April 17, 2019

ምንጭ – ፋና

የሰሜን ተራሮችን ከእሳት አደጋ ለመታደግ ድጋፍ ላደረጉ አስራኤላዊያንና ኬንያውን ባለሙያዎች ምስጋና ቀረበ

On Apr 17, 2019172

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 9፣ 2011 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ ከእሳት አደጋን ለመታደግ ድጋፍ ላደረጉ የእስራኤል የእሳት አደጋ መከላክል አባላት እና ለኬንያዊያን ባለሙያዎች የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር አምባቸው መኮነን ምስጋና አቀረቡ።

ርዕሰ መስተዳድሩ ምስጋና ያቀረቡት የአማራ ወጣቶች ማህበር፣ አብንና ቤተ አማራ በጋራ ባዘጋጁት የምስጋናና እውቅና ፕሮግራም ላይ ነው።

ዶክተር አምባቸው በተለይ የእስራኤል መንግስት ላደረገው አበርክቶ በክልሉ ህዝብና መንግስት ስም ምስጋና አቅርበዋል።

በደም የተሳሰረ ጠንካራ የህዝብ ለህዝብ ትስስር ያላቸው ኢትዮጵያና እስራኤል ግንኙነታቸው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል እምነታቸውን ገልፀዋል።
ለኬንያዊው እሳት አደጋ ተከላካይ ሄሊኮፕተር አብራሪም ዶክተር አምባቸው ምስጋና አቅርበዋል።

የእሳት አደጋውን በቁጥጥር ስር ለማዋል ለተዋደቀው ህዝብ በተለይ በዚሁ ምክንያት ህይወቱን ላጣው ወጣት ምስጋናው ነጋሽ ያላቸውን ክብር ገልጸዋል።

የእስራኤል የእሳት አደጋ ተከላካይ ቡድን ተወካይ ብርጋዴር ጄኔራል ፅዮን ሻንኩር በበኩላቸው ይህንን ውድ የኢትዮጵያ ሀብት ለመታደግ በመመረጣቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልፀዋል።

ኢትዮ-እስራኤላዊ የሆኑ የቡድኑ አባላትም ‘ወደምንጫችን ተመልሰን የጋራችን ሀብት ነው የታደግነው’ ብለዋል።

የፕሮግራሙ አዘጋጆች በአማራ ህዝብ ስም ይህን ብሄራዊ ሀብት ለመታደግ ለተሳተፋ ሁሉ በተለይ ለእስራኤል መንግስትና ህዝብ ምስጋና አቅርበዋል።

በጎሀ ሆቴል በተካሄደው የምስጋና ኘሮግራም ለቡድኑ አባላት እውቅናና ሽልማት ተሰጥቷል።