April 23, 2019

እስቲ ከለውጡ በፊት ወዳ ኋላ ልመልስህ። ያኔ በፌስ ቡክ ሁሉም በየፊናው ሕዝብ እንዲተላለቅ መርዙን ሲረጭ፣ ብሔር ከብሔር እንዲደባደብ ዱላ ሲያቀብል፣ በሐሰት አካውንት የሐሰት ዜና ሲያሰራጭ፣ የራሱን ወገን አንግሶ የሌላው አኮስሶ ሲጽፍ፣ የቴሌቪዥኖቻችን ከሀገር ጥቅም ይልቅ የፓርቲያቸውን ፍላጎት አስቀድመው ሸፋፋና ሸውራራ ማስረጃ ሲያሰራጩ እንዲሁም የሚታመን ሚዛናዊ መረጃ በጠፋበት ጊዜ፤ ሚዛናዊ፣ ተዓማኒና ወቅታዊ ዜና ስትፈልግ ርግጠኛ ነኝ ፌስ ቡክ ላይ ገብተህ ንጉሱ ጥላሁንና አዲሱ አረጋ ብለህ ስሞችን ብዙ ጊዜ ጽፈህ ሰርች አድርገሃል፡፡ ዜናቸውን ላይክ አድርገሃል፣ ጽሁፋቸውን ደጋግመህ አንብበህ ደጋግመህ ሼር አድርገሃል፡፡ ምን ጽሁፋቸውን ብቻ ጽሁፉ ውስጥ ያለውን ፍሬ ሀሳብ ተጋርተሃል፡፡

ግና ሰው ነህና ረስተሃል! ብዙ ሰው መሐል ሰፋሪ ሆኖ ለውጡን ከጀርባ ሆኖ ሲያደባ አቶ ንጉሱ የአማራ ክልል አቶ አዲሱ ደግሞ የኦሮሚያ ክልል የኮሚኒኬሽን ቢሮ ኃላፊዎች በነበሩበት ጊዜ አደባባይ በመውጣት ከፍተኛ የሆነ ተጋድሎ ማድረጋቸውን ዘንግተሃል!….ለምን መሰለህ እንዲህ የምልህ? ..አቶ አዲሱ ላይ የስድብ ናዳ ስታወርድ ስለያዝኩህ ነው፡፡

ስጠረጥር አቶ አዲሱ ከቢሮ ኃላፊነቱ ስራ በተጨማሪ ፌስቡክ ላይ የተጣመመውን ሲያቀና፣ የጎደለውን ሲሞላ ፣ ሐሰት ከእውነት በልጣ ሀገር እንዳታፈርስ ሲታትር የሚውለው ለዚች ሀገር ሁለንተናዊ እድገትና ብልጽግና ብሎ እንጂ፤ የመደበኛ ስራ መዘርዝሩ ላይ የተቀመጠ ግዴታው አድርገህ ቆጥረኸዋል፡፡ አቶ አዲሱ እንደ ሌሎች የቢሮ ኃላፊዎች በ6 ወር አንዴ ጋዜጣዊ መግለጫ እየሰጠ መኖር ይችል እንደነበረም ባላወቀ አልፈኸዋል፡፡
እውነቱን ልንገርህ?!…አዲሱን መዝለፍ ራስህን ነው የሚያስገምትህ።…ይልቁንስ አዲሱ ብዙ ነገር ብትማር ነው የምመክርህ፡፡

የማህበራዊ ሚዲያን በኃላፊነት ስሜት መጠቀም ከፈለግህ፤ ከአዲሱ አረጋ የካበተ ልምድ ቅሰም፡፡ አዲሱ ፌስቡክን ለሀገር ግንባታ፣ ለሀገራዊ አንድነት ፣ ለሕዝቦች መግባባት ከሚያውሉና በኃላፊነት ከሚጠቀሙ ብርቅዬ ሰዎች ግንባር ቀደሙ ነው፡፡ የጻፋቸውን ጽሁፎች ገጹ ላይ ግባና ፈትሽ። ስህተትና ቅጥፈት በፍፁም አታገኝም፡፡ ፈትሸህ ስትጨርስም ክፉ ሃሳብ አይደለም ክፉ ቃል ስለማታገኝ፤ የ60 ዓመት አዛውንት ጽሁፍ እንጂ የአንድ ወጣት ጽሁፍ እንደሚሰማህ ባትነግረኝም አላጣውም፡፡ አዲሱ በወጣትነት ዕድሜው የደረሰበትን ደረጃም አብረህ ብታስበው ይጠቅምሃል.. አይጎዳህም….!! ስኬትን ከክሪስቲያኖ ሮናልዶ ብቻ የሚገኝ ከመሰለህ ብዬ ነው፡፡

ኢትዮጵያ እንደ ሩዋንዳ እንድትሆን ENN ቴሌቪዥን የቡና እና ጊዮርጊስን የእግር ኳስ ግጥሚያ ቀጥታ ስርጭትን ማስተላለፉን አቋርጦ ካሜራውን ከአዲስ አበባ ስቴዲየም ወደ ቡኖ በደሌ ያዞረ ቀን፤ ይቺ ሀገርም አንተም እስከ ስድብህ የተረፍኸው በፈጣሪ ርዳታና አቶ አዲሱ አረጋን የመሰሉ የቁርጥ ቀን ልጆች በመኖራቸው እንደሆነ ግን ትረሳዋለህ ብዬ ባላስብም ላስታውስህ እሻለሁ፡፡

ሌላም ልጨምርልህ! አቶ አዲሱ አረጋ ፌስ ቡክ ላይ ከ200ሺ በላይ ተከታይ ያፈራው በሀገር ወዳድነቱ፣ በተዓማኒነቱ ፣ በሀሳብ ብስለቱ እንጂ ታዋቂ ዘፋኝ ወይም አክቲቪዝም እንጀራው ስለሆነ አይደለም ፡፡ በእኔ እምነት አዲሱ አላጠፋም….. ግን ደግሞ ቢያጠፋስ…? እውን ለዋለው ውለታ ለአዲሱ ይሄ ነው መልሱ?…ያሳዝናል! የአባ ገዳ ልጅ አዲሱ በርታልን፤ ከዚህ በላይም በሆነ የስራ ኃላፊነትም የክልልህንና የሀገርህን ሕዝብ እንደምታገለግልም ሙሉ እምነት አለኝ፡፡