ከብሩክ አበጋዝ መጋዝ ፌስ ቡክ የተወሰደ
ወሎን ከአማራው ለመገንጠል ነው…
.
ማን ነው ተገንጣይ? ማን ነውስ ገንጣይ? ለምንድን ነው ሌሎች ሸዋን፣ ጎጃምን አልያም ጎንደርን ከአማራው ሊገነጥሉ ነው የማይባሉት? አንደኛው ጠባቂና ተከላካይ ሌላኛው ተነጣይ አድርጎ ለማውራት መስፈርቱ ምንድን ነው ሞራሉስ ከየት መጣ? አንድ ስለ ማንነት መታወቅ ያለበት ሀቅ አለ ይኸውም ማንነትን በዘረመልና በደማዊ ትስስር ካደረግነው ምንም እንኳ ዘግይቶ ከኦሮሞ ጋር ቢዋሃደም የአማራነት ደም ግንኙነት ያለው ከወሎ ማኅበረሰብ ጋር ነው። የአማራ ነገድ ጥንታዊ መኖሪያ አገር የዛሬው ወሎ ከፍተኛ ቦታወች፣ ለወሎ ተዋሳኝ የሆኑት የሰሜን ሸዋ እና የደቡብ ጎንደር አካባቢወች ናቸው። በአማራ ክልል ውስጥ ከሚገኙት ጥንታዊ ከሚባሉት አብያተ ክርስትያናት በእኔ ግምት 70% የሚሆኑት የሚገኙት ወሎ ውስጥ ነው። በአማራ ክልል ውስጥ ረጅም እድሜ ያስቆጠረችው ቤተ ክርስትያን የምትገኘው ወሎ ውስጥ ነው። ወሎ የኢትዮጵያ የእስልምና ማዕከል ነው፤ ለመላው ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ከጥንት እስከ ዛሬ ድረስ እንደ ብርሀን የሚያበሩት ክዋክብቶች ሁሉ ወሎየወች ናቸው። በሃይማኖትም፣ በዘርም፣ በስነልቦናም አማራ የነበሩት የመካከለኛው ዘመን ነገሥታት ከዛሬው ወሎ እየተነሱ ነበር ሌላውን ሁሉ አማራ ያደረጉት ያኔ የአማራነት መስፈርቱ ተጠምቆ ኦርቶዶክስ መሆን ነበር፤ አማራ ጎሳዊ ሳይሆን ቤተሰባዊ ማህበረሰብ በመሆኑ እንደ ኦሮሞ፣ አፋር፣ ሶማሌ ወዘተ ዘር በመቁጠር እዚህ ጎሳ ነኝ አይልም። አማራነት እንደ ኦሮሞነት አልያም ትግሬነት የዘመናት የስነ ልቦና ሥሪት ከሆነ ነው ከወሎ ውጭ ያለው ሕዝብ አማራ ሊባል የሚችለው። ይህን የምለው ለዘመናት በጦርነት፣ በስደት፣ በንግድ ወዘተ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ የሚደረገውን ፍልሰት በመዘንጋት አይደለም። ሀቁ ይህ ሆኖ እያለ አንደኛው የአማራን ግዛት ጠባቂ ሆኖ ሌላኛውን ተገንጣይ አድርጎ ፖለቲካ ማውራት አስቂኝ ነው። አሁን ያለው ኢህአዴግ የዘረጋው የክልል አስተዳደር መዋቅር እስካለ እንዲህ ዓይነት ነገርን እንደ ቁምነገር ማውራት ሞኝነት ነው፤ ከሞኝነት ካለፈ ደግሞ ለየት ብለው የሚያስቡ ወሎየወችን ማጥቂያ መንገድ አድርጌ ነው የምወስደው።
.
ወሎ ለየት ያለ ነገር አለው
——————
የወሎ ማሕበረሰብ ከሌሎቹ የአማራ ክፍላተ ሀገራት ብዙ የሚያመሳስለው ነገሮች የመኖሩን ያክል በዚያው ልክ ደግሞ ለየት ያሉ ነገሮች አሉት። ወሎ ልክ እንደሌሎቹ ክፍለ ሀገራት በአብዛኛው ወጥ የሆነ የሃይማኖት፣ ባህል፣ ቋንቋ ወዘተ ተመሳሳይነት የለውም። እንደ ሸዋ፣ ጎጃም፣ ጎንደር ዓይነት ክፍለ ሀገራት የክርስትና አማኙ ቁጥር ከአጠቃላዩ ሕዝብ ከ3/4ኛ በላይ አይደለም። በ1999 የሕዝብና ቤት ቆጠራ መረጃ መሰረት የወሎ ሕዝብ 50% ሙስሊም 50% ክርስትያን ነው አልያም ደግሞ 51% ሙስሊም 49% ክርስትያን ነው። በአንዳንድ የወሎ አካባቢወች የክርስትያኑ ቁጥር ከፍተኛ ሲሆን በተመሳሳይ በሌሎች አካባቢወች ደግሞ የሙስሊሙ ቁጥር ከፍተኛ የሚሆንበት አጋጣሚ በርካታ ነው። ከዚህ በተጨማሪ ከሌሎች ክፍለ ሀገራት ለየት ባለ መልኩ ከሁለት በላይ ቋንቋወች የሚነገሩበት ነው። አርጎብኛ፣ አገውኛ፣ ኦሮምኛ፣ ራይኛ፣ አፋርኛ ወዘተ ቋንቀቋወች ይነገራሉ፤ በሁሉም አካባቢ ደግሞ አማርኛ ይነገራል። በሌሎች አካባቢወች ከእምነት አንጻር አንደኛው ወገን ቁጥሩ እጅግ የገዘፈ መሆኑና በወሎ አካባቢ ደግሞ የተመጣጠነ መሆኑ ለፖለቲካ አሰላለፍም የራሱ ተጽእኖ አለው። ወሎ ውስጥ ከእምነትም ሆነ ከዘውግ አንጻር አንዱን ወገን ያገለለ ፖለቲካ ማራመድ ነጥብ የሚያሳጣ ከመሆኑም በላይ ሕብረተሰቡን በጎራ በመክፈል ውጥረትና እኛና እነሱ ስሜት መፍጠሩ አይቀርም። ያልሰለጠነ የፖለቲካ ባህል ባለው ማሕበረሰብ ውስጥ እኛና እነሱ ስሜት ከተፈጠረ የሚከተለው ውጤት አደገኛ ነው። አርቀው ተመልክተው ይኼን የሚያስተውሉ ወሎየወች ሁሉንም ዘውግና ሃይማኖት ያማከለ የፖለቲካ እይታ ቢከተሉ የሚያሰተቻቸው ሳይሆን የሚያስመሰግናቸው ነው። የአንድ ቤተሰብ አባላት በዘውጋዊ አልያም ሃይማኖታዊ መደባቸው የተለያየ ጫፍ የረገጠ የፖለቲካ አስተሳሰብ የሚያራምዱ ከሆነ ፖለቲካው ጤነኛ አይደለም። ከዚህ በተጨማሪ በእንዲህ ዓይነት ፖለቲካ የሚገፉ ወገኖች የእነሱን ዘውግ ወይም ሃይማኖት በበጎ አልያም ከፍ አድርጎ የሚያይ የፖለቲካ አሰላለፍ ጎን በመሰለፍ ከሌላው ወገን ጋር በተቃራኒ ተገዳዳሪ ለመሆን አይጥሩም ማለት ሞኝነት ነው። ይህን የተገዳዳሪነት መንፈስ በኃይል እጨፈልቃለሁ ማለት ደግሞ እብሪት ይሆናል። ዛሬ ላይ ሆነህ ነገን ካልተመለከትክ ውድቀትህን እያፋጠንክ ነው።
Cc: ለGetachew Shiferaw ዓይነት የአማራ ጠበቃ ነን ባይ ሀሰት ተመግበው ውሸት የሚተፉ ጋዜጠኛ ነን ባዮች። እንትና መጣብህ፣ ወዮልህ፣ አለቀልህ እያሉ ፍራትና ስጋት እየፈበረኩ ሸቅላቸውን ላጧጧፉ ሸቃዮች። እነማን እንደሆን ልብህ ያውቀዋል እኛም ገዝፈን እንታያለን!! ከሁለት ወር በፊት ፍጹም ብርሃኔ አንተ የምታጨበጭብለትን አብንን አወድሶ አሞግሶ የጻፈው እኮ አብን የህወሓት ወኪል ስለሆነ ነው ወይ?

