ፍልሚያ በከሚሴና ሰሜን ሽዋ
ህዝቡ ቤቱን እየለቀቀ ወደ ተራሮች ሸሽቷል
መከላከያ “ትዕዛዝ አልተሰጠኝም” ብሎ ተመልካች ነበር
የመከላከያ ደምብ ልብስ የለበሱ በርካታ ሰዎችን ገድለዋል
ጥቃት አድራሾቹ የኦነግ ታጣቂዎች ናቸው”
አንድ ሽማግሌ ታርደዋል፣ ሴቷ ታግተው ጠፍተዋል
ባልታጠቀ ህዝብ ላይ መትረየስ ተተኩሷል
በኃይማኖት ተቋማት ላይ ቦምብ ተወርውሯል
እውነት፣ ሚዛናዊነት፣ ፅናት፣ ህዝባዊነት2ሚያዝያ 6 ቀን 2011 ዓ.ም 1ኛ ዓመት ቁጥር 030ወደ ቀጣዩ ገጽ
የከሚሰው ጥቃት
በከሚሴና በሰሜን ሽዋ ሰሞኑን በተፈጸሙ ጥቃቶች ለብዙዎች ሞትና መፈናቀል፣ እንዲሁም ለንብረት ውድመት ምክንያት የነበረው ግጭት የተነሳው፣ ሆን ተብሎ በተሰራጨ ሀሰተኛ ወሬ ነው እየተባለ ይገኛል:: ባሳለፍነው ሳምንት መግቢያ ላይ ሲናፈስ የነበረው ወሬና አሉባልታ፣ የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር የሆነው የከሚሴ ዞን ሊፈርስ ነው የሚል ይዘት ነበረው:: ከዚህ አሉባልታ በተጨማሪም፣ በአካባቢው ካለው ኃይማኖታዊ ሰላምና መከባበር በተፃራሪ፣ የእስልምና ተከታዮች ሊጨፈጭፉ ነው የሚል ሀሰተኛ ወሬ ሲናፈስ ነበር:: እነዚህ አሉባልታዎች በማህበራዊ ሚዲያዎች ብቅ ጥልቅ እያሉ ከሰነበቱ በኋላ፣ ውጥረቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያየለ ሄዶ፣ ረብዕ ማለዳ በገጠር አካባቢዎች ከፍተኛ ተኩስ ሊቀሰቀስ ችሏል:: እንደ አካባቢው ነዋሪዎት አገላለፅ፣ በደዌ ሃረዋ ወረዳ ለተቀሰቀሰው ግጭት አሉባልታው ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል:: ግጭት የተቀሰቀሰበት አካባቢ ከአፋር ክልል የሚያዋስን በመሆኑና፣ ከዚህ በፊትም አልፎ አልፎ ግጭት የሚነሳበት በመሆኑ፣ የአማራ ልዩ ኃይል በአካባቢው ይንቀሳቀስ እንደነበር ነዋሪዎቹ ይናገራሉ:: ከግጭቱ በፊትም ቢሆን፣ በአካባቢው መንደር የሚያቃጥሉና የህዝብን ሰላማዊ እንቅስቃሴ የሚያሰናክሉ ኃይሎች ስለነበሩ፣ ልዩ ኃይሉ እነሱን እንዲቆጣጠር ትዕዛዝ ተሰጥቶት በእንቅስቃሴ ላይ ነበር:: በዚህ ድባብ በአካባቢው ሲንቀሳቀስ የቆየው ልዩ ኃይል ረብዕ ወደ ገጠር አካባቢዎች ሲገባ፣ አየር ላይ በነበሩ አሉባልታዎች በተደናገሩ የአካባቢው ታጣቂዎች ተኩስ ተከፍቶበታል:: በዚህ ሁኔታ ግጭቱ መባባሱን ነዋሪዎች ይናገራሉ:: እንዲሁም፣ ልዩ ኃይሉ አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ባንዲራ በመያዙ የተበሳጩ በከሚሴ ገጠራማ አካባቢዎች የሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች ተኩስ ከፍተውበታል የሚል ወሬም በመሰማቱ፣ ለግጭቱ መባባስ አስተዋፅኦ ማበርከቱ እየተነገረ ይገኛል:: በዚህ መልክ በተነሳው የተኩስ ልውውጥ፣ የ4 ሰዎች ህይወት ማለፉን የክልሉ ቃል አቃባይ አቶ አሰማኸኝ አስረስ ተናግረዋል:: ቃል አቀባዩ፣ ከሟቾቹ መካከል የልዩ ኃይል አባላት እንደነበሩበት፣ 5 ሰዎች ደግሞ የመቁሰል አደጋ ደርሶባቸው በደሴ ሆስፒታል ህክምና ላይ እንደሚገኙ ገልፀዋል:: በግጭቱ ህይወቱ ያለፈ የአንድ የፀጥታ ባልደረባ የቀብር ስነ–ሥርዓት በደሴ ከተማ መጠነኛ ግርግር አስነስቶ የነበረ ሲሆን፣ ለተቃውሞው መንስኤ የሆነው ግጭቱ የሚዲያ ሽፋን አላገኘም የሚል ቁጣ እንደነበር ታውቋል:: እንደተባለውም፣ የኢትዮጲስ ዝግጅት ክፍል ባደረገው ማጣራት፣ ማክሰኞ ተቀስቅሶ ረብዕ የተባባሰው ይህ ግጭት፣ እስከ አርብ ድረስ በሚዲያ እንዳልተዘገበ ማረጋገጥ ችሏል:: ይህ ረብዕ የተባባሰው ግጭት፣ ሀሙስ ዕለት እየቀነሰ ሄዶ፣ አርብ ዕለት አንፃራዊ ሰላም ሰፍኖ መዋሉን የአካባቢ ነዋሪዎች ተናግረዋል:: ስለጥቃት አድራሾቹ ማንነት፣ የክልሉ ባለስልጣን አቶ ገደቤ ለመገናኛ ብዙሃን በሰጡት ማብራሪያ፣ “ራሱን በስውር ያደራጀ ያልታወቀ ቡድን” እንደነበርና፣ “ይህም ፀረ ሰላም ኃይል ማን እንደሆነ እያጣራን ነው:: ነገር ግን፣ በህቡዕ በተደራጀ መንገድ የሚንቀሳቀሱ የኦነግ አባላት ያሉ ነው የሚመስለው” ብለዋል:: ይህ ቡድን የተደራጀና የቡድን መሳሪያዎች የያዘ እንደነበረም አክለዋል::
ከኦነግ ጋር የተነሳው ውዝግብ
ግጭቱ አርብ ላይ የቆመና የተፈታ ቢመስልም፣ አቶ ገደቤ ግን በሰጡት አስተያየት፣ ሰላም መጥቷል ማለት እንደማይቻል፤ ስራ እንደሚጠይቅ፤ የልዩ ኃይሉን ስምሪት እንደገና በማየትና ፈትሾ በማስተካከል፣ በህብረተሰቡ ዘንድ ያለውን ስጋት ለመቀነስ መስራት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል:: ከነበረው ሁኔታ አኳያ፣ አለመረጋጋቱ ወደ ሰሜን ሸዋ አካባቢዎችም ሊከሰት እንደሚችል አስቀድመው ጠቁመዋል:: የግጭት አነሳሾቹን ማንነት አስመልክተውም በሰጡት አስተያየት፣ “አካባቢውን ለማተራመስ አጀንዳ ያለው፣ ከኦነግ አባላት ጋር ትስስር ያለው ቡድን እንደሆነ እያየን ስለሆነ፣ ለወደፊት ሊጣራና ሊገመገም ውጤቱ ይታወቃል” ብለዋል:: ለአቶ ገደቤና ለሌሎች የክልሉ ባለስልጣናት ወቀሳዎች ምላሹን በማህበራዊ ድህረ–ገጽ መግለጫ የሰጠው የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ፣) ‹‹ የራስን ጥፋት ለመደበቅ የኦነግን ስም ማጠልሸት ከተጠያቂነት አያስመልጥም ፤ አሁንም ቢሆን ሰላማዊ ትግል ላይ ነን፤ የአማራ ልዩ ኃይሉ ተግባር የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደርን በማፍረስ ወደ ሌላ ዞን ለመቀላቀል የሚደረግ የድንበር ማስፋፋት ነው ብለን እናምናለን›› በማለት “ተጠያቂው የክልሉ መንግስት እንጂ፣ እኛ አይደለንም “ብሏል:: “ክልሉ ግንባሩን ከመክሰስና የህዝቡን ሰላም ከማናጋት ሊቆጠብ ይገባዋል” ያለው ኦነግ፣ የፌዴራል መንግስቱ ችግሩ ወደ ሌላ አቅጣጫ እንዳይሄድ ቁጥጥር እንዲያደርግ ጠይቋል:: ግንባሩ ይህን የጠየቀው የሰሜን ሸዋው ግጭት ከመቀስቀሱ በፊት ነበር::
የሰሜን ሽዋው ጥቃት
ቅዳሜ መጋቢት 28 የከሚሴው ግጭት ወደ አጎራባቹና የሰሜን ሽዋ ኤፍራትና ግድም ወረዳ የተሸጋገረ ሲሆን፣ የአይን እምኞች እንደገለጹልን ታጣቂዎቹ ገና ወደ ኤፌሶን/ አጣዬ ሲዘልቁ፣ ተራራ ላይ መትረየስ ጠምደው ወደ ህዝቡ ተኩስ መክፈታቸው ድንጋጤ ፈጥሯል::የተከፈተውን ድንገተኛ ጥቃት በጥይት ማነስ ሳቢያ ማስቆም ባለመቻሉ፣ ለመከላከል ሲሞክሩ የነበሩ የፀጥታ ኃይሎችና ሚሊሻዎች፣ እንዲሁም ሰላማዊ የከተማዋ ነዋሪዎች በአሰቃቂ ሁኔታ ህይወታቸውን አጥተዋል:: በዚህ ሁኔታ በሰሜን ሽዋ በተቀሰቀሰው ግጭት ከ40 የማያንሱ ሰዎች መገለዳቸውን የከተማዋ ነዋሪዎች ነግረውናል:: አንዳንዶች ደግሞ፣ ቁጥሩን ከ50 በላይ ያደርሱታል:: በሰሜን ሽዋ ጥቃት ከፈፀሙት መካከል በግምት ሦስት መቶ የሚሆኑ መገደላቸውን፣ አስከሬናቸውም በአይሱዙ ተጭኖ መጓጓዙን የአካባቢው ነዋሪዎች ለኢትዮጲስ ጋዜጣ ገልፀዋል:: በተፈጠረው ትርምስም የነዋሪው ስጋት በመጨመሩ ቀዬውን እየለቀቀ መሰደዱን በምስል ጭምር የታገዘ መረጃ ሲሰራጭ ሰንብቷል:: ህዝቡ ከተማ ያለውን ቤት እየለቀቀ ወደ ገጠራማ ቦታዎችና ወደ ተራራ ሸሽቷል:: ጥቃት አድራሾቹ ካጠፏቸው የሰው ህይወቶች ባሻገር፣ የንብረት ውድመትና ዘረፋ ፈፅመዋል:: እንዲሁም፣ ሰውእንዳገቱ፣በተጨማሪም ቤተክርስቲያናት ላይ ቦምብ መወርወራቸውና ቃጠሎ ማድረሳቸው ታውቋል:: በሰሜን ሽዋ ይህንን ጥፋት ያደረሱት ኦነግ ያደራጃቸው ቡድኖች መሆናቸውን፣ ዓላማቸውም ሽብር ፈጥሮ ዝርፊያ መፈፀም እንደ ነበር ሲሉ የዞኑ ኃላፊዎች ለመገናኛ ብዙሃን ገልፀዋል:: የአጣዬ ከተማ ከንቲባ፣ በታጠቁት ኃይሎች የተካሄደው ጥቃትና ዘረፋ ከክልሉ ልዩ ኃይል አቅም በላይ ስለነበር በነጋታው መከላከያ ወደ ከተማዋ እንዲገባ ተደርጓል ብለዋል:: ከቤተክርስቲያናት ሌላ የንግድ ተቋማትና መኖሪያ ቤቶች የጥቃት አድራሾቹ ዒላማ እንደነበሩ የከተማዋ ነዋሪዎች ተናግረዋል:: በአጣዬ ከተማ ጥቃቱ ሲፈፀም የነበሩና የኢትዮጲስ ዝግጅት ክፍል ያነጋገርናቸው አንድ የአይን እማኝ፣ ታጣቂዎቹ ከስድስት ወራት በፊት በከተማዋ አቅራቢያ በሚገኝ ጫካ ውስጥ ሲሰለጥኑ የነበሩ ሲሆን፣ ነዋሪው ለከተማዋና
ለዞኑ ኃላፊዎች ሲጠቁም፣ “ለበላይ አመልክተናል” የሚል ምላሽ እንደተሰጠው ገልፀውልናል:: ጥቃቱ በከተማዋ የተሰነዘረበት ዕለት፣ የቅዳሜ የገበያ ቀን ስለነበር፣ ነዋሪው ሳይታጠቅ ተዘናግቶ እንደነበርና፣ ጥቃት አድራሾቹ አካባቢውን ድንገት ከበው፣ በጉብታ የጠመዱትን መትረየስ በእሩምታ በመተኮስ ከባድ ጉዳት ለማድረስ ችለዋል:: አንዳንድ የከተማው ነዋሪዎችና ሚሊሻዎች አፀፋውን በተኩስ ቢመልሱም፣ የነበራቸው ጥይት አነስተኛ ስለነበር፣ መቋቋም አቅቷቸው ብዙዎች ህይወታቸውን እንዲያጡ ሁኔታዎች ምቹ ሆነዋል::
በኦራል የተጫነና የመከላከያ የደንብ ልብስ የለበሰ አጥቂ ኃይል
በቀጣይ፣ በተከላካይነት ለተሰለፉት ከመንግስት አካል ጥይት እንዲሰጥ ተጠይቆ እምቢ መባሉን የነገሩን እኚህ ነዋሪ፣ ከሞላ ጎደል ባዶ እጃቸውን ቅዳሜን ሲዋጉ መዋላቸውና ዋናው መንገድ መዘጋቱን ገልፅውልናል:: በዚያን ዕለት ከየትኛውም አቅጣጫ የሚረዳቸው ኃይል ሳይደርስላቸው እንደቀረም ይናገራሉ:: በዚህ ሁኔታ ውስጥ እያሉ፣ ከምሽቱ 3 ሰዓት ላይ የጣለው ከባድ ዝናብ ትልቅ እረፍት እንደሰጠና ከፍተኛ መተላለቅን እንዳስቀረ ይናገራሉ::ቅዳሜ ዕለት በነበረው ውሎ፣ በውጊያው መሀል በአንድ ኦራል (የጭነት መኪና) “ልዩ ኃይል መጣ” ተብሎ የነበረ ቢሆንም፣ በተግባር ግን ጥቃት አድራሹ ኃይል (“ የኦነግ ኃይል” ነው ብለው ነው የገለፁት ነዋሪው) ሆኖ ተገኝቷል:: “ብዙ ነዋሪም የሞተው በዚህ የመከላከያ የደንብ ልብስ በለበሰ ኃይል ነው” ብለውናል እማኙ:: ኦራሉ ይህን ዜና እስካዘጋጀንበት ወቅት እየተፈለገ እንደሆነም ሰምተናል::የነዋሪውን ጥቃትና የጥይት እጥረት የቀረፈለት፣ ከላይ ከመንዝ ግሼና ራቤ የመጣ አጋዥ ኃይል እንደሆነና፣ ይህም ኃይል በቀጣዩ ቀን በነበረው ውጊያ የሰው ህይወት ለማትረፍ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን እማኙ ይናገራሉ:: በጥቃቱ ሴትና እናቶች ታግተው የተወሰዱ ሲሆን፣ አንድ ፀሀይ የምትባል እንጀራ በመጋገር የምትተዳደር ሴት በጥቃት አድራሾቹ ታግታ እስካሁን ድረስ የት እንደደረሰች አይታወቅም:: ከከተማው ምክር ቤት ፊት ለፊት የሚኖሩ ጡረታ የወጡ አቅመ ደካማ ሽማግሌንም፣ ከተደበቁበት አውጥተው እንዳረዷቸው፣ በዚህም ነዋሪው ክፉኛ ማዘኑን ሰምተናል:: አንድ የራያ ተወላጅ ተታኩሶ መሰዋቱንም እማኙ ነግረውናል::
አንድ ኩንታል ጥይት
በቀጣይ ቀናትም፣ ሚያዝያ 1/2011 ዓ.ም ላይ አንድ ኩንታል ጥይትና አንድ መትረየስ ወደ አካባቢው ሊገባ ሲል ተይዟል:: እንዲሁም በአውቶቡስ ከወለጋ ተጭነው መጡ የተባሉ ወጣቶች ሸዋሮቢት ተይዘው ተለቀዋል:: እንደ እማኛችን እምነት ከሆነ፣ እንደ እነዚህ አይነት ክስተቶች፣ ጥቃቱ የተከሰተው በአጋጣሚ ሳይሆን ሆን ተብሎ ታቅዶበት የተደረገ መሆኑን ብቻ ሳይሆን፣ ወደፊትም ግጭቶች ሊከሰቱ እንደሚችል ያመላክታሉ:: በግጭቱ ሳቢያ ለተፈናቀሉት በደብረሲናና በሌሎች አካባቢዎች እርዳታ እየተሰበሰበ ሲሆን፣ መሃል ሜዳና ሞላሌ የገቡትን ስደተኞች ነዋሪው እያበላና እየረዳ ይገኛል::
“ትዕዛዝ አልተሰጠኝም”
የእሁዱን ግጭት አስመልክቶ የወረዳው ባለስልጣናት በሰጡት አስተያየት፤ ጥቃቱ ሲፈፀም በቦንብና በከባድ መሳሪያ የታገዘ እንደነበር፣ ጥቃት የደረሰውም በተደራጁና ስልጠና በወሰዱ ቡድኖች የተፈጸመ መሆኑን ተናግረዋል:: እንደነዋሪዎቹ አስተያየት በቦታው የመከላከያ ሰራዊት የነበረ ቢሆንም ‹‹ ትዕዛዝ አልተሰጠኝም›› በሚል በተፈለገው መጠን ከጥፋት እንዳልታደጋቸው በማዘን ይናገራሉ:: መከላከያ ኃይሉ ቅዳሜ ዕለት ምንም ጣልቃ ሳይገባ ከቆየ በኋላ፣ እሁድ ዕለት “ኃይሌ አነስተኛ ነው” በማለቱ፣ ተጨማሪ ኃይል ተልኮለት፣ ከቀኑ 9 ሰዓት ገደማ ተጨማሪ ኃይል ደርሶለት በአካባቢው መንቀሳቀስ በመጀመሩ ግጭቱ መቀነሱን ይናገራሉ:: እሁድ ማምሻውን በከተማ ተረጋጋ የተባለው ግጭት፣ ሰኞ መጋቢት 30ም እንደገና አገርሽቶ፣ በገጠራማ አካባቢዎች እና በመንገድ ዳርቻዎች የፀጥታ ችግር ተፈጥሯል:: ሰኞ ዕለት ማብራሪያ የሰጡት የኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስቴር ኢታማዦር ሹም ጽ/ቤት ኃላፊ ኮሎኔል ተስፋዬ አያሌው፣ በክልሉ ጥያቄ መሰረት መከላከያ ሰራዊቱ ወደ አካባቢው መግባቱንና አልፎ አልፎ ተኩስ መሰማቱንም ተናግረዋል:: ቦታው ሰፊ በመሆኑና ተጨማሪ ኃይል በማስፈለጉ አካባቢውን ሙሉ በሙሉ መቆጣጠር አለመቻላቸውንና፣ የግጭቱን መንስኤ እያጣሩ እንደሆኑ ተናግረዋል:: “በሁለቱም ወገን ያለው ታጣቂ በመሆኑ፣ የአካባቢው አመራሮች ከጉዳዩ እጃቸውን ሊያወጡ ይገባል” ብለዋል:: የኮሎኔሉ አባባል ጥቃት በደረሰባቸው በኩል ጥሩ ስሜት አልፈጠረም::
የጥይት ጉዳይ
ከኤፌሶን/አጣዬ ተነስቶ ወደ ማጀቴ ገጠራማ ክፍል በዘለቀው ግጭት፣ ተጠቂው አርሶ አደርና ሚሊሻው ራሱን ለመከላከል ሲታኮስ ጥይት አልቆበት ተጨማሪ እንዲሰጠው ቢጠይቅም፣ በቦታው በነበሩ ኃላፊዎች መከልከሉን ነዋሪዎች እማኝነታቸውን ሰጥተዋል:: በዚሁ ዕለት፣ 990 የክላሽ ጥይት በህገ–ወጥ መንገድ ከአፋር ክልል ወደ ወሎ መስመር ሲጓጓዝ፣ ሚሌ ባቲ መገንጠያ ባለው የጉምሩክ ኬላ ላይ ተይዟል:: እንደ ብዙዎች ግምት ከሆነ፣ ጥይቱ ለጥቃት አድራሾቹ የተላከ ነበር:: የሰሜን ሸዋ ዞን ኮንስታብል ሰኢድ እንድሪስ ለመገናኛ ብዙሃን በሰጡት አስተያየት፣ ለኦነግ አባላት (ለጥቃት አድራሾቹ) የሚያስታጥቁት የኦሮሞ ብሔርሰብ አስተዳደር ልዩ ዞን ባለስልጣናት ናቸው ብለዋል:: ግጭቱን ተከትሎ በደብረብርሃን ከፍተኛ ህዝብ ጎዳና ወጥቶ የተቃውሞ ድምፅ አሰምቷል:: እንዲሁም፣ በአዲስ አበባም የሚገኙ 500 የሚጠጉ የአካባቢው ተወላጆች ድርጊቱን በማውገዝ የአቋም መግለጫ አውጥተዋል:: ግድያውን አፈናውንና ዘረፋውን የፈጸሙትን መንግስት በአፋጣኝ እርምጃ ይዞ ለፍርድ እንዲያቀርባቸው፣ እንዲሁም፣ ተጨማሪ የፀጥታ አካላት እንዲመደቡ፣ በጥቃቱ የተጎዱም አፋጣኝ እርዳታ እንዲያገኙ ጠይቀዋል:: ግጭቱ ታስቦበት ታቅዶና ተጠንቶ የተደረገ እንጂ ተራ በአካባቢው የተለመደ ግጭት አለመሆኑን፣ ታጣቂዎቹ ስልጠና ወስደው፣ ግለሰብ የማይዘውን ከባድ የቡድን መሳሪያ ታጥቀው በዓላማ ነው ያጠቁት ብለዋል:: ይህን ተከትሎ፣ ሰኞ መጋቢት 30 የፌዴራልና የክልል የፀጥታ አካላት ‹‹ አስፈላጊውን ህጋዊ ተመጣጣኝ እርምጃ›› እንዲወስዱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ የፀጥታ ምክር ቤት አዟል:: ምክር ቤቱ ጥቃቱን ‹‹ ብጥብጥ›› ነው በማለት፣ እጁ ያለበት ማንኛውም አካል ተጠያቂ እንደሚሆን፣ ያነሳሱትን ለህግ ለማቅረብ ጥናት የሚያደርግ ቡደን ማሰማራቱንም አሳውቋል:: ይህን ጥቃት የፈፀሙት የኦነግ ታጣቂዎች መሆናቸውን የክልሉ ኃላፊዎችና በቦታው የነበሩ እማኞች ቢናገሩም፣ ግንባሩ ግን በድጋሚ አስተባብሎታል:: ቃል አቀባዩ አቶ ቶሌራ አዳባ፣ “በአማራ ክልል የሚንቀሳቀስ ምንም የታጠቀ ኃይል የለንም” ብለው ለዶቼቬሌ ቢናገሩም፣ የኦሮሞዎች አባ ገዳ የሆኑት አቶ በየነ ሰንበቶ፣ ከወራት በፊት በሰሜን ሸዋ ከሚሴና ከረዩ የሚገኝ የኦነግ ጦርን በማስመልከት፣ “ከአማራ ክልል ጋር እንነጋገርበታለን” ማለታቸው ይታወሳል:: የኦነግ ቃል አቀባዩ ለጥቃቱ ተጠያቂ ያደረጉት፣ አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ሰንደቅ ዓላማ የያዙ አካላት ሰንደቅ ዓላማ ይዘው ወደ አካባቢው መሄዳቸው ነው ብለዋል:: ይህ አባባላቸው፣ በከሚሴ ይንቀሳቀስ በነበረው የአማራ ክልል ልዩ ኃይል ላይ ተኩሱ የተከፈተው፣ አረንጓዴ ቢጫ ቀይ የሆነውን ሰንደቅ ዓላማ በመያዛቸው በተበሳጩ የኦነግ ታጣቂዎች ነው በማለት ነዋሪዎች የተናገሩትን የሚያረጋግጥ ሆኗል:: የኢትዮጲስ ዝግጅት ክፍል ያነጋገርናቸው የአካባቢው ነዋሪዎች፣ ከሟቾች ላይ የኦነግ መታወቂያ እንደተገኘ ታጣቂዎቹ አርማውን በተለያየ መንገድ እንደሚጠቀሙበት ለማወቅ ተችሏል:: ሚያዚያ አንድ ቀን ሰለ ወቅታዊው ሁኔታ መግለጫ ያወጣው ገዢው ፓርቲ የኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዴፓ፣) ጥቃት አድራሾቹን፣ “በህዝብ ደም የሚነግዱ የፖለቲካ ቁማርተኞች” ያላቸው ሲሆን፣ ጥቃቱን ደግሞ “በየትኛውም መልኩ ተቀባይነት የሌለው፣ ማንኛውንም ህዝብ የማይወክል” ነው ብሎታል:: “ግጭቱ የተቀሰቀሰውም ጽንፈኛ ኃይሎች ከከሰሩ የፖለቲካ ኃይሎች ጋር በመቀናጀት የለኮሱት እሳት ነው ያለው” የፓርቲው መግለጫ፣ “የህዘብ ለህዝብ ግጭት በማስመሰል፣ ችግሩ ወደ ኦሮሚያ ክልል እንዲስፋፋ በማድረግ፤ ወንድማማች ህዝብን ለማጋጨትና በእሳቱ ለመማገድ የታሰበ፣ የፖለቲካ ትርፍ ለማጋበስ አቅደው የተንቀሳቀሱበት ነው” ብሏል:: ግጭቱ እንዳይዛመት፤ ቀስቃሾቹንና ጥፋተኞቹን ለማወቅ እንዲሁም ለመያዝ ከአማራ ክልል ጋር አብሮ እየሰራ መሆኑንም አሳውቋል::
ኢትዮጲስ ጋዜጣ
