=======================
ለጥላቻ ሁሉ መሰረት የሆነውን ሕገመንግስት ስናፈርስ ጥላቻ ከሀገራችን ይወገዳል!
ዶክተር አብይ በአንድ ንግግራቸው ኢትዮጵያ አትፈርስም በአህያ ቆዳ አልተሰራችም የጅብ ጩኸትም አያፈርሳትም የሚል አይነት አባባል ተናግረው ነበር፡፡
ትክክል እኔም ሙሉ በሙሉ ይህን ሀሳብ እጋራለሁ። ህወሓት ወደስልጣን ስትመጣ እኮ የመጀመሪያ ተግባር ብላ የፈጸመችው ኢትዮጵያን ማፍረስ እና ከቴወድሮስ በፊት ለ 70 አመታት የነገሰውን ዘመነ መሳፍንትን በከፋ መልኩ መፍጠር ነበር። በሽግግር መንግስት ተብየው ምስረታ ላይ ኢትዮጵያን የሚወክል አንድ ሰው ብቻ ነበር የተገኘው። የኢትዮጵያ ስም የጭራቅን ስም የመጥራት ያክል ነበር የተወገዘው። የትግራይ ጠባብ ብሄርተኞች ለዘመናት ያለሙትን ህልም እውን ያደረጉበት ኢትዮጵያ የነበራትን ቅርጽ መቀየር እና ያኔ የ 80 ሚሊዮኖችን ሀገር የባህር በር አልባ አድርጎ ማፍረስ ነበር። ሌላ ቢቀር እንኳን በባህር በር እና በኤርትራ የመገንጠል ጥያቄ ላይ ለድርድር እና ለማግባባት ብሎም ሁለቱን ሊያሰራ የሚችል የጋራ ጥቅም አስጠባቂ መላ ሳይሆን ታላቋን ሀገር ሆን ብሎ የሚጎዳ ስራ ነው የፈጸሙ። ልክ ጄኔራል ፔትሮ ቦዶሊዮ 1928 ዓም ሚያዝያ 27 ቀን በድል አድራጊነት ንጉሠ ነገስቱን ከሀገር አሰድዶ አረንጓዴ ቢጫ እና ቀይ ቀለም የመላ ጥቁር ህዝቦችን ባንዲራ አውርዶ፣ የፋሽስት እና አውሮፓ ሰራሽ እንደሰቀለ እና Ethiopia Finita እንዳለ ሁሉ መለስ ዜናዊ እና አባሪ ተባባሪ ኦነጋውያኑ ጭምር የጠላት ሀገር በድል የተያዙትን ያክል የፈነጠዙበት ሁኔታ ነበር ያሳዩን።
ኢትዮጵያን በተግባር ለማፍረስ ለ 27 አመታት ተሰራ። ያ የህወሓት/ኦነግ እና የሀገሪቱ መሰረታዊ ጠላቶች አጀንዳ በስራ ቢውልም ኢትዮጵያ ግን እንደእሳት አቃጥላ ጠላቶቿን ከተቆፈረላት መቃብር ሳትገባ ቀጥላለች። ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያን አሁንም የሚፈልጉት ነጻነት፣ ዴሞክራሲ እና ፍትህ ነው። የዘር ፖለቲካ፣ የዘር አደረጃጀት፣ በዘር ላይ የተመሰረተ ህገመንግስት፣ የዘር ድርጅት አሁንም እያስተዳደረ ባለበት ሁኔታ ለአንዱ ጠቅሞ ለሌላው የሚጎዳ ህግ ማውጣት ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል።
ለማነኛውም የሀገሪቱ እና ሕዝዝቧ ችግር፣ የጥላቻው መሰረት የሆነው ሕገመንግስት ነው፤ ይህ ህገመንግስት ሲወገድ ኢትዮጵያውያን በደማቸው የሌለውን ጥላቻ አንዱ ለሌላው ሊያሳይ አይችልም፡፡ አሁን ህዝብ ከህዝብ ጠላትነት የለውም፡፡ የሀገር ውስጥ መፈናቀል እና ስደት የህገመንግስቱ እና የገዥወች ስራ እና ተግባር እንጅ የግለሰቦች እና በህዝባችን መሀል ያለ ጥላቻ አይደለም።
ጥላቻን ለማስወገድ መለያችን የሆነውን መከባበር እና ፍቅር ለመመለስ ሕገመንግስቱ ይወገድ! የእኔ እና የእናንተ የሚለው መሰረተ እምነት ይጥፋ! መንግስት ከምንም ቅንጭጫቢ ህግጋት በፊት እራሱን ከጥላቻ እና ጥላቻ ሲወልድ ከሚያድረው ሕጉ ይጽዳ
