April 6, 2019

እኔን ጨምሮ ብዙሀኑ የኢትዮጵያ ሕዝብ አብይ ወደ ስልጣን ሲመጣና በመጀመሪያዎቹ ወራት በሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎች በሙሉ ልብ ደግፈናል፡፡ እንደ እውነቱም ከልባችን ስለነበር አሁንም አይጸጽተንም፡፡ እየቆየ ግን አብይና ቡድኑ በሚያደርገው ድርጊት ብዙዎች የልብ ደጋፊ የነበሩ ቅር መሰኘት ብቻም ሳይሆን ዛሬ ላይ የአብይን እንቅስቃሴ በይፋ መንቀፍ ጀምረዋል፡፡ በእኔ ግንዛቤ እነዚህ የአብይ ደጋፊዎች ወረተኛ ሆነው አደለም፡፡ ይልቁንም ከልባቸው ተስፋ ያደረጉት ነገር ሌላ ሆኖ ሲያገኙት የተጋጋለ ተስፋቸው ላይ ቀዝቃዛ ውሃ እየረጨ ያለው የአብይ ቡድን እንቅስቃሴ በተግባር ሲፈተሽ የተጠበቀው ተስፋ ቀርቶ ጭራሽ ብሕልውና ላይ ሳይቀር አደገኛ መስሎ ስለተሰማቸው እንጂ፡፡
አንዳንዶች ከበፊትም ጀምረው አብይን ሲቃወሙ ስለነበር አሁን በተግባር የሚሰራውን እውነት እየፈለፈሉ በማሳያነት እያወጡ ናቸው፡፡ ለእነዚህ የአብይ ቡድን ያልተጠበቀው እንቅስቃሴ እንደ ጥሩ አጋጣመ ሆኖላቸው እናየዋለን፡፡ በመረጃ የተደገፈ እውነትን እያሳዩ ለመንቀፍ አስችሏቸዋል፡፡ በርካታ ተከታዮችም እያገኙ ነው፡፡ ከእነዚህ አንዱ ቴድሮስ ፀጋዬ ነው፡፡ ለቴድሮስም ሆነ ለሌሎች ተከታዮች በተግባር እነ ቴድሮስ የሚያወሩትን ነገር ትክክል አለመሆኑን ከማሳየት ይልቅ አሁንም የአብይን ቡድን ገመና እየፈለፈሉ በማስረጃ የሚያቀርቡትን እነ ቴድሮስ ላይ የመልስ ፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ማድረግ የበለጠ ለእነ ቴድሮስ ጥንካሬና ብዙ ደጋፊ ያፈራላቸው እንደሆነ እንጂ የሚያቆማቸው አይመስለኝም፡፡ ቴድሮስም ሆነ ሌሎች መሰሎቹ የራሳቸው ዓላማ ሊኖራቸው ይችላል፡፡ ግን በግልጽና በመረጃ የተደገፈን እውነት እየተናገሩ የቱንም ያህል የእነሱ አላማ ተቃዋሚ ብንሆንም ለምንም ይሁን ለምን እያወጡት ያለው መረጃ ብዙውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ቆም ብሎ እንዲያስብ ረድቶታል ምን አልባትም ከታደለት ሴራ በጊዜ እንዲነቃ እገዛ አድርጎለታል፡፡ ቴድሮስ ጸጋዬ ያቀረበው ሁሉ ውሸት መሆኑን ሳይሆን ይበልጥ እውነታውን የሚመሰክሩ በተግባር የሚታዩ ድርጊቶችን ሕዝቡ ለመመልከት አይኑን እንዲከፍት አስችሎታል፡፡ የሚከተሉትን ነጥቦች አነሳለሁ፡፡
የአብይ የመጀመሪያ ወራት ስኬት፡- አብይ በሲመተ ንግግሩ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በሚያስበል ሁኔታ ከልብ እንዳዳመጠው፣ ከዛም ብዙዎች በንግግሩ በመመሰጥ በክብር ቆመው እንደሰሙት ከዚም አለፎ አንዳነዶች በደስታ ሲቃ እያነቡ እንደሰሙት አብይም ሆነ የእሱ ቡድን ያውቀዋል፡፡ ሕዝብ ግን አብይን ከንግግሩ ውጭ ምን ሊሠራ እንደሚችል አያውቅም፡፡ ቀጥሎም የኤርትራ፣ የኦርቶዶክስና ሙስሊ እምነት የውስጥ ችግር መፍታቱ ትልቅ ድጋፍ አስገኝቶለታል፡፡ አብይ በዚህ ረገድ ያደረገውን ጥረት ማጣጣል አያስፈልግም፡፡ ሆኖም የእነዚህ ክስተቶች መሣካት የአብይ ጥረት ውጤቶች ሳይሆኑ የሁኔታዎች ዝግጁ መሆንና አብይም ይሄንኑ የተዘጋጀ ነገር እውን እንዲሆን መፍቀዱ ላይ ነው፡፡ ከኤርትራ በኩል የወያኔ መንግስት ከወረደ ወደብ እስከመፍቀድ ሊደራደር እንደሚችል ሲነገር ነበር፡፡ ይሄንኑ አጋጣሚ አብይ ወደ ስልጣን ሲመጣ ተጠቀመበት፡፡ ይሄ በራሱ ጥሩ ነገር ነው፡፡ በእርግጥም አብይ እዚህ ላይ ጉልህ ድርሻ ነበራ ግን ሌሎችም በጉልህ ድርሻ ተሳታፊ ነበሩ፡፡ ራሳቸው የኤርትራው ፕሬዘደንትም ቢሆኑ ብዙ ድርሻ አላቸው፡፡ ከዚህ ውጭ እንደነ አንዳርጋቸው ጽጌ ያሉ ግለሰቦች በውስጥ ትልቁን ሥራ እንደሰሩ ይነገራል፡፡ ይሄን አንዳርጋቸውም በአንድ ወቅት ጠቆም አድርገውታል፡፡ የአርቶዶክስ ቤተክርስቲያንን ችግር ለመፍታት ብዙዎች እየጣሩ ነበር፡፡ አብይ በውሳኔው ተባባሪ መሆን ብቻም ሳይሆን ግፊት ጭምር በማድረግ ስኬታማ እንዲሆን አድርጓል፡፡ ይሄን አጋጣሜ በበጉ መልኩ ተጠቅሞበታል፡፡ በሙስሊሙ ማሕበረሰብም የሆነው ተመሳሳይ ነው፡፡ የእነዚህ ሁሉ ችግሮች ቁልፍ ምክነያት ወያኔ በመሆኑ ወያኔ ሲፈርስ እነዚህን ማሳካት ቀላል ሆነ ብዬ ባላቀለውም ግን እጅግ ከባድ አልነበረም፡፡ እነዚህ ሁሉም በስኬት የተደመደሙ ናቸው ማለት ይቻላል፡፡ ከአገራት ጋር የጀመረው ጥረት መልካም ነው ግን ሙሉ በሙሉ ስኬታማ የሆነ ውጤቱን ገና ሳናይ አሁን ላይ ራሱ በኢትዮጵያ ሕዝብም በወዳጅ አገራቱም ጥርጣሬ ላይ እየገባ ይመስላል፡፡ እና ብዙም ተሳካ የሚባል አደለም፡፡ ከእነዚህ ውጭ ግን አዲስ የስኬት ምዕራፍ ማየት አልቻልንም፡፡ የነበሩ ችግሮች እንደቀጠሉ ሌላ ተጭማሪ ችግር እየመጣ ነው፡፡
የአዲስ አበባ ጉዳይ፡- የአዲስ አበባ ጉዳይ አብይን በብዙዎች ዘንድ ጥርጣሬ ውስጥ እንዲገባ ያደረገው ነው፡፡ ከጅምሩ ከኦሮሚያ አምጥቶ ታከለን የአዲስ አበባ ከንቲባ ሲያደርግ ጥሩ ገጽታን የፈጠረ አልነበረም፡፡ በአካሄድም ይሄ ልክ አልነበረም፡፡ ያም ሆኖ ከዛ በኋላ አዲስ አበባን አስመልክቶ የሚደረጉ ድርጊቶች ይበልጥ አብይን በሕዝብ ዘንድ ጥርጣሬ ውስጥ እንዲገባና ብዙ ደጋፊዎቹንም ወደኋላ እንዲያፈገፍጉ አድርጓል፡፡ በእኔ እይታ የታከለ ኡማ ኦነግ ከውጭ በገባ እለት ያደረገው ንግግር ጥሩ አልነበረም፡፡ በግልጽ አዲስ አበባን ሳይሆን የመጣበትን የኦሮሞ ፓርቲ ወክሎ ነበር የተናገረው፡፡ አሁን በቅርብ ደግሞ የዲሞግራፊ ለውጥ ጉዳይ ትልቅ ጥርጣሬን እንዲፈጥር አድርጎታል፡፡ ለዚሁ የለማ ንግግር እንደማረጋገጫ ቀርቦ በሰፊው ተሰራጭቷል፡፡ ለማ ያን ንግግር ስለሚያምነበት ተናገረው ለማለት ለእኔም እስከዛሬም ያልተቀበልኩት ቢሆንም በምንም ይሁን በምን መናገር አልነበረበትም፡፡ ይልቁንም የንግግሩ ምክነያት የሆነውን ጠያቂ በዛ መልኩ እንዳያስብ መገሰፅ ሲገባው ጭራሽ ራሱ ተናግሮታል፡፡ በምንም ሁኔታ ይናገረው ስህተት ነበር፡፡ ይሄ እንግዲህ ቴድሮስ ጸጋዬ በማሳያነት ከአቀረባቸው ሊካድ የማይቻል ማስረጃ ነው፡፡ ቀጥሎም ሌላው በለውጡ ትልቅ ድርሻ አለው ተብሎ የሚነገርለት አዲሱ አረጋ በተመሳሳይ አርቲስቶችን ሰብስቦ አዲስ አበባ ውስጥ ብዙ ሥራ በኦዴፓ በኩል እየተሰራ እንዳለና ታከለ ኡማም ለዚሁ ተልዕኮ እንደሆነ እየሰራ ያለው በማያሻማ መልኩ ሲናገር አሁንም በድጋሜ የቴድሮስ ጸጋዬ ሬዮት አወጣው፡፡ እንግዲህ እነዚህ የሰማ ኢትዮጵያዊ ከእነአብይ ድጋፍ ማፈገፈግ አደለም እነአብይነ ወደ መቃወም ቢለወጥ ለምን ይፈረድበታል? ቴድሮስና መሰሎቹስ ይሄን እውነት ማውጣታቸውን እንዴት ሊያስወግዛቸው ይችላል? የአዲስ አበባ ጉዳይ በዚህ አላበቃም፡፡ በይፋ ኮንደሚኒየም ዕጣ የወጣላቸው የቤት ባለቤት እንደማይሆኑ አረጋገጡ፡፡ መታወቂያ አላግባብ እየታደለ መሆኑን ያጋለተች የመስተዳድሩ ሰረተኛ በግልጽ በዘረኞች ከስራ ተባረረች፡፡ እስካሁንም ወደ ሥራዋ እንዳልተመለሰች እየተነገረ ነው፡፡ እነዚህ ገሃዳዊ እውነታዎችን ለማረም የአብይም ሆነ የመስተዳደሩ ባለስልጣናት ሲንቀሳቀሱ አለመታየታቸው ሳያንስ ይባስ ጸረ-አዲስ አበባና ኢትዮጵያውያን የሆነውን መግለጫ ኦዴፓ አወጣ፡፡ እነአስክንድር በዚህ ሁኔታ የከተማው ሕዝብ ራሱን መከላከል አለበት ብለው በማመናቸው እንቅስቃሴ አደረጉ ብዙ ሕዝብ በተሰበሰበበት የባለአደራ ማህበር መስርተው አሁን የለየለት ፍጥጫ ውስጥ ገብተዋል፡፡
በዚህ ሁኔታ ነበር አብይ እነ እስክንድር ወደዚህ እርምጃ የገቡበትን ምክነያታዊ ሒደቶች ሁሉንም በማዳፈን እነእስክንድር ላይ ጦርነት እንደሚጀምር ለመጀመሪያ ጊዜ በጦርነት ማሸነፍ አለብኝ በሚል ንግግር ያደረገው፡፡ ቀጥሎም በይፋ የመናገር መብትን እደግፋለሁ እያለ በራስ ሆቴል እነእስክንድር ሊያደርጉት የነበረውን መግለጫ እንዲከለከል የተደረገው፡፡ ለመሆኑ ማን ነው ይሄን ያደረገው? እንደተነገረው የልደታ ክፍለከተማ ፖሊስ ነው፡፡ ይሄ ክስተት የአብይን ማንነት ይበልጥ ያጋለጠ ነበር፡፡ ለምን ፈሩት? በሐሳብ እናሸንፋለን የሚሉት ለምን የእስክንድር መግለጫ አስፈራቸው? የሚያሳዝነው መግለጫውን በመከልከል ይበልጥ ለብዙ ሰው ጥያቄ ሆኑበት፡፡ የእነእስክንድር መግለጫ በመጨረሻም ከራሱ ቢሮ ተሰጠ፡፡ እንግዲህ በሀሳብ ቢያምኑ ከጅምሩ እስኪ እናድምጣችሁ ችግራችሁ ምንድነው ተብሎ ቢሆን እዚህ ባልተደረሰ፡፡ በዚህ አካሄድ ከጉልበተኞቹ ከእነአብይ ይልቅ እነእስክንድር ከሕጋዊነታቸውም በላይ የተነሱበት አላማ ትክክለኛነት እያረጋገጠ መጥቷል፡፡ በአጠቃላይ የአዲስ አበባ ጉዳይ አብይ የተለካበት ትልቁ ጉዳይ ነበር፡፡
የሠላም ጉዳይ፡- የአብይ ቡድን በየቦታው ያሉ የሠላም ችግሮችን ለመፍታት ያደረገው ጥረት የለም ቢባል ይሻላል፡፡ ምክነያቱም የሠላም ሚኒስቴር እስከማለት ቢያቋቁምም ሚዲያን እንኳን ተጠቅሞ ሕዝብን ከሕዝብ የሚያቀራርቡ ሥራዎችን በሠፊው መሥራት አልቻለም ብቻም ሳይሆን መፈለጉም አጠያያቂ ነው፡፡ ከዛ ይልቅ ተቀባይነት ያስገኙልኛል የሚላቸውን ፕሮፓጋንዳዎችን ለማሰራጨት ይጠቀምባቸዋል፡፡ አሁን ይባስ የራሱን ዶኩመንተሪ እያሰራጨባቸው ነው፡፡ ይሄ ነውር ነው፡፡ ከሠላም አንጻር እንዳንድ ክልሎች ለምሳሌ ሱማሌ ክልል በራሳቸው ተሳክቶላቸዋል፡፡ የዚህ ስኬት ምክነያት ደግሞ የሱማሌ ሊሂቃን ከልብና እስከዛሬ በነበረው መከራ ቁጭት ለሕዝባቸውና ክልላቸው ሠላምን ለማስፈን መወሰናቸው ነው፡፡ ለበርካታ ዓመታት በነጻ አውጭነት ሲታግል የነበረው ኦብነግ ሳይቀር ዛሬ ለክልሉ ሠላም ክልሉን ከሚመሩት ጋር እየሰራ እንደሆነ በይፋ እየተናገረ ነው፡፡ በሌላ መልኩ በኦሮሞ ሊሕቃን የሚመራው የኦሮሞ ፖለቲካ ለኢትዮጵያ ሠላም ማጣት ዋናው ምክነያት ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ የኦሮሞ ፖለቲካ በሚመረው ኦሮሚያ አዋሳኝ ያሉ ሁሉ ጋር ክልሉ ግጭት ፈጥሯል፡፡በውስጥ የሚኖሩም ብዙ መንገላታትና፣ ሞትና መፈናቀል ደርሶባቸዋል፡፡ የኢትዮጵያ ጠላት የሆነው አሸባሪው ኦነግ ዛሬ ጉልበት አግኝቶ እንደልቡ እየፈነጨ ይገኛል፡፡ በሌሎች ክልሎችም ችግሮች አሉ ግን ከኦሮሚያው ጋር የሚነጻጸር አደለም፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአማራ ክልል የኦሮሞን ተመሳሳይ የሆነ የፖለቲካ አካሄድ በሰፊው እየተስፋፋ ነው፡፡ የኦሮሞ ፖቲካ ኦሮመን ከማንነቱ አውጥቶ ያዋረደ እንደሆነ ሊሰመርበት ይገባል፡፡ የአማራ ፖለቲካ አሁን ላይ የሚታይበት ይሄው ምልክት ነው፡፡ ቆይቶ ከማንነቱ የወጣ በጥላቻና ዘረኝነት የመረቀዘ ትውልድ ሲበረክት ውሉ እንዳይጠፋ ከወዲሁ ይታሰብበት፡፡ አሁንም ያለው ሁኔታ ቀላል አደለም፡፡ እነዚህንና መሠል ጉዳዮች ለማስተካከል የአብይ ቡድን የቱ ጋር እየሰራ እንደሆነ እንጃ፡፡
መሬቱ የእኛ ለፍኒ ኬኛ ፡- ይሄ አይነት አስተሳሰብ ሁሉም ጋር እየተስፋፋ ነው፡፡ መሬቱ የእኛ ክልል ነው ማለት የተሻለ ነበር ግን መሬት የእኔ ብሔር ነው ሲባል በተለይ የተራ ጥራዝ ነጠቅ አዋቂ ነን ባይች ሳይወሰን ሕዝብን እንመራለን በሚሉና በሊሂቃኑ ሳይቀር ያለ አስተሳሰብ መሆኑን ሳይ እጅግ አዝናለሁ፡፡ ሰሞኑን አቶ በድሩ አደም በአንድ ሚዲያ ቀርበው ይሄንኑ ሲሉ እና ምን ሰው ቀር ብያለሁ፡፡ የአዲስ አበባ መሬት የኦሮሞ ነው አሉ! አዲስ አበባ የኦሮሞ ነች ከሊቅ እስከደቂቅ የኦሮሞ ሊሂቃን ነውረኛ አስተሳሰብ ነው፡፡ አዝናለሁ፡፡ ፕ/ሮ መረራ በቻ ነው በዚህ ጉዳይ ግልጽ ሆኖ ሲናገር የሰማሁት የኦሮሞ ሊሂቅ፡፡ በጠያቂ ጋዜጠኞችም ዘንድ ያለው አስተሳሰብ አሳፋሪ ነው፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ የዋልታው ሚዲያ ጋዜጠኛ ለመረራ ያቀረበላቸውን ጥያቄ ስሰማ በጥም አዝኛለሁ፡፡ ጋዜጠኛው አዲስ አበባ የኦሮሞ ነች ወይ ይላል? ምን ማለቱ እንደሆነ መረራ ማብራሪያ ይጠይቃል፡፡ ለምሳሌ ቢሾፍቱ የኦሮሞ ነች አዲስ አበባስ ብሎ ይጠይቀል፡፡ ይሄን ነበር መረራ ቢሾፍቱ የኦሮሞ ነች ያለህ ማን ነው ያለው፡፡ ሰሞኑን አብይ ያው በተለመደ ገርድፍ ንግግሩ ከተሞችን እየጠራ የሁሉም ናቸው ማለቱ መልካም ነው፡፡ ግን አዲስ አበባ ላይ ወገቡን ይዞታል፡፡ አዲስ አበባ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ነች የሚለውን ከአንደበቱ ማውጣት አልፈለገም፡፡ የትም ቦታና ሥፋራ ቢሆን የነዋሪዎቹ ነው፡፡ ይሄን አስተሳሰብ ግን መቀበል ለብዙዎች ተስኗቸዋል፡፡ ማንም በየትም ቦታ ሄዶ ነዋሪ እስከሆነ ድረስ የዛ ቦታ ባለቤት ነው፡፡ የወለጋ ኦሮሞ ድሬዳዋ የኦሮሞ ነች ይላል፡፡ ሐረር የኦሮሞ ነች ይላል፡፡ የነዋሪዎቹን በለቤትነት አይቀበልም፡፡
የሰሞኑ የዓለማያ ተማሪዎች አመጽ፡- ሰሞኑን በአለማያ ዩኒቨርሲት ይሄው ጉዳይ ምክነያት ሆኖ ብጥብጥ ነበር፡፡ ጥያቄው ሐረር፣ አዲስ አበባና፣ ድሬዳዋ የኦሮሞ መሆን አለባቸው ነው፡፡ ነውረኛው አስተሳሰብ የዩኒቨርሲት ተማሪዎችን እንዳያስቡ ዘግቶባቸዋል፡፡ የቦታ ለብሔረሰብ መሰጠት ከአለበት ሐረር የሐረሪዎች ነች ቢባል ልክ በሆነ ነበር፡፡ ይሄም ራሱ ልክ አደልም እንጂ፡፡ አስተውሉ ሐረር ከሚታወቅባቸው አንዱ የሐረር ታሪካዊ ግንብ ነው፡፡ ይሄ ደግሞ በግልጽ የሐረሪ ሕዝብ ታሪካዊ አሻራ ነው፡፡ እንግዲህ ዛሬ በዛው ታሪካዊ አሻራው በአለበት አጥር ውስጥ እየኖረ ያለውን ሐረሪን ነው ከተማው የእኛ ነው እየተባለ ያለው፡፡ ቆይቶ ይሄ ቤት የእኔ ነው አይቀርም፡፡ በኢርግጥ በኩዬ ፌጫ ያየንው ይሄንኑ ነው፡፡ ሐረር ግን የሐረሪ ሕዝብ ብቻ አደለም፡፡ በዛ የሚኖር የነዋሪው ሁሉ እንጂ፡፡ ድሬዳዋም ያው ነው፡፡ ምን አልባት ሱማሌና ሌላው ሕዝብ ይበረክትበት ይሆናል፡፡ አዲስ አበባን እንግዲህ አሁን ዲሞግራፊ እየቀየርን ነው ከተባለ ወዲህ ምን እንደሆነ አናውቅም፡፡ የሆነ ሆኖ ይሄ አስተሳሰብ ዛሬ ለብዙዎች ጤነኛ ምስሏቸዋል፡፡ ግን የከፋ የአስተሳሰብ ዝቅጠት ነው፡፡ ይሄው የአለማያ አመፅ ያ የፈረደበት አለሙ ስሜ የሚባል ሰው ከስልጣን እንዲነሳ ሲገልጽ ነበር፡፡ እንደ እውነቱ የአለሙ ስሜ ስልጣን ምን እንደሆነ እኔም አላውቅም፡፡ ከእሱ ይልቅ ሌሎች ክልሉን በበላይነት ለሚመሩት መንግስት የአለሙ ስሜ ኢላማ መሆን ዓላማው ምንድነው? ዓለሙ ስሜ በኦዴፓ ከአሉ ጥቂት ከሸዋ ከተወለዱ ከመሆኑ ውጭ፡፡ እንግዲህ በሌሎች አስተሳሰብ ባርነት ስትወድቅ እንዲህ ያለ ምክነያት ባሪያ የገዙህን አስተሳሰብ እያሰብክ እንደነሱ ትጮሀለህ፡፡ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የተባሉት የደረሰባቸው የአእምሮ ውድቀት ይሄ ይመስላል!
በደሴና አንዳንድ አማራ ክልሎች እየሆነ ያለውን በጥሞና ያስተውሉ፡፡ እንደተባለው የአማራ ወጣቶች ማህበር እንዳይቋቋም እንኳን ቢደረግ ይሄ ራሲን የሚያሳጣ ስርኣት የለሽ እንቅስቃሴ አደጋ አለው፡፡ በአለፈው መሳሪያ ይዘው በባህር ዳር የወጡ አስታውሱ፡፡ እንግዲህ ሁሉም ሊያስብበት ይገባል፡፡ ስለዚህ ጉዳይ ሙሉ መረጃው የለኝም፡፡ ያም ሆኖ ግን እየሆነ ያለው ችግር አደጋ አለው፡፡
የእነ አበበ ገላውና ሲሳይ የሰሞኑ ንግግር፡- አበበንም ሲሳይንም በተወሰነ እረዳለሁ፡፡ ግን ሰሞኑን እየተናገሩት ያሉት ለአብይ የፕሮፓጋንዳ ዘብ የቆሙለት መስሎባቸዋል፡፡ ጥሩ ነው በጎ ነገሮችን ማጉላት፡፡ ሆኖም በደጋፊነት ሳይሆን በነጻ አስተሳሰብ ቢሆን እላለሁ፡፡ በደጋፊነት ስሜት ስህተቱ የበዛ ነው፡፡ ለምሳሌ ሰሞኑን ሲሳይ በቴድሮስ ጸጋዬ ላይ ተናገረ የተባለው ስህተት ነው፡፡ የተናረው ነገር እውነት አደለም እያልኩ ሳይሆን የተናገረበት ሁኔታ ጥሩ አደለም፡፡ ቴድሮስ ጸጋዬ እያቀረበ ያለው መረጃ ትክክል ነው አደለም ተብሎ ከተጠየቀ ይሄንኑ ትክክል ወይም ሐሰት የሚሆን ማስረጃ በማቅረብ ማረጋገጥ እንጂ ለዚህ አይነት ጥያቄ የቴደሮስን ሚስጢር ማውጣት ላይ ያተኮረ ንግግር ልክ አደለም፡፡ ቴድሮስ 15ሺ ዶላር ተከፍሎለት የሚሰራበትን ስቱዲዮ ባይሆን በልዩ ሆኔታ ከቴድሮስ ሴራዊ አካሄድ ጋር ማቅረብ ነው፡፡ አሁን ጥያቄው ቴድረስ የሚለው ልክ ነው አደለም ነው፡፡ ቴድሮስ የቱንም አይነት አላማ ይኑረው፡፡ እነ አብይ የሚሠሩት ትክክል እንዳልሆነ የሚያሳየውን መረጃውን እንዳልሆነ መግለጽ ለሕዝብም ይጠቅም ነበር እውነትንም ያጠራ ነበር፡፡
አመሰግናለሁ!
ቅዱስ እግዚአብሔር ማስተዋሉን ይስጠን አሜን! ልዑል አባት አገራችንን ይባርክ! አሜን
ሰርፀ ደስታ
