April 1, 2019

የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ከአርበኞች ግንቦት ሰባት ንቅናቄ ጋር ውህደት ፈጽሟል መባሉን አስተባበለ።መኢአድ ዛሬ በጽህፈት ቤቱ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳስታወቀው፤ ፓርቲው አገራዊ ለውጡን ተከትሎ እንደገና አደረጃጀቱን እያጠናከረ፣ አባላቱን እያሰባሰበና ቢሮ እየከፈተ ይገኛል።

ይህ እየሆነ ባለበት ወቅት በመገናኛ ብዙሃን ‘መኢአድ ውህደት ፈጸመ’ መባሉ የማያውቀው ከመሆኑ ውጪ በድርጅቱ ላይ የተከፈተ ”አባላቶቻችንና ደጋፊዎቻችንን የመከፋፈልና የተነሳንለትን አገርንና ህዝብን ወደተሻለ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት የማሸጋገር ዓላማ የሚያደናቅፍ ነው” ብሏል።

ውህደት ፈጸመ መባሉ ህገ-ወጥና ጸረ-ዴሞክራሲያዊ አካሄድ እንደሆነ በመግለጽ ድርጊቱን ኮንኗል።

”ከግንቦት ሰባት ከፍተኛ አመራሮች ጋር ተገናኝተን ፈርሰን እነሱን እንደማናቋቁምና እነሱ ህጋዊ ፓርቲ ከሆኑ በኋላ በግንባር አብረን የምንሰራ መሆኑን አቋማችንን በግልጽ ካሳወቅናቸው በኋላ በተሳሳተ መንገድ በመላው አገሪቱ አብረን ነው የምንሰራው በማለት አባሎቻችንን የማታለል ስራ ሆን ብለው ቀጥለውበታል።” ሲል በመግለጫው አትቷል።

ግንቦት ሰባት በቅርቡ በፖለቲካ ፓርቲዎች የተፈረመውን የአሰራር ስርዓት ቃል ኪዳን ሰነድ ወደኋላ በመተው በአባሎችና ደጋፊዎች ላይ የመከፋፈል ድርጊት እየፈጸመበት እንደሆነም መኢአድ ጠቁሟል።

ይህንን ድርጊት ለማስቆም በተደጋጋሚ ሙከራ ያደረገው መኢአድ ድርጊቱ ሊታረም ባለመቻሉ ይፋ ለማድረግ መገደዱን አስታውቋል።

የዜናው ምንጭ ኢዜአ ነው።
► መረጃ ፎረም – JOIN US