April 19, 2019

Source: https://mereja.com/amharic

የእምቦጭ አረምን ጨምሮ ከቆሻሻ ነዳጅ ለማምረት የሚያስችል ዝግጅት እያደረገ መሆኑን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ገልጿል፡፡የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የኢትዮጵያውያንን የፈጠራ ስራዎችን ወደ ተግባር ለማስገባት እየሰራ መሆኑን አስታውቋል። ከፈጠራ ስራዎች መካከል አቶ አበሻ ዳጌ የተባሉ ኢትዮጵያዊ በፈጠራ ባለቤትነት የያዙትን ከቆሻሻ ነዳጅ የማምረት ፕሮጀክት ወደ ስራ ለማስገባት እየሰራ መሆኑን ነው ያስታወቀው፡፡

የፈጠራ ስራው እምቦጭ እና የፕላስቲክ ቆሻሻን ጨምሮ ከማንኛውም ቆሻሻ ውጋጅ ነጭ ጋዝ፣ ቤንዚን፣ ኬሮሲን፣ የአውሮፕላን ነዳጅና ሚቴን ማምረት የሚያስችል ነው ብሏል ሚኒስቴሩ፡፡ ከተረፈ ምርቱ ደግሞ የአፈር ማዳበሪያ፣ ግሪስ፣ ሻማ፣ የጫማ ቀለምና ሌሎችንም መስራት የሚያስችል የፈጠራ ስራ ነው፡፡የነዳጅ ምርቱን በፍጥነት ለመጀመርም ለነዳጅ ማምረት ሂደት የሚጠቅም ያልተወሳሰበ ማሽን ለመስራት የሚችል የባለሙያዎች ቡድን ተቋቁሙ ወደ ስራ ገብቷል ብሏል ሚኒስቴሩ፡፡
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታው ጀማል በከር ኢትዮጵያ ለነዳጅ የምታወጣውን ወጪ ለመቀነስ በፍጥነት ወደ ስራ ለመግባት ይሰራል ብለዋል፡፡የፈጠራ ስራው ባለቤት አቶ አበሻ ዳርጌ በበኩላቸው ምርምሩን ከ10 ዓመታት በፊት ጀምሮ ሲሰሩ እንደቆዩ ተናግረዋል፡፡
ምንጭ፦ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር