April 9, 2019

ቀን 29/03/2019

በኑረንበርግ የኢትዮጵያውያን ባህል ማህበር (ኮሚኒቲ) አስተባባሪነት ነዋሪነታቸው በኑረንበርግና አካባቢዋ የሆነ በርካታ ሃገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን በ 24.03.2019 ከቀኑ 15 ሠዓት ጀምሮ Wiesenstr. 86 በሚገኝው የስብሰባ አዳራሽ በመገኝት በደቡብና ደቡብ ምስራቅ የሃገራችን ክፍሎች ሰው ሰራሽ በሆኑ ግጭቶች ከቀያቸው ተፈናቅለው ለከፍተኛ ችግር ለተዳረጉ ወገኖቻችን ዕርዳታ የማሰባሰብ መርሃ ግብር ላይ ተሳትፈዋል።

በዚህ የድጋፍ ማሰባሰቢያ ፕሮግራምና በቀጠሉት ቀናት በዕለቱ ለመታደም ካልቻሉ የከተማችን ኢትዮጵያውያን እስከ አሁን በድምሩ 6745,0 ኦይሮ ማሰባሰብ የቻልን ሲሆን ይህም እርዳታ በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት ለተጎጂዎች እንዲደርስ ይህንን ግብረ ሠናይ ስራ ከጅምሩ ላስተባበረው ግሎባል አሊያንስ እንዲደርስ እምናደርግ መሆኑን እናሳውቃለን። በዚህ በጎ ተግባር ላይ ለተባበራችሁን ሁሉ በተረጂዎች ስም በድጋሚ ልባዊ ምስጋና እናቀርባለን።

በእለቱ በአዳራሹ ተገኝቶ እርዳታ ማሰባሰቡ ላይ ከተሳተፈው ሕዝብ ጋር ካደረግነው ሠፊ ውይይትና ታዳሚው ለሁሉም ኢትዮጵያዊ ዜጋ እንዲደርስ ከሚፈልገው መልዕክት በመነሳት የሚከተለውን የአቋም መግለጫ እናቀርባልን።

የአቋም መግለጫ

እንደሚታወቀው ማህበራችን ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ በማህበራዊና በሰብአዊ ጉዳዮች ላይ ትንሽ የማይባል እንቅስቃሴ ሲያድርግ ቆይቷል፤ በማድረግ ላይም ይገኛል፤ወደፊትም እንደ አንድ ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ ማህበር የሚጠበቅበትን አስተዋፅኦ አቅም በፈቀደ መጠን ለመወጣት ይጥራል። በኢትዮጵያ የመጣውን የለውጥ ጅማሮምና አራማጁንም የለውጥ ሃይል በአለን አቅም ሁሉ እየደገፍን እንገኛለን። ሆኖም ግን በአሁኑ ወቅት በሀገራችን ውስጥ እየታዩ ያሉ ዜጎችን ያለ አግባብ ለዘመናት ከኖሩበት ቀያቸው የማፈናቀል የሰብአዊ መብት ጥሰትን ያካተቱ አድልኦ የሚስተዋልባቸው አስተዳደራዊ ውሳኔዎች ከእለት ወደ እለት እየተባባሰ መምጣቱ ስላሳሰበን ከማህበራችን አባላትና ከአካባቢው ኢትዮጵያዊ ማህበረሰብ ጋር በመመካከር የሚከተለውን የአቋም መግለጫ አውጥተናል።

  1. በወገኖቻችን በማንነታቸው ምክንያት ለዘመናት ከኖሩበት ቀያቸው እና ደክመው ለፍተው ካፈሩት ቤት ንብረታቸው ላይ እየደረሰ ያለውን ማንኛውንም ማፈናቀል እና የዜግነት መብት ጥሰቶች አጥብቀን እናወግዛለን።
  2. በልማትና ህግ ማስከበር ሽፋን የሚደረጉ ኢሰብአዊ ማፈናቀሎች እንዲቆሙ እንጠይቃለን። ለልማት ተፈላጊ ቦታዎች ዜጎችን በማፈናቀልና ጎዳና ላይ በመበተን ሳይሆን በዓለም ዙሪያ እንደሚተገበረው በህጋዊ መንገድ ተመጣጣኝ ካሳ በመስጠት፣ ሌላ ተተኪ የመኖሪያ ቦታ በማዘጋጀትና ከልማቱም ተጠቃሚ የሚሆኑበትን አሰራር በማመቻቸት መሆን ይኖርበታል። ይህ ሁሉ ባልሆነበት ሁኔታ የሚደረጉ ማፈናቀሎች ትልቅ የሰብአዊ መብት ጥሰት ስልሆኑ አጥብቀን እንቃወማለን። ይህንንም ተግባር የሚፈጽሙ የመንግስት ሀላፊዎችና የድርጊቱ ተባባሪዎች በህግ ተጠያቂ የሚሆኑበት አግባብ እንዲመቻች እንጠይቃለን።
  3. ለዘመናት በመተሳሰብና በጋራ የኖረውን ኢትዮጲያዊ፣ጎሳ ተኮር የሆነ የጥላቻን መንፈስ በመስበክ ህዝብን ለከፋ እልቂት ለመዳረግ በፖለቲካ ስም የሚንቀሳቀሱ ግለሰቦችንና ተቋማትን መንግስት በህጋዊ መንገድ ለሚፈፅሙት ሃገርን ጎጂና ህገ ወጥ እንቅስቃሴ መጠየቅም እንዳለ እንዲያሳይ እንጠይቃለን።
  4. አዲስ አበባንም ሆነ ሌሎችን የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች በስብጥር የሚኖሩባቸውን ትላልቅ የኢትዮጵያ ከተሞች የአስተዳደርና የባለቤትነት ጥያቄ በተመለከተ የሚነሱ ጥያቄዎች የሁሉንም ነዋሪዎች ፍላጎቶችና ጥቅሞች ባማከለ መንገድ ሊፈቱ የሚችሉት በስሜትና በሆይሆይታ ወይንም በጉልበት አለኝ አመንክዮ ሳይሆን ከትክክለኛው የፌደራሊዝም ፅንሰ ሃሳብ ትግበራ ጋር ተያይዞ በጣም በብዙ ሃገሮች ላይ ከተተገበሩ አዎንታዊ ልምዶች ትምህርት በመውሰድ ከሚዘረጋ ለሁሉም ያገሪቱ ዜጎች ፍትሃዊ ከሆነ አሰራር ነው ብለን እናምናለን። በነዚህ ከተሞች ላይ ለብቻው የባለቤትነት መብት ሊኖረው የሚችል አንድ ግሩፕ ሊኖር እንደማይችልና፣የዚህ አይነቱ አመለካከት በሕዝቦች አብሮነት ላይ ከሚፈጥረው አሉታዊ ተፅዕኖ በመነሳት አጥብቀን የምንቃወመው መሆናችንን እንገልጻለን።
  5. ዜጎች ተፈጥሮሃዊና ህገ መንግስታዊ መብታቸው ተከብሮ ከቦታ ቦታ በነጻነት የመንቀሳቀስ፣ በመረጡበት ስፍራ የመኖር፣ የመስራትና ንብረት የማፍራት መብታቸው መጠበቅ አለበት። ሁሉም ሕዝባችን መንግስት ይህን የዜጎቹን ደህንነት የመጠበቅ ግደታውን በአግባቡ ለመወጣትና መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ያለ ምንም ስጋት በሃገሩ በነጻነት የመኖር ዋስትናው እንዲረጋገጥለት በሚያደርገው ጥረት ሙሉና ልባዊ ድጋፍና ትብብር እንዲያደርግ አበክረን እንጠይቃለን።
  6. ወጣቶቻችን ማስተዋል የሚገባቸው አብዛኛው ህዝብ ዘሩ ሳይለይ በመሠረታዊ የሕክምና ግልጋሎት እጦት ህይወቱ የሚቀጠፍባት፣ ሊያጣሉን የሚከጅላቸው ከተሞቻችን በአየር ብከላ ምክንያት ገና እንደ ልብ ንጹህ ዓየር እንኳ የማይተነፈስባቸው፣ ብዙ ህፃናት ዘራቸው ሳይለይ በህፃናት መዋያና በጥሩ ትምህርት ቤቶች ታንፀው የማድግ ዕድል ያልተረጋገጠባት አገር እንዳለችን ነው። ይህንን ዕውነታ ለመለወጥ ጥሩ አለም አቀፋዊና አገራዊ ድባብ በሚስተዋልበት በዚህ የታሪክ አጋጣሚ አጣናና መትረየስ እየተሸከሙ ከተማ ማጥለቅለቅ ሃገራት የሚያነጥፉላቸውን ቀይ ምንጣፍ ከሚያማርጡ ስራና ሃብት ፈጣሪ ኢንቨስተሮች ዘንዳ የመመርጥ እድል አሳጥቶ የሕዝባችን የሰቆቃ ኑሮ እንዲራዘም ከማድረግ ውጪ የሚያመጣው ፋይዳ እንደሌለ ነው። የራሳችሁም የወደፊት ዕድል ሠላሟ ከተጠበቀ፣ የተረጋጋ ኑሮ፣ የትምህርትና የሥራ ዕድል ልትፈጥር ከምትችል ሃገር ጋር እንደሚቆምና እንደሚወድቅ በነገሮች ሁሉ ላፍታም እንዳትዘንጉት እንመክራለን።

ፈጣሪ ኢትዮጵያና ሕዝቦቿን ይባርክ!!!

ኢትዮጵያ ሃገራችን ለዘላለም ትኑር!!!

በኑረንበርግ የኢትዮጵያውያን ባህል ማህበር (ኮሚኒቲ)