April 5, 2019

FanaBC

በለውጡ የፀጥታና ደህንነት ተቋማት ኢትዮጵያዊ ቅርፅ እንዲኖራቸው ተደርጓል- መንግስት

On Apr 5, 2019 690

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 27፣ 2011 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በፀጥታና ደህንነት ተቋማት ላይ በተካሄደው ለውጥ ተቋማቱ ኢትዮጵያዊ ቅርፅ እንዲኖራቸው መደረጉ ተገለፀ።

በፀጥታና ደህንነት ተቋማት ላይ የሚካሄዱ ለውጦችን በተመለከተ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሄራዊ ደህንነት ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ እና የጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት የፕሬስ ሴክሪታሪ ኃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸው በመከላከያ ሚኒስቴር፣ በብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት፣ በፌዴራል ፓሊስ እና በኢንፎርሜሽንና የመረጃ መረብ ድህንነት ኤጄንሲ በተካሄደው ሪፎርም የተመዘገቡ ውጤቶችን ዘርዝረው አስቀምጠዋል።

በዚህም ተቋማቱ ከየዕለት ተግባራቶቻቸው ባሻገር በህዝቡ ዘንድ የነበራቸውን ስም ለመቀየር ከፍተኛ ስራ እንደተሰራ የብሄራዊ ደህንነት ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

በተካሄደው ሪፎርም እነዚህ ተቋማት የአመራር ችግር ሲነሳባቸው የነበረ በመሆኑ ለውጡን ሊሸከሙ የሚችሉ አመራሮች ወደ ሀላፊነት እንዲመጡ ተሰርቷል ነው ያሉት።

ከዚህ ቀደም በአመራር ደረጃ በተቋማቱ የነበረውን የብሄር ስብጥር በማስተካከል ኢትዮጵያዊ ቅርፅ እንዲኖራቸው መደረጉን ገልፀዋል።

ከለውጡ በፊት በአመራርነት የነበሩ እና የአቅም ክፍተት የነበረባቸው በደረጃቸው እንዲሰሩ መደረጉን በመግልፅ በህግ መጠየቅ ያለባቸውም በህግ እንዲጠየቁ መደረጉን አብራርተዋል።

በሁለተኛ ደረጃ በተቋማቱ ለውጡን ተከትሎ እንዲመጣ የተደረገው የአመለካከት ለውጥ መሆኑ ተነግሯል።

በዚህም የፓለቲካ ወገንተኝነት ሲታይባቸው የነበሩ ተቋማት ገለልተኛና ነፃ ሆነው እንዲንቀሳቀሱ እንዲሁም በህዝብ ዘንድ ተቀባይነታቸው እንዲሻሻል ሰፊ ስራ እንደተሰራ ነው የጠቆሙት።

እነዚህን ተቋማት ህብረተሰቡ በጥርጣሬ ሲመለከታቸው እንደነበረ የገለፁት አማካሪ ሚኒስትሩ፥ ይህም እንዲስተካከልና ተቀባይነት እንዲኖራቸው የህዝብ ግንኙነት ስራ ተሰርቷል ብሏል።

በዚህ ለውጥ ሌላኛው የተሰራው ስራ የአሰራር ስራ ለውጥ መሆኑን በመግለፅ ለዚህም የእስራኤል፣ አሜሪካ እና ሩሲያ ልምዶች መወሰዳቸውን ተናግረዋል።

ይህንንም ተከትሎ በግልፀኝነትና ተጠያቂነት፣ ከግዳጅ፣ አዋጅ የማሻሻል እና በኦፕሬሽናል ስራዎችና አፈፃፀሞች ለውጥ ማምጣት እንደተቻለ ነው ያብራሩት።

በእነዚህ በፀጥታና ደህንነት ተቋማት የመጣው ሌላኛው ለውጥ የአደረጃጀት መሆኑ ተብራርቷል።

በአደረጃጀት ለውጡም ከነበሩት አደረጃጀቶች በተጨማሪ የባህር፣ የስፔስ እና የሳይበር አደረጃጀቶች በአዲስ መልኩ እንዲቋቋሙ መደረጉን አስታውቀዋል።

በተጨማሪ የሰራዊቱ አሰፋፈር ላይ በተካሄደው ለውጥ በአራት አቅጣጫዎች ተመጣጣኝ የሰራዊት አሰፋፈር እንዲኖር መደረጉ ተጠቁሟል።

የብሄራዊ ደህንነትና መረጃ ኤጄንሲ ለውጡን ተከትሎ በአራት ክላስተሮች እንዲቋቋም መደረጉንም ነው ያብራሩት።

ከዚህ ባለፈ በኤጀንሲው የኢኮኖሚ ደህንነት ዋና መምሪያ፣ የህግ ዳይሮክቶሬት እና የህግ ወጥ የጦር መሳሪያን ለመከላከል እራሱን የቻለ ዳይሮክቶሬት ተቋቁሟል።

እንዲሁም በእነዚህ የፀጥታና ደህንነት ተቋማት መካከል የነበረውን በቅንጅት የመስራት ችግር ለመቅረፍ በጋራና በቅንጅት እንዲሰሩ የሚያስችል ባህል እንዲዳብር እየተደረገ ነው ብለዋል።

የክልል የፀጥታ ተቋማትን በተመለከተ በጋራ እየተሰራ መሆኑን ያብራሩ ሲሆን፥ የፌዴራል የፀጥታ አካላት ከክልሎች ፈቃድ ውጭ እንዳይገቡ እየተደረገ ነው ብለዋል።

አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝና ከክልሎች ጥያቄ ሲቀርብ ብቻ የፌዴራል የፀጥታ አካላት እንደሚገቡ እና ድጋፍ እንደሚደረግ በመግለጫው ተመልክቷል።

በሌላ በኩል በሀገሪቱ በዋነኝነት ያለው ስጋት ምንድን ነው ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ፥ የብሄር ፓለቲካው መሆኑን ያብራሩት አማካሪ ሚኒስትሩ ለዚህም በተለያዩ ባለድርሻ አካላት ፓለቲካዊ መፍትሄ ሊሰጥ እንደሚገባ ነው የተናገሩት።

በማሳያነትም በአሁን ወቅት የግል ግጭቶችም ወደ ብሄር እየተወሰዱ የተለያዩ የፀጥታ ስጋቶች እየተፈጠሩ መሆኑን በመጥቀስ፥ ለዚህም ልዩነቶች ማጥበብ እና መግባባትን መፍጠር ይገባል ብለዋል።

በኤፍሬም ምትኩ