የአዲስ አበባ ባላደራ ምክር ቤት/ባልደራስ ዛሬ በራስ ሆቴል ሊያደርግ ያቀደው ሰብሰባ እንዳይካሄድ መከልከሉን አስመልክቶ ከጥቂት ደቂቃዎች በፊት አንዲት ፅሁፍ አውጥቼ ነበር። ነገር ግን ወዲያው ለጠ/ሚኒስትር ቢሮ ቅርበት ያለው አንድ የመንግስት ሃላፊ ስልክ ደውሎ ስለ ጉዳዩ ማብራሪያ ሰጥቶኛል። በስልክ የነገረኝን መረጃ በፌስቡክ እንዳወጣው ጠይቄው ፍቃደኛ በመሆኑ እንደሚከተለው አቀርበዋለሁ። በመጀመሪያ ደረጃ ዛሬ በራስ ሆቴል ሊያካሂድ የነበረው ጋዜጣዊ መግለጫ እንዲቀር የተደረገው በከፍተኛ የመንግስት ኃላፊዎች ትዕዛዝ ነው። ለዚህ ዋናው ምክንያት ደግሞ በጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ላይ አካላዊ ጥቃት ለማድረስ የተጠነሰሰ ሴራ መኖሩ በደህንነት መስሪያ ቤቱ ስለተደረሰበት ነው።
ባለፈው ሳምንት በውጪ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ፊርማ በማሰባሰብ የሀገሪቱ መንግስት ለጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ልዩ ጥበቃ እንዲያደርግለት መጠየቃቸው ይታወሳል። በዛሬው እለት ሊካሄድ በታሰበው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ደግሞ ህጋዊ እውቅና እና ፍቃድ ያላቸው ጋዜጠኞች ብቻ የሚታደሙበት አይደለም። ከዚያ ይልቅ ማንኛውም ግለሰብ በቦታው ተገኝቶ ለመታደም ይችላል። ይህ ደግሞ በእስክንድር ነጋ ላይ ጥቃት ለማድረስ ዓላማ ላላቸው ሰዎች ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል። በዚህ መሰረት በጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ላይ ሊቃጣ የሚችለውን አደጋ ለማስቀረት ሲባል የዛሬው መግለጫ እንዲሰረዝ መደረጉን ከላይ የተጠቀሱት የመንግስት ኃላፊ ነግረውኛል።
ከዚሁ ጋር አያይዤ “በቀጣይ ችግሩን ለመቅረፍ በመንግስት በኩል ምን ለማድረግ ታቅዷል?” በሚል ላቀረብኩላቸው ጥያቄ ሃላፉው ምላሽ ሰጥተውኛል። በዚህ መሰረት የአዲስ አበባ ባላደራ ምክር ቤት/ባልደራስ በየትኛውም ግዜና ቦታ ጋዜጣዊ መግለጫ ሆነ ስብሰባ የማድረግ መብት እንዳላቸው ገልፀዋል። ነገር ግን ከላይ ለመጥቀስ እንደተሞከረው፣ የጋዜጠኛ እስክንድር ነጋን ሆነ የሌሎቹን ሰላምና ደህንነት በተገቢው ሁኔታ ለማስከበር እንዲያመች ኮሚቴው የሚያካሂደው ስብሰባ ይሁን መግለጫ በግልፅ ለይቶ እንዲያቀርብ ጠይቀዋል። እንደ እሳቸው አገላለፅ፣ ጋዜጣዊ መግለጫ የሚሰጥ ከሆነ ህጋዊ ፍቃድና ዕውቅና ያላቸው ጋዜጠኞች እና ሌሎች ባለሞያዎች ስለሚገኙ የፀጥታና ደህንነት ችግር እንዳይፈጠር መቆጣጠር ይቻላል። ህዝባዊ ስብሰባ ከሆነ ደግሞ የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳደር ጋር በመነጋገር ለዚህ በቂ የሆነ የሰው ኃይል እና ማቴሪያል በመመደብ ጥበቃ እንደሚደረግ አስታውቀዋል።
ሆኖም ግን ልክ እንደ ዛሬው መግለጫ ይሁን ስብሰባ በግልፅ በማይለይበት ሁኔታ ማንኛውም የህብረተሰብ ክፍል የሚገኝበት መድረክ ላይ አስፈላጊውን ጥበቃና ድጋፍ ለማድረግ አስቸጋሪ መሆኑን ገልፀዋል። ከዚሁ ጋር በተያያዘ ባለፈው ሳምንት የአዲስ አበባ ባላደራ ምክር ቤት/ባልደራስ የስብሰባ አዳራሽ እንዳይከራዩ ጫና እና ግፊት ሲደረግባቸው እንደነበር በመጥቀስ እንዲህ ያሉ አፍራሽ ተግባራት በማስቀረት ረገድ በእናንተ በኩል ምን ታስቧል የሚል ጥያቄ አቅርቤላቸው ነበር። የተጠቀሱት የመንግስት ኃላፊ እንደነገሩኝ ከሆነ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ጋዜጣዊ መግለጫ ለመስጠት ከፈለገ የጠ/ሚኒስትር ፕሬስ ሴክሬታሪያት ቢሮ ሊተባበረው ፍቃደኛ መሆኑን ገልፀዋል። በዚህ መሰረት የኮሚቴው አባላት በጠ/ሚኒስትር ቢሮ በሚገኘው የስብሰባ ክፍል (Conference room) ወይም በህዝብ ተወካዪች ምክር ቤት የሚገኘውን የስብሰባ አዳራሽ መጠቀም ይችላሉ ብለዋል።
በመጨረሻም ጠ/ሚ አብይ አህመድ የአዲስ አበባ ባላደራ ምክር ቤት/ባልደራስን አስመልክቶ የሰጧቸውን አሉታዊ አስተያየቶች በመጥቀስ ስለ ሁኔታው ጠይቄያቸው ነበር። እሳቸው እንደነገሩኝ ከሆነ ጠ/ሚ አብይ ከጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ጋር በስልክ እንደተነጋገሩ እና በቀጣይ ቀናት በአካል ተገናኝተው ለመነጋገር እቅድ እንደነበራቸው ጠቁመዋል። ጠ/ሚኒስትሩ በዚህ ጉዳይ ላይ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋን ጨምሮ ሌሎች የኮሚቴው አባላትን ለማናገር ፍቃደኛ መሆናቸውን በመጥቀስ ዛሬ የተፈጠረው ችግር በጉዳዩ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ሊኖረው እንደማይገባ ተናግረዋል። እኔም ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥተው አፋጣኝ ምላሽ የሰጡኝን የመንግስት ኃላፊ በማመስገን መረጃውን እንሆ ብያለሁ።
