
በአማራ ክልል ኦሮሞ ብሄረሰብ አስተዳደር ባለፈው ሳምንት መጨረሻ የተከሰተውን ግጭት ተከትሎ ከብሔራዊ የጸጥታ ምክር ቤት መግለጫ ተሰጥቷል። መግለጫው በአካባቢው የተፈጠረውን አለመረጋጋት ጠቅሶ “የተከሰተውን የሰላም መደፍረስ ለማረጋጋትና የሚመለከታቸው የፌደራልና የክልል የፀጥታ አስከባሪ ተቋማት አስፈላጊውን ሕጋዊና ተመጣጣኝ እርምጃ እንዲወስዱ” ትእዛዝ አስተላልፏል።
ከሰሞኑ በአማራ ክልል በኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር የተከሰተው አለመረጋጋት ወደ ሰሜን ሽዋ ዞን ኤፍራታና ግድም ወረዳ ተሸጋገሮ የሰው ህይዎት መጥፋቱ፣ ንብረት መውደሙ እና ዝርፊያ መፈፀሙ ተነግሯል።
አቶ ሰማቸው የተባሉ የማጀቴ ከተማ ነዋሪ እንደተናገሩት ከትናንት ጀመሮ በተደራጀ መልኩ የቡድን መሳሪያ የታጠቁ አካላት በንጹሃን ዜጎች ላይ ሲተኩሱ ውለዋል፤ በዚህም 14 ሰዎች የተገደሉ ሲሆን ከእነዚህም መካከል ሁለቱ የፖሊስ አባላት ናቸው ብለዋል።
አሁንም ስጋት በመኖሩ ነዋሪው አካባቢውን ለቅቆ ወደ ገጠር ቀበሌዎች እየተሰደደ ነው ያሉት አቶ ሰማቸው በዚህ ሰአት የሚካሄድ ተኩስ የለም ነገር ግን የጸጥታ አካላት ባለመድረሳቸው ስጋት አለን ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
• በሰሜን ሸዋ በተከሰተ ግጭት ህይወት ጠፍቷል ንብረት ወድሟል
• በትሪፖሊ አቅራቢያ በተደረገ ውጊያ የ21 ሰዎች ሕይወት ጠፋ
ሌላኛው የአካባቢው ነዋሪና ስሙን መግለጽ ያልፈለገው ግለሰብ ደግሞ “ከትናንት ጀምሮ ባልተዘጋጀንበት ሁኔታ ከቀያችን ድረስ መጥተው ተኩስ ከፈቱብን ባለን አቅም ስንከላከል ለጊዜው ከሁለታችንም ወገን ቁጥራቸውን የማላውቃቸው ሰዎች ሞተውብናል” ብሏል።
የሰሜን ሸዋ ዞን አስተዳደርና ፀጥታ መምሪያ ሃላፊ አቶ ካሳሁን እምቢአለ እንደገለጹት ደግሞ የጸጥታ አካላት በሁሉም ቦታ ደርሰዋል። አስፈላጊ ከሆኑ አካላት ጋርም እየተነጋገርንና ነገሮች ወደ ቀደመ ሰላማቸው የሚመለሱበትን ሁኔታ እያመቻቸን ነው ሲሉ ለቢቢሲ ገልፀዋል።
ትናንት በነበረው ግጭት አንድ ቤተ ክርስቲያን የተቃጠለ መሆኑን የተናገሩት የመምሪያው ኃላፊው በሌላ አካባቢ ቤተክርስቲያንም የማቃጠል ሙከራ ተካሂዶ ባይሳካም በዙሪያው የሚገኙ ቤቶች ግን ተቃጥለዋል ብለዋል። አጣዬ ላይ የግለሰብ ቤቶች እንደተቃጠሉና ዝርፊያም እንደተፈጸመ አብራርተዋል።
“ኦነግ ያደራጃቸው ናቸው ይህን የፈጸሙት” የሚሉት አቶ ካሳሁን “አላማቸውም ሽብር መፍጠርና ዝርፊያ ማካሄድ ነው” ብለዋል። በዚህ ወቅት በስፍራው የሚገኙት የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር አበረ አዳሙ እንደገለጹት ደግሞ በአሁኑ ወቅት ሁሉም አካባቢዎችን ማረጋጋት ተችሏል።
አክለውም ሁኔታውን ዘላቂ ሰላም እንዲኖረው ለማድረግም ከሃይማኖት አባቶችና ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር ውይይት እየተደረገ ነው ብለዋል።
ትናንት የተከሰተውን ግጭት ተከትሎ ደብረ ብርሃንም ከፍተኛ የሆነ ህዝብ ጎዳና ወጥቶ ችግሩን ሲቃወም መስተዋሉን ከስፍራው ያነጋገርናቸው ነዋሪዎች ነግረውናል።
ዛሬ በአጣዬ ማጀቴና ካራቆሬ አንጻራዊ መረጋጋት የታየ መሆኑን የተናገሩት አቶ ካሳሁን ከባንኮችና አንዳንድ ተቋማት ውጭ ሌሎች አገልግሎቶች መደበኛ ስራቸውን በመስራት ላይ ናቸው ብለዋል። በስፍራው የመከላከያ ሠራዊትም ደርሷል ብለዋል።
