March 26, 2019

እሁድ መጋቢት አስራ አምስት ቀን ግንቦት ሰባት በባህር ዳር ለማድረግ አስብት የነበረው ስብሰባ በተቃዉሞ መደረግ አለመቻሉን በስፋት በተለያዩ ሜድያዎች እየተነገረ ነው። በባህር ዳር ግንቦት ሰባት የቀረበበትን ተቃዉሞ ተመርኩዞም በተለያዩ አቅጣጫዎች የተእያዩ አስተያየቶች ይሰጣሉ። የግንቦት ሰባት ደጋፊዎች በዋናነት በባህር ዳር ስብሰባ የማድረግ መብታችንን የአማራ ብሄረተኞች ተጋፍተዋል በሚል በተለይም አብን ላይ ከፍተኛ ትችት እያቀረቡ ነው።
አብን የግንቦት ሰብሰባን በተመለከተ ደጋፊዎቹ ተቃዉሞ እንዲያስነሱ ጥሩ ባላቀረበበት መልኩ ያለ መረጃ አብንን መክሰስ ተገቢ አይደለም የሚሉ ሌሎች ወገኖች ደግሞ፣ ተቃዉሞ የተነሳው ከራሳቸው ከግንቦት ሰባቶች ነው ብለው ይከራከራሉ። “የግንቦት ሰባት አባላት የነበሩ ናቸው ተቃዉሞ ያስነሱት”” ተቃዉሞ ማሰማት ደግሞ መብታቸውም” ነው ይላሉ።
በዚህ ጉዳይ ላይ የአዲስ ድምጽ ዋና አዘጋጅ አበበ በለው፣ ሁኔታውን ተከታትሎ፣ በቦታው የነበረዉን አጣርቶ እንደሚከተለው ዘግቧል
–
በባህር ዳር የነበረውን ችግር የፈጠሩት እነማን ናቸው ብላችሁ ማወቅ ለምትፈልጉ ግን፡ እቦታው ደውዬ ተነጋግሬ የተለያዩ ሰዎችን መረጃ አጠናቅሬ እንደሚከተለው አቀርበዋለሁ፡፡
ለመሆኑ በመጀመርያ ይህን ሰላማዊ ሰልፍ (ግንቦት ስባትን የሚቃወመው ሰልፍ) የጠሩት እነማን ናቸው? ለምትሉ የአርበኞች ግንቦት 7 የቀድሞ ጦር ሠራዊትና የቀድሞ አባሎች መሆናቸውን በመረጃ የተደገፈ ሆኖ አግኝቸዋለሁ።
እነዚህ የቀድሞ አርበኞች ግንቦት 7 ወታደሮች በድርጅታቸው አመራር ደረሰብን ያሉዋቸውን በደሎች ለማሰማት መንግስት እና ሚዲያዎች ትኩረት እና የማስረዳት እድል ስለነፈጓቸው፡ ህዝቡን በዉይይት ውስጥ ጣልቃ እንዲገባ የህዝብን ድጋፍ ለማግኘት እንዳደረጉት ገልፀውልኛል።ይህም እውነት መሆኑን የአርበኞች ግንቦት 7 አመራር አቶ ንዓምን የስራ ሃላፊነቱን የለቀቀበት ምክኔያት ችግሩ በመንግስት ቸል መባሉ መሆኑን በይፋ ተናግሯል።
አንባቢዎች ልብ እንድትሉ የሚያስፈልገው ይህን ሰላማዊ ሰልፍ ያደረጉት በሙሉ የአማራ ብሔር ተወላጆች ናቸው ብሎ መደምደም እንደማይቻልም ገልጸውልኛል ። ምክንያቱም በዚህ ሰልፍ ለመሳተፍ ከአማራ ክልል ውጭም የመጡ የአርበኞች ግንቦት 7 ሰራዊት አባላት እንደነበሩበትም ገልፀዉልኛል። ይህን ጉዳይ አርበኞች ግንቦት 7ም አማሮች ወይም የአማራ ተወላጆች ናቸው ብሎ መግለጫም ክስም አላወጣም። ከሁሉም በላይ የዚህ ድርጅት አባላት ወይም ደጋፊዎች ህገወጥ ሰልፍ አድርገው በጠበጡኝም አላለም። ችግር ለመፍጠር አንዴ የአማራ ወጣቶች አደረጉት ሌላ ጊዜ እገሌ የሚባል ድርጅት አደረገው የገሌ ድርጅት ደጋፊዎች አደረጉት እየተባለ የሚነገረው ነገር ሁሉ ፡እውነቱን የሚደብቅና መፍትሄ እንዳይገኝለት የሚያደርግ ኃላፊነት የጎደለው የጥቂቶች ንግግር ነው ።
በዚህ ጉዳይ ላይ አብን እና የአብን አባላትን ደጋፊዎችን ከፍ ሲልም የባህርዳር ከተማ ነዋሪዎችንና ወጣቶችን መወንጀል ጅልነት ነው።ትላንት ደሜ ኢትዮጵያዊ ነው ብሎ ግምባሩን ለጥይት ሰጥቶ የድሉ አንድ አካል የሆነን የሃገር ተስፋ ወጣት ባልዋለበት ቦታ ስሙን ጠርቶ ማውገዝ እጅ ነካሽነት ነው። ሰልፉን በህገወጥነት ያካሄዱት ሰዎች እንደሚጠየቁ ሁሉ ህግ አክብረው የተሰለፉት ወገኖችም ስለነበሩ ፡ጥያቂያቸው እንደገና በሚዲያ ህዝብ ሊያዳምጠው ይገባል። አንድ ሰላማዊ ሰልፍ በጥቂት በጥባጭ ሰወች ሲበተን የበጠበጡትን ህግ ፊት ማቅረብ የሚጠበቅ ቢሆንም ሰልፈኞች የተሰለፉበት ዋና ምክንያት ግን በተለያዩ ሚዲያዎች ሊነገር እና ሊብራራ ይገባዋል ።
ይህ ኃላፊነት አዲስ ድምጽ ሬድዮም የሚመለከተው በመሆኑ በአጭር ጊዜ ውስጥ ጉዳዩን ሊያስረዱ የሚችሉ የሚመለከታቸው ኃይሎች በቀኝም በግራም እናቀርባለን:: ሌሎች የሚዲያ አካላትም ድርጊቱን ማውገዛቸው እንደተጠበቀ ሆኖ ፡ የሰልፈኞችን ጥያቄ እና ማንነት ለህዝብ ማሰማት :ግድ ይላቸዋል። ከዚህ በተረፈ አንድን ድርጅት ለመደገፍ ሌለን ድርጅት ማጥፋት ላለፉት 27 ና አርባ አመት በሃገራችን የተለመደ ኋላ ቀር የፖለቲካ አካሄድ ስለሆነ ልናቆመው ይገባል:: ይህን ጉዳይ ግልፅ ለማድረግ የሚከተሉትን ነገሮች መተንተን ተገቢ ነው።
አንደኛ ሰልፈኞች ጥያቄያቸውን የጠየቁበት መንገድ ሁለተኛ ሰልፈኞቹ እነማን እና የማን ድርጅት አባላት እና ደጋፊዎች ናቸው ሶስተኛ ጥያቄያቸው ምንድነው የሚሉት መሆን አለባቸው:: በዚይ የምንስማማ ከሆነ የመጀመሪያው ሰልፈኞች ጦር መሳሪያ ይዞ መውጣት ህገወጥ መሆኑ ያለ ክርክር ያስማማንን ያህል ሠልፉን ያዘጋጁት እና ሰልፈኞቹ እነማን ናቸው የሚለውም ሊያስማማን ይገባል ።
ይህን ሠልፉ ያዘጋጁት ኤርትራ በረሃ እና በኢትዮጵያ ውስጥ ግንቦት ሰባትና አርበኞች ግንባርን አምነው ሂወታቸውን ሰጥተው ከድርጅቱ ጋር ሲታገሉ የነበሩ መሆናቸው ቅንጣት ታህል ሊያከራክረን አይገባም:: ሦስተኛው ጥያቄያቸው ምንድነው የሚለው ነው፡ ይህን ጥያቄ በራሳቸው ጥፋት ጥያቄያቸው በጥሞና እንዳይደመጥ ስላደረጉ : ጥፋታቸውን ተረድተው በሰላማዊ መልክ እንደገና ጥያቄያቸውን ያቅርቡ እና ልንሰማቸው ግድል ይለናል:: የምንሰማቸውም ዳግም ሰላማዊ ሰልፍ በማድረግ ሳይሆን ፡በስውርም ይሁን በግልጽ ተጭኖ ብናል የሚሉት የሚዲያ አፈና ተነስቶላቸው በየትኛውም ሚዲያ እየቀረቡ ችግራቸውን እንዲያሰሙ ስናደርግ ብቻ ነው:: ልብ እንበል የዛሬን አያርገውና፡ እነዚህ ወጣቶች ጠበንጃ ይዘው በረሃ በገቡ ጊዜ አድናቂያቸው እና ጀግኖቻችን ናችሁ ይላቸው የነበረው ህብረተሰብ፡ ወጣትነታቸውን ግምት ውስጥ በማስገባት ያደረጉትን ስህተት ሚዛናዊ በሆነ ጉዳይ በማየት፡ ቀደም ሲል የሰጡትን አገልግሎት ግምት ውስጥ በማስገባት፡በረሃ ሄዶ ጀግንነታቸውን የዘገበው ሚዲያም ፡የለም አያዋጣም ይቅርባችሁ ይል የነበረው ሚዲያም ፡ሁሉም ሊያቀርባቸው ይገባል። በሚዲያ እና በስብሰባ እየተገኙ ጥያቄያቸውን እንዲያቀርቡ ማድረግ የሁላችንም የህሊና ግዴታ ነው:: አርበኞች ግንቦት 7ትም ድርጅቱን አክስሞ ከሌሎች ጋር ተቀላቅሎ አዲስ ድርጅት ከመመስረቱ በፊት ይህን ችግር ተከትሎት እንዳይሄድ ዛሬውኑ ሊፈታው ይገባል።
በሌላ በኩል ከአርበኞች ግንቦት ሰባት ጋር የራሳቸውን ፓርቲ አፍርሰው አዲስ ፓርቲ በጋራ ለመፍጠር የሚፈልጉ ወገኖች ሁሉ ፡ይህ የግንቦት7 ችግር አዲስ ወደሚመሰርቱት ፓርቲ እንዳይተላለፍ ካሁኑ ለመጨረሻ ጊዜ እንዲወገድ ሊያግዙ ይገባል።መቸም ብዙ እዳ ያለበት ሰው ስታገባ ወደድክም ጠላህም እዳው እዳህ ይሆንብሃል።
ይህ ካልሆነ አዲስ የሚፈጥሩት ፓርቲ ሊሠራ የሚገባውን ስራ ትቶ ከግንቦት 7 በመጡ ወገኖች ክርክር የሚጠመዱ መሆኑን ካሁኑ ልብ ሊሉት ይገባል:: የግንቦት ሰባት አመራሮችም በዚህ ጉዳይ ላይ ትኩረት ሰጥተው ጠያቂዎችን እና ጥያቄውን ሳያድበሰብሱ እውቅና ሰጥተው በሃቅ ቢያስተናግዱት ትልቅነት ነው።ለነገሩ አብረው ለአንድ አላማ ለመሞት ተንከራተው አልነበር እንዴ? መጨካከንን ምን አመጣው? እስኪ በጭዋ ደምብ ፍቱት እና ይህን በትንሽ ደስታ እፎይ የሚል የዋህ ህዝብ አስደስቱት።
እኛም ቢሆን እድሚያችንም ልምዳችንም ለሽምግልና ብቁ ነው ፈቃደኛም ነን።ቸር ያሰማን።
አበበ በለው
ከዋሽንግተን ዲሲ
