ሐራ ዘተዋሕዶ
March 31, 2019 t

- ፓትርያርኩም ኾኑ የበላይ ሓላፊው፣ለቋሚ ሲኖዶሱ ያቀረቡት ምክንያት ጥልቀት ይጎድለዋል፤
- “ያለፈቃድ የውጭ ጉዞ ማድረግ እና አለመታዘዝ” በማለት ብቻ ነው ለቋሚ ሲኖዶሱ ያስረዱት፤
- በውጭ ግንኙነት ሥራ የፈጸመውን ሻጥር በዝርዝር ማቅረብ እየቻሉ አላቀረቡም፤ በደፈና ነው፤
- “በአለመግባባት” በሚል ውሳኔ ብቻ ታልፎ፣በጠቅላይ ጽ/ቤቱ ሌላ ምደባ እንዲሰጠው ተወሰነ፤
- ከፈጸመው ደባ፣የመናፍቅነት ዝንባሌውና ምግባረ ቢስነቱ አኳያ ከዳግም ምደባ በፊት ይታረም!
***
- የውጭ ጉዳይ መምሪያው፣ የኢኦተቤ – ቴቪ ሥራ አስኪያጅ ተዛውረው እንዲተኩለት ጠይቋል፤
- በዋና ሓላፊነት ደረጃ የሚኖር ብቸኛ ክፍት ቦታ ስለሚያደርገው ሚዲያውን ለአደጋ ያጋልጣል፤
- ‘አባ’ ቃለ ጽድቅን በሚዲያ ሥራ አስኪያጅነት መመደብ፣ በጅብ ትክሻ ሥጋ እንደመጫን ነው፤
- የውጭ ጉዳይ መምሪያው፣ ቅዱስ ሲኖዶስ እንደወሰነው፣የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ይቀረፅለት፤
- በዴስኮች ይደራጅ፤ ዓለም አቀፍ ግንዛቤ ባላቸው ሞያተኞችና የሥራ መሣሪያዎች ይጠናከር!
***
ቋሚ ሲኖዶስ፣ ከትላንት በስቲያ ዓርብ፣ መጋቢት 20 ቀን 2011 ዓ.ም. በአካሔደው ሳምንታዊ መደበኛ ስብሰባው፣ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት የውጭ ጉዳይ መምሪያ ዋና ሓላፊ ‘መልአከ ሰላም ቆሞስ አባ’ ቃለ ጽድቅ ሙሉጌታ፣ ከቦታው እንዲነሣ ወስኗል፤ በጠቅላይ ጽ/ቤቱ ቦታ ተፈልጎለትና ደረጃው ተጠብቆ እንዲመደብም ትእዛዝ ሰጥቷል፡፡
ቋሚ ሲኖዶሱ ውሳኔውን የሰጠው፣ የውጭ ጉዳይ መምሪያው የበላይ ሓላፊ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ አረጋዊ፣ ዋና ሓላፊው ‘አባ’ ቃለ ጽድቅ ተነሥቶ በሌላ ሓላፊ እንዲተካ፣ ከኹለት ወራት በፊት ለብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ በጽሑፍ በማመልከታቸውና ይህም ቅዱስነታቸው በአቀረቡት አቤቱታ በመጠናከሩ ነው፡፡

ሲኖዶሳዊ አንድነቱ መመለሱን ተከትሎ የውጭ ግንኙነት መምሪያው፣ በማዕከል ለሚመራው የቤተ ክርስቲያን ዓለም አቀፋዊ ተልእኮ በርካታ ተግባራትን ማከናወን እንደሚጠበቅበት፣ የበላይ ሓላፊው ጳጳስ፣ ባለፈው ጥር 1 ቀን ለቅዱስነታቸው በጻፉት ማመልከቻ ጠቅሰዋል፤ ሥራውን በአግባቡ ለማከናወን ይረዳ ዘንድም፣ ‘አባ’ ቃለ ጽድቅ ሙሉጌታ ከቦታው ተነሥቶ በምትኩ መ/ር ዳንኤል ሰይፈ ሚካኤል እንዲመደቡላቸው ጠይቀዋል፡፡
የውጭ ጉዳይ መምሪያው ተጠሪነት፣ አንድ ጊዜ ወደ ፓትርያርኩ ልዩ ጽ/ቤት ሌላ ጊዜ ወደ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት እየኾነ ቢዋዥቅም፣ በዚህ ወቅት ጉዳዩ ከቅዱስነታቸው ወደ ዋና ሥራ አስኪያጁ ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ ተመርቶ ስለነበር፣ የጠቅላይ ጽ/ቤቱ [የሠራተኛ]አስተዳደር መግለጫ እንዲያቀርብበት ተሰጥቶታል፡፡ የ‘አባ’ ቃለ ጽድቅ ሙሉጌታን ማኅደር የመረመረው የአስተዳደር መምሪያው በበኩሉ፣ ግለሰቡ በውጭ ጉዳይ መምሪያ ሓላፊነት የተመደበው በቋሚ ሲኖዶሱ እንደነበረ አስታውሶ፣ የቀረበው የይነሣልኝ ጥያቄም በዚያው በቋሚ ሲኖዶሱ በኩል ቢታይ የተሻለ እንደሚኾን ለብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ መግለጫ አቅርቧል፤ ብፁዕነታቸውም፣ መግለጫውን በመሸኛ ለቅዱስነታቸው አቅርበው አመራር እንዲሰጡበት በመጠየቃቸው፣ ቋሚ ሲኖዶሱ፣ ባለፈው ረቡዕ እና ዓርብ ባካሔዳቸው ስብሰባዎቹ ተነጋግሮበታል፡፡

ይነሣልኝ ከሚለው የውጭ ጉዳይ መምሪያው ጥያቄ በቀር ስለ ግለሰቡ በዝርዝር የቀረበ ምክንያት አለመኖሩን የገመገመው ቋሚ ሲኖዶሱ፣ የበላይ ሓላፊውን ጳጳስ ብፁዕ አቡነ አረጋዊን ጠርቶ ማብራሪያ ጠይቋል፡፡ የመምሪያው የበላይ ሓላፊ እንደመኾናቸው በሥራቸው ያሉትን ማስተባበር፣ መምራትና መቆጣጠር እንደሚጠበቅባቸው ለቋሚ ሲኖዶሱ የገለጹት ብፁዕነታቸው፣ ‘አባ’ ቃለ ጽድቅ ሙሉጌታ እንደማይታዘዛቸው አስረድተዋል፤ ርእሰ መንበሩም፣ ሳያስፈቅዳቸው ወደ ውጭ መጓዝ እንደሚያዘወትር በመጥቀስ የብፁዕነታቸውን ማብራሪያ አጠናክረዋል፡፡ ‘አባ’ ቃለ ጽድቅ በበኩሉ፣ ኹለቱንም ተቃውሞ በመከራከሩ ለውሳኔ አስቸጋሪ እንዳደረገው ተገልጿል፡፡ በመጨረሻም ጉዳዩ፣ “እርስ በርስ አለመግባባት” የሚል ምክንያት ተሰጥቶት ከዋና ሓላፊነቱ እንዲነሣ ተወስኗል፤ ወደ ጠቅላይ ጽ/ቤቱ ተዛውሮና ደረጃው ተጠብቆ እንዲመደብም ትእዛዝ ተሰጥቷል፡፡

ከሦስት ዓመት በፊት፣ በፓትርያርኩ በኩል ከአሜሪካ የተጠራው ‘አባ’ ቃለ ጽድቅ ሙሉጌታ፣ በቋሚ ሲኖዶስ ውሳኔ የውጭ ጉዳይ መምሪያ ዋና ሓላፊ ኾኖ የተመደበው፣ ታኅሣሥ 22 ቀን 2007 ዓ.ም. ነበር፡፡ ከዘመኑ ትምህርት በአይ.ሲ.ቲ የበርክሌይ ዩኒቨርስቲ ምሩቅ፣ ከአብነቱም የቅኔና ቅዳሴ ዐዋቂ እንደ ኾነ ተነግሯል፤ “የውጭ ቋንቋ ተናጋሪ ነው፤ ይረዳዎታል” በሚል አግባቢነት ለፓትርያርኩ ተልኮላቸው በቀጥታ በውጭ ጉዳይ መምሪያ ዋና ሓላፊነት እንዲመደብ አድርገዋል፡፡ ኾኖም፣ ሓላፊነቱን ተገን በማድረግ በቤተ ክርስቲያናችን የውጭ ግንኙነት ሥራ ላይ ሲፈጽም ከቆየው ደባ፣ ከዚያም በፊት ባለበትና በኋላም በቀጠለበት የመናፍቅነት ዝንባሌና የሥነ ምግባር ችግር አንጻር፣ በቀኖና እና በሕግ ሊጠየቅና ሊታረም እንጂ ዳግም የምደባ ዕድል ሊሰጠው የሚገባ ሰው አልነበረም፡፡
“አሜሪካም አውሮጳም ሔዶ ያተራመሳቸው ነገሮች አሉ፤ ገንዘብም ተቀብሏል፤” ያሉት አንድ የቋሚ ሲኖዶሱ አባል፦ በጅቡቲ ምሥራቀ ፀሐይ ቅዱስ ገብርኤል፣ በጆሐንስበርግ ጽርሐ ጽዮን መድኀኔዓለም ካቴድራል፣ በአቴንስ ኪዳነ ምሕረት እና በኦስትርያ ተክለ ሃይማኖት አቤቱታዎች ማጣራትና የውሳኔዎች አተገባበር፣ አስተዳደሩን ከምእመናን፣ ምእመናንን ከምእመናን በሚለያይ አድሏዊነት ጠብንና ዓምባጓሮን በማበረታታት የፈጸማቸውን በደሎች በአስረጅነት ጠቅሰዋል፡፡
ይነሣልን ተብሎ ሲጠየቅ፣ ቀደም ተብሎ የተረጋገጠውን የሃይማኖትም የምግባርም ሕጸጾቹን፣ በተለያዩ ጊዜያት ከየክፍላተ ዓለሙ በምእመናን ከቀረቡበት አቤቱታዎች ጋራ በዝርዝርና በጥልቀት ፈትሾ የተጠያቂነት ሥርዓትን የሚያረጋግጥና ለቤተ ክርስቲያን የሚጠቅም ኹነኛ ውሳኔ ማሳለፍ እየተቻለ አልተደረገም፡፡ ይህም፣ የበላይ ሓላፊው ጳጳስም ይኹን የፓትርያርኩ ጥያቄ መነሻ፣ ግላዊ አለመግባባት መስሎ ብቻ እንዲታይ አድርጎታል፡፡ ይብሱኑ፣ ‘አባ’ ቃለ ጽድቅ፣ ተዛውሮና ደረጃው ተጠብቆ ይመደብ የሚል ውሳኔ እንዲተላለፍ ምክንያት እንደኾነ ግንዛቤ ተወስዷል፡፡
ለየሥራ ዘርፉ ተገቢውን ሰው ከመፈለግ ይልቅ ለሰው ሥራ በሚፈለግበት፤ የበደለኛ ሰው ትልቁ ቅጣት የሕግ ተጠያቂነት ሳይኾን ዝውውር ተደርጎ በሚታይበት ቤተ ክህነታችን፥ ሻጥረኛው፣ ጥቅመኛው፣ መናፍቁና ምግባረ ቢሱ ‘አባ’ ቃለ ጽድቅ ሙሉጌታ፣ ተዛውሮና ደረጃው ተጠብቆ እንዲመደብ መወሰኑ፣ አሳዛኝ ባይኾን ኖሮ አስገራሚ አይደለም፡፡ የውሳኔው አፈጻጸም፣ ለጠቅላይ ጽ/ቤቱ የሚቸግር እንደ ኾነ ከወዲሁ ታይቷል፤ ለቤተ ክርስቲያናችን በአጠቃላይም ስጋት እንደኾነ ተጠቁሟል፡፡
የመጀመሪያው፣ የውጭ ጉዳይ መምሪያው፣ በ‘አባ’ ቃለ ጽድቅ ሙሉጌታ ቦታ እንዲተካለት የጠየቀው፣ ኢኦተቤ – ቴቪን በበላይነት የሚመራው የብዙኃን መገናኛ አገልግሎት ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅን መ/ር ዳንኤል ሰይፈ ሚካኤልን መኾኑ ነው፡፡ በትምህርት ይኹን በቋንቋ ችሎታ ከፍተኛ ዝግጅት ያላቸው መ/ር ዳንኤል ሰይፈ ሚካኤል፣ ለውጭ ግንኙነት ሥራው፣ የተሻለና አግባብነት ያለው ልምድ እንዳላቸው ይታወቃል፡፡ ኾኖም፣ ወደ ውጭ ጉዳይ መምሪያው ሲዛወሩ፣ ጠቅላይ ጽ/ቤቱ፣ በዋና ሓላፊነት ደረጃ የሚኖረው ብቸኛ ክፍት ቦታ፣ የብዙኀን መገናኛ አገልግሎት ድርጅቱ ሥራ አስኪያጅነት ይኾናል፤ የመምሪያ ዋና ሓላፊነት ደረጃው ተጠብቆ ይዛወር ለተባለው ‘አባ’ ቃለ ጽድቅ ሙሉጌታ የሚኾን ክፍት መምሪያ ይኹን ድርጅት የለም፤ ተብሏል፡፡ በብዙኀን መገናኛ አገልግሎት ድርጅቱ ሥራ አስኪያጅነት መመደብ ማለት ደግሞ፣ በስርቆቷ አፏን ሲመቷት አሁን ከብሆው ለመግባት ተመቸኝ እንዳለችው ውሻ መኾኑ ነው፤ ሥጋን በጅብ ትክሻ እንደ መጫን ነው፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተሻለ አደረጃጀትና በከፍተኛ ሞያዊ መነሣሣት ላይ ለሚገኙት የቴሌቪዥን ጣቢያው ባለሞያዎችም ታላቅ ስድብ ነው፤ ጠቅላላ ተቋማዊ አደጋው ግልጽ ነው፡፡
በመኾኑም፣ የውጭ ጉዳይ መምሪያው የበላይ ሓላፊ ጳጳስ በጠየቁት መሠረት፣ መ/ር ዳንኤል ሰይፈ ሚካኤል ከኢኦተቤ-ቴቪ ዋና ሥራ አስኪያጅነት የሚዛወሩ ከኾነ፣ በኦርቶዶክሳዊ አስተምህሮ ብስለቱና በተግባቦት ክህሎቱ የላቀ፣ ከግለሰቦች ይልቅ የቤተ ክርስቲያንን መብትና ጥቅም ቅድሚያ ሰጥቶ ከማስከበር አኳያ የሚዲያውን አንጻራዊ ነጻነት አስከብሮ በመምራት ብቃቱ የሚታመንበት፣ አሁን የሚታየውን የጣቢያውን ባለሞያዎች ተነሣሽነት የሚመጥንና ሠርቶ የሚያሠራ ዋና ሓላፊ በጥንቃቄ ተለይቶ ሊተካለት ይገባል፡፡
የውጭ ጉዳይ መምሪያውም ቢኾን፣ የውጭ ግንኙነት ሥራውን የሚመራበት ግልጽ ፖሊሲ ተቀርፆለት፣ ስትራተጅና ዕቅድ ወጥቶለት የቤተ ክርስቲያንን ሐዋርያዊ ተልእኮ በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚያሳካ፣ ክብሯንና ጥቅሟን በሚስጠብቅ መልኩ ተግባሩን መፈጸም ይጠበቅበታል፤ አድማሳዊ ግንዛቤ ባላቸው ብቁ ባለሞያዎችና የሥራ መሣሪያዎች መደራጀት፣ በበጀትም መጠናከር ይኖርበታል፡፡
መምሪያው፣ በክፍላተ ዓለም ዴስኮች እንዲደራጅና በተለያዩ ቋንቋዎች መደበኛ ኅትመቶች እንዲኖሩት፣ ቅዱስ ሲኖዶስ ከጥቅምት 2005 ዓ.ም. ጀምሮ ልዩ ልዩ ውሳኔዎችን ቢያስተላልፍም፣ ለተግባራዊነቱ የተደረገ የጎላ እንቅስቃሴ አልታየም፡፡ ከሪፖርቶች እንደሚታየው፣ የውጭ ግንኙነት ተብለው የሚቀርቡት ዓመታዊ ዘገባዎች፣ በፓትርያርኩ ኦፌሴልያዊ ጉብኝቶችና ለአገልግሎት በሚመደቡ ልኡካን አላላክ ላይ የሚያተኩሩና በዚሁ ጉዳይ ዙሪያ የታጠሩ ናቸው፡፡ ተልእኮው ግን ከዚህም የገዘፈና የሰፋ በመኾኑ፣ ተጠሪነቱ በግልጽ ተወስኖለትና የሥራ ዝርዝሩም ተቀምጦለት፣ ከፓትርያርኩ ልዩ ጽ/ቤት ጥገኝነት መላቀቅ ያስፈልገዋል፡፡
በዓለም አቀፍ ግንኙነት እጅግ ጥንታዊ ታሪክ ያላት ሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያናችን፣ ለተጽዕኖ ፈጣሪነቷም ዋናው ምክንያት፣ የውጭ ግንኙነት ሥራዎችዋ ውጤት እንደኾኑ ሊዘነጋ አይገባም፡፡ ከመቼውም ጊዜ በላይ፣ በውጭ አገሮች፣ አብያተ ክርስቲያን እየጨመሩና እየተጠናከሩ የመጡበት ጊዜ ነው፡፡ የመምሪያው የበላይ ሓላፊም በማመልከቻቸው እንዳሰፈሩት፣ ከሲኖዶሳዊው አንድነት መመለስ ጋራ ተያይዞ፣ ዓለም አቀፋዊውን ተልእኮ በማቀናጀት በአንድ ማዕከል የመምራት ሓላፊነት ስላለበት፣ “ብዙ ሥራዎች ከመምሪያው ይጠበቃሉና”፣ የሰው ኀይል ምደባው በእጅጉ ይታሰብበት፡፡
አባ’ ቃለ ጽድቅ ሙሉጌታ ግን፡-
- ገና ከመንፈሳዊ ኮሌጅ ተማሪነቱ አንሥቶ፣ ኦርቶዶክሳዊነትን በማንኳሰስና ፕሮቴስታንታዊነትን በማነጋገሥ የሸቃጭነት ዝንባሌው የሚታወቅና ከሌሎች ግብረ አበሮቹ ጋራ በርቱዓን ደቀ መዛሙርት ተጋልጦ አቋም የተወሰደበት በመኾኑ፤
- በአሜሪካ ኦሃዮ እና በካሊፎርንያ ኦክላንድ ደብረ ኢየሱስ፣ በተደጋጋሚ የዝሙት ቅሌት ለተቀደሰው ጋብቻ መፍረስና ለቤተሰብ መበተን መንሥኤ መኾኑ፤ ያለሰነድ የርዳታ ገንዘብ በመሰብሰብ ለግሉ መጠቀሙንና አምነው ያስጠጉትን ምእመናን እምነት ማጉደሉ በጥቅሉ፥ የኖላዊነት አደራን በመብላትና ማዕርገ ምንኵስናን በማዋረድ ከቤተ ክርስቲያን መባረሩ በሰነድ፣ በቪዲዮና በፎቶ ማስረጃዎች የተደገፈ የምእመናኑ ተቃውሞ የቀረበበት መኾኑ፤
- ሲኖዶሳዊ አንድነቱ በአባቶች ስምምነት ከመመለሱ በፊት፣ በሓላፊነቱ አጋጣሚ ያገኘውን መረጃ በዕርቀ ሰላሙ ሾልከው ለገቡት ቀሣጥያን እያቀበለ፣ አስተዳደራዊ አንድነትን የሚሸረሽርና ግጭትንና መከፋፈልን የሚያባብስ እኩይነት በመፈጸም ሓላፊነቱን በአግባቡ ባለመወጣቱ፤
- በውጭ አህጉረ ስብከት የሚገኙ ካህናትንና ምእመናንን ጥያቄዎች ከትክክለኛ ይዘታቸው ውጭ በማቅረብ፣ ቅዱስ ፓትርያርኩንና ቋሚ ሲኖዶሱን ከመዋሸቱም በላይ በተደጋጋሚ የተጻፉ ደብዳቤዎች ቀርበው እንዳይታዩ በማፈኑ፤
- በአቤቱታዎቹ ላይ ቋሚ ሲኖዶስ የሚያሳልፋቸውን ውሳኔዎች አፈጻጸም በማዘግየትና በመቀሠጥ መንበረ ፓትርያርኩን አስነቅፏል፤ በምትኩ ጥቅም እየተቀበለ ለግለሰቦችን ፍላጎት በማድላት በውጭ አህጉረ ስብከት የእናት ቤተ ክርስቲያን አስተዳደራዊ አንድነት እንዳይጠናከር ደባ በመፈጸሙ፤
- ቅዱስ ሲኖዶስ፣ በ2009 ዓ.ም. የርክበ ካህናት ምልዓተ ጉባኤው፣ ቤተ ክርስቲያናችን ዓለም አቀፋዊት እንደ መኾኗ፣ ከሀገር ውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ምእመናን፣ አስፈላጊውን መንፈሳዊ አገልግሎት ማግኘት እንዲችሉ፣ አብያተ ክርስቲያናት እንዲታነጹላቸው፣ ብፁዓን አባቶችና አገልጋይ ካህናት እንዲመደቡላቸው መደረጉን ካወሳ በኋላ፣ “ያለው ማዕከላዊ አሠራር ግን አመርቂ ኾኖ አልተገኘም፤” በማለት ነው፣ የ‘አባ’ ቃለ ጽድቅን የውጭ ግንኙነት ሥራዎች አፈጻጸም በድክመት የገመገመ በመኾኑ፤
- ምልዓተ ጉባኤው በዚያው ግምገማው፣ የውጭ ግንኙነቱን በማቃወስ በርካታ አሻጥር እየፈጸመ መኾኑን በመረዳት ከዋና ሓላፊነቱ እንዲወገድ ወስኖ እንደነበር በማስታወስ፣ ዘግይቶም ቢኾን ከሓላፊነቱ የመነሣቱ ተገቢነት አያጠያይቅም፡፡
ኾኖም፣ በዳግም ምደባው ሌሎች መምሪያዎችንና ድርጅቶችን ለበለጠ አደጋ ከማጋለጥ ይልቅ፣ በዝርዝር በተገለጹት ሕጸጾቹና ጥፋቶቹ እርምት መውሰዱ ቅድሚያ ቢሰጠው፣ ርምጃውን የተሟላና አብነታዊ ያደርገዋል፡፡
ኾኖም፣ በዳግም ምደባው ሌሎች መምሪያዎችንና ድርጅቶችን ለበለጠ አደጋ ከማጋለጥ ይልቅ፣ በዝርዝር በተገለጹት ሕጸጾቹና ጥፋቶቹ እርምት መውሰዱ ቅድሚያ ቢሰጠው፣ ርምጃውን የተሟላና አብነታዊ ያደርገዋል፡፡
