ምንጭ – እኢትዮኦንላይ

አዲስ አበባን አጼ ምኒልክና እቴጌ ጣይቱ የመንግስታቸው መቀመጫ ዋና ከተማ እንድትሆን ከመወሰናቸው በፊት፤ ስፍራው በርካታ ታሪኮች የተከናወኑበት እንደነበር ከሚነገሩት ታሪኮች፣ የረር ተራራን ማዕከል የሚያደርገው በዝቶ ይታያል፡፡ ለስያሜዋ ምክንያት የሆኑት አጼ ምኒልክና እቴጌ ጣይቱ መናገሻ ከተማ ሳያደርጓት በፊት፣ ጥቂት ለማይባሉ መንግስታት መቀመጫ እንደነበረች፣ በርካታ ትውልዶች እንደተፈራረቁባት፣ አያሌ ታሪኮች እንደተከናወኑባት  የሚቀርቡ መረጃዎች አሉ፡፡

ደራሲ ጤንነት ሰጠኝ ‹‹ምስጢረ ሰማያትና ምስጢረ ኢትዮጵያ ፍልስፍና›› እና ‹‹በኤረር ተራራ ድምጾች›› በሚል ርዕስ ሁለት መጻሕፍት አሳትሟል፡፡ በመጻሕፍቱም በእግዚአብሔር የተፈጠረው አዳም ‹‹ርስት ሀገሩ›› ኢትዮጵያ መሆኗን፣ ልእለ ኃያል የሆነ  ሀሳብ ከሚተገበርባቸው 7 የዓለም ስፍራዎች ሦስቱ በኢትዮጵያ እንደሚገኙ፣ በመካከለኛው ኢትዮጵያ የሚገኘው ሸዋ ክፍለ ሀገር በተለይም የረር ተራራ የ7ቱ ማዕከልና ዋነኛው ቦታ መሆኑን ማሳይ አድርጎ የሚያቀርባቸው በርካታ ታሪኮች አሉ፡፡

‹‹በአገራችን ታሪክ ውስጥ ሙሉ ለሙሉ ማለት ይቻላል መካከለኛው ኢትዮጵያን ሳይይዙ ብዙ ርቀት የሄዱ ነገስታት የሉም፡፡ ንግስናው በየጥጋጥጉ ቢካሄድም መካከለኛው ስፍራ በቋሚነት ይያዛል›› የሚለው ደራሲ ጤንነት ሰጠኝ፤ ለዚህ እውነታ በማሳያነት አክሱማዊያኑ ወንድማማቾች አብርሐና አጽብሃ በሰሜን ኢትዮጵያ ነግሰው ወደ መሐል መጥተው በየረር ተራራ እና ዙሪያው ቤተ መንግስታቸውንና የተለያዩ ዋሻዎችን መስራታቸውን ያመለክታል፡፡

ደራሲ በላይ ግደይ አምኃ ‹‹አዲስ አበባ ያብባል ገና›› በሚል ርዕስ በ1997 ዓ.ም ባሳተሙት መጽሐፍ ውስጥም፣ በኢትዮጵያ የንግስና ታሪክ መካከለኛው ኢትዮጵያ ወሳኝ መዳረሻ መሆኑን ሲገልጹ  ‹‹ስለ አዲስ አበባ ከተማ አመሠራረት ከቀደሙ አባቶች ተያይዞ የመጣው ነባር ሁኔታ በቅድሚያ ለማቅረብ ሲሞከር የኢትዮጵያ ሥርወ መንግሥት መነሻው አክሱም፣ መድረሻው አዲስ አበባ መሆኑን መሠረት በማድረግ ነው ›› ይላሉ፡፡

ደራሲ ጤንነት ሰጠኝ የልእለ ኃያል ሀሳብ መገለጫ ስፍራ የሆነው የረር ተራራ፤ ኢትዮጵያ የክርስትና ሀይማኖትን ከመቀበሏ በፊት የሚጀምር ታሪክ ያለው ነው ሲል፤ ደራሲ በላይ ግደይ አምኃ በበኩላቸው፣ የየረር ተራራ ታሪካዊነት የሚጀምረው በአክሱማዊያን ዘመን የየካ ሚካዔል ዋሻ ከተሰራ ጀምሮ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ ‹‹የአክሱም ነገሥታት ወደ ሸዋ ከመጡ በኋላ የከተሙት የረር ተራራ ላይ ሲሆን በጠንካራ ምሽግነቱ ታምኖበት ነው›› የሚሉት በላይ ግደይ፤ ከዚያን ዘመን ጀምሮ አዲስ አበባ ከተለያየ አቅጣጫ የሚመጣ ሕዝብ ማረፊያ መሆን እንደጀመረች ይገልጻሉ፡፡ አጼ ምኒልክና እቴጌ ጣይቱ የመንግስታቸው መቀመጫ ከተማ እንጦጦ ተራራን ማዕከል ያደረገ እንዲሆን ምክንያት የሆናቸው፤ ስፍራው የንጉሥ ዳዊት መቀመጫ እንደነበር መረጃ ከተገኘ በኋላ ነው በማለት ሲገልጹ፡ –

‹‹ዐፄ ምኒልክ በመጀመሪያ ከአንኮበር እንደመጡ ለጥቂት ጊዜ በምዕራብ አዲስ አበባ በሚገኘው በረጅሙ የወጨጫ ተራራ ላይ ከሰፈሩ በኋላ በ15ኛው ክፍለ ዘመን የነገሡት አጼ ዳዊት እንጦጦ ላይ ከተማቸውን አድርገው ይቀመጡ ነበር የሚል የብራና ጽሑፍ በዝዋይ ደሴት ስለተገኘ ወጨጫ ተራራን ትተው የዐፄ ዳዊት ወደ ነበረችው ከተማ እንጦጦ ተራራ መጥተው ሰፈሩ፡፡››

ኢትዮጵያዊያን ክርስትናና ከመቀበላቸው በፊት ‹‹የልእለ ኃያል ሀሳብ›› መገለጫ ዋነኛ ስፍራ የነበረው የረር ተራራ፤ በአክሱማዊያን ዘመን የሕዝቦች መኖሪያነቱ ቀጥሎ፣ ‹‹ንግስናን ለማጽናት መሐል ኢትዮጵያን የመያዝ አስፈላጊነት›› ሚስጢሩ ከገባቸው መሐል፤ ንጉሥ ዳዊት በ15ኛው ክፍለ ዘመን፣ ንጉሥ ልብነ ድንግል በ16ኛው ክፍለ ዘመን በስፍራው ቆይተው የታሪኩ አካል ሆነዋል፡፡ የንጉስ ልብነ ድንግል የልጅ ልጆች ደግሞ የአዲስ አበባ ታሪክ ከአጼ ምኒልክ ጋር እንዲያያዝ ምክንያት ሆኑ፡፡

አጼ ልብነ ድንግል በግራኝ አህመድ ወረራ ጊዜ ከልጆቻቸው አንዱ (አቤቶ ያዕቆብን) መንዝ ላይ ትተውት እንደሄዱ፣ እሱ ለሸዋ ነገስታት መነሻ እንደሆነ፣ አንኮበርን ከተማቸው አድርገው አቤቶ በሚል ማዕረግ እየተጠሩ ለ150 ዓመታት ሸዋን መግዛታቸውን፣ ቀጥሎ የማዕረግ ሥማቸው ወደ መርዕድ አዝማች መለወጡን፣ ንጉሥ መባል የጀመሩት ከሣህለሥላሴ በኋላ መሆኑን  ደራሲ በላይ ግደይ አምኃ ይገልጻሉ፡፡

በክርስትና ስማቸው አብርሃና አጽብሃ በሚል የሚታወቁት፣ አክሱማዊያን ወንድማማቾች (ኢዛና እና ሳይዛና) ከ1600 ዓመት በፊት በየረርና የካ ተራራዎች የሰሯቸው ቤተ ክርስቲያናትና ዋሻዎች ቀዳሚ ሆነው፤ በእንጦጦ፣ ፉሪ፣ መናገሻ ተራራና መሐል ላይ ባሉ ስፍራዎች፤ በንጉሥ ዳዊት፣ በንጉሥ ዘርዓ ያእቆብ፣ በአጼ ልብነ ድንግል፣ በንጉሥ ሣህለሥላሴ … የተሰሩት ታሪካዊ ሥራዎች፣ በአካባቢው ነገስታቱን ማዕከል ያደረጉ ሕዝቦች ይኖሩ እንደነበር ያሳያሉ፡፡

አዲስ አበባ ከተማ የተመሠረተችበት 100ኛ ዓመት በ1979 ዓ.ም ሲከበር ‹‹PROCEEDINGS OF THE INTERNATIONAL SYMPOSIUM ON THE CENTENARY OF ADDIS ABABA›› በሚል ርዕስ በታተመ መጽሐፍ እና የገነት ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን የምሥረታ 100ኛ ዓመት ጥር 1988 ዓ.ም ሲያከብር በዓሉን ምክንያት በማድረግ በታተመ መጽሔት፤ አዲስ አበባ በአጼ ምኒልክና እቴጌ ጣይቱ ከመመሥረቷ ቀደም ያለ ታሪክ እንደነበራት የሚያሳይ መረጃ አቅርበዋል፡፡

በ1916 ዓ.ም የቀራኒዮ መድሐኒዓለም ቤተ ክርስቲያንን የመሠረቱት ንጉሥ ሣህለሥላሴ፣ በ1843 ዓ.ም የጉለሌን (በኋላ አራዳ) አካባቢ ጎብኝተው፣ ቤተ ክርስቲያን የማቋቋም እቅድ ነበራቸው፡፡ አዲስ አበባ የመንግስት መቀመጫ እንድትሆን ታስባ በ1879 ዓ.ም ከመቆርቆሯ በፊት፤ በጉለሌ (አራዳ) መንደር ቤተ ክርስቲያን እንደነበር የሚያረጋግጥ መረጃ በቁፋሮ ተገኝቷል፡፡ መረጃው ሊገኝ የቻለው ለምኒልክ ከቀረበ ጥያቄ ጋር በተያያዘ ነበር፡፡

በከፋ ክፍለ ሀገር የካቶሊክ ሚሲዮን የማቋቋም እቅድ የነበራቸው ካህን፣ ሸዋ ደርሰው በሊቼ ይገኙ ለነበሩት ምኒልክ እቅዳቸውን አቀረቡ፡፡ ጥያቄው የቀረበላቸው ምኒልክ፣ በ1843 ዓ.ም አያታቸው ንጉሥ ሣህለሥላሴ ያዩትን (በኋላ አዲስ አበባ የተባለውን) ቦታ እንዲያጠኑላቸው ጠየቋቸው፡፡ በቀረበው የጥናት መረጃም፤ ከሊቼ እስከ ‹‹ጉለሌ›› ለመድረስ የአራት ቀን የእግር ጉዞ እንደሚጠይቅ፣ በጉለሌ የኦሮሞ ጎሳዎች እንደሚኖሩ፣ በአካባቢው ፍል ውሃ እንደሚገኝበት፣ ‹‹ቢርቢርሳ›› በሚባለው መንደር (ቃሉ ኦሮሚኛ ሲሆን ትርጉሙም የዝግባ ዛፍ ማለት ነው) ቤተ ክርስቲያን እንደነበር የሚያመለክት የግድግዳ ፍራሽ እንደተገኘ፣ የፈረሰው ቤተ ክርስቲያን በዘርዓ ያእቆብ ዘመን እንደተሰራ እንደሚገመት፣ የመፍረስ አደጋ የደረሰበትም በግራኝ አህመድ ወረራ ዘመን እንደሆነ ታወቀ፡፡

ቤተክርስቲያኑን ኦሮሞዎች ‹‹ማሬያም ጊፊቲ›› ሲሉት አማሮች ደግሞ ‹‹እቴጌ ማርያም›› በማለት ይጠሩት እንደነበር፣ የቤተ ክርስቲያኑ የአርክቴክት ጥበብ የግሪክና ፖርቹጋሎች አሻራ የሚታይበት መሆኑን … የሰሙት አጼ ምንልክ፣ ቦታው ላይ ቤተ ክርስቲያን ለመስራት እቅድ አወጡ፡፡ ይህ መነሻ ሆኖ የአጼ ምኒልክ አጎት ራስ ዳርጌ በ1869 ዓ.ም የጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያንን አሰሩ፡፡ አሁን የሚገኘውን የአራዳ ጊዮርጊስ ሕንፃ አጼ ምኒልክ አስጀምረው በንግስት ዘውዲቱ ዘመን እንደተጠናቀቀ ለ100ኛ ዓመት የተዘጋጁት ጥራዞች ያመለክታሉ፡፡

ደራሲ ጤንነት ሰጠኝ በአራዳ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን የሚገኘው ታቦት (ጽላት) ከየረር ተራራ የመጣ መሆኑን አባ አውራሪስ የሚባሉ የሀይማኖት አባት የነገሩትን መረጃ ጠቅሶ ሲናገር ‹‹የየካ ሚካኤልን ታቦት ከየረር ወደ የካ ዋሻ ሚካኤል የወሰዱት ንጉሥ ዳዊት ሲሆኑ፤ የጊዮርጊስን ታቦት ከየረር ተራራ ወደ አራዳ ያመጡት አጼ ምኒልክ ናቸው፡፡ ይህ መረጃ በታቦቱ መቀመጫ መንበር ላይ (አሁን ካልተቀየረ) ባለ ጽሑፍ ማረጋገጥ ይቻላል›› ይላል፡፡

‹‹ከአዳም ርስት ሀገር›› የሚጀምረው የአዲስ አበባ ታሪክ ‹‹አጼ ምኒልክ መሥርተዋት ነበር›› በሚል የሚቆም አይደለም የሚለው ደራሲ ጤንነት ሰጠኝ፤ አዲስ አበባ ለአፍሪካዊያን ጥላና ከለላ ከመሆኗም ባሻገር ለመካከለኛው ምስራቅና ለዓለም ሕዝቦች ያላት ፋይዳ ታላቅ መሆኑ ያስረዳል፡፡