ሁሌ እናስታውሳቸው
ተቀብሮ እንዳይቀር
አኩሪ ታሪካቸው!!!!!

ሙሉ አምባው ማን ነው??

Image may contain: 1 person, hat

በባለቤቱና በልጆቹ እናት በ ወ/ሮ አመልማል ደምሰው አንዳርጌ በወያኔ ደብዛው ስለጠፋው ባለቤቷ እንደተነገረው፤……..

“ሙሉ አምባው ከእናቱ ከወ/ሮ ማሚቴ ጌታሁንና ከአባቱ ከአቶ አምባው ፈረደ በ ጥር 7/ 1947 በጎጃም (ጠቅላይ ግዛት በንጉሱ አጠራር)በደጀን ከተማ ተወለደ፡፡ እስከ አስራ አንደኛ ክፍል እዛው ደጀን ከተማ ከተማረ በኋላ የማህበራዊ ኑሮ እድገት ኮርስ በመውሰድና ጥሩ ውጤት አምጥቶ በማለፍ ጉዞውን ወደ አዋሳ አደረገ፡፡ ሁለት አመት ይፈጅ የነበረውን ኮርስ እያገባደደ በነበረበት ወቅት ነው የ 1966 አብዮት የፈነዳው። ደርግ “የእድገት በሕብረት የእውቀትና የሥራ ዘመቻን”ብሎ ሲያውጅ ሙሉ አምባው እዛው አዋሳ ውስጥ ገና ትምህርት ላይ ስለነበረ፤ በአዋሳ አካባቢ እንዲዘምት ተደረገ። ሙሉ የደርግን አምባገነን መንግሥት መታገል የጀመረው ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ነበር፡፡

ዘመቻ ጣቢያ እያለ ለእስር ተዳርጎ ተፈቷል፡፡ ከተፈታ በኋላም ዘመቻውን አቋርጠው ደርግን ለመታገል ወደ የቤታቸው ከተመለሱት ተማሪዎች ግንባር ቀደም ነበር፡፡ የደርግ መንግሥትም ሲጨንቀው ዘመቻውን አቋርጠው ወደ ቢታቸው የተመለሱትን ተማሪዎች እንደገና ጥሪ አድርጎ ትምህርታቸውን እንዲቀጥሉ አደረገ፡፡ ሙሉ ወደ አዋሳ ተመልሶ በሕዝባዊ ኖሮ እድገት በዲፕሎማ ተመርቆ ወደ ሥራው አለም ከገባ በኋላ በወቅቱ ኤፒድ ተብሎ ይጠራ በነበረው የግብርና ድርጅት ውስጥ ተመደበ፡፡

የመጀመርያ የሥራ ቦታው በጎንደር ክፍለ ሀገር በደብረታቦር አውራጃ አንበሳሜ የምትባል ትንሽ የገጠር ከተማ ነበረች፡፡ ሙሉ አምባው ምንም እንኳን የመንግሥት ሰራተኝነቱን እንደ ሽፋን ቢጠቀምበትም፤ ዋና ተልእኮው ለሥራ በሚንቀሳቀስባቸው ደራ ወረዳና ፎገራ ወረዳ ውስጥ የኢሕአፓን መዋቅር መዘርጋት ነበር፡፡ በከተሞችና በገበሬ ማሕበራት ውስጥ በጣም ጠንካራ የሆኑ ጓዶችን የመለመለ ጠንካራ ጓድ ነበር፡፡

በኋላም ከመደበኛ ሥራው ይልቅ ለድርጅታዊ ሥራው ቅድሚያ እየሰጠ በመምጣቱ የደርግ ሰላዮች ዐይን ውስጥ ሊገባ ችሏል፡፡ ደርግ ሊይዘው መሆኑ ሲታወቅም ለሥራ በሄደበት በፎገራ ወረዳ ጉማራ ገበሬ ማህበር ውስጥ፤ የታወቀው የት ኑራ የአምራቾች የገበሬዎች ማህበር ሕቡዕ ገብቶ ነበር፡፡ ልክ እሱ ሕቡዕ መግባቱ እንደታወቀና ፋሺስቱ የደርግ መንግሥት የየትኑራ ገበሬዎችን አፍሶ እስርቤት ሲያስገባ ፤ ለህዝብ ተቆርቋሪ የነበረው ሙሉ አንባው የገበሬዎችን መታሰር እንደ ሰማ ሳይውል ሳያድር እጁን ለመንግሥት ሰጠ፡፡

ጎንደር ክ/ሃገር የተያዘው የተያዘው ሙሉ አምባው ጎጃም ክፍለ ሀገር ባህርዳር ወህኒ ቤት ተወሰዶ ወደ አራት ዓመት ታስሮ ተፈታ፡፡ ማክሰኞ ተይዞ ለእስር ሲዳረግ የመጀመርያ ልጃችን ክርስትና እንደሃሙስ ስለነበር አባቱ ሲፈታ የ 4 አመት ልጅ ሆኖ ነበር የጠበቀው። ከዚያም በፊት እኔም ነፍሰ ጡር ሆኜ ከነእህቴ ጎንደር ውስጥ ለእስር ተዳርጌ ነበር።

ደርግ የኢሕአፓን መዋቅር ለማዳከም የሚጠቀምበት የነበረው ስልት እስረኞች ሲፈቱ ከነበሩበት አካባቢ አንስቶ ሌላ ቦታ በመመደብ ስለነበረ እኔንም ከእስር ስፈታ ከነበርኩበት አንበሳሜ አንስቶ አዲስ ዘመን መደበኝ። የባለቤቴ ሙሉ አምባውም የሥራ ቦታ አዲስ ዘመን ሆነ፡፡ ያንግዜም የደርግ መንግሥት ክትትሉን በሁለታችንም ላይ አላቆመም ነበር፤ በዚህም ምክንያት ሁለታችንም እንደገና ለሁለተኛ ጊዜ ለእስር ተዳረግን፡፡ እኔ አዲስ ዘመን ፖሊስ ጣቢያ አስራ አምስት ቀን ታስሬ ተፈታሁ፡፡ ባለቤቴ ግን ጎንደር ባታ ወህኒ ቤት ለስድስት ወር ታስሮ ተፈታ፡፡
በዚህ ሁኔታ ጎንደር ክፍለ ሀገር መኖር አስጊ ሲሆንበት እኛን ትቶ ለከፍተኛ ትምህርት አዲስ አበባ ገባ፡፡ ከአሰፋ ማሩ ጋር የመተዋወቅ እድል የገጠመውም እዚሁ አዲስ አበባ ስድስት ኪሎ ዩኒቭርሲቲ ነበር፡፡ ባለቤቴ ሙሉ አምባው፤ ያደገች፣የበለጸገች፣ ዲሞክራሲ የሰፈነባት ኢትዮጵያን ለማየት በአገር ፍቅር ልክፍት የተያዘው ገና በጠዋቱ ነበር፡፡ ከኃይለስላሴ ዘመነ መንግሥት የጀመረ እስከ ህወሃት መራሹ ዘመን ቀጥሎ ደብዛውን አጥፍቷል፡፡

የደርግ ፋሺስት መንግሥት አገሪቱን ሊለውጡ የሚችሉ ባለ ብሩህ አእምሮ የያ ትውልድ ቅን አሳቢ አንድ ትውልድ ከመጨረሱም በላይ እጅግ የሚያሳዝነው ኢሕአፓን የመሰለ ብዙ የሕዝብ ድጋፍ የነበረውን ድርጅት ተከታትሎ አዳክሞ ህወሃትን ለመሰለ አገር ሻጭ ቡድን አገሪቱን አስረክቦ መንኮታኮቱ ነው፡፡

ሙሉ የህወሃት አገር አፍራሽነትን፣ ዘረኝነትንና ኢ-ሰብአዊነት ከጅምሩ ሊታገል የኢሰመጉ አባል ሆኖ ነበር፡፡ ከአሰፋ ማሩ ጋር ጥብቅ ግንኙነት እንደ ነበራቸው የተገነዘበው ወያኔም ሙሉን ሚያዚያ 24 ቀን 1989 ዓ.ም አፍኖ ሲሰውረውና ደብዛውን ሲያጠፋ ሚያዚያ 30 1989 ዓ.ም ደግሞ አሰፋ ማሩን በጠራራ ፀሃይ ሕዝብ እያየ በጥይት በግፍ ገድሎታል፡፡ አሰፋ ታሪኩን በደም አቅልሞ አልፏል፡፡ ቤተሰቦቹም እርማቸውን አውጥተዋል፡፡ ባለቢቴ ሙሉ አምባውን ግን ህወሃት ወያኔ ከሚያዚያ 24 ቀን 1989 አንስቶ እስከዛሬ መጋቢት 20 ቀን 2011 ዓ.ም ድረስ ለ 22 አመት የት እንዳደረሰው አይታቅም፡፡

እኔና ሶስት ልጆቼ ሞተ ብለን እስካሁንም እርም አላወጣንም ይኑር የሙት አናውቅም። በር በር እያየን በሰቆቃ እንኖራለን፡፡ ህወሃት በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ የፈጸመው በደል ተጽፎ–ተነግሮ አያልቅም፡፡”

ሙሉ አምባው በአሁኑ ሰአት ከወያኔ ጋር እየተዋደቀ ላለው ወጣት ትውልድ አርአያና ምሳሌ ነው። በጣም እንኮራበታለን!!!!!

የተለያዩ የህዝብ ልጆችና ሰማዕታት አጭር ታሪክ (BIO)ይቀጥላል !!!