March 26, 2019

በሀገራችን አንድነትን የሚያስተናግድ ብዝሃነት በመቀበል መደመሩ መልካም ሆኖ ካለንበት የፖለቲካ አወቃቀር ችግር እንዴት መላቀቅ እንደሚቻል ተስፋ የተጣለበት ቡራቡሬ ለውጥ እስከምን ድረስ ይዘልቃል ሲሉ በርካቶች ስጋታቸውን  ያንፀባርቃሉ፡፡

ባለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት የአብዮታዊ ዴሞክራሲ አስተሳሰብ ሲምታታበት የሚታየው ኢሕአዴግ ሀገሪቱን ከተቆጣጠረበት ጊዜ ጀምሮ ከሽንገላ ያለፈ ሀገራዊ አንድነት ሳያመጣ እንዲሁ የሕዝብን ህልውና አዘቅት ውስጥ ከቶ መጓዙን ስፍር ቁጥር የሌላቸው ዜጎች እያወገዙትም ይገኛሉ፡፡ ገዥው ፓርቲ በፈፀማቸው ፖለቲካዊ ስህተቶች ምክንያት የሀገሪቱን ብሔራዊ አንድነት ከማስጠበቅ አኳያ ይህ ነው የሚባል በታሪክ ውስጥ ተገቢውን ድርሻ ተወጥቷል ለማለት አያስችልም፡፡ በዘውጌነት/ጎሣዊነት አራማጅነት የዜግነት ፖለቲካ በሚያራምዱ ቡድኖች ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ የመደረጉ አባዜ ሕዝብን ግራ ለማጋባት እንደ ስልት የሙጥኝ ማለት ችግሩን የበለጠ አወሳስቦታል፡፡

ኢሕአዴግ መሰረታዊ የአስተዳደር ችግሮችን ከምንጩ አጢኖ እንኳ ለማረም በባህሪው ፈፅሞ ዝግጁነት የለውም፡፡ በዴሞክራሲ ስም ክህደትና ተንኮል የተጠናወተውና በዘውግ ፖለቲካ የተለወሰ አብዮት አራማጅነቱም ወደር በዓለም አይገኝለትም፡፡ እንዲያው ድብቅ የፖለቲካ ዓላማ በጉያ ሸጉጦ ምን ዓይነት ትክክለኛ ለውጥ ሊመጣ ይችላል  ብሎ መጠበቅ  ራስን ማሞኘት ይሆናል፡፡ በገጠር የአርሶ አደሩ በከተማ ደግሞ የድሃ ተቆርቋሪ መስሎ ለመታየት የሕዝቡን የአስተሳሰብ እድገት ደረጃ የማይመጥን  ሆኖ ሳለ በከንቱ መዳከር ፍንትው ያለበት የምርጫ 97ን መጥቀስ በቂ ነው፡፡ እስከዛሬም ቢሆን በተጨባጭ የኢትዮጵያዊነት መሰረትን ለመናድ ርባና በሌለው ስትራቴጂክ ደባ እየተፈፀመ ለመምጣቱ ማስረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

የአዲስ አበቤ መክሊቶች አብሮነት፣ ሰላም፣ መቻቻል፣ ፍቅርና መተሳሰብ በዳበሩበት ሁኔታ ለጥቂት ፅንፈኛ የፖለቲካ ቡድኖች ፍላጎት መፈንጫ አጀንዳ መንገድ ማቻቸቸት ፈፅሞ አይገባም፡፡ ከሰሞኑ አዲስ አበባን ውጥረት ውስጥ ለመክተትና ነዋሪዎችን የተረጋጋ ሕይወት እንዳይመሩ ለማሸበር በፅንፈኛ ብሔርተኞች የሚደረግ ማናቸውም ሙከራ ሕጋዊ አግባብ የሌለው በተጨባጭ የፓለቲካ መርህ ቅጥ አምባሩ የጠፋበት መሆኑን ያመላክታል፡፡

አዲስ አበባን ሰቅዞ የያዛት የባለቤትነትና የራሷ አስተዳደር መብት ተጠቃሚ እንዳትሆን ዋናው እንቅፋት የይስሙላ ፓርቲ ውክልና የያዙ የምክር ቤት አባላት ለነዋሪው ተቆርቋሪነት የሌላቸው መሆኑ ነው፡፡ ይህ ሁሉ ቱማታ ገዥው ፓርቲ በሚከተለው የፖለቲካ ክስረት የተነሳ አዲስ አበቤ ሕዝባዊ ውክልና ኖሮት በመረጠው ከንቲባ መተዳደር እንዳይችል አድርጎታል፡፡ አሁን የሚስተዋለው የነዋሪውን መብትና ጥቅም የሚያስጠብቅ ሳይሆን ከፓርቲው በኩል የቀረቡለትን ዓላማዎች ወክሎ የሚጨነቅ አሻንጉሊት አስተዳደር መሆኑ ያሳዝናል፡፡ ነዋሪው ሕዝብ በሴራ ፖለቲካ የተደቀነበትን ማጋለጥና እውነተኛ ለሚሆን ብቻ ድጋፉን መስጠት ይኖርበታል፡፡ ከነዋሪው ፍላጎት ቅድሚያ ይልቅ ለፓርቲ ጥቅም ውገና የተሰለፉ የሕግ ህልውና የሌላቸው አፈቀላጤዎችን ቦታ ለማስያዝና ለመሾም መሯሯጡ ወደ አዲስ ምዕራፍ ለመሸጋገር እንቅፋት መሆኑ አያጠራጥም፡፡

ታዲያ አዲስ አበባን በተመለከተ በሕግ እንዲወሰን ከዚያ ውጭ ለፍሬ ቢስ የፖለቲካ ፍጆታ ብቻ ማተኮርና ግልፀኝነት የጎደላቸው የሕግ ሐረጎችን በሕገ መንግሥቱ አንቀፅ ላይ መደርደር ችግሩን ያባባሰው ስለሆነ መፈተሽ ያስፈልጋል፡፡ የዚያን ጊዜ (በሽግግሩ ወቅት) ሕገ መንግሥቱ ሲረቀቅ ለመጭው ትውልድ የቤት ሥራ መስጠት ላይ የተጠመዱ የጠባብ ፖለቲካ አቀንቃኞች ስውር ደባ እንደሰሩበት ለመገንዘብ እህልና ውሀ ያላመጠ መደዴ መሆን እንጂ የኮሚቴ ጥናት የግድ ላያስፈልግ ይችላል፡፡ የለውጡ ሀይል እየተባለ የሚንቆለጳጰሰው ቡድን ጊዜያዊ ተቀባይት ለማግኘት  ደፋ ቀና ከማለት ተላቆ ጥግ ይዞ የተሸጎጠውን አክራሪ ሀይል  በማኮላሸት አሽቀንጥሮ በመጣል ዘላቂ መፍትሄ ማምጣት መቻል አለበት፡፡ ያለበለዚያ ግን የነዋሪዎቿን መብት ለሚፃረር ፅንፈኛ ቡድን እድል መስጠት ስለሚሆን ጉዳቱ እጅግ የከፋ ይሆናል፡፡ በመደመር እሳቤ ጥሪ በሰላማዊ ትግል ለመሳተፍ ወደ ሀገር ቤት ገብቻለሁ ያለው ቡድን ሳይውል ሳያድር ዋጋ ቢስነቱን አስመስክሯል፡፡  አሁን ያለውን የዶ/ር አቢይ  መንግስት እጁን ጠምዝዞ በማስጨነቅ ምርጫው ከመድረሱ አስቀድሞ ፖለቲካዊ ድብቅ አጀንዳን በአዲስ አበቤው ላይ በመጫን ለማሳካት የሚራወጡትን ከማየት በላይ ማረጋገጫ ማስረጃ ማቅረብ አያሻም፡፡

ዶ/ር አቢይ በእነዚህ ግብዝ አክራሪ ብሔርተኞች መዳፍ ላለመውደቁ እርግጠኛ መሆን ባይቻልም እርምጃ ከመውሰድ የተቆጠበበትና ኢትዮጵያዊነትን እናጠንክር ሰፊ ዲስኩር በስተጀርባ እውነታው ለመገንዘብ የቻሉ በርካቶች አስተያየት ከመስጠት ተቆጥበው በጥርጣሬ መከታልን መርጠዋል፡፡ አዳዲሶቹ አክራሪ ፖለቲከኞችና አክቲቪስቶች ለሚመኙት ኢትዮጵያን የማፈራረስ ቀመር ምቹ አጋጣሚ አድርገው የሚወስዱበት አንዳች እድል ካገኙ ለሕዝብ እልቂት በር ከፋች እንደሚሆን መገመት አያስቸግርም፡፡ ችግሩ ያለው እንግዲህ እዚህ ላይ ነው እልባት ያላገኘው የአዲስ አበባን ጉዳይ በሚመለከት  የዶ/ር አቢይ እርምጃ ምን ሊሆን እንደሚችል በኮሚቴ ጥናት ላይ ይወሰናል ወይስ በተጨባጭ ምልክቶች ማስተካከያ ሊያደርግ ይችላል? የምናየው ይሆናል፡፡ በአሁኑ ወቅትም በከተማዋ ባለቤነት ጉዳይ ላይ ለሚነሱ የያገባኛል ጥያቄ  የከተማው ምክር ቤት  የዳር ተመልካች መሆኑ የሚያጠያይቅ ነው፡፡

አዲስ አበቤ ዝም ብሎ አንገቱን ደፍቶ ለፅንፈኛው ቡድን ፀረ-አዲስ አበባ የሕልውና መብት በር ከፋች ሆኖ ሊቀመጥ አይገባም፡፡ በራሱ አስተዳደራዊ መብት ጉዳይ ነዋሪው ራሱ የተሳተፈበት መወሰን መቻል ይኖርበታል እንጂ ከዚህ ውጭ ተቀባይነት ሊኖር እንደማይችል በገሀድ በማሳየት ለደቂቃም ቢሆን መደራደር የለበትም፡፡ ሰሞኑን ከኮንዶሚኒየም እጣ ጋር ተያይዞ እየሰማነውና እየተመለከትነው ያለው ዛቻና የጥላቻ ጥቃት ለመሰንዘር ሙከራ አድሮ ውሎ ወዴት ሊያመራ እንደሚችል ግልፅ ሆኗል፡፡ የአዲስ አበባ ጉዳይ በሕግና ሕግ ብቻ ሊታይ የሚገባው እንጂ አብዮታዊ ዴሞክራሲ የወለዳቸው ጥራዝ ነጠቆች በዱላና ገጀራ ልዩ ፍላጎትን ለመወሰን የሚዳዱበት መሆን አይገባውም፡፡ ከተማዋ የሁሉም ኢትዮጵያውያን መኖሪያ እንዲሁም የመላው አፍሪካ መዲና ናትና አጀንዳው ማንም ተጎጅ ማንም ደግሞ ብቸኛ ልዩ ተጠቃሚ የሚሆንበትን አሰራር ለመተግበር የሥነ ሕዝብ አሰፋፈርና ፖለቲካን ሽፋን ማድረግ ሌላ የዘመናችን ታሪካዊ ስህተትን ያስከትላል፡፡

የገዥው ፓርቲ መልካም ፈቃድ ተቀፅላ አሰራርን ማስቀረትና ፖለቲካዊ አሻጥርን በማጋለጥ ረገድ የአዲስ አበባ ተወላጅም ሆነ ነዋሪ በሙሉ ነቅቶ መደራጀት ብቻ ነው የሚያዋጣው፡፡ ዛሬም ያንኑ የገዥው ፓርቲ በተቃርኖ አሰላለፍ ቅኖናዊ አስተሳሰብ ሕዝቡ ላይ ለመጫን የሚያንፀባርቁ ቡድኖችና ግለሰቦች ለአዲስ አበባ ነዋሪ ጥቅም እንደማይቆሙ በተግባር አሳይተዋል፡፡ አዲስ አበቤ ሆይ ወላዋይነት፣ ራስ ወዳድነትና የፍርሃት ቆፈን ሳይግድህ ለመብህና ሕልውናህ ተስማሚ ውሳኔዎችን ማስጠበቅ ላይ ንቃ፤ ተደራጅተህ መብትህን አስከብር፡፡ መዘናጋቱ ዋጋ ያስከፍላልና ትግልህ በተደራጀ ስልጡን የፖለቲካ አስተሳሰብ እንዲመራ ይታሰብበት፡፡

ሕገ መንግሥቱ ሲረቀቅ አዲስ አበባን በሚመለከት ሆነ ተብለው የተሰራ ሸፍጥና ታክቲካዊ አንቀፅ ለንትርክ ዳርገውን ትርጉሙን በቅጡ የማይረዱ አክራሪ ብሔርተኞች ወደፊት መራመድ እንዳንችል የተንኮል ሴራ ሸርበውብናል፡፡ ሆኖም ግን ዛሬ ላይ ጉዳዩ ቁጭት በፈጠረባቸው የከተማዋ ነዋሪዎች ተቆርቋሪነታቸውን ከመቼውም ጊዜ በላይ ያሳዩበት በጎ ጅምር አበረታች ነው፡፡

ከሰሞኑ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ባስተባበረው በባልደራስ አዳራሽ በተጠራ ሕዝባዊ ስብሰባ “ለአዲስ አበባ ምን ይደረግ?” ፓለቲካዊ መተባበር ላይ የተደረገ  ውይይትና ውሳኔ ማሳለፍ አፍ ተልብ ሆኖ ቃል ኪዳኑ መጠናከር ያለበት ጉዳይ ነው፡፡ በስብሰባው የተንፀባረቀው ስሜት በራሱ ለውጥ ለማምጣት ዓይነተኛ አስተዋፅዖ አለው፡፡  ይህ ሲባል ግን ማናቸውም የውሳኔ ሃሳብ ከዙሪያ ገባው አጎራባች የአርሶ አደር ሁለንተናዊ የኑሮ ይዞታ መሻሻል ጋር እየተጣጣመ እንዲሄድ እንጂ የሚያናጋ የስጋት መንፈስ እንዳይፈጠር ከወዲሁ ማጤን ውጤቱ የሰመረ ያደርገዋል፡፡ አዲስ አበባ የተጋረጡባት መሰረታዊ ተግዳሮቶች ለመቅረፍ ከነዋሪዎቿ ጋር ትኩረት ሰጥቶ የሚሰራበትን የአመክንዮ ለውጥ ካላመጣ እንዲሁ ተብለጭልጮና ተቀባብቶ መቅረቡ ጊዜው አይደለም፡፡ ከመነሻው ጀምሮ ዶ/ር አቢይ እንደተጠበቀው አድልኦ የሌለበት ፍትህና ርትዕ ለአዲስ አበባ ነዋሪ የሚያሰፍን ሕግና ደንብ እንዲከበር ፅኑ ሆኖ መገኘት ካልቻለ እጣው ድጋፍ ማጣት ብቻም ሳይሆን የታሪክ ተወቃሽነት አይቀሬ ነው፡፡ አሁን በሚስተዋለው እሰጥ አገባ ወደ ቀጣይ አላስፈላጊ ግጭት ውስጥ መገባቱን ለማስቀረት ቻርተሩ ለነዋሪው ሕጋዊ አካሄድን እንደ መፍትሄ አማራጭ ማስቀመጥ ተገቢ ይሆናል፡፡