April 9, 2019

ከወደ አጣዬ የሚሰማው;

ትላንት አንድት ዘመዴ ደውላ አጣዬ እየተፈፀመ ስላለው ዘግናኝ ድርጊት አረዳችኝ። እሷ የነገረችኝን እንደወረደ ለመቀበል ተቸገርኩና ለእሷ መረጃውን የሰጣትን ሰው ስልክ ቁጥር እንድትሰጠኝ ጠይቄያት ከጥቃቱ የተረፈች ሴት አናገርኩ።

ሴትዮዋ እንዳለችኝ ኦሮምኛ ቋንቋ የሚናገሩ; ገጀራን ጨምሮ የተለያዩ ተተኳሽ መሣሪያዎችን የያዙ አስፈሪ ሰዎች ቤት ለቤት እየዞሩ ወንዶችን ይሰበስቡ ነበር። እነሱ የሚኖሩበት ሰፊ ግቢ ውስጥ ወደ 50 የሚሆኑ ሰዎች ይኖሩ ነበር። ወንዶቹን ለይተው በማስወጣት በኦራል መኪና ጭነው እንደወሰዷቸው ነግራኛለች።

በዚህ መሐል አንዲት አቅመ-ደካማ ሴት ሀፃን ወንድ ልጃቸውን “አትውሰዱብኝ” ብለው በመማፀናቸው እሳቸውንም ህፃኑንም በጥይት እንደገደሏቸው ሴትዮዋ ሳግ እየተናነቃት ነግራኛለች። በኋላ የፌዴራል ፖሊሶች መጥተው ሴቶቹን ወደሌላ ሰፈር ሲወስዷቸው ሟቾቹን አንሶላ አልብሰዋቸው እንደሄዱ የነገረችኝ እያለቀሰች ነው።

አሁን ያሉበትን ሁኔታ ስጠይቃት መጀመሪያ የተወሰዱበት ሰፈርም ሰላሙ አስተማማኝ ስላልሆነ ሆስፒታል ግቢ ውስጥ እንዳስቀመጧቸውና የሞቱ ሰዎች አስክሬንም ወደሆስፒታል እየመጣ መሆኑን ነግራኛለች። ሴትዮዋ እንደነገረችኝ በከተማው ውስጥ የሚገኝ ንብረት በሙሉ ከየቤቱ ስለተዘረፈ ለጊዜው ሆስፒታል ውስጥ የተጠለሉት ሰዎች የሚበሉትና የሚጠጡት ነገር የላቸውም።

አሁን ለጊዜው የተኩስ ድምፅ የማይሰማ ቢሆንም ሁኔታው አስፈሪ መሆኑን ሴትዮዋ አስረድታኛለች። በዚህ አስፈሪ ሁኔታና ሥጋት ውስጥ ያለችው ሴትዮ የመከላከያ ሠራዊት ከጥቃት ሊታደጋቸው እንዳልቻለ በቁጭት ትናገራለች።

ሴትዮዋ በዐይኗ ያየችውን ብቻ ነው የነገረችኝ። ሴቶቹ የፌዴራል ፖሊሶች እስከሚመጡ በነበሩበት ግቢ ውስጥ ተዘግቶባቸውና ታግተው ስለነበር በከተማው ውስጥ የሆነውን ነገር ሙሉ በሙሉ አላየችም። ስለሆነም ይህ መረጃ በአጣዬ ስለሆነውና እየሆነ ስላለው ነገር የተሟላ ሥዕል አይሰጥም።

* * *
በዚህ መሐል ዶ/ር አብይ አህመድ በትናንትናው ዕለት በተዘከረው የሩዋንዳ የዘር ፍጅት የተፈፀመበት 25ኛ ዓመት ሥነ-ሥርዓት ላይ ተገኝተው ማምሻውን ወደ አዲስ አበባ መመለሳቸው ተዘግቧል።

ለመሆኑ ዶ/ር አብይ አገርና ህዝብ እየመራ ነው?

* * *

ሌላው አሳዛኝ ነገር “በእከክልኝ ልከክልህ” የተደራጀውና ጥግ ጥጉን የሚሄደው mainstream media ተልዕኮና ተግባሩ ምን እንደሆነ ግልፅ አይደለም።