March 26, 2019

በአዲስ አበባ የደሃዴን አመራሮች ባደረጉት ስብሰባ፣ አዲስ አበባ የኦሮሞ ናት የሚለው የኦህዴድ/ኦዴፓ፣ የኦሮሞ ክልል መንግስትና የኦሮሞ ብሄረተኞችን አመለካከት ውድቅ በማድረግ፣ አዲስ አበባ የኢትዮጵያና የአፍሪና መዲና፣ የሁሉም ኢትዮጵያዊያን በዋናነት ደግሞ የነዋሪዎቿ መሆኗን የደሃዴን አመራሮች በግልጽ ማስቀመጣቸውን ፋና ዘግቧል።

በተመሳሳይ ሁኔታ አዴፓ አዲስ አበባ የአንድ ክልል ብቻ ናት የሚል አመለካከት ተቀባየነት የሌለው እንደሆነ ገልጾ፣ አዲስ አበባ በዋናነት የነዋሪዎቿ መሆኗም እንደ ኢትዮጵያ መዲናነቷ ኢትዮጵያዊያን፣ እንደ ዜጋ በመዲናቸው ጉዳይ እንደሚያገባቸው አዴፓ በአጽኖት አስቀምጧል።

አዲስ አበባ የኦሮሞ ናት፣ ኦሮሞ በአዲስ አበባ ልዩ ጥቅም ይገብዋል የሚለው ኦዴፓዎች አመለካከት በኢሕአዴግ ውስጥ የተሸነፈ አመለካከት ሲሆን፣ በተቀረው የኢትዮጵያ ህዝብ ዘንድ ደግሞ እስከ መወገዝ የደረሰ አመለካከት ነው።

ፋና በደሃዴኖች ስብሰባ ዙሪያ የሚከተለውን ዘግቧል

———————

በአዲስ አበባ የደኢህዴን አመራሮች መድረክ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ በመምከር ተጠናቀቀ

አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 16 ፣ 2011 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደኢህዴን) አመራሮች መድረክ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ በመምከር ተጠናቋል።

በመድረኩ ማጠቃለያም የተለያዩ አቅጣጫዎችን ያስቀመጠ ሲሆን፥ አሁን ላይ ሃገሪቱ በከፍተኛ የለውጥ እንቅስቃሴ ውስጥ እንደምትገኝ አንስቷል።

ለውጡ እውን መሆን በጀመረባቸው አጭር ጊዜያት ውስጥም በርካታ አመርቂ ስራዎች መሰራታቸውን ያነሳው መድረኩ፥ ይሁን እንጅ ለውጡ በተሳካ መንገድ ተጉዞ የሚፈለገውን ግብ እንዳይመታ በርካታ ተግዳሮቶች እየተፈታተኑት ይገኛልም ነው ያለው።

ባለፈው አንድ አመት ውስጥም የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት የተለያዩ ጥረቶች መደረጋቸውን፣ በኢኮኖሚያዊ እና ዲፕሎማሲያዊ መስክ ተስፋ ሰጭ ለውጦች መታየታቸውን በማህበራዊ ልማት እና ሰብዓዊ መብት ዙሪያ ተስፋ ሰጭ ስራዎች ስለመሰራታቸውም ተወያይቷል።

ከዚህ አንጻርም መልካም እድሎች እና ጠንካራ ጎኖች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን፣ ለውጡን ወደ ኋላ የሚጎትቱ ሁኔታዎችን ለመቅረፍ በሚደረገው እንቅስቃሴ የደኢህዴን አመራሮች፣ አባላትና የህዝቡ ሚና ከፍተኛ መሆኑንም አንስቶ መክሯል።

ድርጅቱ በርካታ ብዝሃነቶችን አቅፎና አቻችሎ የጋራ አጀንዳ በሆነው ሠላም፣ ዴሞክራሲ እና በልማት ዙሪያ ምልአተ ሕዝቡን በማሰለፍ አመርቂ ውጤት ማስመዝገቡም በመድረኩ ተነስቷል።

ይሁን እንጅ በእነዚህ ጊዜያት አሁንም የክልሉን ህዝቦች አንድነትና የድርጅቱን ቀጣይነት የሚፈታተኑ ጉዳዮች መኖራቸውን በመጥቀስ፥ በቀጣይ ለድርጅቱ ቀጣይነት፣ ለህዝቦች ተጠቃሚነት እና ለአጠቃላይ ለውጡ ቀጣይነት መስራት እንደሚገባ አቅጣጫ አስቀምጧል።

ከዚህ ጋር ተያይዞም ከድርጅቱ ቀጣይነት ጋር በተያያዘ የሚሰነዘሩ ጥቃቶችን በመመከት እና ውስጣዊ አንድነትን በማጠናከር የድርጅቱን ቀጣይነቱን ለማረጋገጥ በትጋት መስራት ይገባልም ነው ያለው።

በክልሉ የሚነሱ የመዋቅር ጥያቄዎችና የጸጥታ ችግሮችን በደኢህዴን መሪነት የህዝቡን ትስስርና አንድነት በሚያጠናክር፣ የድርጅቱን ቀጣይነት በሚያጎለብት፣ የሁሉንም ሕዝብ ተጠቃሚነት በሚያረጋግጥ እና ሀገራዊ ጉዳዮችን ታሳቢ ባደረገ መልኩ በጥናት እንዲመለሱ ለማስቻል መስራት ይገባልም ብሏል።

በሃገሪቱ ህብረ-ብሄራዊነትን ለመናድ የሚነሳን ኃይል የብሄር ብሄረሰቦችን እና የሀገሪቱን ህልውና እና ስርዓቱን ለመጠበቅና ለማበልፀግ በሚያስችል አግባብ ግንባር ቀደም ሆኖ መታገል እንደሚያስፈልግም ተወያይቷል።፡

በአዲስ አበባ ጉዳይ ላይም የተወያየ ሲሆን በአስተዳደሩ ከፍተኛ የለውጥና የማሻሻያ እንቅስቃሴ ውስጥ የተገባበት መሆኑን በማንሳት፥ ማሻሻያው በሀገራዊ አጀንዳዎች የታጀበና የመላውን ህዝብ ተስፋ የቀሰቀሰ በመሆኑ በአግባቡ ተመርቶ ወደ ውጤት ማሸጋገር ከተቻለ ተስፋ ሰጭ እንቅስቃሴ መሆኑንም አንስቷል።

በመሆኑም መልካም ጅምሮችን በማሳደግና የሚስተካከሉ ጉዳዮችን ፈጥኖ በማስተካከል የማሻሻያ እንቅስቃሴውን ማሳካት እንዲሁም ለውጡን መሸከም የሚችል አመራር፣ አባልና ፐብሊክ ሠርቫንት በመገንባት የህዝቡን መሰረታዊ የልማትና መልካም አስተዳደር ጥያቄዎች በለውጥ መንፈስ ምላሽ መስጠት እንደሚያስፈልግም ገልጿል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለያዩ መንገዶች የሚተላለፉ አጀንዳዎችም የአዲስ አበባንና የመላውን ህዝብ ቀልብ በመሳብ አመራሩን ሥራ በማስፈታትና ከልማት ሥራ ወደ ኋላ በመጎተት፥ ህዝቡ ለውጡን በጥርጣሬ እንዲመለከት የሚያደርጉ አዝማሚያዎች እያቆጠቆጡ መምጣታቸውንም ነው የገመገመው።

አዲስ አበባ የኢትዮጵያ ዋና ከተማ፣ የአፍሪካ መዲናና አለም አቀፍ ግዙፍ ተቋማት ማዕከል መሆኗን ያነሳው መድረኩ፥ አዲስ አበባ የመላ ኢትዮጵያውያን ብሎም የነዋሪዎቿ መሆኗንም አውስቷል፤ ሌሎች ጉዳዮች ህገ-መንግስቱንና ህጉን ተከትለው የሚፈጸሙ መሆኑን በመጥቀስ።

ስለሆነም በአዲስ አበባ ከተማ ጉዳይ በህገ-መንግስቱ ጭብጦች ላይ በመመስረት ትግል ማድረግ እንደሚገባና በነዋሪው ዘንድ ጥርጣሬን ሊፈጥሩ የሚችሉ ጉዳዮችን እውነቱን በመረዳት የተሳሳተውን አስተሳሰብ በማረም ረገድ ንቁ ተሳትፎ ማድረግ እንደሚገባም ተጠቅሷል።

በአጠቃላይ አመራሩ አሁን በሀገሪቱ ብሎም በአዲስ አበባ የተጀመረውን የለውጥ እንቅስቃሴ በአግባቡ ወደሚቀጥለው የዕድገትና ብልጽግና መስመር እንዲገባ፥ በጥንቃቄ መጠበቅና ማስቀጠል የህዝቦች የህልውና ጉዳይ መሆኑን በመረዳት በትክክለኛ መንገድ የመምራት እና ሀገርና ወገንን የማዳን ሀላፊነትና ግዴታ እንዳለበት አስታውሷል።