
ግርምት
በደሴ ሰማይ ስር በደሴ ምድር ላይ
ከአውቶቡሱ ተራ ትይዩ ሕንፃ ላይ
ድንገት ባየው ስሙን ደምቆ ባደባባይ
ኢሕአፓ ይሉ ቃል ጽሕፈት ቤት አግኝቶ
ዓየኖቼ ጉድ አዩ ማስታወቂያው ጎልቶ፡፡
ደንገጥገጥ አልኩና ዙሪያየን ማተርኩት
ሕልም ነው ዕውነት ነው? ራሴን ጠየቅሁት፡፡
እጄ ኪሴ ገብቶ ሰልኬን አወጣና
ቁጥሮቹን ነካካ ሊያስተላልፍ ዜና፡፡
የጠራ ሳይመስለኝ ስጠብቀው ስልኩን
ልቤ እንደቸኮለ ለመግለጽ ስሜቴን
ገና ሳልናገር ሳልከፍት አንደበቴን፤
ከወዲያኛው ጫፍ ላይ ስልኩን ያነሳው ሰው ሄሎ! አለ ተቻኩሎ
ስለደወልኩለት የነደደው መስሎ፡፡
“ለጥቂት ቀደምከኝ ዛሬ ጉድ አይቼ
ድንጋጤ ገብቶ በየደም ሥሮቼ
በካዛንቺስ ምድር ከሂልተን ባሻገር
ልቤን ያሸበረ አየሁ አንድ ነገር፡፡
ከከፍታው ማማ ከህንፃው ወገብ ላይ
በጉልህ ፊደላት የተጻፈውን ሳይ
በእርግጠኝነት ራሴን ስቻልሁ
ስንቴ እንደሁ ባላውቅም ቃሉን ደግሜአለሁ
ኢሕ አ ፓ! ኢ ሕ አ ፓ! ኢ ሐ አ ፓ… ብያለሁ
ከግርምት ጋራ፣ ድብልቅልቅ ስሜቴን አስተናግዳለሁ”
አለኝ አብሮ አደጌ በደስታ ስሜት
ተናጋሪ ሆኖ እኔ በደወልኩት ፡፡
