April 9, 2019

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 01፣ 2011 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በአማራ ክልል ኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር እና በሰሜን ሸዋ ዞኖች ጥቃት በፈፀሙ ታጣቂ ሃይሎች ላይ መንግስት የማያዳግም እርምጃ እንደሚወስድ በጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት የፕሬስ ሴክሬታሪ አቶ ንጉሱ ጥላሁን ተናግረዋል።

አቶ ንጉሱ ጥላሁን ጉዳዩን አስመልክቶ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ባደረጉት ቆይታ የፌዴራልና የክልል የፀጥታ አካላት አካባቢውን ለማረጋጋትና ነዋሪዎቹን ለመታደግ ተመጣጣኝ ህጋዊ እርምጃ እንዲወሰድ ትዕዛዝ ተላልፏል ብለዋል።

ከዚህ ባለፈም ጉዳዩን በዝርዝር አጣርቶ ለቀጣይ እርምጃ በሚያመች መልኩ የሚያጣራ ከፌደራልና ከክልሉ የተውጣጡ አባላትን ያካተተ አንድ ቡድን ተቋቁሞ ወደ ስራ መግባቱን አንስተዋል።

ከትናንት በስቲያ ከፍተኛ ችግር ተስተውሎባቸው የነበሩት ኬሚሲ፣አጣዬ እና ማጀቴ የመሳሰሉት አካባቢዎች በትናንትናው ዕለት አንፃራዊ መረጋጋት የታየባቸው መሆኑንም ተናግረዋል።

በአካባቢው ሰላማዊ ነዋሪዎች ላይ የታጠቁ ሃይሎች ጥቃት ማደረሳቸውን ተከትሎም የደብረ ብርሃን ከተማና የአካባቢው ነዋሪዎች ድርጊቱን በሰላማዊ ሰልፍ ማውገዛቸውን አክለዋል።

የአካባቢው ነዋሪዎችና የመንግስት አመራሮች በድርጊቱ መቆጣታቸውን ለማወቅ ችለናል ያሉት አቶ ንጉሱ፥ በሰላማዊ ዜጎች ላይ ጥቃት የፈፀሙ ፣ያቀናበሩና ያስተባበሩ አካላት ላይ መንግሰት የማያዳግም እርምጃ የሚወስድ መሆኑን ነዋሪዎች ሊገነዘቡ ይገባል ብለዋል።

ለዚህም ማህበረሰቡ በድርጊቱ የተሳተፉና ያስተባበሩ አካላትን አሳልፎ በመስጥት በኩል የራሱን ሃላፊነት እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል ።

በሌላ በኩል ግጭቱን በአማራና ኦሮሞ ህዝቦች መካከል የተፈጠረ በማስመሰል የሚሰሩ አካላት በመኖራቸው ህብረተሰቡ እንደዚህ አይነት ጉዳዮችን በአንክሮ መከታተል እንዳለበት አሳስበዋል።

መንግስትም የሁለቱ ህዝቦች የዘመናት አብሮ የመኖር ባህልን በመጋፋት መቃቃቅርን ለመፍጠር ብሎም ወደ ግጭት ለመውሰድ የሚሰሩ አጥፊ ሃይሎችን ከማህበረሰቡ ጋር በመተባበር አስተማሪ የሆነ እርምጃ ለመውሰድ በጥንካሬ ይሰራል ነው ያሉት።

ክስተቱን ተከትሎ በማህበራዊ የትስስር ገጾች ላይ ግጭቱ በአማራ እና በኦሮሞ ብሄሮች መካከል የተፈጠረ ተደርጎ የሚሰራጫው መረጃም መሰረተ ቢስና ሃላፊነት የጎደለው ነው ብለዋል።

ስለሆነም በማህበራዊ የትስስር ገጾች የህዝቦችን ማህበራዊ ኑሮ የሚያናጉ የሀሰት መረጃዎችንና የጥላቻ ንግግሮችን የሚያሰራጩ አካላት ከእኩይ ድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አሳስበዋል።/

FBC