April 22,2019

የአራት ብሔራዊ ፓርቲዎች ጥምረት የሆነው የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ)፣ ከግንባርነት ወደ አንድ አገራዊ ፓርቲ ሽግግር እንደሚያደርግ ሲነገር ከቆየ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ከቀድሞው የግንባሩ ሊቀመንበር አቶ መለስ ዜናዊ አመራር ጊዜ ጀምሮ በፓርቲው አጀንዳነት ውይይት ሲደረግበትና ጥናት ሲካሄድበት የቆየው ይኼ አጀንዳ ረዥም ዓመታትን አስቆጥሮ፣ አሁንም የግንባሩ አጀንዳና የሌሎችም የመወያያ ርዕስ እንደሆነ ዘልቋል፡፡

የግንባሩን ውህደት በሚመለከት የመጨረሻው ውሳኔ በሐዋሳ ከተማ በተካሄደው የኢሕአዴግ 11ኛው ድርጅታዊ ጉባዔ ላይ ይተላለፋል ተብሎ የተጠበቀ ቢሆንም፣ ለውህደቱ ሲደረግ የነበረው ጥናት አልተጠናቀቀም በሚል ሰበብ ውሳኔ ተሰጥቶበታል፡፡

በዚህ ጉባዔ በጥናቱ ውጤት ላይ ተመርኩዞ የውሳኔ ሐሳብ እንዲያዘጋጅ ለኢሕአዴግ ምክር ቤት ሥልጣን የተሰጠው ሲሆን፣ ከሚያዝያ 7 እስከ 8 ቀን 2011 ዓ.ም. በተካሄደው የኢሕአዴግ ምክር ቤት ስብሰባ መግለጫ እምብዛም ሳይነሳ ታልፏል፡፡

ምንም እንኳን የምክር ቤቱ መግለጫ ስለውህደቱ ባያወሳም በአጀንዳነት እንዲወያይበት የተሰጠ ሲሆን፣ በበርካቶች ዘንድ የኢሕአዴግ ወደ አንድ ወጥ አገራዊ ፓርቲነት ማደግ ትኩረት የሚስብና ለውይይት የሚጋብዝ ርዕሰ ጉዳይ ከሆነ ቆይቷል፡፡

የኢሕአዴግ ውህደት በሁሉም ዘንድ ትኩረት ሊስብ የቻለበትን ምክንያት በሚመለከት ለሪፖርተር አስተያየታቸውን የሰጡት ዕውቁ ፖለቲከኛና የቀድሞ የኢዴፓ አመራር አቶ ሙሼ ሰሙ ለዚህ ሦስት ምክንያቶች አሉ ይላሉ፡፡

‹‹የመጀመርያው የብሔር አወቃቀር ሥርዓትን ትቶ አንድ ልሁን ማለቱ ነው፤›› የሚሉት አቶ ሙሼ፣ ኢሕአዴግ ከመነሻው ጀምሮ ይዞት የመጣውን የብሔር የፖለቲካ አደረጃጀት መዋቅር መቀየሩ አዲስ የፖለቲካ ሥርዓት ስለሚያስከትል ትኩረት ሊስብ የሚችል ነው ይላሉ፡፡

በሌላ በኩል የውህደቱ ትልም ዕውን ነው ወይ የሚለው እንደሆነ ያወሳሉ፡፡ ይኼም ከፓርቲው ልምድ፣ መርህና የአሠራር ዘዴ አኳያ ብሎም ካለው ጊዜ አንፃር ዕውን ሊሆን ይችላል ወይ የሚል ጥያቄ ስለሚያስነሳ ነው ሲሉ ያብራራሉ፡፡ በሦስተኛ ደረጃ ደግሞ የብሔር ፖለቲካን ለረዥም ጊዜ ሲያራምድና በጎራ አከፋፍሎ ሲያታግል የቆየ ፓርቲ፣ ይኼንን የሞት ሽረት ጉዳይ ነው የሚለውን አደረጃጀት ለመተው መወሰኑ አስደሳችና አነጋጋሪ ነው ይላሉ፡፡ በተለይም መሀል ላይ ያለውን የፖለቲካ ኃይል የሚያስደስት ነው ሲሉ ያክላሉ፡፡

የኢሕአዴግ ውህደት በግንባሩ  የተለያዩ የሥራ ኃላፊዎች በተደጋጋሚ ሐሳብ የተሰጠበት ሲሆን፣ የግንባሩ አባላትም ሆኑ አጋር ፓርቲዎች የሥነ ምግባርም ሆነ የአሠራር ሕገ ደንብ ተመሳሳይ ስለሆነ መዋሀዳቸው ጠቃሚ ነው በማለት ይናገራሉ፡፡ ይኼንንም የቀድሞ የግንባሩ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሽፈራው ሽጉጤ ሲገልጹ፣ ‹‹በሦስት ቋንቋዎች የተጻፈ አንድ ሕገ ደንብ ያለው ድርጅት ነው፤›› ብለው ነበር፡፡

መጋቢት 19 ቀን 2011 ዓ.ም. በጽሕፈት ቤታቸው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ስለጉዳዩ ተጠይቀው ማብራሪያ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)፣ የኢሕአዴግ አባል ፓርቲዎች ተመሳሳይ የውስጥ አሠራርና ዓላማ ስላላቸው መዋሀዳቸው ምክንያታዊ ነው ብለው ነበር፡፡

‹‹የኢሕአዴግ የውህደት ጥያቄ በጣም ረዥም ዓመታት ሲያጨቃጭቅ የኖረ ነው፡፡ አዲስ ጥያቄ አይደለም፡፡ በባህርይው ቅንጅት፣ ውህደት፣ ኅብረት የሚባል ነገር ታክቲካዊ ነው፡፡ ለዘለዓለም ውህደት፣ ኅብረት አይፈጠርም፡፡ ለዘለዓለም ቅንጅት አይባልም፡፡ ተቀናጅቶ የተወሰነ ከተጓዙ በኋላ መዋሀድ የፓርቲዎች ባህርይ ነው፤›› ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ‹‹እኛን የሚመለከት ሁሉም ፓርቲዎች አንድ ዓይነት የውስጥ አሠራር፣ አንድ ዓይነት ሐሳብና ዓላማ ያለን ስለሆነ ለረዘመ ጊዜ ግንባር ሆነን መቆየታችን ተገቢ አልነበረም የሚሉ ውይይቶች ይነሱ ነበር፡፡ እነዚያን ውይይቶች ከሐዋሳው ጉባዔ በፊት ጨርሰን በሐዋሳው ጉባዔ እንዲፀድቅ ነበር የቀደመው ጉባዔ አቅጣጫ ያስቀመጠው፡፡ ነገር ግን በመሀል ለውጥ በመደረጉ እኛም ሁለት ሦስት ወር ጊዜ ስላልነበረን ለጉባዔው አቅርበን ጉባዔው እስከሚቀጥለው ጉባዔ አትጠብቁ፣ ምክር ቤቱ ጥናቱ ሲያልቅ ማፅደቅ ይችላል ብሎ መልስ ሰጥቶናል፡፡ ማፅደቅ ያለበት ጉባዔው ነው፣ ግን ለኢሕአዴግ ምክር ቤት ሰጥቷል፤›› ሲሉ ሒደቱን አብራርተዋል፡፡

ጥናቱ የተለያዩ ምሁራንን በማካተት እየተሠራ እንዳለ የሚታወቅ ሲሆን፣ ለምክር ቤቱ ቀርቦ ሲፀድቅ ወደ ተግባር ይገባል ተብሏል፡፡

ኢሕአዴግ እንደሚለው ወደ አንድ ፓርቲ የሚዋሀድ ከሆነ ሌሎች በብሔር የተደራጁ ኃይሎች የሚኖራቸው ሚና ጉልህ እንደማይሆን፣ ሊኖሩ የሚችሉት እንኳን በብሔር መደራጀት የማይከላከል ከሆነ ነው ሲሉ አቶ ሙሼ ያስረዳሉ፡፡

‹‹ያ አጀንዳ የትግል አጀንዳ መሆኑ ይቀራል፡፡ ሥር ነቀል ለውጥ ነው የሚያካሂደው፤›› ያሉት አቶ ሙሼ፣ ይኼንን አስተሳሰብ ደግፈው ሲታገሉ በነበሩ ኃይሎች ላይ ተፅዕኖው የጎላ ነው ይላሉ፡፡ ‹‹ኢሕአዴግን በዚህ ምክንያት ሲጣሉና ሲርቁ የነበሩ ኃይሎች በዚህ ዙሪያ ይሰባሰባሉ፤›› በማለትም ይገልጻሉ፡፡

ነገር ግን ኢሕአዴግ ወደ አንድ አገራዊ ፓርቲ ይዋሀዳል ማለት የብሔር ፖለቲካን ያስቀራል ማለት እንዳልሆነ፣ የኢሕአዴግና የሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል አቶ ጌታቸው ረዳ ይከራከራሉ፡፡

‹‹ሐሳብ ያለው ኢሕአዴግ መኖር አለበት፡፡ ለሥልጣን ሲባል የሚሰበሰብ ቡድን ሳይሆን በርዕዮተ ዓለም ላይ የተመሠረተ ውህደት መኖር አለበት፤›› የሚሉት አቶ ጌታቸው፣ የብሔር ፖለቲካን ማስቀረት የሚለውን ሐሳብ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች በጋራ ይታገሉታል በማለትም ያስገነዝባሉ፡፡

‹‹ለሚቀጥሉት 30 እና 40 ዓመታት የብሔር ፖለቲካ ይቀራል፣ በብሔር የተደራጁ ፓርቲዎች አይኖሩም የሚል ካለ ሞኝ ነው፡፡ ይቀጥላል አማራጭ የለውም፡፡ ከአገራዊ ሁኔታው የተነቀለና የተለየ ሰው ብቻ ነው ይኼንን የሚለው፤›› በማለት ያስረግጣሉ፡፡

በብሔር ላይ የተመሠረተ የፖለቲካ አደረጃጀት በሕግ ቢከለከል እንኳን፣ ‹‹ሕጉን እኛ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እናፈርሰዋለን፤›› የሚሉት አቶ ጌታቸው፣ ‹‹የብሔር ፖለቲካን የኢሕአዴግ ውህደት ሊያስቀር አይችልም፡፡ በዚህ ከተነሳ የውሸት ኢሕአዴግ ነው ማለት ነው፤›› ይላሉ፡፡

አቶ ሙሼ ሰሙ ግን ኢሕአዴግ አንድ ወጥ አገራዊ ፓርቲ ሆኖ የብሔር አደረጃጀት ሊኖረው አይችልም ሲሉ ይከራከራሉ፡፡ በዚህ ምክንያት ግን በኢሕአዴግ ውስጥ የጎራ መደበላለቅ እንደሚኖርና ከውስጥና ከውጭ አዳዲስ ትግሎችን ሊቀሰቅስ እንደሚችል ያወሳሉ፡፡

ሆኖም በአባል ድርጅቶች ውስጥ መተማመን ጠፍቶ ጥርጣሬ በነገሠበትና የሐሳብና የተግባር አንድነት በሌለበት ሁኔታ ውህደቱ የሚታሰብ እንዳልሆነና በእሳቸው አስተያየት የመሆን ዕድል እንደሌለው፣ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ሊቀመንበር ደሳለኝ ጫኔ (ዶ/ር) ያስረዳሉ፡፡ እንዲያውም አሁን ያለው የውህደት ሐሳብ የጠቅላይ ሚኒስትሩ እንጂ የፓርቲው እንደማይመስላቸው ይገልጻሉ፡፡

‹‹በፓርቲዎች መካከል መጠራጠር እንዳለ ዓይተናል፡፡ በቅርቡ የተጠናቀቀው የኢሕአዴግ ምክር ቤት ስብሰባ መግለጫም ይኼንኑ ነው ያረጋገጠልን፤›› ይላሉ፡፡

የኢሕአዴግ ምክር ቤት ለሁለት ቀናት ካካሄደው ስብሰባ በኋላ ባወጣው መግለጫ፣ በግንባሩ አባል ድርጅቶችና በአመራሩ መካከል የሚታየውን መጠራጠር መፍታት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መምከሩን ገልጿል፡፡

‹‹ምክር ቤቱ በእህት ድርጅቶችና በአሠራሩ መካከል የሚታየውን መጠራጠር በመፍታት፣ የአስተሳሰብና የተግባር አንድነት ማምጣት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መክሯል፡፡ ከዚህ አኳያ መታረምና መስተካከል ያለባቸው ነጥቦች ላይ ፍጹም በሆነ መንገድ ሐሳብ እንዲንሸራሸርና በመጨረሻም አገርንና ሕዝብን ማዕከል ያደረጉ ጉዳዮች ላይ መግባባት ተፈጥሯል፤›› ሲል ምክር ቤቱ በመግለጫው አስታውቋል፡፡

ነገር ግን በፓርቲው አባል ድርጅቶች መካከል የውህደት ጥያቄው እኩል ተቀባይነትና ፍላጎት አይታይበትም፡፡ በቅርቡ የሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ ባወጣው መግለጫ፣ ‹‹ኢሕአዴግ ከሚታወቅበትና ከሚለይበት መሠረታዊ እምነቶች እያፈነገጠ፣ የአገሪቱን እውነታ ወደ ጎን በመተው ቅጥ ያጣ ደባል አመለካከት እየተበረዘ የፌዴራል ሥርዓቱ አደጋ ውስጥ የሚያስገባ አስተሳሰብ ተፈጥሯል፤›› ሲል ወቅሷል፡፡

ኢሕአዴግ በቅርብ ዓመታት ጀምሮት የነበረው በጥልቀት የመታደስ ጉዞ መኮላሸቱን የጠቆመው የሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ መግለጫ፣ ይኼንን ወደ ትክክለኛው መንገድ ከመመለስ ይልቅ ኢሕአዴግን አዋህዶ አገራዊ ፓርቲ ማድረግ አማራጭ ተደርጎ እየተወሰደ እንደሆነ ያትታል፡፡

‹‹በመሠረቱ የፓርቲ ውህደት ጥያቄ በተለያዩ ጊዜያት ሲነሳ የነበረና በጥናት እንዲመለስ አቅጣጫ ተቀምጦ እንደነበር ግልጽ ነው፡፡ ይኼ አቅጣጫ የተቀመጠው ደግሞ ኢሕአዴግ ጤናማ በነበረበት፣ በመሠረታዊ የድርጅቱ እምነቶችና መስመር ላይ ፅኑ እምነት በነበረበትና ምንም መሸራረፎች ባልነበሩበት ወቅት ነው፡፡ ይሁን እንጂ የደፈረሰና ጉራማይሌ አመለካከትና እምነት የያዘ ኢሕአዴግ፣ አይደለም ለውህደት ከዚህ ቀደም ለነበረው አደረጃጀቱም የሚሆን የአስተሳሰብና የተግባር አንድነት የሌለው ኢሕአዴግ ነው ያለው፡፡ በሁሉም መሠረታዊ ጥያቄዎች የፕሮግራም፣ የስትራቴጂና የመለያ እምነቶች በእህት ድርጅቶች መካከል አንድ የሚያደርግ አቅጣጫ በሚጋለጥበት ውህድ አንድ ፓርቲ ሊታሰብ የሚችል አይደለም፤›› ሲል መግለጫው የፓርቲውን አቋም አንፀባርቋል፡፡

ይኼ የሚሆን ከሆነም ያለውን ችግር የሚያባብስ እንጂ መፍትሔ ሊመጣ አይችልም ሲል ያትታል፡፡

ኢሕአዴግ ለውህደት የሚወስደው ዕርምጃ የፖለቲካ ምኅዳሩን ሊያሰፋው እንደሚችል፣ የብሔር ፖለቲካ የሚገራበት ዕድል እንደሚሆንም አቶ ሙሼ ያስረዳሉ፡፡ የኢሕአዴግ ችግር ብሔር ላይ ያለው ከፍተኛ ትኩረትና የራሱ አፋኝና ጨቋኝ ባህርያት መሆናቸውን የሚያወሱት አቶ ሙሼ፣ ‹‹ለሌሎቹ የፖለቲካ ፓርቲዎች ዕድል ነው ይዞ የሚመጣ የርዕዮተ ዓለም ትግል ነው የሚፈጠረው፤›› ሲሉም ተስፋ ያደርጋሉ፡፡

እስካሁን ክልሎችን በቁጥጥር ይዞ ሲያሸንፍ የነበረን ፓርቲ ለመጋፈጥ የሚያስችላቸውን የርዕዮተ ዓለም የውድድር መድረክ ይፈጥራል ባይ ናቸው፡፡

ብሔርን መሠረት ካደረገው አደረጃጀቱ በተጨማሪ የኢሕአዴግ ተፈጥሯዊ የሆነው አምባገነን፣ ጨቋኝና አፋኝ የሆነው ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት ለዴሞክራሲ ምኅዳሩ መጥበብ ምክንያት መሆኑን የሚያምኑት ደሳለኝ (ዶር) በበኩላቸው፣ የፖለቲካ ምኅዳሩን ለማስፋት የኢሕአዴግ የብሔር አደረጃጀትና ባህርይው ላይ ለውጥ ሊመጣ ይገባል ይላሉ፡፡

‹‹ነገር ግን የብሔር አደረጃጀት እንዲቀር ስለተፈለገ ብቻ አይቀርም፡፡ ሕገ መንግሥቱን ከማሻሻል ይጀምራል፤›› ሲሉም ያስረዳሉ፡፡

ይሁንና መጋቢት 7 ቀን 2011 ዓ.ም. በወጣው አዲስ ዘመን ጋዜጣ ሐሳባቸውን በቃለ መጠይቅ የገለጹት የኢሕአዴግ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፍቃዱ ተሰማ፣ ሕወሓት እንደ ድርጅት ከውህደት እወጣለሁ የሚል አቋም እንዳላሳየ በመግለጽ፣ ‹‹ማንኛውም ድርጅት በውህደቱ አግባብ ላይ ነፃ ፍላጎቱ የሚጠበቅ እንደመሆኑ፣ መዋሀድም ሆነ አለመዋሀድ መብቱ ነው፡፡ ስለዚህ ውህደቱ ከልብ በሚቀበሉት ተግባራዊ ይሆናል፤›› ብለዋል፡፡

የኢሕአዴግ ውህደት የማይሳካ ከሆነ ግን ይላሉ ደሳለኝ (ዶ/ር)፣ ድርጅቱ ተሰንጥቆ ከግንባሩ የሚወጡና ወደ ግንባሩ የሚገቡ አዳዲስ ፓርቲዎች እንደሚኖሩ ይገምታሉ፡፡