Source: https://fanabc.com

Apr 18, 20192

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 10፣ 2011 (ኤፍ.ቢ.ሲ) አለም አቀፉ ድንበር የለሽ የጋዜጠኞች ቡድን በኢትዮጵያ ያለው የሚዲያ ነፃነት ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር 40 ደረጃዎች ማሻሻሉን ገለፀ።

መቀመጫውን ፈረንሳይ ያደረገው የዓለም አቀፉ ድንበር የለሽ የጋዜጠኞች ቡድን በዛሬው ዕለት ዓመታዊውን ዓለም አቀፍ “የሚዲያ ነፃነት” መለኪያ የደረጃ ሰንጠረዥን ይፋ አድርጓል።

በዚህ መሰረትም ኢትዮጵያ ከ180 ሀገሮች መካከል ባለፈው ዓመት ከነበረችበት 150ኛ ደረጃ ላይ 40 ደረጃዎችን በማሻሻል 110 ኛ መሆኗን አስታውቋል።

ኢትዮጵያ ደረጃዋን ያሻሻለችውም በቅርቡ ጠቅላይ ሚነስትር ዶክተር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን መምጣታቸውን ተከትሎ በሀገሪቱ በተከሰተው የለውጥ ሂድት በሀገሪቱ የመገናኛ ብዙሃን ላይ ከፍተኛ የሆነ የሚዲያ ነፃነት በመስተዋሉ ነው ተብሏል።

ይህን ተከትሎም በኢትዮጵያ ታስረው የነበሩ በርካታ ጋዜጠኞችና ጦማሪያን መፈታታቸውን እና ተዘግተው የነበሩ በርካታ ድረ ገጾች መከፈታቸውን በዋቢነት ጠቅሷል።

ከዚህ ባለፈም በሀገሪቱ ሃሳብን በነፃነት መግለፅ ይከለክሉ የነበሩ አፋኝ ህጎች መሻሻላቸውን ነው ያስታወቀው።

በተጨማሪም ባለፉት አስርት ዓመታት በሀገሪቱ ለመጀመሪያ ጊዜ ከፈረንጆቹ 2018 መጨረሻ ላይ ጀምሮ የታሰረ ጋዜጠኛ አለመኖሩን አንስቷል።

አለም አቀፉ ድንበር የለሽ የጋዜጠኞች ቡድን የሚዲያ ነፃነት መለኪያ በየ ዓመቱ 180 ሀገሮች ላይ ያለውን የሚዲያ ነፃነት የሚመረምር ድርጅት ነው።

በዚህ ዓመት የሚከበረው የዓለም የሚዲያ ነፃነት ቀን ጉባኤም የፊታችን ሚያዚያ 24 እና 25 ቀን 2011 ዓ.ም በአዲስ አበባ ይካሄዳል ።

ጉባኤውም መገናኛ ብዙሃን ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን ለመገንባትና ነፃ ምርጫ ለማካሄድ ያላቸው ሚና ላይ ትኩረቱን ያደርጋል ተብሏል።

በጉባኤውም 1 ሺህ 500 በላይ የሚሆኑ ከተለያዩ ሀገራት መንግስታትና እና አለም አቀፍ የግል ድርጅቶች የተውጣጡ ተወካዮች ይሳተፋሉ ተብሎይጠበቃል።