የሲኤንኤን ዘገባ እንዲስተካከል ግፊት አድርገዋል

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ኩባንያ ካስተናገደው አስከፊ አደጋ ጀርባ አውሮፕላን አምራቹ የአሜሪካ ቦይንግ ኩባንያ ላይ ጫናዎች ተበራክተዋል፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ንብረት የሆነው ቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላን 157 መንገደኞችንና የበረራ ሠራተኞችን አሳፍሮ ወደ ኬንያ በመጓዝ ላይ ሳለ ባጋጠመው አደጋ መከስከሱን ተከትሎ፣ ቦይንግ ኩባንያ በርካታ ጥያቄዎች እየተነሱበት ነው፡፡ ከበረራ ደኅንነትና የአውሮፕላኑን የበረራ ሥርዓት ከሚቆጣጠረው ሶፍትዌርና ከሌሎችም የቴክኒክ ጉዳዮች አኳያ ኩባንያው አጥጋቢ ምላሽ እንዲሰጥባቸው የሚሹ ጥያቄዎች ከወዲሁ መንሸራሸር ጀምረዋል፡፡
በኢትዮጵያ የተከሰተው አደጋ ከኢንዶኔዥያው አውሮፕላን አደጋ ጋር ተመሳሳይ ሆኖ መገኘቱ የአደጋዎቹ መንስዔ ከቦይንግ ኩባንያ ጋር የተያያዘ ጉዳይ እንዳላቸው በርካቶች ባመኑበትና የአደጋውን ሁኔታ ሊያሳዩ የሚችሉ የቅድመ ምርመራ መረጃዎችም ወደዚህ ያዘመሙ መነሻዎች ማሳየት በመጀመሩበት ወቅት፤ ይህ ብቻም ሳይሆን ኩባንያው በኢትዮጵያ አደጋ ሳቢያ ከ40 ቢሊዮን ዶላር በላይ የገበያ ኪሳራ እንዳጋጠመው መነገር በጀመረበት ወቅት፣ ከወደ አሜሪካ አዲስ የሚዲያ ዘመቻ መከፈቱ ታይቷል፡፡
ፋይናንሺያል ታይምስ፣ ዎል ስትሪት ጆርናልና ዘ ዋሺንግተን ፖስት የተሰኙት ጋዜጦች ያወጧቸው ዘገባዎች ያስተናገዷቸውን ሐሳቦች የኢትዮጵያ አየር መንገድ ኩባንያ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረ ማርያም ፈጣን ምላሽ እንዲሰጡ አስገድደዋቸዋል፡፡ አቶ ተወልደ ብቻቸውን እንዳልነበሩ የታየበት አጋጣሚ የታየው ግን ሰሞኑን ሲኤንኤን በትዊተር ገጹ ያሠራጨው ዘገባ ነው፡፡ ለዚህ ዘገባ አቶ ተወልደም ሆኑ የአየር መንገዱ ሌሎች ኃላፊዎች ቀጥተኛ ምላሽ ባይደመጥም፣ ድፍን አፍሪካውያን ግን ዳር እስከ ከዳር የሲኤንኤን ዘገባን አጣጥለው ይብሱን ቦንይንግ ኩባንያም ሆነ የአሜሪካ ሚዲያዎች የሰላ ትችትና ከባድ ወቀሳ አስነስቶባቸዋል፡፡
ሲኤንኤን ያቀረበው ዘገባ ‹‹የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከዓለም ቁንጮ አየር መንገዶች አንዱና በደኅንነት ደረጃውም እንዲሁ የሚወደስ ነበር፡፡ የአደጋው መከሰት ግን ይህንን መልካም ስሙን የሚያሳጣው ነው፤›› የሚል አንድምታ ያለው ርዕስ በመጠቀም ያወጣው ዘገባ፣ በሺዎች የሚቆጠሩ አፍሪካውያን ወዲያውኑ ውርጅቢኝ ያወረዱበት ሲኤንኤን፣ የዘገባውን ርዕስ ከማስተካከል ባሻገር፣ በዚሁ ዘገባ ውስጥ ሰፊ ሽፋን በመስጠትም የአየር መንገዱን ታሪክ ከመነሻው ጊዜ ጀምሮ ያለውን ሒደት በማቅረብ ስለአየር መንገዱ አትቷል፡፡ ዘገባው ማስተላለፍ የፈለገው መልዕክት አየር መንገዱ ከዚህ ቀደም እንጂ አሁን የዓለም ደረጃን ያሟላ መሆኑ አብቅቶለታል የሚመስል ዓይነት ይዘትን ያለው ከመምሰሉም ባሻገር፣ ያጋጠመው አደጋም ተቀባይነቱን አሳጥቶታል የሚልም አስከታይ ነበረው፡፡
በርካታ አፍሪካውያን ትችታቸውን፣ ቁጭታቸውንና ንዴታቸውን ያወረዱበት ምክንያትም፣ ዘገባው ሆነ ተብሎ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከሥልጠና፣ ከበረራ ብቃትና መሰል ጉዳዮች ጋር የተያያዙ ችግሮች አሉበት በማለት ለማሳጣት የሚደረገውን ሙከራ እንገነዘባለን የሚሉ ድምፆች ተስተጋብተዋል፡፡ እንደውም ቦይንግ ኩባንያ ችግሮቹን በሌሎች ላይ ለማላከክ ያደረገው ሙከራ ብቻ ሳይሆን፣ አፍሪካውያን ስለሆንን ብቻ የተቃጣብን ጥቃት ነው በማለት ጭምር በርካቶች ከፍተኛ ትችት በዘገባው ላይ አሰምተዋል፡፡ በውርጅብኙ ሳቢያ ሲኤንኤንን ጨምሮ የአሜሪካ ሚዲያዎች የሙያ ሥነ ምግባር ጥያቄዎችን ብቻም ሳይሆን፣ ለራሳቸው መልካም ስምና ዝናን ለማስጠበቅ ያደሉ፣ ሚዛናዊነት የጎደላቸውን ዘገባዎች አሠራጭተዋል በማለት ዘለፋ ሳይቀር አውርደውባቸዋል፡፡
ሲንኤንኤን በተለይ በአንዳንዶች አፍሪካውያን ዘንድ ለዘለፋና ለስድብ ውርጅብኝ ያበቃው ያሠራጨው ዘገባ ብቻ አልነበረም፡፡ የተጠቀመበት የአውሮፕላን ምስልም ጭምርም ጥያቄ አስነስቶበት ነበር፡፡ እ.ኤ.አ. በ1980ዎቹ የአየር መንገዱ ንብረት የነበረውን ቦይንግ 767-200 ኢአር የተሰኘውን አውሮፕላን ለዘገባው ማሳያነት ማቅረቡ ሆነ ብሎ አየር መንገዱን ለማጠልሸት ያደረገው ነው በማለት የተሟገቱም ነበሩ፡፡
ዘገባውን ባወጣ በአፍታ ለማስተካከል የተገደደው ሲኤንኤን፣ ከጠበቀው በላይ ውርጅብኝ ማስናገዱን ተከትሎም ይመስላል፣ ‹‹የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአፍሪካ ኩራት ነው የደረሰው አደጋ ግን ጥያቄዎችን አስነስቶበታል›› በማለት የተሻሻለ ርዕስ የሰጠውን ዘገባ አስነብቧል፡፡ ይህንን ተከትሎም አንዳንድ የድረ ገጽ ሚዲዎች ‹‹የቲዊተር ተጠቃሚዎች ሲኤንኤንን ስለ ኢትዮጵያ አየር መንገድ ስምና በረራ ደኅንነት አስተማሩት›› እስከማለት ያደረሳቸውን ዘገባ ለማስነበብ አብቅቷቸዋል፡፡ ለአብነትም አፍሪካኒውስ የተሰኘው ድረ ገጽ ይህንኑ ርዕስ የያዘ ዘገባ በማስነበብ፣ የቀደመውንና የተሻሻለውን የሲኤንኤን ዘገባ፣ ከአንባብያን ተቃውሞ ጋር በማጣቀስ አቅርቧል፡፡
ከወዲያ ማዶ የሚዲያ አግድሞሽ ዘመቻዎችን ያስተናገደው የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ የምርመራው ውጤት ከመታወቁ በፊት እየቀረቡ ያሉትን ዘገባዎች በመቃወም አጸፋውን መስጠቱ ይታወሳል፡፡ ዋና ሥራ አስፈጻሚው ሰኞ መጋቢት 16 ቀን 2011 ዓ.ም. ለጋዜጦች በጻፉት አስተያየት፣ ተዛብቶና ከእውነታው አፈንግጦ ቀርቧል ስላሉት ዘገባና አየር መንገዱ ከቦንይግ ኩባንያ ጋር ስላለው ግንኙነትም በሰፊው አትተዋል፡፡ ‹‹እኛ በቦይንግ እምነት አለን፡፡ ለረዥም ዓመታትም አጋሮች ነን፡፡ ከሁለት ሦስተኛው በላይ በረራችን በቦንግ አውሮፕላኖች የሚካሄድ ነው፤›› ብለዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር በአፍሪካ የቦንግ 737 ማክስና 737 ኤንጂ አውሮፕላኖች ምስለ በበረራዎች የታገዘ ሙሉ ሥልጠና በመስጠት ጭምር አብራሪዎቹን በብቃት እንደሚያስተምር አስታውቀዋል፡፡ ከአደጋው በኋላም ቦንይግና አየር መንገዱ አብረው መሥራታቸውን እንደሚቀጥሉ በአስተያየታቸው አስፍረዋል፡፡
ይህም ሆኖ በሩንዋዳ ኪጋሊ በተካሄደው የንግድ ኩባንያዎች ዋና ሥራ አስፈጻሚዎች ፎረም ወቅት፣ የአፍሪካ የዓመቱ ሻምፒዮና በሚለው የሽልማት ዘርፍ አሸናፊ በመሆን አየር መንገዱ ሽልማት ተቀብሏል፡፡ ሽልማቱን የተቀበሉት አቶ ተወልደም፣ ኩባንያው በታሪኩ ፈታኝ የሆነ አደጋ ባስተናገደበት ወቅት፣ የአፍሪካውያንን ድጋፍ ማግኘቱ እንዳስደሰታቸው፣ ሆኖም አሁንም ድረስ የኩባንያው ሠራተኞችና አመራራቸው፣ ሕይወታቸው ባለፈው መንገደኞችና ሠራተኞች ሐዘን ውስጥ እንደሚገኙ ጠቅሰው፣ አፍሪካውያን ላሳዩት ድጋፍና አመኔታ ምሥጋናቸውን አቅርበዋል፡፡
► መረጃ ፎረም – JOIN US
