April 1, 2019

ዶክተር አምባቸው መኮንን ወደ ርዕሰ መስተዳድርነት ከመጡ በኋላ በክልሉ የተለያዩ ቦታዎች በመዘዋወር ከህዝብ ጋር እየተወያዩ ነው፡፡ በዛሬው የወልድያ ከተማ ውይይት የመክፈቻ ንግግራቸው ‹‹የዚህ ውይይት ዓላማ የምታነሷቸውን ጥያቄዎች መፍታት እና ቃል መግባት ሳይሆን ሃሳባችሁን ተቀብለን ለቀጣይ ስራችን በግብዓትነት መጠቀም ነው›› ብለዋል ርዕሰ መስተዳድሩ፡፡

ከሰሜን ወሎ ዞን የተለያዩ አካባቢዎች በውይይቱ የተሳተፉ የህዝብ ተወካዮች ሃገራዊ፣ ክልላዊ እና አካባቢያዊ ጥያቄዎችንና ለአመራሮቹ ይጠቅማሉ ያሏቸውን አስተያየቶች ሰንዝረዋል፡፡

በመሰረተ ልማት ግንባታ የወልድያ ከተማ የውሃ፣ የመብራት እና የመንገድ ችግር፣ ለወጣቶች የስራ ዕድል አለመፍጠር፣ የመሰረተ ልማት ስራዎች በታቀደላቸው ጊዜ አለመጠናቀቅ፣ በአንዳንድ ወረዳዎች ሆስፒታል አለመኖር፣ ከወልድያ ጋሸና እና ከወልድያ አዲስ አበባ ያለው የአስፓልት መንገድ የጥራት ችግር፣ ከቆቦ ላሊበላ ይገነባል የተባለው የአስፓልት መንገድ አለመጀመር እንዲስተካከሉ ጠይቀዋል።

የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ የአውሮፕላን ማረፊያ እና የባቡር መስመር እንዲሰራ የገቡት ቃል አለመፈፀም፣ በከተማዋ ውስጥ የሚታየው ፍትሃዊ ያልሆነ የግብር ስርዓት፣ በዞኑ ምንም አይነት ፋብሪካ አለመኖር እና ተያያዥ የመልማት እና የማህበራዊ አገልግሎት ጥያቄዎችን ነዋሪዎቹ አንተስተዋል፡፡

ከመልካም አስተዳደር፣ ከሰላም እና ከደኅንነት አንፃር ደግሞ የቦታ ውዝግቦች አለመቋጨት፣ በክልሉ ውስጥ የተፈናቃዮች ቁጥር መጨመር፣ የሰላምና ደኅንነት ውጥረቶች መባባስ፣ የቆቦ ከተማ ሰላም አሳሳቢ መሆን፣ የአመራር ብቃት ችግሮች፣ የህግ የበላይነት አለመስፈን እና በከተማ ዳር ያሉ አርሶ አደሮች ህይዎት ስጋት ውስጥ መውደቅ በጥያቄነት ቀርበዋል፡፡

በፌደራል መንግስት የአዴፓ ውክልና፣ የአዲስ አበባ ጉዳይ፣ ሁሉም ብሄሮች እራሳቸውን ከማጠናከር በዘለለ ሃገራዊ አንድነት ለመገንባት ያላቸው ቁርጠኝነት እና አዴፓ ከሌሎች ድርጅቶች ጋር ያለው መስተጋብር ግልፅ ይደረግልን የሚሉ ሀሳቦች በተወያዮቹ የቀረቡ ጥያቄዎች ናቸው፡፡

ከዞን አስተዳደሩ እና ከክልሉ ከፍተኛ አመራሮችም ምላሽ ተሰጥቷል፡፡ የሰሜን ወሎ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ወልደ ትንሳኤ መኮንን አሁን በስራ ላይ ከሚገኘው አመራር ውስጥ 76 በመቶ የሚሆነው ከለውጥ በኋላ የተመደበ አዲስ አመራር መሆኑን ጠቁመው አመራር ማውጣት እና ማውረድ ዞኑን መለማመጃ ከማድረግ የዘለለ ፋይዳ አይኖረውም ብለዋል፡፡ ህዝቡም ከአመራሮች ጋር ተቀራርቦ በመስራት አቅማቸው እንዲያድግ ማገዝ እንደሚገባው ጠይቀዋል፡፡

ከመሰረተ ልማት ጋር ተያያዥነት ያላቸውን ጥያቄዎችም በዞኑ አቅም የሚሰሩትን ከህዝቡ ጋር ሆነን እንፈፅማለን ብለዋል፡፡

ርዕሰ መስተዳድር ዶር. አምባቸው መኮንን ደግሞ በክልሉ የሚገነቡትን የእቅዳችን አካል አድርገን እንሰራለን፤ በቀድሞ አመራሮች ቃል የተገቡ ጥያቄዎችንም የሚመለከተውን አካል እንጠይቃለን ብለዋል፡፡

የከተማ ዙሪያ አርሶ አደሮችን በሚመለከት የተነሳው ጥያቄ ትክክል ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ ህይዎታቸውን በዘላቂነት የሚቀይር የካሳ ስርዓት ተግባራዊ ለማድረግ እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡

አዴፓ እንደ ክልል ብቻ ሳይሆን ሃገራዊ ጉዳዮችንም በንቃት እየተከታተለ እንደሆነ የተናገሩት ደግሞ የአዴፓ ማዕከላዊ ኮሚቴ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዮሃንስ ቧያለው ናቸው። አዴፓ ከሁሉም ድርጅቶች ጋር ያለው ግንኙነት መልካም መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

ተወያዮቹ በበኩላቸው ‹‹ጎንደር ሲነካ ወልድያን ያመዋል፤ ራያ ሲነካ ጎጃምን ያመዋልና ስለሰላም ቅድሚያ ሰጥታችሁ ብትሰሩ›› መልካም ነው ብለዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው – ከወልድያ