March 28, 2019

አርበኞች ግንቦት 7 ራሱን ከፎቅ ከስክሷል –
ዘረኞችም ገበያ ይደራላቸዋል
===============================
ከፕሮፍ ብርሀኑ የኦቢኤን ቃለምልልስ ቅንጫቢ ንግግር የተረዳሁት ሁለት ነጥቦችን ነው።
1.የፓርቲው ሁለት ዋና አመራሮች ወቅታዊ የፖለቲካ አረዳድ ለየቅል ሆኗል:: አቶ አንዳርጋቸው ከሰሞኑ በሰጧቸው ሁለት ቃለምልልሶች ያደመጥነው የእነ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ መንግሥት ሀዲድ እየሳተና ሀገሪቷ ወደለየለየት እርስበርስ ግጭት እያመራች መሆኗን ነው።ፕሮፍ ብርሀኑ ደግሞ የሚያሻግረን የእነ ዐቢይ መንገድ ነው ይላሉ:- “ዶክተር ዐቢይ፣ አቶ ታከለ ሆነ አቶ ለማ አሻጋሪዎቻችን ናቸው::”
ሁለቱ አንጋፋ ፖለቲከኞች የዛሬ ዓመት የነበራቸው አመለካከት አንድ እንደነበር ያስታውሷል። አሁን አንዳርጋቸው ይሰጋሉ፣ ብርሀኑ ተሰፋ ያደርጋሉ።
2.ፕሮፌሰሩ የእነ እስክንድር ባልደራስ ምክርቤትን “ባለአደራ የሚባለው ነገር ትክክል አይመስለኝም” ሲሉ በቀጥታ የዐቢይን ተቃውሞ ይደግማሉ።
ይህ ምን ማለት ነው? አርበኞች ግንቦት 7 ላይስ ምን ያስከተላል?
=================
ፕሮፍ ብርሀኑ በእነ ዐቢይ ላይ የፀና እምነት የጣሉበት የራሳቸው አሳማኝ ምክንያት ሊኖራቸው ቢችልም የድርጅታቸውየደጋፍ መሠረትን ያላገናዘበ ነው። በእነ ዐቢይ የአንድ ዓመት ሥልጣን ዘመን በርካታ ለውጦች ቢታዩም በአዲስ አበባና ዙሪያዋ ሕዝብ ላይ የተቃጣው ጥቃትና ስጋትን የቡራዩ ተፈነቃዮችን ከመጎብኘት በስተቀር ማውገዙ ቀርቶ በአደባባይ ሕመሙን አለመጋራታቸው እምነት የጣለባቸውን ደጋፊ መሠረት እየናደ ነው።
የእነ ዐቢይ መንግሥት በአክራሪ ኦሮሞ ፖለቲከኞች ሴራ በየቦታው መሠንጠቅ እንዲገጥመውና ለውጡ እንዲደናቀፍ ማፈናቀልና የኬኛ ስግብግብ ፖለቲካን ሆን ብለው እያራመዱ እንደሆነ ቢገለጽም ያንን የማክሸፍና ሕዝብን አንድ አደርጎ ሀገርን የመምራት ኃላፊነት በዋነኛነት የሥርዓቱ ፈንታ እንጂ የአርበኞች ግንቦት 7 አይደለም። የተቃዋሚ ድርጅቱ ኃላፊነት ለውጥ እንዲደናቀፍ መንስዔ ባለመሆን የራሱን ፖለቲካ በማራመድ የደጋፊዎቹንና የሕዝብን ጥያቄ አጀንዳው እያደረገ በአጭርና ረጅም ጊዜ እቅድ ምላሽ መፈለግ ነው። ይሁን እንጂ አርበኞች ግንቦት 7 ከተቃዋሚ ድርጅትነት ይልቅ ወደ እነ ዐቢይ መንግሥት ፍጹም ደጋፊነት ተቀይሯል። ሀገር እንድትረጋጋ ከገዢ ሥርዓት ጋር መተባበርና የራስን ሕዝባዊ መሠረት መጣል ለየቅል ነው። ለራስ ፓርቲ አደጋው ከፍተኛ ነው። ከዚያ ይልቅ አንድ ፊቱን ከኢህአዴግ ጋር መዋሃድ ይሻላል።
በተለይ የእነ እስክንድር እንቅስቃሴ ላይ የተያዘው አቋም ራስን ከፎቅ ከፍታ እንደመከስከስ ነው። ስሌቱ ተወራርዶ የማያልቅ ዋጋ የሚያስከፍል ነው።በመከራ ዘመን የታነፀ ሕዝባዊ ድጋፍን አሁን በተገኘው የመንቀሳቀስ ዕድል ይበለጥ አደራጅቶ ለምርጫ የመዘጋጀት አጋጣሚ አምልጧል። እውነቱን ለመናገር ድርጅቱ በዚህ ከቀጠለ ድጋፍ ሊያገኝ የሚችለው ምናልባት በኃዘኔታ ጀረባውን መታ-መታ ሊያደርጉት ከሚችሉ የዐቢይ ደጋፊዎች ብቻ ነው። ከዚህ በኋላ አልማዝን ባህር ውስጥ ወርውሮ እንደመፈለግ ይሆናል። ፖለቲካ ውለታ አያውቅም።
ይህ ምን ይፈጥራል?
==================
በተለይ የአንድነት ፖለቲካ የሚያራምዱ ድርጅቶች የሌሉት ደጋፊ ሌላ ምንም አማራጭ መግቢያ ያጣል። ይህ ደግሞ ለዘረኞቹ የብሔር ድርጅቶች ትኩስ ገቢያ ይፈጥራል። ዘረኞች እንደሚያደርጉት ቅድመ አያት ፣ እናት፣ አጎት … ወዘተ የዘር ሐረግ ቆፍረው እየፈለጉ ወደ አብን፣ ኦነግ፣ ህወሓት፣ … እና ሌሎች የብሔርተኛ ድርጅቶች ይሰገሰጋሉ። የፀና ብቻ ሀገሩን አስቀድሞ ኢትዪጵያዊነቱን ይዞ የራሱን ትክክለኛ መርከብ ይፈልጋል። የሚያሻግረው የራስ አቋም ነው።
ማሳሳቢያ
ይህ በእንዲህ እንዳለ ከመለስ በታች መቃብር ውስጥ ያለውን ሙት ልደቱ አያሌውን ይቺን አጋጣሚ ተጠቅሞ ያለኃፍረት ወደ መድረክ ለመጎተት የምትደረገው ጉተታን እዚያው መቃብር ውስጥ ተውት። አማራ ቅብርጥስዮ የዘር ጭምብል አይሰራም።
ሌላው ትምህርት መጨረስ አቅቶት በብርሀኑ እያሳበበ ውድቀቱን ለመሸፋፈን የሚጥረው እብድ መዳኛ የለውም።
(ለበለጠ ግንዛቤ የፕሮፍ ብርሀኑን ሙሉ ቃለምልልስ መስማት ያስፍለጋል)
