Source – EthioOnline

2019-04-17 Author: ጥበቡ በለጠ

ደራሲያን ስለ ኢትዮጵያ ምን ፃፉ?

ኢትዮጵያን በተመለከተ በርካታ ደራሲያን፣ ፈላስፋዎችና ተመራማሪዎች አያሌ ርዕሰ ጉዳዮችን ጽፈዋል፡፡ ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊያን በተለይም በውጭ ሀገር ፀሐፊዎች ዘንድ እንዴት ተገለፁ የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ ሁሉንም ጽሁፎች ማንበብ ግድ ይላል፡፡ ነገር ግን የእውቀትና የምርምር ፀጋ የተሰጣቸው አንዳንድ ፀሐፍት ያነበቧቸውን ሁሉ ሰብስበው እንዲህ ተፅፏል ብለው ያቀብሉናል፡፡ በዚህም የተነሳ የዛሬ ሦስት ሺ ዓመት ግድም ከተፃፉት ሠነዶች ጀምሮ ኢትዮጵያ ነክ ርዕሰ ጉዳዮች እንዴት ተፃፉ? ምንስ ይላሉ? በሚለው ኃሳብ ላይ ቆይታ እናደርጋለን፡፡

በኢትዮጵያ የሥነ-ጽሑፈ ታሪክ ውስጥ አንድ አስገራሚ ገጠመኝ አለ፡፡ ይህም አፄ ኃይለሥላሴ ከመንበረ ስልጣናቸው የወረዱ ቀን፣ ወታደሮችም ኢትዮጵያን ለመምራት ስልጣን የያዙ ቀን፣ አንድ ሰፊ እውቅና የተሰጠው መጽሐፍም የዚያኑ ቀን ለንባብ ገበያ ላይ የወጣበት እለት ነበር፡፡ የህ መጽሐፍ በፕሮፌሰር ዶናልድ ሌቪን አማካይነት የተፃፈው Greater Ethiopia (ገናናዋ ኢትዮጵያ) የተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ ደራሲው ፕሮፌሰር ዶናልድ ሌቪን ፔንስልቬኒያ ውስጥ እ.ኤ.አ በ1931 ዓ.ም ተወልደው እ.ኤ.አ. ኤፕሪል 4 2015 ነው ከዚህች አለም በሞት የተለዩት፡፡

Greater Ethiopia የተሰኘው መጽሐፍ በውስጡ እጅግ በርካታ የሚባሉ ትልልቅ ኃሳቦችና ምርምሮችን የያዘ ነው፡፡ ስለ ኢትዮጵያም ማንነትና ታሪክ በሰፊው የተተነተነበት የአያሌ አስተሳሰቦች ጥርቅምና ትንታኔ ያለበት መጽሐፍ ነው፡፡ ይህ መጽሐፍ ኢትዮጵያን ከአንትሮፖሎጂ እና ከሶሲዮሎጂ አንፃር ዝርዝር አድርጐ ለማሳየት የተፃፈ የጥናትና ምርምር ውጤትም ነው፡፡ በአጼ ኃይለስላሴ ዘመነ-መንግስት ሚኒስቴር የነበሩትና አሁን በህይወት የሌሉት አቶ ሚሊዮን ነቅንቅ ታላቋ ኢትዮጵያ በማለት መጽሃፉን ተርጉመውታል፡፡

ፀሐፊው ዶናልድ ሌቪንም በቺካጐ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ፕሮፌሰር ቢሆኑም በኢትዮጵያ ውስጥ ለረጅም ጊዜ በመቆየት ሀገሪቷን አጥንተዋት በርካታ ጥናትና ምርምር የፃፉ ገናና ምሁር ናቸው፡፡ ፕሮፌሰር ዶናልድ ሌቪን በዚሁ Greater Ethiopia በተሰኘው መጽሐፋቸው ውስጥ እንዳመለከቱት ኢትዮጵያ በፕላኔታችን ካሉት ሀገሮች ውስጥ በቀደምት ስልጣኔ ከሚታወቁት መካከል አንዷ መሆኗን የልዩ ልዩ ደራሲያንን ጽሁፎች በዋቢነት እያሳዩ መስክረውላታል፡፡ ከዚሁ ጋርም ተያይዞ ኢትዮጵያን በአሉታዊ መልኩ የገለጿትን ደራሲያንንም አስተዋውቀውናል፡፡

ፕሮፌሰር ዶናልድ ሌቪን ኢትዮጵያን የውጭ ሀገር ፀሐፊዎች በአምስት ደረጃዎች ከፋፍለው እንደሚገልጿት ጽፈዋል፡፡ እነዚህም የሚከተሉት ናቸው፡፡
1. ኢትዮጵያ በጣም የራቀች ምድር ነች ብለው ያስባሉ፡፡ /A far – off place/
2. ኢትዮጵያ የአማኒያን ሀገር ናት ይላሉ፡፡ /Ethiopia the pious/
3. ኢትዮጵያ ድንቅ የሆነች የንጉሥ ሀገር ነች ይላሉ፡፡ /A magnificent Kingdom/
4. ኢትዮጵያ የአረመኔ ሀገር ነች ይላሉ፡፡ /Savage Abyssinia/
5. ኢትዮጵያ የአፍሪካ ነፃነት ሰንደቅ ነች ይላሉ፡፡ /A bastion of African Independence/
በእነዚህ ከላይ በተዘረዘሩት ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ በልዩ ልዩ አለማት ያሉ ደራሲያን ኢትዮጵያን እንዴት እንደገለጿት ፕሮፌሰር ዶናልድ ሌቪን በመፅሐፋቸው ውስጥ ያብራራሉ፡፡

1. ኢትዮጵያ በጣም የራቀች ሀገር ናት

በዚህ ርዕስ ዙሪያ የተለያዩ ጥንታዊ ደራሲያን ጽፈውበታል፡፡ ለምሳሌ የዛሬ ሦስት ሺ ዘመን ላይ እንደኖረ የሚነገርለት ዓይነስውሩ የግሪክ ታሪክ ፀሐፊ ሆሜር፣ ኢትዮጵያን በተመለከተ ጽፏል፡፡ ሆሜር ኦዴሴ በተባለው መጽሐፉ ውስጥ በመጀመሪያው አንቀፅ ላይ ኢትዮጵያዊያን ከሰው ዘር ሁሉ በርቀት ላይ የሚገኙ ህዝቦች መሆናቸውን ጽፏል፡፡ በዚህም የተነሳ ሰዎች ኢትዮጵያን እጅግ ሩቅ ቦታ ላይ የምትገኝ ምድር አድርገው ያስቧት ነበር፡፡ ሄሮዱተስ የተባለው ጦረኛም ጦሩን ሲያዝ እስከ ምድር መጨረሻ ማለትም እስከ ኢትዮጵያ ድረስ ማዘዙ ተፅፏል፡፡

ኤስኪለስ /Aeschylus/ የተባለው ጥንታዊው ፀሐፌ-ተውኔት ፕሮሚስስ ባውንድ በተሰኘው መጽሐፉ ውስጥ አንዲት “ኢዮ” የምትባል ሴትን በመጥቀስ፤ ይህችም ሴት “ወደ ሩቅ ምድር፣ ወደ ጥቁሮች አገር፣ ህዝቡ የፈካች የፀሐይ ጨረር እየሞቀ ወደሚኖርባት እና ጅረት ወደሚፈልቅባት” እንድትሄድ አድርጓታል፡፡ “ኢዮ” የሄደችው ወደ ኢትዮጵያ ነበር፡፡

እንግዲህ ለጥንታዊያኑ ግሪኰችና ለሮማዎች ኢትዮጵያ ሩቅ ምድር ሆና ነው በህሊናቸው የተሳለችው፡፡ ፍራንክ ስኖውድን የተባለ ፀሐፊ Blacks in Antiquity /ጥቁሮች በጥንት ዘመናት/ በተሰኘው መፅሐፉ ኢትዮጵያዊያን ለምን የሩቅ ሀገር ህዝቦች ሆነው እንደተፃፉ ያብራራል፡፡ የመጀመሪያውን ምክንያት ሲገልፅ በጣም የራቁ ሀገሮች የቆዳ ቀለማቸው እንደሚለይ እና በዚህም የተነሳ መሆኑን ያብራራል፡፡

ጥንታዊው የግሪክ ፈላስፋ አሪስ ጣጣሊስ (አርስቶትል) የኢትዮጵያዊያን ጠጉር ከርዳዳ የሆነው የሚኖሩበት ቦታ ላይ ያለው አየር ሞቃት ስለሆነ ነው በሚል እንደፃፈ ፕሮፌሰር ዶናልድ ሌቪን Greater Ethiopia በተሰኘው መጽሐፋቸው ውስጥ ገልፀዋል፡፡
በክርስትናው ዓለም ውስጥ በደራሲነቱ የሚታወቀው ቅዱስ አውግስቲንም፤ የቀደሙትን ደራሲያን ኃሳብ በመመርኰዝ “ንግስተ ሣባ ኢትዮጵያዊት እንደሆነች አስረግጦ ከገለፀ በኋላ በአዲስ ኪዳን “የሰለሞንን ጥበብ ለመስማት በጣም እጅግ ሩቅ ከሆነ ቦታ መጣች” ተብሎ ከተፃፈ ኃሳብ ጋር ያያይዘዋል፡፡

የቤዛንታይኑ ፀሐፊ አስጢፋኖስም ኢትኒኮን /Ethnikon/ በተባለው የመልክዐም ምድር ኢንሳይክሎፒዲያ መፅሐፉ ውስጥ ኢትዮጵያዊያንን በተመለከተ የገለፀው ከሆሜር ጋር ተመሣሣይ ነው፡፡ ይህም “እጅግ የሩቅ አገር ሰዎች” በማለት ይጠራቸዋል፡፡ ከዚህ በመለጠቅም በዚያን ወቅት የኢትዮጵያ ርዕሰ ከተማ አክሱም እንደሆነችም ጽፏል በማለት ፕሮፌሰር ዶናልድ ሌቪን ገልፀዋል፡፡

ሐይማኖተኛዋ ኢትዮጵያ

በዚህ ክፍል ውስጥም በርካታ ፀሐፊያን ልዩ ልዩ አመለካከታቸውን እንዳሰፈሩ Greater Ethiopia የተሰኘው መፅሐፍ ይገልፃል፡፡ ለምሳሌ የዛሬ ሦስት ሺ ዓመት የተፃፈው የግሪካዊው ደራሲ የሆሜር ኦሊያድ የተሰኘው መፅሐፍ ገና ከመግቢያው ላይ፣ የግሪኰች የአማልክት አምላክ የሚባለው “ዚየስ” ከርሱ በታች የሚገኙትን አመልክቶች ሁሉንም ይዞ ለአስራ ሁለት ቀናት ፍፁም ቅዱስ ወደሆኑት ኢትዮጵያውያንን ለመጐብኘት መሄዱ ተፅፏል፡፡ በዚሁ በሆሜር በተፃፈው ሌላኛው መፅሐፍ ማለትም በኦድሴይ ውስጥ ደግሞ ፓሲዶን የተባለው ገፀ ባህሪ፣ “ከሩቆቹ ኢትዮጵያዊያን ድግስ ላይ እጅግ ተደስቶ ቆየ” ይላል፡፡

ከክርስቶስ ልደት በፊት በመጀመሪያው ምዕተ ዓመት ላይ የነበረው የግሪኩ ሊቅ ዲዎደረስ ሲክለስ ሲፅፍ፣ ኢትዮጵያዊያን አማልክቶች ሁሉ የሚገዙላቸው፣ እንደውም የአማልክቶች ሁሉ ፈጣሪና አዛዥ መሆናቸውን ሁሉ ዘርዝሮ ጽፏል፡፡
የቤዛንታይኑ እስጢፋኖስም “በአማልክት ማምለክን የጀመሩ እና ያስፋፉ ኢትዮጵያዊን ናቸው” በማለት እንደፃፈም ተገልጿል፡፡ ከዚሁ ከአስጢፋኖስ ጋር ዘመንተኛ የነበረው ላክታኒሻስ ፕላሲደስ የተሰኘ ሌላ ደራሲ ይህንኑ ኃሳብ በማጐልመስ የሚከተለውን ጽፏል፡፡

“አማልክት ኢትዮጵያዊያንን የሚወዱበት ምክንያት ፍትሀዊ ስለሆኑ ነው፡፡ ፍትሀዊነት የእኩልነት ባህልና ሀቀኝነት ስላላቸው ጁፒተር ከሰማየ ሰማያት ተነስቶ ወደ ኢትዮጵያዊያን እየሄደ ከነርሱ ጋር መዝናናት ያዘወትራል ሲል ሆሜር እንኳ ሳይቀር ጽፏል፡፡ ምክንያቱም ኢትዮጵያዊያን ከማንኛውም ህዝብ የላቀ ፍትሐዊነት ስላላቸው አማልክቱ ከተከበረ መኖሪያቸው እየወጡ እነሱን መጐብኘት ያዘወትራሉ፡፡”

ፕሮፌሰር ዶናልድ ሌቪን በዚህ Greater Ethiopia በተሰኘው መጽሐፋቸው ውስጥ እንደሚያወሱት ኢትዮጵያዊያን ፍትሃዊ እና ሃይማኖት አጥባቂዎች እንደሆኑ ጥንታዊ ፀሐፊያን መግለፃቸውን አፅንኦት ሰጥተው ፅፈውበታል፡፡

በሦስተኛው ምዕተ ዓመት ኢትዮፒካ በሚል ርዕሰ ሄሊዮዶሩስ የተባለው ደራሲ በፃፈው ልቦለድ ውስጥ የቀረቡት ገፀ-ባህርያት በሃይማኖታቸው የበቁ እና ወደ ፅድቅ መንገድ ላይ ያሉ ነበሩ፡፡ ይህንን የፅድቅ ኃሳብ በመከተል ይመስላል ሳሙኤል ጆንሰን የተባሉት ደራሲ ራሴላስ በተሰኘው መፅሐፋቸው ውስጥ የቀረበውን ኢትዮጵያዊ መስፍን ሐቀኛ፣ ቅን እና የበጐ ምግባሮች መፍለቂያ አድርገው የሳሉት፡፡

በእስልምናው ዓለምም ኢትዮጵያ ገናና ሀገር ሆና ትጠቀሳለች፡፡ የዓለም ሙስሊሞች ባብዛኛው ኢትዮጵያ የተከበረች እና በነብያቸውም የምትወደድ የሰላም ምድር መሆኗ ይነገራል፡፡ ለምሳሌ ሲራ በሚል ርዕስ ስለ ነቢዩ መሐመድ የሕይወት ታሪክ ያዘጋጀው ኢብን ሒሻም የፃፈው በዋቢነት ይጠቀሳል፡፡ እንደ እርሱ ገለፃ፣ “ቁራይሽ” የሚሰኙት የመካ ገዢዎች የነብዩ መሐመድን ተከታዮች እያሳደዱ ቢያስቸግሩዋቸው፣ ለተከታዮቻቸው የሚከተለውን ምክር እንደለገሷቸው ሲራ በተሰኘው ጥንታዊ መጽሐፍ ውስጥ ተመዝግቦ ይገኛል፤

“ወደ ሀበሻ ሀገር ብትሄዱ፣ በግዛቱ ማንንም የማይጨቁን ንጉሥ ታገኛላችሁ፡፡ ያቺ ሀገር የጽድቅ ሀገር ናት፡፡ እግዚአብሔር አሁን ካለባችሁ ስቃይ ሁሉ የሚያሳርፋችሁ እዚያ ብትሄዱ ነው”

አስደናቂዋ የንጉሥ ሀገር

በኢትዮጵያ ውስጥ የነበሩ ታላላቅ ነገስታት በልዩ ልዩ ደራሲያን ሥራዎች ውስጥ ተጠቅሰዋል፡፡ ለምሳሌ ፐሊኒ /Pliny/ የተባለው የጥንት ፀሐፊ ኢትዮጵያ እና ነገስታቶቿ ኃይለኞች እንደሆኑ፣ እስከ ትሮጃን ጦርነቶች ድረስ ዝነኛ እና ገናና እንደነበረች ጽፏል፡፡

በሦስተኛው ምዕተ ዓመት አካባቢ የነበረው ማኒ የተባለው ፀሐፊ፣ በዚህች ፕላኔት ላይ ካሉ ሃያላን መካከል አክሱም (ኢትዮጵያ) ሦስተኛ ነች ብሎ ጽፏል፡፡ የቀዳማዊ ጀስትን ተከታይ ደስትያን (527-67) ፋርስን ለመቋቋም እርዳታ ፈልጐ መልዕክተኞቹን ወደ ኢትዮጵያ ልኳል፡፡ ከነኚህ መልዕክተኞች ውስጥ አንዱ ቡድን የኢትዮጵያን ቤተ-መንግሥት ሲያደንቅ እንዲህ ብሏል ይላሉ ፕ/ር ዶናልድ ሌቪን፤

“የኢትዮጵያ ንጉሥ የወርቅ ቅብ ጦርና ጋሻ ባነገቡ መማክርት ታጅቦ አራት ዝሆኖች የሚስቡት፣ በወርቅ የተለበጠ ባለ አራት እግር መንኰራኩር ሰረገላ ላይ ተቀምጦ፣ ህዝቡን ይቀበላል”

አረመኔዋ ኢትዮጵያ

ኢትዮጵያን እየካቡ የፃፉ በርካታ ደራሲያን የመኖራቸውን ያህል ያንጓጠጡ እና መጥፎ ብዕራቸውንም ያነሱ አሉ፡፡ ከእነዚህም አንዱ ዴዎደረስ የተባለ ፀሐፊ ነው፡፡ እሱም ሲፅፍ “ኢትዮጵያዊያን በአባይ ወንዝ በስተደቡብ በወንዙ ግራና ቀኝ ሰፍረው የሚገኙ አሉ፡፡ ፍፁም አውሬዎች ስለሆኑ የዱር አውሬን ተፈጥሮ ያሳያሉ፡፡ ገላቸው ጭቅቅታም ነው፡፡ ጥፍራቸው እንደ አውሬ ጥፍር እንዲተልቅ ያደርጉታል፡፡ ሰብአዊ ልግስና በመካከላቸው የለም፡፡ በሌላ ሥፍራ ያለው የሰው ዘር እንደሚያደርገው ለሥልጣኔ ህይወት የሚሰሩ ተግባሮችን ሲፈፅሙ አይታዩም” ብሏል፡፡

ሌሎች የላቲን የጂኦግራፊ ሊቆች እነ ፕሊኒ፣ እነ ሶሊነስ፣ እንዲሁም ፖምፓኒያስ ሜላን ስለ ኢትዮጰያ ከእውነት የራቀ አስቀያሚ ነገር ጽፈዋል፡፡ ይሁን እንጂ በ1520 እ.ኤ.አ ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ ስድስት ዓመት ቆይቶ፣ ዞሮ ታሪክ የፃፈው ፖርቹጋላዊው ፍራንሲስኮ አልቫሬዝ ኢትዮጵያ በዚያን ዘመን ከአውሮፓ ሀገራት ጋር ያን ያህል ልዩነት እንደሌላት ፅፏል፡፡

በ18ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ላይ የአባይን መነሻ ለማጥናት ወደ ኢትዮጵያ የመጣው ጀምስ ብሩስ በፃፈው መፅሐፍ ኢትዮጵያዊያን አንድ በሬ በቁሙ እያለ ከነህይወቱ ከላዩ ላይ ሙዳ ሥጋ እየቆረጡ እንደሚበሉ ጽፏል፡፡ ይህም ጽሁፍ ስህተት ነው፡፡ ጀምስ ብሩስ “መጽሐፈ ሄኖክ” የተሰኘውን የብራና ጽሁፍ ወደ ሀገሩ ስኰትላንድ ሰርቆ ይዞ ሄዷል፡፡ ኢትዮጵያ በነበረበት ጊዜም ጐንደር ውሰጥ የእቴጌ ምንትዋብን ልጅ አስቴርን አግብቶ ቤተ-መንግስት ውስጥ ይኖር ነበር፡፡

ሌሎችም ደራሲያን ኢትዮጵያ ያልሰለጠነች፣ የጨካኞች ሀገር እንደሆነች በ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን አጋማሽ ጀምሮ ፃፉ፡፡ ይህ ደግሞ ከአውሮፓ ውስጥ ኢጣሊያ ወደ ኢትዮጵያ መጥታ በቅኝ ግዛት ለመያዝ እንዲያነሳሳት አደረገ፡፡ በመጨረሻም ወደ ኢትዮጵያ ዘምታ በ1888 ዓ.ም ላይ በአድዋ ጦርነት ኢጣሊያ ብቻ ሳትሆን ነጭ የተባለ ዘር ሁሉ ትልቅ ሽንፈት ደረሰበት፡፡

የአፍሪካ የነፃነት ምድር

በኢትዮጵያ ላይ በልዩ ልዩ መንገድ የሚፃፈው ሁሉ በነጮች መዳፍ ውስጥ በመግባቷ ነው፡፡ ዲወደረስ የተባለው ደራሲ ሲገልፅ እንዲህ ብሏል፤
“ኢትዮጵያዊያን በባዕድ ንጉስ ከቶ ተገዝተን አናውቅም፤ በመካከላችን ሙሉ ሰላም ሰፍኖ ነፃ ህዝቦች ሆነን ኖረናል ይላሉ” በማለት ፅፏል፡፡

የ17ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የታሪክ ሊቅ የነበረው ፖርቹጋላዊው ሉዊስ ኡሬታ “ሐበሻ የሚለው ቃል ትርጉም (በአረብኛ በቱርክና በኢትዮጵያ ቋንቋዎች) የባዕድ ንጉስ ግዛት የማይታወቅ ነፃና ራስ ገዝ ማለት ነው፤ ኢትዮጵያ የምትባለው አገርም ልክ እንደምነግራችሁ ነች” ብሎ ፅፏል፡፡

ኢትዮጵያ ዝናዋ እየጐላ የመጣው የተቃጡባትን ጦርነቶች ሁሉ ማሸነፍ በመቻሏ ነው፡፡ ለምሳሌ በ1870 የግብፅን ወራሪ ጦር፣ በ1880 የመሀዲስቶችን ወረራ ማሸነፍ፣ በ1888 የኢጣሊያን ወረራ የውርደት ማቅ ማልበስ፣ እና በሌሎችም የዓለም ትኩረት መሆን ጀመረች፡፡

ኢትዮጵያ በነጮች መዳፍ ስር ለነበሩ የአፍሪካ ሀገራትና ለጥቁር ዘር ሁሉ የነፃነት ሞዴል ሆነች፡፡ የናይጄሪያው መሪ ናምዲ አዚክዊ የፃፉትን አቶ ሚሊዮን ነቅንቅ እንዲህ ተርጉመውታል፡፡

“ኢትዮጵያ በዓለም ገፅ ከጠፉ የጥቁር ግዛቶች የተረፈች ብቸኛ የተስፋ ችቦ ነች፡፡ የአፍሪካዊያን አባቶችና አያቶች በዚህ አህጉር አቋቁመውት ለነበረው ሥርዓተ መንግሥት ሐውልት ነች፡፡ ጓደኞቿ አገሮችና ወራሾቻቸው ከፖለቲካ ታሪክ ገፅ ውስጥ ከተሰረዙ በኋላ ኢትዮጵያ በነፃነት መቆየቷ እጅግ የሚያስደንቅ ነው፡፡”

የጋናው ኑክሩማን፣ የኬንያው ጆሞ ኬኒያታ፤ የደቡብ አፍሪካው ማንዴላ በኢትዮጵያ ላይ ብዙ ጽፈዋል፡፡ የጥቁሮች የነፃነት ተምሳሌት ነች ብለዋል፡፡ የዌስት ኢንዲስ ሰው የሆነው ማርክስ ጋርቬይም ኢትዮጵያን እና ንጉሷን ከፍ ከፍ በማድረግ የጥቁሮች መሪ አደረጋት፡፡

ኢጣሊያ ኢትዮጵያን ስትወር የጥቁሮች ተቃውሞ አየለ፡፡ እ.ኤ.አ በ1935 ዓ.ም ላይ አፍሮ አሜሪካን በተባለው መጽሔት ላይ W.E.B.D እንዲህ ፃፈ፤ “የኢጣሊያ ወረራ የጥቁር ህዝቦች የታሪክ መታጠፊያ” ብሎ በመሰየም “ነጭ እንዳሰኘው ‘የቀለም’ ህዝቦችን ወግቶና ወሮ የራሱ የሚያደርግበት ጊዜ አከተመ፡፡ አበቃ” በማለት የትንቢት ጽሁፍ አቅርቧል፡፡
ኦፖርቹኒቲ የተባለ የጥቁሮች ህይወት ዜና ጋዜጣ የገለፀው እንዲህ ተተርጉሟል፡፡

“ኢትዮጵያ በመላው ዓለም የጥቁር ህዝቦች የመንፈሣዊ አባት አገር ሆናለች፡፡ ከባሂያ እስከ በርሚንግሃም፣ ከኒውዮርክ እስከ ናይጄሪያ የአፍሪካ ደም ያለባቸው ሁሉ ከዚህ ቀደም ተሞክሮ በማያውቀው አስተሳሰብ አንድነት ተቆስቆሰዋል” ብሏል፡፡
ጆርጅ ኤድመንድ ሄይንስ የተባለ ጥቁር አሜሪካዊ እንደፃፈው፤ “ኩሩዋ እና ነፃዋ ኢትዮጵያ አፍሪካዊ ደም ላላቸው ለጥቁሮች የነፃነት፣ የራስ መቻል፣ ከዘመናዊ ስልጣኔ መልካም መልካሙን የመቅሰምና የንቃተ ህሊና ምልክት ሆናለች” ብሏል፡፡

ለዛሬ ጽሁፌ መነሻ የሆኑኝ ፕሮፌሰር ዶናልድ ሌቪን ከዚህ በፊት በአያሌ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ኢትዮጵያዊ ጥናቶችን አድርገዋል፡፡ ከነዚህም ውስጥ እ.ኤ.አ 1996 The Battle of Adwa, Ethiopia and the Bible (1968) Wax and Gold (1965) እና ሌሎች ውብ የጥናትና ምርምር ስራዎተን አበርክተዋል፡

ለዛሬ ጽሁፌ መነሻ የሆኑኝ ፕሮፌሰር ዶናልድ ሌቪን ከዚህ በፊት በአያሌ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ኢትዮጵያዊ ጥናቶችን አድርገዋል፡፡ ከነዚህም ውስጥ እ.ኤ.አ 1996 The Battle of Adwa, Ethiopia and the Bible (1968) Wax and Gold (1965) እና ሌሎች ውብ የጥናትና ምርምር ስራዎተን አበርክተዋል፡፡