April 11, 2019
Source: https://mereja.com

‹‹የኦሮሞንና የአማራን ሕዝብ በማጋጨት የከፋ ሁኔታ እንዲኖር ለማድረግ ታቅዶ የተፈፀመ ይመስላል፡፡››
‹‹በተደራጀ አግባብ የተንቀሳቀሰ አካል አጥንቶ ሕዝብ ላይ ጉዳት አድርሷል››፡፡አቶ ንጉሱ ጥላሁን
በኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ከሰሞኑ የተነሳው ግጭት ወደ ስፍራው በገባው የፀጥታ ኃይል እና በአካባቢው ማኅበረሰብ ድጋፍ ቢረጋጋም ለጉዳዩ ዘላቂ እልባት እስካልተሰጠው ድረስ ከስጋት ነፃ መሆን እንደማይችሉ ነው ያነጋገርናቸው የከሚሴ ነዋሪዎች የተናገሩት፡፡
ከሚሴ ለዘመናት ሙስሊም ከክርስቲያን፣ ኦሮሞ ከአማራና ከአርጎባ፣ ቄስ ከቃልቻ ተከባብረው እና ተቻችለው የሚኖሩባት ከተማ መሆኗን የከተማዋ ነዋሪዎች አስታውሰው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ይህንን ውብ አብሮ የመኖር እሴትና አንድነት የሚፈታተኑ አደጋዎች ገጥመዋታል ብለዋል፡፡
የተፈጠረው ችግር የሕዝብ ግጭት አለመሆኑን የሚስማሙት አስተያየት ሰጭዎቹ፤ ለችግሩ ምክንያት ናቸው የሚሏቸው አካላት ከወረዳ እስከ ቀበሌ ድረስ ያሉ የመንግሥት አመራሮች እና የተለየ ድብቅ ዓላማ ያላቸው ቡድኖች እንደሆኑ ይስማማሉ፡፡
‹‹የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ሊፈርስ ነው፤ ለዘመናት ዕውቅና ያገኘው ማንነታችሁም አደጋ ውስጥ ሊገባ ነው›› የሚል አሉባልታ በሰፊው መናፈሱ ለግጭቱ መንስኤ መሆኑን የከተማዋ ነዋሪ መልአከ ገነት ደጀን ተስፋዬ ተናግረዋል፡፡ ‹‹አመራሩም የአሉባልታ ሰለባ ሆኗል›› ነው ያሉት፡፡
ወጣት ተሾመ ጥላዬ ደግሞ ‹‹ለተፈጠረው ግጭት አመራሩ ምክንያት እና ተሳታፊ በመሆኑ የክልሉ እና የፌደራል መንግሥታት በአግባቡ ሊመረምሩት ይገባል›› ብሎናል፡፡
የከሚሴ ከተማ ነዋሪው ሀጅ ሰኢድ ሙሐመድ እንዳሉት ደግሞ የተፈጠረው ግጭት የፖለቲካ ኪሳራ የደረሰባቸው ኃይሎች ሆን ብለው ያደራጁት እና የለኮሱት እሳት ነው፡፡ ‹‹ግጭቱ በአጭር ጊዜ ውስጥ በርካታ የሰው ሕይወትና ንብረት ሳያጠፋ በቁጥጥር ስር ማዋል የተቻለውም ሕዝብ አምኖና
