April 21, 2019

- የአኖሌና ጨለንቆ የታሪክ እውነት በአጭሩ እንደወረደ፡፡ አዲሱ አረጋ የተናገረው እውነት ያስደነገጣቸው ፌስቡኩን በጦርነት ሞልተውታል፡፡ እስኪ ከታች እኔም ከማውቀው እውነት ልጨምርላችሁ፡፡ አደለም የሚል እንግዲህ ተጨባጭ ማስረጃ ካለው ያቅርብ፡፡
- የአርሲ ጦርነት ማንነትን መሠረት ያላደረገ ሲሆን የጨለንቆው ጦርነት ከእነጭርሱም በሚኒሊክ ወታደሮችና በሐረሪው ኢሚር መካከል የተደረገ ጦርነት ነበር እንጂ ከኦሮሞ ባለአባት ጋርም አልነበረም፡፡ ጦርነቱም የአንድ ቀን ምን አልባትም ከ6 ሰዓት ያልበለጠ ጦርነት ነው፡፡
- እውነቶች ሳይሸራረፉ እንደወረዱ በሚኒሊክ መዋዕለ ዜና አሉ፡፡ ሚኒሊክ በአርሲ ጦርነት በማዘናቸው ከጦርነት በኋላ ወታደሮቻቸው ሕዝቡን ከመሬቱ እንዳያፈናቅሉ በወታደሮቻቸው ላይ አርሲ ባለማወቅ ብዙ ተጎዳ አሁንም አሸንፌዋለሁ ብለህ ከመሬቱ እንዳታፈናቅለው ሌላም በደል እንዳታደርስበት የሚል አዋጅ አውጥተው ነበር፡፡ በወቅቱ አሸንፎ የገባ መሬት ይቀማል ሰዎችንም አገልጋይ የማድረግ ልማድ ነበርና፡፡
- በሚኒልክ አገርን አንድ የማደረግ ሂደት ከአርሲና ወላይታ በቀር ይሄ ነው የሚባል ጦርነት አልነበረም፡፡ ኦሮሞን አስመልክቶ ግን የጅማው አባጂፋር፣ የወለጋና ከፊል ኢሉ አባቦራው ቦረዳ በከሬ ተባባሪ ሲሆኑ የሸዋው ገበና ከሚኒሊክ ጋር በዋናነት ተሳታፊ ነበሩ፡፡ ቦረና በሚኒሊክ ዘመናዊ አስተዳደር የገዳ ሥርዓት የሚመራው ሲሆን ከኢንግሊዝም የተረፈው በሚኒሊክ በመሆኑ ለሚኒሊክ ትልቅ ፍቅር ነበረው፡፡ እስከዛሬም የቦረና አባቶች ይሄን የሚናገሩ አሉ፡፡ ለዚህ ተስፋዬ ገብረአብ ሳይሆን የገዳውን ተመራማሪ ፕሮፌሰር አስመሮምን አንብቡ ጠይቁ፡፡ ገዳን ሚኒሊክ እንዴት እንዳዳኑት አስመሮምን ላስደምጣችሁ፡፡ https://streamable.com/bpkxt
- በኢትዮጵያ ሥር ከተጠቃለሉ በኋላ በጦርነት ሳይቀር የገቡት ለሚኒሊክ ትልቅ ፍቅር ነበራቸው፡፡ ጦርነቶችም በአለማወቅ እነጂ ሚኒሊክ ሊጎዷቸውና መሬታቸውን ሊቀሙ እንዳልነበር ሁሉም ተረድቶ ነበር፡፡ ኢትዮጵያን አንድ በአደረጉ ጥቂት አመታት ነበር አደዋን ድል ለማረግ ሁሉም ከጎናቸው የቆመው፡፡ ሕዝቡ በሚኒሊክ ያለው እምነት ትልቅ ነበርና፡፡
- የሚኒሊክ አስተዳደር ፍጹም ፌደራላዊ የሚባል አይነት ነበር፡፡ ነገሮች የተበላሹት ከዛ በኋላ ነው (በኃይለ ሥላሴ በተለይ)፡፡
ከሁሉ በፊት አንደ እናቴ የነገረችኝን አስተማሪ ታሪክ ልንገራችሁ፡፡ አንዱ በጣም የሚወደው ልጁ ይሞትበትና እጅግ ያዝናል፡፡ ይህ ሰው አንድ በጣም ወዳጄ ብሎ የሚያምናቸው ሁለት ጎረቤቶች አሉት፡፡ ከጎረቤቶቹ አንዱ ተንኮለኛና ምቀኛ ነበር፡፡ ልጁ የሞተበት ሰው በጣም ማዘን ስላወቀ ስለልጁ እንዲያዝንና ራሱንም እንዲጥል ያ ተንኮለኛ ጉረቤቱ ልጁ የሞተበትን ሰው ባገኘ ቁጥር “እንዴት ያለ ጀግና ልጅ አጣህ ድንቅ ልጅ ነበር፡፡ ምን ያደርጋል ሞት ነጠቀህ ……” እያለ የልጁን ሀዘን እየቀሰቀሰበት ሰውዬውን ሥራ በማይችልበት ደረጃ በሐዘን እንዲማቀቅ ያደርገዋል፡፡ ይሄን ያውተዋለው ሌላኛው ጎረቤቱ ልጁ ለሞተበት ቤቱ ይሄድና ለመሆኑ ይሄ ጎረቤትህ (ተንኮለኛውን) ምን ከሀዘን እንዳትወጣና አንትም ሥራ ባለመሥራት በችግርና በሐዘን እንድትሞት ሆን ብሎ ሀዘንህን እየቀሰቀሰብህ እንደሆነ ታስተውላለህ? ወዳጄ ሆይ የሞተው ልጅህ ወደ አንተ አይመጣም አነት ወደሱ ትሄዳለህ እንጂ፡፡ ይልቅስ በሐዘን ምክነያት መሥራት ሳትችል አንትም በችግርና ሐዘን ትሞታለህ ቀሪ ልጆችህንም ታጣለህ፡፡ ጥሩ አደለም፡፡ ወዳጄ ነው ብለህ ያዘነልህ መስሎህ እንድትሞት ሆን ብሎ እያደረገህ ነውና አስተውል ይለዋል፡፡ ልጁ የሞተበትም የጥሩ ጎረቤቱን ምክር ሰማ አስተዋለ፡፡ ከሀዘኑም ተመለሰ፡፡ የተስፋዬ ገ/አብን የቡርቃው ዝምታ ባስታወስሁ ቁጥር በተስፋዬ ገ/አብ የተንኮል ትርክት የተጠለፉ ብዙ ኦሮሞ ከደቂቅ እስከ ሊቅ ይታሰቡኛል፡፡
የአኖሌ ጦርነት ታሪክ በአጭሩ እውነቱ እንዲህ ነው፡፡ በመጀመሪያ አጼ ሚኒሊክ ማንንም ሰው በማንነቱ አልወጉም፡፡ ከዚህ ይልቅ አጼ ሚኒሊክ የሚታወቁበት በጦርነት እንኳን አሸንፈው አሸነፍኩት ብለው ጮቤ የሚረግጡ ወይም ተሸንፈሀልና ብለው መከራ የሚያደርሱ መሪ አልነበሩም፡፡ የአጼ ሚኒሊክ ልዩ ስኬቶችም ከዚህ ባሕሪያቸው የመነጨ ነው፡፡ ስለ አኖሌ ስናነሳ የኦኖሌ በአጠቃላይ አርሲ ጦርነት የተደረገው አገርን በአንድ አደርጋለሁ ብሎ በተነሳ በአጼ ሚኒሊክ በሚመራ ኃይልና በወቅቱ በአርሲ በነበሩ ባላባቶች መካከል እንጂ በሚኒሊክ (ብዙዎች አንደሚያስቡት አማራ)ና ኦሮሞ መካከል አደለም፡፡ በወቅቱ በፐርሰንት መግለጽ ቢያስቸግርም ግን ይበልጠው የሚኒሊክ ጦርና ባለሟል ዛሬ ኦሮሞ ተብሎ ከሚጠራው ማህበረሰብ ናቸው፡፡ የውጊያውም አላማ ምንም አይነት ከማንነት ጋር የተያያዘ ነገር የለውም፡፡ በሠላም አገር አንድ የማድረግ ሂደቱን የተቀበለ በሰላም ይዋሃዳል ያልተቀበለ ጦርነት ገጥሞ ተሸንፎ በግድ ይዋህደ ነበር፡፡ ግዛት ማስፋፋት የሁሉም ባላባቶች ሥራ ነው፡፡ የሚኒሊክን ለየት የሚያደርገው ዛሬ ኢትዮጵያ ብለን የምንጠራትን አገር ከአካባቢ ግዛቶች አልፎ በትልቅ አገርነት ዛሬ ኢትዮጵያ ብለን የምንጠራትን አገር መመሥረት ላይ መሆኑ ነው፡፡ ጦርነት ከታሰበ ብዙ አስከፊ ጦርነቶች በመሳፍንቶች ተካሂደዋል፡፡ የሆነ ሆኖ የአርሲ ጦርነት ምንም ከኦሮሞነት ጋር የተያያዘ ታሪክ የለውም፡፡ ጦርነቱ ግን አስከፊ መሆኑን እናውቃለን፡፡ በዚህም ከጦርነቱ በኋላ በጠፋው ሰው ብዛት ሚኒሊክ እጅግ አዝነውም ነበር፡፡ ከዛም የተነሳ በወቅቱ በተለመደው ባህል በጦርነት አሸንፎ አንድን ቦታ የያዘ የተሸነፈውን መሬቱን ይወስድበትና የራሱ አገልጋይ ያደርግ ነበር፡፡ ሚኒሊክ በሕዝቡ ሞት እጅግ አዝነው ስለነበር ዳግም ደግሞ በወታደሮቻቸው ሌላ በደል እንዳይፈጸምበት አዋጅ አውጥተው ነበር፡፡ አዋጁም እንዲህ የሚል ነበር፡፡ የአሩሲ ሰው ባላወቀው ነገር ጦርነት እገጥማለሁ ብሎ እጅግ ተጎዳ፡፡ አሁን ግን አሸንፌዋለሁ ብለህ ከመሬቱ እንዳታፈልሰው ሌላም በደል እንዳታደርስበት አዝዣለሁ ብለው በወታደሮቻቸው ላይ አዋጅ አውጥተው ነበር፡፡ ይሄ ነው እውነቱ፡፡
ሌላው ከአኖሌ ጋር ተያይዞ የሚወራው የጡት ቆረጣ ነው፡፡ በእውነት ይሄን ትርክት ከየት ከየት እንደመጣ አላውቅም፡፡ በወንዶች ላይ የእጅ ቆረጣ በዛ ሌላም አካል ማጉደል በዛ ዘምን ሊሆኑ ከሚችሉ ጥፋቶች ናቸው፡፡ የጡት ቆረጣን ይቅርና ሴትን መግደል ራሱ ነውር አንደውም እንደሴት (ፈሪ) የሚቆጠርበት ነው፡፡ ከዛም በላይ በተለይ በሚኒሊክ በአደጉበት ማሕበረሰብ ሴትን አልፎ ሌላ ወንድ ላይ ራሱ ጥቃት መፈጸም ነውር ነው፡፡ ሁለት ሰዎች ለግድያ ተሰልፈው መሀል ሴት ከገባች ጥላቸወን ለጊዜው አቆመው መጋደልም ከሆነ ሌላ ጊዜ ጠብቀው ነው የሚጋደሉት፡፡ የሆነ ሆኖ ግን የሴት ልጅን ጡት ቆረጡ ተብሎ የሚወራው ሴራዊ ትርክት እንጂ እውነት አደለም፡፡ የአርሲ ጦርነት ግን በእርግጥም ከላይ እንደነገርኳችሁ ነው አስከፊነቱ፡፡ የአርሲው የጦር መሪ/ዎች ማን አንደነበሩ በታሪክ አልተጻፈም፡፡ በተመሳሳይ አስከፊ የሚባል ጦርነት በወላይታ የነበረው ጦርነት ነው፡፡ ይሄን ጦርነት የተደረገው በአካባቢው በንጉስነት (ካኦ) ከሚታወቁት ከንጉስ ጦና ጋር ነው፡፡ በመጨረሻም ጦርነቱ አሁንም በሚኒሊክ ተዋጊዎች ድል አድራጊነት ተጠናቆ እንደ እድል ጦናም በሕይወት ተማረኩ፡፡ ጦና ሲማረኩ ቆስለው ስለነበር ሚኒሊክ ሌላ ሰው ስላላመኑ እንዲታከሙና እንዲያገግሙ ያደረጉት በራሳቸው ቁጥጥር በሚታዘዙ ሰዎች ነበር፡፡ ጦናም ዳኑ ሚኒሊክም ዓላማቸውን ለጦና ነገሯቸው ጦናም ጦርነቱን በአለማወቅና አገር እነጠጋለሁ ብለው የተዋጉት መሆኑን አምነው ሚኒሊክ በነበረ ንግስናቸው አገራቸውን እንዲያስተዳድሩ ጦናን ሾሙ፡፡ በትልቋ ኢትዮጵያ ሥር መሰበሰብን እንጂ ስልጣንህንም ሆነ አገርህ የራስህ ግዛት ሆኖ ይቀጥላል ብለው አስረዷቸው፡፡ እንግዲህ ከላይ እንዳልኩት የአርሲዎቹ የጦር መሪዎች ወይም አንድ ሰው ሊሆን ይችላል ሞቶ ከሆነ አላውቅም፡፡ ሚኒሊክ ከጦርነትም በኋላ በብዙ ቦታዎች የሚሹሙት ጦናን እንደሾሙት ነው፡፡ ያም ሆኖ ከእነዚህ ሁለት በታሪክ ከምናውቃቸው ጦርነቶች ውጭ ዛሬ እንደሚነገረው የከፋ ይቅርና ይሄ ነው የሚባል ተቃውሞ እንኳን ሚኒሊክ አልገጠማቸውም፡፡
የጨለንቆን አረሳሁትም እመጣበታለሁ፡፡ከላይ ከአነሳሁት የሚኒሊክ መስፋፋት ከሚታወቁ አንድ እውነት ልንገራችሁ፡፡ ነገሩ ትንሽ ፈገግ ሊያደርግም ስለሚችል፡፡ የሚኒሊክ ጦር አርሲን አሸንፎ ወደ ባሌ እየተስፋፋ በሚሄድበት ወቅት ባሌ ሮቤ አካባቢ ሲደርስ ሻያ የሚባል ወንዝ ሞልቶ ያገኛል፡፡ ባሌዎች ከወዲያ ማዶ ጦርና ጎራዴያቸውን ይዘው የሚኒሊክን ወታደር ሊሞክሩ አስበው ከማዶ ተሰልፈዋል፡፡የሚኒሊክ ወታደር አንዱ ማዶ፡፡ ባሌዎች ወንዙን በደንብ የሚያውቁትና ዋናም የሚችሉ ነበሩና ተሻግረውም ለመዋጋት ያስባሉ ግን ወታደሩ የሚያስፈራ ነበርና እዛው ማዶ ቆዩ፡፡ ግን ብዙም ሳይቆዩ የሚኒሊክ ወታደሮች በሆነ በሚያስፈራ ድምጽ ከማዶ ሆነው ባሌዎችን መግደል ጀመሩ፡፡ ባሌዎች ለዚህ ነገር ፍጹም እንግዳ ናቸው፡፡ በምን ተዓምር እየተመቱ እየወደቁ እንደሆነ ሊገባቸው አልቻለም፡፡ ብቻ አንድ ኃይለኛ ድምጽ ከተሰማ በኋላ የሆነ ሰዋቸው ይወድቃል፡፡ ከዛ “ሲላ በከካdhan ኑፊጣ ጂረን?” በመብረቅ እየፈጁን ነው እንዴ በለው ጥለው ይሸሻሉ፡፡ ይሄን ታሪክ የሚነግሩን አባቶቻቸው በዛን ወቅት የሆነውን የነገሯቸው የዛሬ አዛውንቶች ናቸው፡፡ ከዚህ ያለፈ ጦርነት ብሎ ነገር የለም፡፡ ይሄንንም የሚያወሩት አንደው የነበረውን እውነት አንደ መዝናኛም ነው እንጂ በቁጭትም በንዴትም አደለም፡፡ እንግዲህ ባሌዎች ቆመህ ጠብቀኝ መሣሪያ እንዳለ አያውቁም እነሱ ጠብቀው የነበረው በጦር እንፋለማለን ብለው ነበር፡፡ እንግዲህ እንዲህ ያሉ ከአሳዛኝነታቸው ይልቅ አስቂኝ (ሁሉም አሳዛኝ ነው ግን ራሳቸው ተዋጊዎቹም የሚያስቃቸው እውነት ስለሆነ ነው) የሆኑ ግጭቶች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡
እንግዲህ ከእንደነዚህ አይነት ውጭ የከፋ ጦርነት አልነበረም፡፡ አንዳንዶች በውጭ ሰው ተጻፈ ብለው ሪፈር ሊያደርጉ ይሞክራሉ፡፡ ከውጭዎቹ በላይ እውነቱን ምንም ሳይሸሽግ የሚኒሊክ መዋዕለ ዜና ይናገረዋል፡፡ እንግዲህ ታሪክን እንወቅ ከተባለ ምንም የተደበቀ ነገር የለም፡፡ ከአርሲ ጦርነት ውጭ ግን ዛሬ ኦሮሞ የተባለው ሁሉ የሚኒሊክና ጎበናን የአገር አንድ ማድረግን የተቀላቀለው በውዴታ ብቻም ሳይሆን በተባባሪነት ጭምር ነው፡፡ የምዕራቡ ቦረዳም በከሬም ሆነ አባ ጅፋር የሚኒሊክ ወዳጆች ነበሩ፡፡ ቦረዳ ዛሬ ወለጋና ኢሊ አባቦራን በከፊል የሚያስተዳድሩ ነበሩ፡፡ ቦረዳ ከደርቡሽ (ሱዳን) ጦርነት በገጠማቸው ጊዜ ጎበና ከሸዋ ሄደው የደርቡሽን ጦር ድል አድርገው የቦረዳን ግዛት አስጠብቀዋል፡፡ ቦረና ይተዳደር የነበረው በገዳዎች ነበር፡፡ እነ ቦረዳና ጎበና አንዲሁም አባ ጂፋር የገዳ አስተዳደር እንዳላቸው አላውቅም፡፡ ይልቁንም የእነሱ አስተዳደር የባላባት አይነት ነበር አንጂ፡፡ ቦረና ግን እንደዛ አልነበረም፡፡ በገዳ ይመራ ነበር እንጂ፡፡ ሁለት ገዳዎች ነበሩ፡፡ ሚኒሊክ በቦረና አስተዳደር ወኪል ማስቀመጥ ፈልገው የገዳ መሪዎች በየ8 ዓመት ስለሚቀያየሩ አስቸጋሪ ሆነባቸው፡፡ በኋላ ግን ቃሉዎቹ በየጊዜው ስለማይቀየየሩ ለአስተዳደሩ ተስማሚ ሆኖ ተገኙ፡፡ የውስጥ ሥርዓቱ እንዳለ ሆነ በኢትዮጵያ አስተዳደራዊ ጥላ ሥር ለመሆን ነው ይሄ፡፡ ያም ሆኖ ግን ቃሉዎቹም ልክ እንደገዳው ሁለት ነበሩ፡፡ ይሄ ማለት ግዛት ተከፋፍለው ሳይሆን በአንድ ቦታ ሁለት ማለት ነበር፡፡ አንዱን ቃሉ ሚኒሊክ እንዲያስተዳደር ሲጠይቋቸው ቃሉው በሥርዓታቸውን ሁለት ቃሉ ነው ያለን እኔ ብቻዬን መሾም አልችልም ይላሉ፡፡ ሚኒሊክም በዚህ ነገር ተገርመው እንዴት ብቻህን ስሾምህ ሌላ ሰው ስልጣንህን እንዲጋራ ትፈልጋለህ ስሏቸው ቃሉው ሥርዓታችን ነውና አይሆንም ይላሉ፡፡ በዚህ ምክነያት ሁለተኛውንም ቃሉ ያስጠሩና ሚኒሊክ ሁለቱንም ለቦረና ይሾሟቸዋል፡፡ በዚህም የተነሳ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የቦረና አስተዳደር እስከ ቀበሌ ድረስ ሁለት ሁለት ሹም ነበር ያለው፡፡ ስለዚህ ጉዳይ በተደጋጋሚ የገዳ ሥርዓትን ከመሠረቱ ያጠኑትን ፕሮፌሰር አስመሮምን ዋቢ አድርጌ አቅርቤ ነበር፡፡ ዛሬ ትውልዱ እንደ ተስፋዬ ገ/አብ የመሳሰሉ ሴረኛ ነጋዴዎችን የሐሰት ትርክት እንጂ የምሁርን መረጃ ማዳመጥም ሆነ ማንበብ ስለማይፈልግ እንጂ፣ የተሸሸገ ታሪክ የለም፡፡ በአጠቃላይ ሲታይ የሚኒሊክ አስተዳደር ትክክለኛ ፌደራሊዝም በሚመስል ሁኔታ የተዋቀረ ነበር፡፡ በአስታደሩም ስኬታማ ነበር፡፡ አገርን እንደ ባደረጉ በጥቂት አመታት ታላቅ ጦርነት አደዋን ተዋግተው ድል የማድረጋቸው ሚስጢረም በወቅቱ ሁሉም በኢትዮጵያ አገር ጥላ ሥር የተሰበሰበ በሚኒሊክ ፍጹም መተማመንና ምንም አይነት ጥላቻና ቂም ስላልነበረው ነው፡፡ ይሄን እውነት ነው ዛሬ ተማርኩ የሚለው በሀሰት ትርክት ትውልድን የሚበክልበት፡፡
የጨለንቆው ጦርነት በነገራችን ላይ የተደረገው በወቅቱ በቱርኮችና ግብጾች እንደሚታገዝ በሚነገርለት በሐረሩ ኢሚርና በሚኒሊክ ተዋጊዎች እንጂ ከእነጭርሱም ከኦሮሞ ማህበረሰብ ባላባት ከሆነ ሰው ጋር አደለም፡፡ ምን አልባት የሐረሩ ኢሚር በወታደርነት ብዙ ኦሮሞዎችን አሰልፎ ይሆናል፡፡ በሚኒሊክም በኩል ያለው አብዛኛው እንግዲህ ኦሮሞ ነው፡፡ ግን ይሄ ታሪክ ተዛብቶ ዛሬ ልክ እንደ አርሲው ከኦሮሞ ባላባት ጋር የተደረገ በሚመስል መልኩ እየተተረተ ነው፡፡ ጦርነቱም እንደው ተጋኖ እንጂ የአንድ ቀን ምን አልባትም ከ6 ሰዓት ያልበለጠ ጦርነት ነው፡፡ እንደ አርሲውና ወላይታው የከፋ እልቂትም አላስከተለም፡፡ እነዛ ጦርነቶች ለወራት ምን አልባትም ለአመታት የዘለቁ ነበርና፡፡ የጨለንቆው ጦርነት ለታሪክ ትልቅ ትኩረት የሆነው በሚኒሊክና በሐረሪው ኢሚር መካከል በመሆኑና ሁለቱም በወቅቱ ዘመናዊ የተባለ አንዳንድ የጦር መሳሪያዎች ያሏቸው መሆኑን ሊሆን ይችላል፡፡ የሆነ ሆኖ ይሄም ታሪክ ዛሬ በሚተረከው አይነት አደለም፡፡ በወቅቱ ግን ታሪኩ በደንብ ተመዝግቦ አለ፡፡ ማንበብ የእኛ ፋንታ ነው፡፡
ዛሬ አዲሱ አረጋ በኦሮሞና አማራ መካከል ሠላም እንዳይኖር ሆን ተብሎ በእነደነ ተስፋዬ ገ/አብ የመሳሰሉት ሴረኞች እንደተጻፈ መናገሩን ተከትሎ ፌስቡክን ሌላ የጦርነት አውድ የፈጠረለት እስከሚመስል አጥለቅልቆት አየሁ፡፡ አዲሱ አልሳሳተም፡፡ የተደበቀ ታሪክ የለም፡፡ ከጀምሩ የሚኒሊክና ጎበናን አነሳስ ስናስተውል የቀድሞ አባቶቻችንን አገር የሚል ነው፡፡ ይህ ከሚገርመኝ እውነት አንዱ ነው፡፡ ኬኒያ ጠረፍ ሲደርሱ ቦረናን ወደ ኢትዮጵያ አስገብተው ቆሙ፡፡ በነገራችን ላይ ቦረናን ኢንግሊዝ ለመወሰድ ብዙ ሞክራ ነበር፡፡ የሚኒሊክ ጠንካራ ውሳኔ ነው፡፡ በሁሉም አቅጣጫ ብታዩ ይሄን ታስተውላላችሁ፡፡ ከዚህ በፊት የኢትዮጵያውያን የዘረመል ትስስርን የሚያሳይ ሰነድ አስነቢቢያችሁ ነበር፡፡ ሚኒሊክ የተከተሉትና የአባቶቻችን አገር የሚሉት የዚህ ሕዝብ ሰፍሮበት ያለውን አገር ነው፡፡ እጅግ የሚገርም ነው፡፡ እነሱ ይተዋወቁ ነበር፡፡ ዛሬ እኛ ነን የወረድንው፡፡ ለማንኛውም ኦሮሞ ከአማራ የተለየሁ ነኝ ብሎ ሲያስብ፣ አማራውም ሌላውም እንደዛ ሲያስብ ነው የወረድነው፡፡ ማንም እየተነሳ የገበያ ዕቃ ያደረገን፡፡ ከላይ ያነሳሁትን ተንኮለኛ ጎረቤት አስተውሉ፡፡ እነ ተስፋዬ በዚህ ስልት ነው በሕዝብ መካከል ሴራን ከማኖርም በላይ ዋና የገቢ ምንጭ ገበያቸው ሊያደርጉን የቻሉት፡፡ ወደፊት የጄኔቲከስ ሴንሰስ (በመለዘር የታገዘ የሕዝብ ቆጠራ ሲካሄድ፣ በአላሰባችሁት ፍጥነት ይሄ ሊሆን ይችላል) ሁሉም ስለራ ዛሬ በሚያወራበት እንደሚያፍር አትጠራጠሩ፡፡ ለወለጋ ከቦረና ይልቅ ጎጃሜው ነው ቅርቡ፡፡ በአጠቃላይ ሐበሾች ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ ከሌሎች አፍሪካውያን ጭምር የማንጋራቸው ሶስት መሠረታዊ የዘር ሐረጎች አሉን፡፡ ሌቫንት(ጥንታዊ ሶሪያና እስራኤል አካባቢ የሚኖር ሕዝብ)፤ የዛሬው የእኛው አሪ፣ እና አንድ ሌላ የዘር ግንድ ከኬንያዎቹ ማሳይ ጋር በትልቁ የምንጋራው፡፡ በተለይ የአሪና ከማሳይ ጋር የምንጋራው የዘር አረጎች በሌሎች ከማሳይ ውጭ በሌሎች አፍሪካውያን ጭምር አናገኛቸውም፡፡ የሌቫንት በእርግጥም በሰሜን አፍሪካ በብዛት አለ፡፡ እነዚህ የዘር ሐረጎች በሱማሌ፣ ኢትዮጵያ፣ ሱዳን፣ ጂበቡቲ፣ ኤርትራና ከፊል ግብጽ የተወሰኑ ናቸው፡፡ ሐበሻ የሚባለው ሕዝብ ማለት ነው፡፡ ዛሬ ደግሜ ሊንኩን ማስቀመጥ አልፈለኩም፡፡
እውነትን እንጋፈጥ እውነት ሲነገር ከመደንገጣችን በፊት በራሳችን ፈልገን እንወቅ፡፡ ማንም እንደፈለገው አይዘውረን፡፡ የአኖሌ ሐውልት የሴረኞች ነው በሐሰት የጡት ቆረጣ ታሪክ ነው አልን እንጂ አርሲ በጦርነት አልተጎዳም፡፡ ጦርነት አልነበረም አላልንም፡፡ የሚኒለክ መዋዕለ ዜና እንደወረደ ታሪኩን ይናገራል፡፡ እንደእውነቱ በዛ ጦርነት ምክነያት ለሞቱ ተብሎ በዛ ቦታ ሐውልት ይቁም የሚል ሐሳብ ለሚኒሊክ ቢቀርብ አይቃወሙትም ነበር፡፡ ይህ ጦርነት ሚኒሊክ ከአዘኑባቸው ጦርነቶች አንዱ ነውና፡፡ አባቶቻችን ግን አደዋም ላይ አላቆሙም፡፡ ሀሉም ቦታ እንዲሁ፡፡ እነሱ በዓላማ እንጂ በማንነት አልተዋጉም፡፡ ማንንም አልወጉም፡፡ የዛሬው ሐውልት ግን የቆመው የአርሲ ጦርነትን በታሪክ እንዲታወስላቸው ለሚፈልጉ ሳይሆን በሐሰት ትርክት በሕዝቦች መካከል የበቀልን የጥላቻን ሐውልት ለማኖር ነው፡፡ እንደዛ ባይሆን ስለ አርሲ ኦሮሞን ምን ምን ያገባዋል? በኦሮሞነት የአልሆን ታሪክ ለኦሮሞ የሴራ ፖለቲካ ለመጠቀም ከአልሆነ፡፡ አንብቡ እኔ የታሪክም የፖለቲካም ሰው አደለሁም፡፡ ታሪክን አስመልክቶ ከልጅነት ጀምሮ አባታችን (ገበሬ ነው ግን ያነባል) ይነግረን የነበረው እውነት ትልቅ እገዛ አድርጎልኛል፡፡ አሁን አሁን የታሪክ ምሁር ነን የሚሉ ሳይቀር በሚናገሯቸው የተሳከሩ ትርክቶች የተነሳ ለማጥራት በምሞክርበት ብዙ ተጨማሪ ለማወቅ ችዬአለሁ፡፡ ለዚህ የረዳኝ ቀድሞውን የተነገረኝ እውነት ስላለ ነው፡፡ አባታችን ስለነ ወርዶፋ ጨገሬ ሳይቀር ይነግረን የነበረው ተረት ጭምር ይመስለኝ ነበር እንጂ እውን በሕወት ኖረው ታሪካቸው የሚታወቁ ሰዎች አይመስሉኝም ነበር፡፡ አንዳንድ ሥሞች ተዝ የሚሉኝ አሁን ነው፡፡ የኢትዮጵያውያን የመለዘር ትስስር በአነበብኩበት ወቅት ፌቴ ድቅን ያለው በልጅነት ተረት እየመሠለኝ የተነገረኝ እውነት ነው፡፡ አሁን የማስተውለው አባቶቻችን ራሳቸውን ያውቁ ነበር፡፡ የአብረሀም ዘሮች ነን ሲሉ አልተሳሳቱም፡፡ ወደ ግማሽ የተጠጋው የሌቫንት ደማችን የሚነግረን እንደዛ ነው፡፡ አሪና ከማሳይ ጋር የምንጋራው ደማችን ግን እዛው ኢትዮጵያና አካባቢው የኖረ ይመስላል፡፡ ጥንታውያን ኢትዮጵያውያን ይሆኑ? ሰሞኑን የሱማሌው ክልል ፕሬዘደንት የተናገረው ይገርማል፡፡ በውጭ ስትገናኝ ሳታውቀው የሆነ ነገር ይስብሀል፡፡ እኔ ለራሴ ፈግግ ነበር ያልኩት፡፡ እኔን አይቶ ሱማሌ አያልፈኝም፡፡ ከሁሉ የሚገርመኝ ግን አንዴ ፍራንክፈርት ላይ የገጠመኝ ወጣት ሱማሊኛ ተናጋሪ ነው፡፡ ወንድሙን ያገኘ ነው የመሠለኝ፡፡ አሁንም በአለሁበት አገር ተደጋጋሚ የሚገጥመኝ ነው፡፡ የሚገርመኝ በሱማሊኛ ሲያነጋግሩኝ እርግጠኞች የሆኑ ነው የሚመስለው፡፡ አብዛኞቹ ኢትዮጵያ ሱማሌ አደሉም፡፡ በሆነ አጋጣሚ ትንትንሽ አማርኛም የሚሞክሩ ገጥመውኛል (ኢትዮጵያ ሱማሌ ከአልሆኑት)፡፡ በአንድ ምግብ አዳራሽ (ፉድ ኮርት) ከወንድሜ (በእንግድነት መጥቶ) ጋር ምግብ ለመብላት ተቀምጠን አንድ ሱማሊኛ ከዛ ሁሉ ሰው ወደእኛ ቀርቦ የሆነ ነገር እንድናግዘው ጠየቀን፡፡ እኛም የምር ነበር ያስደሰተን፡፡ አዎ በተፈጥሮ የሚመስልህ ሰው ጋር ሳታውቀው ትሳባለህ፡፡ ዘረኝነት ይሆን? አመሰግናለሁ! ቸር ይግጠመን
ልዑል አባት እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ይባርክ! አሜን!
