
የአዲስ አበባ ጥያቄ ማስተካከያ ይደረግበት፡፡ሁለት ነገሮች ላይ 1ኛ-ህጋዊነትን በተመለከተ 2ኛ-ቃላት አጠቃቀምን (ፖለቲካዊ) በተመለከተ፡፡ይህ አሰተያየቴ የዶ/ር አብይን መግለጫ የተንተራሰ አይደለም፡፡ትግሉ ራሱን በራሱ እንዳይጠልፍ ከመስጋት እንጂ፡፡የጠ/ሚሩን ንግግር መስከረም አበራ የምትባል ጸሐፊ በደንብ ውሥጥን የምታነብ፤ሞራ የምትገልጥ ስለ ሄሰችው አንባቢወቼን እግረ መንገዴን እጋብዛለሁ፡፡ብለው፤ብለው ሱሉልታ፤ሰበታ …አለ ይሉ ጀመር፡፡አደገኛ ንግግር ለሁለተኛ ጊዜ፡፡ወታደሮች ቤተ-መንግስት ባቀኑ ጊዜ ተመሳሳይ ንግግር አድርገዋል፡፡በወቅቱ ለህትመት ባይበቃም በእጅጉ ነቅፌ ለዚሁ ጋዜጣ ልኬ ነበር፡፡ምናልባት ለህትመት በቅቶ ቢሆን ሊታረሙ ይችሉ ነበር፡፡ይሄ ጃዋር በየጊዜው ቄሮ እያለ ከሚዝተው በምን ተለየ፡፡ኧረ እባኮትን የጋንዲን፤የኪንግን ስም እያነሱ፤የማንዴላን ቲ-ሸርት እየለበሱ ይሄ ንግግር አይመጥንወትም፡፡የጋንዲንና የኪንግና ግለ-ታሪክ እንድ ህንድ ወዳጄ አምጥቶልኝ እንግሊዝኛውን አንብቤአለሁ፡፡የማንዴላን ደግሞ አገር ውስጥ ስላጣሁ እንግሊዝ ገዝቼ ባልጨርሰውም ጊዜ ባገኘሁ አጋጣሚ እያነበብሁ ነው፡፡ታላላቅ ሰብዕናወች ናቸው፡፡በጥሞና ያጢኗቸው፡፡
1ኛ-ህጋዊነን በተመለከተ
ትግሉ ህጋዊ መሠረት ላይ መቆም አለበት፡፡ለዚህም የህግ ምሁራንን ምክር መጠየቁ ይጠቅመናል፡፡የአዲስ አበባ ትግል ውጤታማ የሚሆነው በዋናነት በነዋሪወቿ ትግልና በኢትዮጵያ ህዝብ ደጀንነት ነው፡፡ከህወሃት ውጪ ያለው ሃይል እየተቀላቀለ ነው፡፡በቅርቡ አዲስ አድማስ የሰራውን የዳሰሳ ዘገባ ማየት ይቻላል፡፡ህጋዊ መሠረት ያልሁት ስለ ባለ አደራ ምክር ቤት ጉዳይ ነው፡፡ስለ “ባልደራስ ም/ቤት”፡፡ይህንን ማቋቋም ስልጣን ያለው ማን ነው? የአዲስ አበባ ህዝብ ራሱን በራሱ የማስተዳደር ህገ-መንግስታዊ መብቱ ይከበርለት፤አሁን ያለው አስተዳደር እኛን አይወክልም ስለሆነም መንግስት የሽግግር ም/ቤት ያቋቁምልን፤ወይም ከንቲባ ይቀየርልን ወዘተ…ብሎ መንግስት ላይ ጫና ለመፍጠር ልዩ ልዩ ሰላማዊ ትግሎችን መቀየስና ማታገል አንድ ነገር ነው፡፡መንግስት እያለ ያንኑ መንግስት ቁጭ አድርጎ በጎን ሌላ መንግስት(ሽግግር ም/ቤት) ለመመስረት መሞከር ትንሽ ግራ ገብቶኛል፡፡አቶ ያሬድ ጥበቡ ይህን ሃሳብ ከዚህ በፊት ጽፈውት አንብቤአለሁ፡፡አንዳንዴ ምክር ስንሰጥም ሰወችን እንዳናሳስት መጠንቀቅ አለብን፡፡አገር ቤት የገቡ ይህን መንግስት አምነው መሰለኝ፡፡ይገባኛል ትናትና ዛሬ አንድ አይደሉም፡፡እዚህ ላይ ልዩነት የለንም፡፡ይሄ ጥያቄ ቀጥታ መቅረብ ያለበት ለመንግስት ነው፡፡ህዝብ ሉዐላዊ ነው፡፡የመጨረሻው የስልጣን ባለቤት ነው፡፡ስለሆነም የአዲስ አበባ ህዝብ እንኳን የሽግግር ም/ቤት መንግስት ምርጫ ያዘጋጅና መንግስት መመስረት እንፈልጋለን ማለት ይችላል፡፡በእርግጥ ለአዲስ አበባ ህዝብ ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብት የሚታገል ማህበር መንግስትን መጠየቅ ሳያስፈልግ ህጉን ተከትሎ ከሚመለከተው አካል ዕውቅና ማግኘት ይቻላል፡፡ይህንንም ማህበር በተለያየ አደረጃጀት ማዋቀር ይቻላል፤እስከ ወረዳ ድረስ፡፡ይህ ህዝባዊ ድርጅት የአዲስ አበባን ህዝብ ለመብቱ ሊያታግል ይችላል፡፡ቀጥሎ ያለው ጥያቄ መንግስትማ እንኳን የሽግግር ም/ቤት ሊያቋቁምልን በሰላም ከስብሰባ ስንመለስ እያሰረን ነው ልትሉኝ ትችላላችሁ፡፡ እውነት ነው አዲስ አበባ ተጠሪነቷ ለፌደራል መንግስት ቢሆንም ጠ/ሚ/ሩ ከሸኔ የተሰጣቸውን የቤት ስራ በሚቀጥለው ምርጫ ለማሸነፍ ትኩረት ሰጥተዋል፡፡ዴሞግራፊ፤መታወቂያ ወዘተ…የሚያዋጣው መንግስት የህዝብ ጥያቄ መልስ እንዲሰጥ/እንዲቀበል ልዩ ልዩ ትግሎችን ፤ሰላማዊ ሰልፍን ጨምሮ ማካሄድ ነው፡፡ይህም ሆኖ ካልሰማና እንደ ህወሃት ከህዝብ ይሁንታ ውጪ በጉልበት እቀጥላለሁ ካለ እንደ ህወሃት በሰላማዊ ትግል ከቦታው መገፍተር ነው፡፡አካሄዱ ይሄ መሰለኝ!
2ኛ-ቃላት አጠቃቀምን (ፖለቲካዊ) በተመለከተ
አዲስ አበባን አዲስ አበቤ ይምራት የሚለው አነጋገር ሌላ ትርጉም እንዳያሰጠው ከፍተኛ ጥንቃቄ ያስፈልጋል፡፡የፖለቲካ ዋጋ ያስከፍላል፡፡ይሄንን ቀዳዳ ዘረኞችና ጎጠኞች አጀንዳውን ለማስቀየስ ሊጠቀሙበት ይችላሉ፡፡አሁን ጊዜ ደግሞ ተከታይ ሞልቷል፡፡አዲስ አበባ ስልጡን ከተማ ስለሆነች መምራት ያለበት አዲስ አበባ ተወልዶ ያደገ፤ከተማ የሚያውቅ የሚለው ወደ ተራ ነገር ይወስደናል፡፡በጊዜ ቢታረም መልካም ነው፡፡አቶ ያሬድን ያህል ልምድ ያለው፤በዕድሜም ከነ በረከት፤አዲሱ፤ታምራት…አካባቢ ያለ ሰው ይሄን ነገር በተዘዋዋሪ ካነሳው ማዘን እንጂ ሌላ ምን እላለሁ፡፡እርሶ አራዳ መወለድወ አራዳ አያደርገወትም፤ፋርጣ የተወለደውም እዚያ መወለድ ፋራ አያደርገውም፡፡ይህን ስጽፍ አዝናለሁ፡፡ፋርጣም፤ሆነ አምቦ ተወልዶ አዲስ አበባ ነዋሪ ከሆነ፤በህግ የተቀመጠውን ካሟላ ቀጥሎ ያለው ምርጫ የአዲስ አበባ ህዝብ መሠለኝ፡፡አብይ ጂማ ተወለደ፤አሁን ህዝብን የሚያስከፋ ነገር ባይፈጽም የአዲስ አበባ ህዝብ ማንን ይመርጥ ነበር? ስለሆነም የአዲስ አበባ ትግል አዲስ አበቤነት የሚል አዲስ ማንነት የሚወልድ ከሆነ ብዙ ርቀት የሚያስኬድ አይሆንም፡፡አዲስ አበባ ራሷ ትንሿ ኢትዮጵያ መሆኗ ነው፡ጉልበቷ፡፡
