April 22, 2019

የአገራችን ነገር ብዙ ስሱ ነገሮች ስለሚበዙበት በአንዳንድ ነገሮች ላይ አስተያየቴን ከመስጠት እቆጠብ ነበር። ዛሬም ተመሳሳይ ነገር ገጥሞኝ ነበር። አቶ አዲሱ አረጋ (የኦዲፒ ማዕከላዊ ጽ/ቤት ሃላፊ) አምቦ ላይ ”የቡርቃ ዝምታ” የተሰኘውን መጽሐፉን አስመልክቶ “ገንዘብ ተከፍሎት፣ አማራና ኦሮሞን ለማጋጨት የጻፈው ነው” ብለው ነበር።

ስለአቶ አዲሱ አባባልም፤ ስለቡርቃ ዝምታ መጽሐፍም እስኪ ይደር ብዬ ትቼው ነበር። አቶ ተስፋዬ ገ/አብ ግን ከሰዓታት በፊት በfb ገጹ የለቀቀውን(ከስር ያያያዝኩት) አይቼ ዝም ማለት አልቻልኩም።

አቶ ተስፋዬ ለአቶ አረጋ በሰጠው ምላሽ ሲጀምር የእሱ ጽሑፍ “ነፍጠኞችን የሚያንበረክክ ከሆነ…” ይላል። በተጨባጭ እሱ በሚያነሳው አውድ እነዚያ “ነፍጠኞች” በዛሬይቱ ኢትዮጵያ የሉም። በትንሹ የዛሬ 45 ዓመት ወደ ቤተመዘክር የገባን ፊውዳላዊ ሥርዓት አስታኮ “ነፍጠኛ” እያሉ ሙሾ ማውረድ ሰሚውን ዝቅ አድርጎ መመልከት ነው። አንሶ ማሳነስ ነው።
በእርግጥ ዛሬም እንኳ ይህን በዘመናዊው አስተሳሰብ አፍራሽ የሆነና በተጨባጭ ዘመኑን የማይዋጅ አገላለጽ “ነፍጠኛ ነኝ” በማለት እልህ እያጋቡ ያሉ ወገኖች እንዳሉ አውቃለሁ። ማን እንደላካቸው፣ ምን እንደሚፈልጉ፤ ምንስ እንደሚጠቅም አላውቅም። (በቀናነት ይህን የሚያደርጉ እንዳሉ ሆኖ)

አቶ ተስፋዬ አቶ አዲሱን “ከጥቂት ወራት በፊት ወደ ፊንፊኔ እንድመጣ ተማጽነኸኛል” ይላል። ሊሆን ይችላል ብዬ ላልፈው ስል ለጠ/ሚ/ር ዓብይም ተመሳሳይ ነገር ይላል። “አብይ አሕመድ ወደ አዲስ አበባ ከነባለቤቴ ለምነህ አስመጥተኸኝ ለምን ስብጠለጠሌ ዝም ትላለህ?” ይላል። ልብ በሉ ያኛውን “ፊንፊኔ” እኒህኛውን “አዲስ አበባ” ተማጽናችሁ፣ ለምናችሁኝ ይላል። በኢትዮጵያ ባሕል አንድ ግለሰብ የአገር መሪን እንዲህ አብጠልጥሎ አይጠራም። በአፋን ኦሮሞ Safuu! (ተገቢ ያልሆነ) ይባላል።

ክቡር ጠ/ሚ/ር ዓብይ አቶ ተስፋዬን ወደኢትዮጵያ እንዲመጣ ሊጋብዙት ይችላሉ፤ እሱን የሚያስለምን ነገር አላቸው ብዬ ለማመን ግን አዕምሮዬ ይቸገራል። የመሆን ዕድሉ 5% አከባቢ ነው። ታዲያ የአገሪቱን መሪ በዚህ መንገድ ለምን ዝቅ ማድረግ ፈለገ?
‘በቅርቡ ስለመጪው ዕጣችን በሚሌኒየም አዳራሽ እንወያያለን’ ይላል። የማንና የማን ዕጣ? ስለዕጣ ፈንታ የሚወስንልን ሰው …
#የመጨረሻ ቃል!
አቶ ተስፋዬ ገ/አብ “የእኔ መመኪያ ቄሮ ነው እንጂ ለነፍጠኛ የሚሽኮረመመው አዲሱ ወይም ሽመልስ (የኦሮሚያ ም/ፕሬዝዳንት) አይደለም” ይላል። ቄሮ ወይም ወጣቱ ትውልድ የሕዝቡ መመኪያ ነው። አምባገነኖችን በአናታቸው ያቆመ፣ ጭቆናን የደረመሰ የሕዝብ ልጅ ነው።
የአገሪቱን መሪዎች ከላይ እስከታች ተቆንጥጦ እንዳላደገ ጎረምሳ እየዘረጠጡ፤ “ቄሮ መከታዬ” እያሉ መቅለስለስ አስተዋይ አዕምሮ ላለው አስገራሚ ተምኔት ይሆናል። የቀድሞው የአገራችን ርዕሰ ብሔር ዶ/ነጋሶ ጊዳዳ የአቶ ተስፋዬን አካሄድ ካጤኑ በኋላ “ከኦሮሞ በላይ ኦሮሞ ለመሆን የሚፈልግ” ያሉት ለምን እንደሆነ የገባኝ አሁን ነው።
ኢትዮጵያውያንን ኦሮሞና አማራ በሚል ለመከፋፈል መሞከር አስጸያፊ ብቻ ሳይሆን ወንጀል ነው። አማራና ኦሮሞ እንደሚባለው የተሳሰሩ፣ አብረው የኖሩና በየወንዙ የሚማማሉ፤ በግራና በቀኝ የተሰለፉ ሃይሎች ሳይሆኑ ከአንድ ምንጭ የመነጩ፣ የአንድ አያት ልጆች ናቸው። በቅርቡ በስፋት እመለስበታለሁ። ከዚህ ያፈነገጠ ዋሾ ከሃዲ ነው። ከባሕሉ አፈንግጠህ አጉል የምትብለጠለጥበት ቄሮ እንዲህ ይልሃል፦
Gantuu karaa gadhiisi! Qeerroon mataa isaa hin dadhabu! Oromoon jaalala malee; jibba,Tokkummaa malee; garaagarummaa barsiisee hin beeku!እንዲህ ማለት ነው፦

ከሃዲ ዞር በል! ቄሮ ለራሱ አያንስም ! ኦሮሞ ፍቅርን እንጂ ጥላቻን፣ አንድነትን እንጂ ልዩነትን አስተምሮ አያውቅም!
#ጥላቻ፣ ቁርሾ፣ መለያየትና ቅጥረኝነት ይጥፉ!!!

እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ያስብ፤ ሕዝቧን ይባርክ

እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ያስብ፤ ሕዝቧን ይባርክ!