ሳር በእሳት ሲቃጠል

እ.ኤ.አ በ1978 በዩኔስኮ የዓለም ቅርስነት የተመዘገበው የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ውስጥ ከሳምንት በፊት እሳት ተነስቶ መቆጣጠር መቻሉ ይታወሳል።

በድጋሚም በትናንትናው ዕለት በፓርኩ ውስጥ እሳት ተነስቷል።

እሳቱ ከፍተኛ በሚባል ደረጃ ትላንት ከሰዓት በኋላ መጀመሩን የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ የህብረተሰብ እና ቱሪዝም ኃላፊ አቶ ታደሠ ይግዛው ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

እሳቱን ለመቆጣጠርም የአካባቢው ህብረተብ፣ የክልሉ ልዩ ኃይል እና የመከላከያ ሠራዊት አባላት በጋራ እየሰሩ ነው ብለዋል።

“በሙጭላ በኩል ወደ ገደሉ በመውረዱ እሳቱን መከላከል አልተቻለም። ገደል በመሆኑም ለመከላከል አዳጋች አድርጎታል። ሜዳማውን ክፍል ተቆጣጥረነዋል። ንፋስ እና ጸሐይ ሲኖር ካልተነሳ በአሁኑ ሰዓት ጋብ ያለ ይመስላል” ሲሉ ገልጸዋል።

የሰሜን ተራሮች ፓርክ እሳት ሙሉ በሙሉ አልጠፋም

እሳቱ የተነሳበት ምክንያት አለመታወቁን የሚናገሩት ኃላፊው ከሳምንት በፊት የተነሳውንም ሆነ አሁን የተቀሰቀሰውን እሳት መንስዔ ለማወቅ ጥናት እየተደረገ ይገኛል ሲሉ ይናገራሉ።

አክለውም እሳቱ ፓርኩን ከዓለም ቅርስ መዝገብ ውጭ የሚያደርግ ስጋት አለመፍጠሩን አስታውቀዋል። ለዚህ ደግሞ በምክንያትነት ያቀረቡት በእሳቱ ጉዳት የደረሰበት የፓርኩ ሣር ብቻ መሆኑን ነው።

“አሁን ከተቃጠለው አንድ ሶስተኛ የሚሆነው ሳር ነው። ዛፎች ካሉበት እሳቱ የገባው ትንሽ ቦታ ነው። ሣር ደግሞ ዝናብ ሲጀምር ስለሚመለስ በዓለም ቅርስነቱ ላይ ተጽዕኖ ይኖረዋል ብዬ አላስብም። ስለዚህ ከዓለም ቅርስነት ውጭ ይሆናል የሚል ስጋት የለንም። በዱር እንስሳት በኩልም አንድም ጉዳት አልደረሰም።” ብለዋል።

በሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ከዚህ ቀደምም እሳት የተነሳ ሲሆን እንዳሁኑ ግን ስፋት `ያለው አልነበረም።

ተያያዥ ርዕሶች