንም በጥናታቸው አንስተዋል፡፡ በሁለቱም መንገዶች ከ100 በላይ ከነገሥታትና እቴጌዎች በንጉሣዊ የአገዛዝ ሥርዓት አገር መምራታቸውን በጽሑፋቸው አሳይተዋል፡፡
ሴቶች እርስ በርስ የሚረዳዱባቸው ማኅበራት መቋቋም መጀመራቸውም፣ በፖለቲካው መስክ ውስንም ቢሆን ተሰሚነት እንዲኖራቸው አንዱ መንገድ ነበር ብለዋል፡፡
ሴቶች እርስ በርስ የሚረዳዱበት ማኅበር እ.ኤ.አ. በ1935 በእቴጌ መነን አማካይነት የተመሠረተ ሲሆን፣ ብዙዎችን መረዳት መቻሉን ወ/ሮ የልፍኝ ገልጸዋል፡፡ ሌሎችም የሴቶች ማኅበራት ተቋቁመው ሴቶች እርስ በራስ እንዲረዳዱ ሆኗል፡፡ በደርግ አገዛዝ ዘመን ደግሞ ከአምስት ሚሊዮን የሚበልጡ አባላት ያለው የሴቶች ማኅበር (የአብዮታዊት ኢትዮጵያ ሴቶች ማኅበር/አኢሴማ) ተቋቁሞ ጥቂት የማይባሉ ሴቶች እንዲወጡ ተደርጓል ብለዋል፡፡
በወቅቱ ይደረጉ በነበሩ የፖለቲካ ትግሎች የሴቶችም ተሳትፎ ከፍተኛ እንደነበር ይነገራል፡፡ ወ/ሮ የልፍኝ እንደሚሉት፣ የደርግ የአገዛዝ ሥርዓትን ታግለው ከጣሉ ታጋዮች መካከል 40 ሺሕ ሴቶች ይገኛሉ፡፡ አሳዛኙ ነገር ግን ኢሕአዴግ ሥልጣን ላይ ከወጣ በኋላ በትግል ላይ የነበሩት ሴቶች ሥልጣን ይዘው አለመታየታቸው ነው፡፡ ‹‹ትልቅ መስዋዕትነት ከፍለው ታሪክ ከቀየሩ በኋላ ሥልጣን ላይ ጠፉ፡፡ የት ሄዱ ስንል ትዳር መያዝ ፈለጉና ወደ ትዳር ገቡ አሉን፤›› የሚሉት ወ/ሮ የልፍኝ ናቸው፡፡
ከአጠቃላይ ኅብረተሰቡ ሰፊውን ቁጥር የሚይዙት ሴቶች በተለያዩ ጊዜያት በፓርላማ የነበራቸው ውክልና የሚያሳየውም የሴቶች የፖለቲካ ተሳትፎ እጅግ ውስን መሆኑን ነው፡፡ በአንድ ወቅት 7.7 ከመቶ፣ በሌላ ጊዜ 22 ከመቶ፣ 27 ከመቶ 38.8 ከመቶ እንደነበር ይነገራል፡፡ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ የመጣው የሴቶቹ ተሳትፎ ግን በአሁኑ ወቅት የካቢኔውን 50 ከመቶ መቀመጫ እንዲያገኙ አስችሏል፡፡ የአገሪቱ ርዕሰ ብሔርም ለመጀመርያ ጊዜ ሴት ሆነዋል፡፡ ይኼንን የፖለቲካ ቁርጠኝነት በርካቶች አድንቀውታል፡፡ የፆታ እኩልነት ጉዳይ ላይ የሚሠሩ ሁሉ ያጨበጨቡለት ነው፡፡ ይሁንና አሁንም በቂ አለመሆኑን የሚናገሩ አሉ፡፡ መጋቢት 9 ቀን 2011 ዓ.ም. በብሔራዊ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት ኤጀንሲ (ወመዘክር) በኢምፓወር አፍሪካ በተዘጋጀው የውይይት መድረከ ላይ አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች፣ 50 በመቶ የሚሆነው ካቢኔ በሴቶች ቢያዝም በተቀሩት የሥልጣን ተዋረዶች የሴቶች ውክልና እጅግ አናሳ ነው ብለዋል፡፡
በተቃራኒው ደግሞ የፖለቲካን የፆታ እኩልነት ከቁጥር አንፃር ማየት የለብንም ያሉ አስተያየት ሰጪዎች፣ አቅሙ ካላቸው ሴቶች 98 በመቶ የሚሆነውን የፖለቲካ ሥልጣን ቢይዙስ ምን አለበት? የሚል ሐሳብ አንስተዋል፡፡
ወ/ሮ ሰሎሜ ግን ‹‹ሴቶች ከውክልና አንፃር በበቂ መወከል አለባቸው፡፡ ይኼኔ ብሔር ብሔረሰቦች ቢሆኑ ያልተወከሉት አገር በአንድ እግሯ ቆማ ነበር፡፡ ስለዚህ በቁጥሩ አምናለሁ፡፡ እንዲያውም ሴቶች ከጠቅላላው ሕዝብ 51 ከመቶ ድርሻ ነው ያላቸው ውክልናቸውም 51 ከመቶ መሆን አለበት፤›› ብለዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር ሴቶች ወደ ሥልጣን ሲወጡ ከወንዶች በተለየ እንዲሠሩና ተዓምር እንዲፈጥሩ መጠበቅ የለበትም ሲሉ ተደምጠዋል፡፡
