March 25, 2019

በትላንትናው ዕለት በኦሮሚያ ምን እየተሰራ እንደሆነ ከሞላ ጎደል ፊንጭ ለመስጠት ሞክሪያለሁ፡፡ ብዙም አልረዳው የነበረው የአማራ ፖለቲካ አካሄዱ ባያምረኝም ብዙ ለመስጠት አልተመቸኝም፡፡ ያም ሆኖ ስጋቴን መጠቆም ከጀምርኩ ቆይቼ ነበር፡፡ እንደኔ ግንዛቤ የአማራ ወጣት ከአንድ 5 ዓመት በኋላ ከኢትዮጵያዊነት ወጥቶ ባዶደውን ሲቀር ማንም ሴረኞች በሰሩለት አስተሳሰብ ባርነት ወድቆ የፈለጋቸውን ንግድ ይነግዱበታል የሚል ነበር፡፡ አሁን በማየው ግን 5 ዓመት አልጠበቀም፡፡ ይሄው ዛሬውኑ በአደባባይ መሣሪያ ይዞ ሠላማዊ ጎዳና ላይ ሲንጋጋ አይተናል፡፡ ስትወርድ እንዲህ ነው! መዋረድ የማይገባው አሁንም ይወርዳል፡፡
ብርሀኑ ነጋን አለመፈለግ መብት ሊሆን ይችላል እንዲህ በወረደ መልኩ እራስን ከማዋረድም በላይ እስከወዲያኛው የማይታረቅ የተበላሸ አእምሮ እያደገ መሆኑ ሲታይ አሳዛኝ ነው፡፡ ከዚህ በፊት በጎጃም ሁለት ተመራማሪዎች ለሥራ ሄደው በወሮበሎች ተደብድበው መሞታቸውን አስታውሳለሁ፡፡ ከህግና ሥርዓት ውጭ ማንም እየተነሳ ሲጨፍር ብዙዎች የእነሱ ወገን ከሆነ ጀግና ነው፡፡ ሌላው ሲሆን አሸባሪ ነው፡፡ ብዙ ስለማይገባኝ እንጂ አማራ ክልል እየመጣ ያለው የዘረኝነትና ጥላቻ መንፈስ ታውቆኝ ነበር፡፡ ስትዋረድ እንዲህ እንድታስብ ትደረጋለህ ከዛ ማንም ወደፈለገው አማራ እያለ ይዘውርሀል፡፡ በኦሮሞ የምናየውን ራሱን አሁን አማራ በይፋ እንደተቀላቀለው እናያለን፡፡ አገርና ሕዝብ ማለት የማይገባቸው ማንም ያልሆን ከየትም መጥተው እንደልባቸው ይደነፋሉ፡፡
በዘረኝነትና ጥላቻ እያበጠ መጥቶ አሁን ሁሉም ቦታ እየፈነዳ እንደሆነ ግልጽ ሆኖልናል፡፡ ቀደም ብዬ ስጋቴን ገልጬ ነበር፡፡ የሆነው ይሄው ነው፡፡ ያኔ ቤተ-ዓማራ ነኝ የሚለው ቡድን ነበር፡፡ አሁን የምናየው እውነት የዚሁ ውጤት ነው፡፡ በአማራ ክልል የኦነግ ግልባጭ እየመጣ መሆኑን በዚህ ሊንክ ተናግሬ ነበር፡፡
ከጥቂት ወራት በፊት እነዚያ ጎዳናዎች ወጣቶች በወሮበሎች የወደቁባቸው ነበሩ ዛሬ ይሄው ወጣት ነኝ ባይ በዘረኝነትና ጥላቻ የተበከለው እሱ ሌላ ሊገድል መሣሪያ ይዞ ሲያቅራራ ከማየት የበለጠ እርግማን የለም፡፡ በታላቁመ መጻፍ ታላቁ ፈላስፋ እንዲህ ይላል እግዚአብሔርን ለማወቅ ባልወደዱት መጠን የማይገባውን ያደርጉ ዘንድ ለማይረባ አእምሮ አሳልፎ ሰጣቸው፡፡ አንዴ ለማይረባ አእምሮ ከተሰጠህ በምን አእምሮ ማሰብ ትችላለህ! ስለ ኦነጋውያን ብዙ የማውቀው አለኝ ዛሬ በባህር ዳሩ ቄሮ በስተጀርባ አብን የተባለ ቡድን እንዳለ ብዙ ሰው እየተናገረ ነው፡፡ እኔ አላውቅም ግን አብን ስለተባለው ቡድን ከዚህ በፊት የበኩሌን አስተያየት ሰጥቻለሁ፡፡ በተለይ ዋና ጸሐፊ ነኝ የሚለው ሰው በብዙ ነገር አይመቸኝም፡፡ ቀድሞም በወያኔ የወጣቶች ሊግ አባል እንደነበር የሚናገሩ አሉ፡፡ እንደዛ ከሆነ ደግሞ ግልጽ ነበር፡፡ በወያኔ ቡድን የወጣት ሊግ ተብለው የሚመረጡት እነማን እንደሆኑ እናውቃለንና፡፡ ሊቀምንበር ተብዬውም ያለመብሰል ችግር ይታይበታል፡፡ የነሻለ ሆኖ አይቼው የነበረው በለጠ የሚሉት ነበር፡፡ የዛሬው ድንፋታ ጀርባ እንግዲህ ይሄ ቡድን አለ ከተባለ ሰዎችን ለያይተን ማየት ስለሚጠቀም ነው፡፡ እስካሁን በአለኝ ግንዛቤ ዘረኛው በቀለ ገርባና ዶ/ር ደመረራ ጉዲና በአንድ ቡድን እንደሚሠሩ አውቃለሁ ግን በቀለ የፈለገውን ቢል መረራም እንደሱ ነው የሚል ጅምላዊ ፍረጃ መግባት ይቅርና እሰካሁን በአየሁት ስለመረራ ጥብቅናም ልቆም እችላለሁ፡፡ የእኔ እይታ እያንዳንዱን ሰው ላይ ነው፡፡ ችግሮች እየተሴሩ ያሉት በግለሰቦች ነውና፡፡ በግለሰብ ተሴረው የቡድን እንዲሆኑ በማድረግ ቡድኑ ውስጥ ያሉትን ሁሉ መበከልን፣ በሌሎች ማስጠላትን የመሳሰሉ ሴራዎች አሉና፡፡ ዛሬ እናገራለሁ፡፡ ኢሳት ውስጥ ኤርሚያስ ለገሰና ሀብታሙ አያሌ የተባሉ ግለሰቦች አደገኞች ሊሆኑ እንደሚችሉ ይሰማኛል፡፡ ሐብታሙ በእስር ቤት ብዙ ማቀቀ ተብሎ ወደ ምድረ አሜሪካ የመጣበትን ሂደት ሁሉ ሳስብ ጉዳዩ ሁሉ ቁማር መስሎ ይታየኛልና፡፡ የኤርምያስም ወያኔ በመክዳት ሰበብ ኢሳት ጎራ የተቀላቀለበት ሂደት ተመሳሳይ ነው፡፡ እንግዲህ ሕዝቤ ሆይ በራስህ ገንዘብ ጠላቶችህን እያኖረክ እንደሆነ አትዘንጋ፡፡
ማሰብ ካልቻልን ብዙዎች እኛን እየጨረሱና እያጫረሱ ይኖሩብናል፡፡ በራሳችን መስዋዕትነትና ገንዘብ በእኛ ጥፋት እነሱ ይኖራሉ፡፡ ጤነኛ የሆናችሁ ኦሮሞ ነን የምትሉ ስሙ፣ ጤነኛ የሆንክ አማራም ስማ፡፡ በየፌስቡኩ የሁለት ድኩላዎች ጸብ ለአንበሳ ሲሳይ መሆኑን ማሰራጨት ታውቅበታለህ፡፡ ግን እራስህ እያደረግህ ያለውን ማስተዋል ሞክር፡፡ በዙሪያህ በአንት ሞትና መቃብር ላይ አንትን እየገበሩና እየነገዱ የሚኖሩብህ ብዙ ናቸው፡፡ ለመሆኑ የሀይማኖት አባቶች፣ ሽማግሌዎች ይት ናችሁ፡፡ ዛሬ በባህርዳር መሳሪያ ይዞ ሲደነፋ የምታዩት ለአንዳንዶቻችሁ ጭራሽ የጀግንነት ሆኖላችኋል፡፡ ከወራት በፊት በእነዚሁ ጎዳናዎች ንጹሀን በሌሎች ሲገደሉ እነዚህ ዛሬ የሚደነፉት እንዳልነበሩ ሁልህም ታቀዋለህ፡፡ እግዚአብሔርም አልታሰበም! በገዛ ጥጋብ ሌላ እርግማን ፈቅደህና ወደህ ሞትን ቤትህ እየጠራህ መሆኑን ማሰብ ስላልቻልክ እንዴት የተሻለ ዘመን እንዲሆንልህ ትፈልጋለህ? እስከሚገባኝ ለአብዛኛው የባሕርዳር ማሕበረሰብ አሁን ጊዜው የጾም ወቅት ነው፡፡ እንዲህ በጥላቻና ዘረኝነት ተበክሎ ጾም…. ለመሆኑ የሀይማኖት አባቶች የት ናቸው? ሽማግሌዎችስ የት ናቸው? እናቶችስ? ጭራሽ ወሮበላነትን እንደጀግና የሚያበረታቱም አልጠፉም፡፡ ዛሬ የሆነውን ዝም ብላ ያለፈች እናት ነገ ልጇ መንግድ ላይ በሌሎች ቢወድቅ ይሄን ቀን ታስብ፡፡ ያለፈውን መከራ ማሰብ አልቻለችምና የጥጋበኝነቱ ጊዜ መከራ ሲመጣ ትዝ ይበላት፡፡ የዛሬውን አይቶ ዝም ያለ ክህን ሽማግሌ በኢትዮጵያ ምድር ጥላቻንና ዘረኝነትን ከሰበኩት እንዳንዱ እንደሆነ ያስብ፡፡
ሁሉም ግን የፈላስፋውን ቃል ያስብ እግዚአብሔርን ለማወቅ ባልፈለጉት መጠን የማይገባውን ያደርጉ ዘንድ ለማይረባ አእምሮ አሳልፎ ሰጣቸው!
ቅዱስ እግዚአብሔር ከማይረባ አእምሮ ይጠብቀን! አሜን!
ሰርፀ ደስታ
