March 30, 2019

በነእስክንድር ነጋ የሚመራው. ሰላማዊ በሆነ መንገድ በመጋቢት አንድ በተደረገውና በአስር ሺሆች የሚቆጠሩ አዲስ አበቤዎች በተገኙበት ስብሰባ በተቀመጡት አምስት ነጥቦች ዙሪያ፣ የአዲስ አበባን ህዝብ ለማደራጀትና የአዲስ አበባን ህዝብ ጥቅም የሚያስጠበቁ በመጪው ምርጫ እንዲያሸንፉ ለማድረግ፣  የባለአደራ ምክር ቤት ቤት በሚል እንቅስቃሴ ማድረጋቸው ይታወቃል። ያንን ተከትሎ  ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አብይ አሀመድ፣ ባላአደራውን “መፈንቀለ መንግስት” ለማድረግ እንዳሰባ አድርገው በማቅረብ ባልተለመደ ሁኔታ ጠንካራ ትችት ማቅረባቸውም የሚዘነጋ አይደለም።

ያንን ተከትሎ የባለ አደራ ምክር ቤት፣ የሚታገልለት አላማ፣ ዶ/ር አብይ እንደገለጹት ሳይሆን፣  ሰላማዊ እንደሆነ ለሕዝብ ለማስረዳት፣  በቦሌና አቃቂ/ቃሊት ክፍለ ከተሞች ሕዝባዊ ስብሰባዎች ለማድረግ መጋቢት አስራ አምስት ቀን፣  ዛሬ ደግሞ ጋዜጣዊ መግለጫ ለመስጠት አቅዶ የነበረ ቢሆንም፣ የዜጎች ህግ መንግስታዊ መብትን በመገፈፍ ፖሊሶች ከበላይ ታዘናል በሚል  እገዳ እንዳደረጉባቸው ከአዲስ አበባ የመጡ መረጃዎች ይጠቁማሉ።

ዛሬ በራስ ሆቴል ባለአደራው ሊሰጠው የነበረዉን ስብሰባ ተመልከቶ ፣ አንድ የሆቴሎ ሰራተኛ፣  ” .እስካሁን መግለጫ ለመስጠት ክፍያ ተፈፅሞ የተከለከለ አንድም ሰዉ አናዉቅም፡፡ የአሁኑ የተለየ የሚያደርገዉ አዘጋጆቹ ምን ስላደረጉ ነው? በገዛ ሀገራችን ሁለተኛ ዜግነት ማየት እጅግ ያማል።  ስለ አዲስ አበባ ህዝብ ለመናገር ሚስማር የተቸነከረ ዱላ አልያዛችሁ ።  ጠጠር በእጃችሁ አልጨበጣችሁ። ይሄ ክልከላ ምን ማለት ነው? ህዝብ ይፈርደዉ ” ስትል በድርጊቱ ማዘኗን ገልጻለች።

የባለ አደራ ምክር ቤት አባላት ፖሊሶች እንዳይሰበሰቡ ባገዷቸው ጊዜ በሰላም ወደ መጡበት የተመለሱ ሲሆን፣ ከዚህ በኋላ ስለሚኖራቸው እንቅስቃሴ በቀጣይነት ለሕዝብ ያሳወቃሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የባለ አደራው ምክር  ቤት ምክትል የሆኑት አቶ እሊያስ ገብሩ በጉዳዩ ላይ የሚከተለውን አስተያየት ሰጥተዋል

————————-

ዛሬ በራስ ሆቴል አዳራሽ ለበርካታ የሚዲያ ድርጅቶች ጋዜጣዊ መግለጫ ለመስጠት አቅደን፣ በቀጠለው የአገዛዝ አፈና ተደናቅፏል። ድርጊቱ ብዙዎችን አሳዝኗል። በቦታው ቀድማችሁ በመድረስ የተገኛችሁ የሚዲያ ባለሞያዎችና ሌሎች ሰዎችም ጭምር (በሙሉ) ከልብ እናመሰግናለን!

አሁን ባደረሰን መረጃ መሠረት ደግሞ፣ በአሁን ሰዓት በባልደራስ አዳራሽ ኦዴፓ ስብሰባ እያደረገ ይገኛል።

እንዲሁም ስለ”7ኛው ንጉስ” ትንቢት ተናግራለች የተባለች አንዲት ሴት፣ በቦሌ መንገድ መንገድ ተዘግቶ ጭምር አቀባበል ሲደረግላት እንደነበረም መረጃዎች ደረሰውኛል።

እንግዲህ፣ በአንድ ሀገር ውስጥ …ሁለት አይነት ዜግነት በግልጽ እያየን እንገኛለን። አድሏዊነትም በግልጽ እየተተገበረ ነው!

…በአሁን ወቅት ሰላማዊ እንቅስቃሴን የማዳፈን ዝማሜ በግልጽ እየተስተዋለ ነው። እኛም በቻልነው መጠን የህግ አግባብንና በመከተልና ሰላማዊነትን በማንገብ፣ እየታገልን እንገኛለን። የቀረውን ልቦና ያለው ህዝብ ይፍረድ!