April 13,2019
Source – Fana

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 05 ፣2011 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ላይ እየደረሰ ያለውን የእሳት ቃጠሎ ለመቆጣጠር ባለ ድርሻ አካላት ፈጣን ምላሽ እንዲሰጡ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር አምባቸው መኮንን ጥሪ አቅርበዋል።
ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር አምባቸው ጉዳዩን አስመልክተው ባስተላለፉት መልዕክት የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ላይ እየደረሰ ያለውን የእሳት ቃጠሎ አደጋ ለመታደግ ከክልሉ አቅም ውጭ የሆኑ ድጋፎችን በማድረግ በኩል ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ሁሉ ጊዜ ሳይሰጡ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።
የክልሉ መንግሥት ከፌዴራል መንግሥት ጋር በጋራ እየሠራ ቢሆንም ምላሹ ፈጣን አልሆነም፤ አሁንም ግን ጥረታችን ቀጥሏል ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፡፡
የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ የኛ ብቻ ሳይሆን የዓለም ሀብት ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳደድሩ፥ በተለያዩ ጊዜያት ፓርኩ የተለያዮ ጉዳቶችን ቢያስተናግድም አሁን እየደረሰ ያለው የቃጠሎ ጉዳት ግን ዓድማሱን ያሰፋ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የክልሉ መንግሥት የሚችለውን ሁሉ ጥረት ቢያደርግም በሰው ኃይል መቆጣጠር የማይቻልበት ደረጃ ላይ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
የእሳት ቃጠሎውን በአነስተኛ ሰው እና የመሣሪያ ድጋፍ ለማጥፋት ጥረቶች ቢደረጉም ቃጠሎውን ማጥፋት የማይችልባቸው ቦታዎች ላይ በመድረሱ ከፍተኛ ስጋት መፍጠሩን ነው ርዕሰ መስተዳድሩ የተናገሩት፡፡
ከፌዴራል መንግሥት ጋር በጋራ እየተሠራ ቢሆንም ምላሹ ፈጣን አልሆነም ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ መምጣት ያለባቸው ማሽኖች ሁሉ በፍጥነት እንዲመጡ ከፌዴራል መንግሥት ጋር ጥረት መቀጠሉን ገልጸዋል፡፡
የእሳት ማጥፊያ አውሮፕላኖች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ ማድረግ ጊዜ የሚሰጠው አለመሆኑን ያስታወቁት ዶክተር አምባቸው የመንግሥት አካላት ፈጣን ውሳኔ እንዲያሳልፉም አሳስበዋል ፡፡
የዓለም ትልቁ ሀብት የሆነው የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ሀብቱን እያጣ ነው፤ ከሆነ ወዲያም ሙሾ አውራጅ እንዳንሆን ከክልሉ አቅም ውጭ የሆኑ ድጋፎችን በማድረግ በኩል ሁሉም ባለድርሻ አካላት ሁሉ የበኩላቸውን ጊዜ ሳይሰጡ እንዲሠሩ ርዕሰ መስተዳድሩ ዶክተር አምባቸው መኮንን ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡
በተፈጥሮ አደጋው ላይ የደረሰው ጉዳት ሰፊ መሆኑን ያነሱት ርዕሰ መስተዳደሩ አደጋውን ለመታደግ እየተሳተፉ ያሉትን ሁሉ በክልሉ መንግሥትት ስም አመስግነዋል፡፡
ምንጭ ፦አብመድ
