April 22, 2019

ተስፋዬ ገብረአብ “የቡርቃ ዝምታ” ቅድመ ታሪክ ብሎ መንደርደሪያ ያደረገው ሃየሎም አርአያ በመሸታ ቤት አምባጓሮ መገደሉ ያስከተለውን ድንጋጤ በመተረት ነው። በድንጋጤው ጸሃፊው የተሰማውን ስሜት ሲገልጽ፣ “ጨርሶ ማመን አቃተኝ። ግን ጆሮዬ ይሰማል። አይኔ ያያል። የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ያበደ መሰለኝ፤” ይላል።
እርሱ ብቻ ሳይሆን በአዲስ አበባ ዮርዳኖስ ሆቴል አልኮል ሲጎነጭ የነበረው ታዳሚ ሁሉ በሃዘን ጤዛ እንደተመታ ይተርካል። ዝቅ ብሎ ከሃዘን ለማገገምና ቀብር ላይ ለመገኘት ወደ አስመራ ሊያደርግ የነበርውን ጉዞ ለለሶስት ቀናት አራዝሞ አስመራ ሲደርስ አንድ ያልጠበቀው ነገር ያጋጥመዋል።
ስለ አንዲት በሃየሎም ሞት ታማ ምግብ ውሃ መቅመስ የተሳናት ሴት ይሰማል። ወጣቷ ለሊት ለሊት የሃየሎምን ስም እያነሳች እንደምትቃዥም ተነገረው። ከሁሉም የገረመው ደግሞ ልጅቷ ኢትዮጵያዊ ሆና መገኘቷ ነው። ሀወኒ ዋቆ።
ሃወኒ ውሎዋ ከእነ ስብሃት፣ ሃየሎምና ክንፈ ገብረመድህን የሆነች ምናባዊ ገጸ ባህሪ ነች። ተስፋዬ በዚች የልብወለድ ገጸ ባህሪ አማካኝነት እነ ሃየሎምን ያጀግናል፣ አኖሌ፣ ቡርቃ…እያለ በመርዝ የተለወሰ ተረት ይተርካል። ትረካውም በምስኪኑ አማራና ኦሮሞ ህዝብ መሃል ጥላቻና መቃቃር መዝራት እንደሆነ ግልጽ ነው።
ተስፋዬ በወቅቱ ለህወሃቶች ያደረ ምርጥ ካድሬ ነበር። ሆኖም ዛሬ አንዳንዶች የብርቃው ዝምታ ወያኔ የፈተለው ልብ ወለድ መሆኑን ሊክዱ ይሞክራሉ።
ዛሬ አቶ አዲሱ አረጋ በኦህዴድ ውስጥ እየተጋቱ ያደጉበትን ወተት መርዝ እንደ ነበር በመናገር ከህሊና ወቀሳ እራሳቸውን ነጻ በማውጣታቸው አቧራ መነሳቱ አይገርምም። ያም ሆነ ይህ ህዝብ ለማናቆር የተጻፈ ፖለቲካዊ ልብ ወለድ ከፉ ተረት መሆኑን አለመገንዘብ ሞኝነት ነው።
አቶ አዲሱ የሚያውቁትን እውነት በመናገራቸው ሊመሰገኑ እንጂ ሊወገዙ ፈጽሞ አይገባም።
