April 6, 2019
ምርጡ ሰው ጋሸ ስብሃት ገ/እግዚአብሄር መሞቱን የሰማሁ ዕለት ማለዳ በጣም አዝኜ ባዶ ቢሮ ውስጥ ብቻየን ተቀምጬ እያለ ትምህርት ቤት እያለ ከሚሰጠው ሪፈረንስ መፅሃፍ ውጭ ምንም አይነት መፅሃፍ አንብቦ እንደማያውቅ ሁሌ የሚነግረኝ የቢሮ ተጋሪ ባልደረባየ ገርበብ ያለውን ቢሮ በርግዶ ገባ፡፡ቀና ብየ አይቸው እሱ መሆኑን ሳዉቅ አይኔን ወደጠረቤዛው መለስኩ፡፡ያለወትሮየ እንደዘጋሁት አስተዋለ መሰኝ “አኩርፈሻል፤ ልክ ነኝ?” አለኝ፡፡ ዝም አልኩት፡፡ “ዛሬ ደግሞ ማን ታሰረናነው ያኮረፍሽው?” አለኝ፡፡የኢህአዴግ ካድሬ ስለሆነ ሰው በታሰረ ቁጥር ንዴቴን የምወጣው በእሱ ነበርና ነው እንዲህ የሚለኝ፡፡
“ዛሬ ኩርፊያ አይደለም ሃዘን ነው” አልኩት፡፡ “ማን ሞተ?” አለኝ ደንገጥ ብሎ፡፡ “ጋሽ ስብኃት ገ/እግዚአብሄር” አልኩት እንደማያውቀው እርግጠኛ ነበርኩ፡፡ “አላውቀውም፤ የቱነው?” ሲለኝ “ታዋቂ ፀሃፊ ነው አንተ ምንም አላነብም ስለምትል ላታውቀው ትችላለህ፤ ግን በቃ ጥያቄ አታብዛብኝ ልዘንበት” አልኩት፡፡ “የመጨረሻ ጥያቄ ነው ዘመድሽ ነው ወይስ ፅፎ ለሃገር ሁሉ የሸጠውን መፅሃፍ አነበብኩ ብለሽ ነው እንዲህ ፍራሽ ልታነጥፊ የደረስሽው?” አለኝ እየሳቀ፡፡ሳልፈልግ ሳቄን አመጣው!
በብዙ ነገር ሁሌ እንደምገርመው ይገባኛል፤የማያስጨንቀው የሚያስጨንቀኝ እንደምመስለው አውቃለሁ፡፡ በአንፃሩ ለእኔ ደግሞ እሱ ይገርመኛል፡፡በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ራሱን ለማይነካው ነገር ትኩረቱን አይሰጥም፡፡በተቃራኒውእንኳን በቀጥታ በተዘዋዋሪም ራሱን የሚነካው ከመሰለው ደግሞ ያው ነው! “ለራስ ብቻ መኖርን የመሰለ ጎስቋላ ህይወት የለም” ይላል የእግዜር ሰው ነን ከሚሉ ሁሉ ለይቼ ቀልቤን ሰብስቤ የማዳምጠው ብቸኛው ሰው ዮናታን አክሊሉ፡፡እውነት ነው ለራስ ብቻ መኖር ጣዕም የሌለው አዘቦታዊ ነገር ነው፡፡በራስ ፍቅር የተመታ ሰውም ቢሆን ለሌላውም ሰው የሚሞግትበት አንድ ነገር አለ -“ነግ በእኔ በማለት”፡፡
ኤርሚያስ አመርጋን በጋዜጦች እና በቲቪ ከማየው በቀር በአካል አላውቀውም፡፡እሱም በምንም መንገድ የሚያውቀኝ አይመስለኝም ወይም እኔ እንደሚያውቀኝ አላውቅም፡፡ስለዚህ አንተዋወቅም ማለት ነው! ከአንድ ወር በፊት ስለ ኤርሚያስ አመርጋ አንድ ፅሁፍ መፃፌን ተከትሎ አንድ ሰው በውስጥ መስመር ገባና “ኤርሚያስን ታዉቂዋለሽ?” አለኝ፡፡ “አላውቀውም” አልኩት፡፡ “ሰዎች ግን እንደምታውቂው፤ እንደውም ከፍሎሽ እንደፃፍሽለት ነው እያወሩ ያሉት” አለኝ፡፡ “ኤርሚያስ በክፍያ ለማፃፍ ቢፈልግ ኖሮ እኔ ድረስ ማን ያደርሰው ነበር፤ ከሁሉም በላይ ግን እኔ ራሴን የቻልኩ ሰው ነኝ ከገንዘብ ይልቅ ኢፍትሃዊነት ብዕሬን ያነቃቃዋል” ብየው በዚሁ አቆምን፡፡
እንዲህ ያሰበ ሰው ስለ ፍትሃዊነት ብታወሩለት የሚገባው አይደለም፡፡ሁሉ በገንዘብ እንደማይገዛ ለማስረዳት መሞከርም ከንቱ ድካም ነው፡፡ እንዴት እንዲህ ታሰበ ብሎ ፀጉር መንጨትም አይገባም! የሚገባው ኢ-ፍትሃዊነትን ለማውገዝ የሚነቃቃ ማንነት ባይኖረን እንኳን ነግ በእኔ ብለን በሰዎች ላይ የሚደረገውን ግፍ እናውግዝ ማለቱ ነው፡፡ስራ ፈጣሪው ኤርሚያስ አመርጋ የተከሰሰው ሃገር ጠቅልለው ከጎረሱ የሜቴክ ሌቦች ጋር ነው፡፡እነዚህ ሰዎች ደግሞ መሳሪያ የሰቀለ ዘመዳቸውን እየላኩ አፉ ያመጣለትን ገንዘብ ክፈለኝ እንዲለው ሲያደርጉ የነበሩ ሰዎች ናቸው፡፡ጭራሽ አንተን ብገድልህ ማንም አይጠይቀኝም እስከማለት ሄደዋል፡፡ ከነዚህ ሰዎች ጋር በመመሳጠር መከሰሱ ጠብ ያለሽ በዳቦ ነገር ነው፡፡
በዚህ ላይ የክሱ ጭብጥ “ለምን ንብረትህን በውድ ሸጥክ? ገዥ ብታገኝ እንኳን የምትሸጥበት ዋጋ ውድነት ሃገር እንደማይጎዳ ማመዛዘን ነበረብህ” ተብሎ ነው፡፡ይህን ያህል ቀናት ነገሩ እልባት አጥቶ የቆየውም አቃቤ ህግ ኤርሚየስ ከሜቴክ ጋር “ተመሳጥሮ” ሆቴሉን በውድ ሸጧል ሲል ምን ማለቱ እንደሆነ እንዲያስረዳ ሲጠየቅ የሚለው ስለጠፋበት ነው፡፡ በዚህ ምክንያት ደህና ቀን መጣ ባልንበት ዘመን ባለ ፈጣን ጭንቅላቱ ኤርሚያስ አመርጋ እስርቤት ተከርችሞበታል!የሃገራችን ኢኮኖሚ የእምብርክክ የሚሄደው እንዲህ ባለው ጭንቅላት የማሰር አባዜያችን ነው፡፡
አቃቢ ህግ ራሱ ያመጣውን “መመሳጠር” የሚል ቃል ማስረዳት ስላቃተው ሲጓተት የኖረው የኤርሚያስ ጉዳይ ችሎት ምስክሮች ለመስማት በመጭው ሰኞ ይሰየማል፡፡የዘገየ ፍርድ እንዳልተሰጠ ይቆጠራልና የኤርሚያስ ነገር እልባት እንዲያገኝ ሁላችንም ድምፃችንን ማሰማት አለብን፡፡እዚህ ሃገር ግር ብሎ ከገጠር የሚመጣ የዘሩን ጎረምሳ ያላዘጋጀ ሰው ምንም ሊደረግ ይችላልና ዘራችን ከሰው ዘር የሆንን ሁሉ ስለኤርሚያስ ግድ ሊለን ይገባል!
