ከመንግስቱ ሙሴ ፌስ ቡክ የተወሰደ
ግለሰብን በተናገረው ነቅሶ አውጥቶ ለትችት ማብቃት ትክክል አይደለም የሚል እምነት አለኝ ሆኖም ግለሰብ እና የፖለቲካ መሪ፣ በብዙ ሰወች የፖለቲካ ህይወት ተጽእኖ ሊኖረው የሚችል ሰውን እንደግለሰብ ቆጥሮ ችላ ማለት አግባብ አይደለም የሚል እምነት እጋራለሁ እናም በዶክተር ብርሐኑ የ መጋቢት 19 ቀን ከ ኦምን ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ በቀጥታ ንግግራቸው “የባላደራ ምናምን የሚባል ነገር የለም አይሰራም። አሸጋጋሪያችን አቶ ታከለ ኡማ አለ እርሱ ይጨርሰው” ብለዋል።
አጀብ የሚያስብል ነው ጉዳዩ። ለመተቸት አመል ለማውጣት አስቤ አይደለም። ሆኖም እጅግ ብዙ ዜጋን ያሳሰበ ጉዳይን ወደጎን ገፍትሮ ማጣጣሉ ብቻ ሳይሆን ታሪክ እራሷን ስትደግም በማየቴም ነበር። 1968 የመጀመሪያው የለውጥ ክሽፈት ትዝ ብሎኝ ነው። ዶክተር አብይ ደጋግመው የያን ዘመኑን ጉዳይ “በ ቸ እና ሸ” ፊደላት ልዩነት ሲፈርጁት አይቻለሁ። ጉዳዩ ያንን ያክል ቀሎ ግን እንዳልሆነ ከልባቸው ያውቁታል እናም በዚያ ልዩነት የተከተለው በመቶ ሽሆቹ ዜጎች በቀይ ሽብርን እና ነጻ እርምጃ ሲመተሩ አይቻለሁ። ያ ልዩነት በመኢሶን እና ኢሕአፓ የተነሳ ሲሆን መኢሶን critical support (እየወቀሱ መደገፍ) ሲል ኢሕአፓ ከጅምሩም ዴሞክራሲ ያለገደብ ይሰጥ አንባገነንነትን እንታገል አለ። ይህ ልዩነት የት እንደደረሰም አይተናል። የ መኢሶን critical support መሆኑ ቀርቶ አፋሽ አጎንባሽ መሆን እና እንዴውም የቀይ ሽብሩ እና የነጻው እርምጃ ፊታውራሪ በመሆን ለትውልድ እልቂት ግንባር ቀደም ድርሻ አበረከተ።
መንግስትን መደገፍ በሰራው ስራ ብቻ ቢሆን መልካም ነው እስከምናምኑ መደገፍ ሲጀመር የመጨረሻ ዳርቻው አንባገነንነትን ማበረታታት ይሆን እና በኋላ በነ ኃይሌ ፊዳ የደረሰው (ተቀምጠው የሰቀሉት ቆመው ማውረድ ተሳናቸው) እንዲሉ ያገዙት እና ያጠናከሩት መንግስት እንደበላቸው አይነት እንዳይሆን ከታሪካችን መማር ጥሩ ነው።
ዶክተር ብርሀኑ ዶክተር አብይን ማመናቸው ተገቢ ነው የግልም እምነታቸው ነው። እንደ ድርጅት ካልን አቶ አንዳርጋቸው የፖለቲካ ምህዳሩ ጠቧል የታሰበውን ጎዳና እየሳተ ነው የሚል ሰምቻለሁ እና ግንቦት 7 ማለት ብርሀኑ ብቻ ካልሆነ የድርጅቱ አቋም አይደለም ማለት ነው። ስለዚህ ይህ መጣጥፍ ዶክተር ብርሀኑን እንደግለሰብ ያያል ማለት ነው። ዶክተር ብርሐኑ ዶክተር አብይን በተመሳሳይ ቃለምልልስ “እኔ አብይን ሙሉ በሙሉ አምናለሁ። ወደ ዴሞክራሲ ይወስደናል” ይላሉ። ችግራችን ከአረዳድ እየሆነ እንጅ የመደገፍ ወይንም የመቃወም ጉዳይ አይመስለኝም እናም ብዙ ዜጎች ዶክተር አብይን ደግፈዋል። በሀገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን በውጭ ያገኙትን ድጋፍ ሰፊ እንደነበር አይተናል በዚያ ችግር የለም ዶክተር ብርሀኑም ማመን እና መደገፋቸው ከአየነው ህዝባዊ ድጋፍ የሚርቅ አይደለም ማለት ነው። ሆኖም “ፍየል ወዲያ፣ ቅዝምዝም ወዲህ” የሚል አባባል አለ። ግለሰቡን ማመን እና መደገፍ አንድ ነገር ነው። ሀገ መንግስቱ ተቀይሮ መሰረታዊ ለውጥ እንዲመጣ ጥያቄ ማቅረብ የተለያዩ ናቸው። ኢሕአዴግ አሁንም አልተለወጠም አሁንም አፋኝ በሆነው እና ዘርን ማህከል ባደረገው ሕገመንግስት ይመካል። ጠ/ሚኒስቴሩም የዚህ ሕገመንግስት አካል እና አስፈጻሚ ስለሆኑ እንዲቀየር መታገል የለውጥ ፈላጊው ድርሻ ነው የሚል ሰፊ ግንዛቤ አለ። ይህ ማለት ግለሰቡን አለማመን ወይንም መጻረር ማለት አይደለም። ሁልግዜ የተቋም እና የስርአት ለውጥ ስንፈልግ ጠያቂው ግለሰብን ያነጣጠረ ጥያቄ አያቀርብም ስርአቱ ይቀየር በምንለው ግለሰቡ ከተስማማ የትግላችን አካል እና አጋር ይሆናል። ጥያቄአችን ጥያቄው ነው። ስለዚህ ስርአቱን አብረን እናፍርስ እና ሊያሰራን የሚችል በጋራ እንገንባ ማለት ነው። ዶክተር ብርሀኑ ሙሉ ለሙሉ እደግፈዋለሁ አምነዋለሁ ይላሉ ያ ግን በቂ አይደለም የሚል ሰፊ የህብረተሰብ ክፍል ይኖራል። ማለትም ከላይ እንደገለጽሁት ትግሉ እና ጥያቄ ግለሰብ ላይ ያነጣጠረ አይደለም። ስርአት ለውጥ ላይ ነው። በዚህ አባባል ለምሳሌ ዶክተር አብይ ዴሞክራት ናቸው ግን ያለው ህገመንግስትን ሙሉውን በስራ ብናውል ዴሞክራሲ ሊያመጣ ይችላል ብለው ሊያምኑ ይችላሉ። እዚህ ላይ በዴሞክራሲ ኃይሎች መካከል ልዩነት አለ ማለት ነው። አንዱ እና የኔብጤው የዚህ ስርአት ብልሽቱ ከመሰረቱ ሕገመንግስቱ ነው። የተረቀቀው ሕዝብን ሳያማክር እና የሕዝብ ይሁንታ ሳያገኝ በድርጅት የፖለቲካ ፕሮግራም ስለሆነ ዘርን ያማከለ፣ ቋንቋን መሰረት ያደረገ ፌደራላዊነት፣ የፖለቲካ አደረጃጀት፣ ክልልተኝነት ወዘተረፈ ሁሉ እድገቱ ዴሞክራሲን ማምጣት ላይ ሳይሆን መከፋፈል እና መለያየት፣ የኔ እና የናንተ የሚል አስተሳሰብን ማሳደግ፣ የግል ነጻነትን ሳይሆን የስብስብ መብትን ብቻ የሚያተኩር በመሆኑ የኋላ ኋላ ውጤቱ አገርን ማፍረስ እና የባንቱስታን አይነት መመስረት ነው። ባጭሩ ዴሞክራሲ ስንል የግል መብት መሰረት ያደረገ ማለት እና ያለው ህገመንግስት ደግሞ ይህን የግለሰብ ነጻነትን ያማከለ ሳይሆን የብሄር፣ ብሄረሰቦች ሕዝቦች በሚል በግልጽ ያስቀመጠ ነው።
ሌላው ዶክተር ብርሀኑ ታከለ ኦማ ያሸጋግራናል ብየ አምናለሁ ይላሉ። ጥያቄው ያ አይደለም። ጥያቄው የአዲስ አበባን የማንነት ጉዳይ ኦዴፓ ባወጣው መግለጫ ከነዋሪው ጋር ይቃረናል። የአዲስ አበባ ጉዳይ በፖለቲካ ድርጅት ያውም የዘር ድርጅቶች የሚወሰን እና በጠረጴዛ የሚያልቅ ብቻ አይደለም እስክንድርን እና የከተማዋን ነዋሪወች ሁሉ ያስጨነቀ ዋና ጉዳይ አዲስ አበባ የነዋሪወቿ ናት፣ የኢትዮጵያም ዋና ከተማ ናት፣ አለም አቀፍ እና አህጉር አቀፍ ተቋማትን ያቀፈች ናት እናም እንዲህ እከሌን አምናለሁ እርሱ ይጨርሰው የምታሰኝ ባለመሆኗ መፍትሄ ለመፈለግ የተዘየደ ነው። የባላደራ ምናምን የሚባል ቀሎ የሚታይም መሆን የለበትም ዜጎች በግልም ሆነ በስብስብ መፍትሄ ሲሹ አባሪ ተባባሪ መሆነ ፍትሀዊነት ነው። ዶክተር ብርሀኑ በተናገሩት እደግፋለሁ፣ ይህ ባላደራ ምናምን የሚባለውን አልደግፍም ሲሉ የ ኦዴፓን አቋም እደግፋለሁ ማለት ነው ይህ ካልሆነ ትንሽ ማብራራት ይገባል እላለሁ።
ዛሬ ሌላ ከዚህ ከማህበራዊ ገጽ ያየሁት የዶክተር ብርሀነመስቀል ስኝ “ምርጫ አያስፈልግም” የሚል ሀሳብ እና የዶክተር ብርሀኑ ባላደራ ምናምን አያአስፈልግም የሚሉት ሁለት ተመሳሳይ አስተሳሰቦች እንደሚመስለኝ የብዙሀንን (ሕዝብን) ፍላጎት የሚያቅፉ አይደሉም የሚል አስተሳሰብ ነው በዚህ ያንጸባረቅሁ እናም ሌላ አሳማኝ ሀሳብ ለማየት ዝግጁ ነኝ።
