April 23, 2019

አሁን ባለው ስልጣኔ የመካንነትን ህመም ለመቀነስ አንዱ አቋራጭ መንገድ ገንዘብ አውጥቶ የሌላዋን ማህጸን ለዘጠኝ ወራት መከራየት ነው። አዲሱ ዲክሽነሪ “ሰሮጌት ማዘር” ይላታል። ዘርህን ተሸክማ ትቆያለች፤ ከዚያም ልጅህን ዱብ ታደርግልህና የነፍስም የስጋም ግንኙነት የሌላትን ነገር ግን በማህጸኗ ዘጠኝ ወር ሙሉ ተሸክማው የቆየችውን እንግዳ ፍጡር መልኩን ምን እንደሚመስል እንኳን ለማየት መብቱም ፍላጎቱም ሳይኖራት ገንዘቧን ተቀብላ በሆስፒታሉ የጓሮ በር በኩል ወልቅ ብላ ትሄዳልሃለች። እዚህ ላይ እርሷ በልጁ ላይ ቅንጣት መብት እንደሌላት ሁሉ ልጁም አድጎ ነገ “እናቴ” ብሎ የሚሄድበት አመክንዮ የለም።የአዲሱ ኦሮሞ ትውልድ አንዱ ክሽፈት ወያኔ አንድ ብሎ አፉን በቁቤ ቋንቋ የሚፈታ የቄሮን ትውልድ ሲፈጥር በተስፋዬ ገብረ አብ በኩል በቡርቃ ዝምታ የጀመረውን ትርክት እንደ እውነት ተቀብሎ እራሱን በዚያ ልክ ለማየት መሞከሩ ነው። የሰሮጌት ማዘሩን ወላጅ እናቴ ብሎ የሙጥኝ የማለት ልክፍት።

ተስፋዬ ገብረ አብ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በቅጡ ያላጠናቀቀ አደገኛ መሃይም ነው። አደገኛ መሃይም ያልኩት እንዲህ አይነቱ ድንቁርና ምንም አይነት የማንበብና የመጻፍ ችሎታ ከሌላቸውና ፊደል ካልቆጠሩት ሰዎች ይልቅ ይበልጥ አክሳሪና በምንም አይነት ስር ነቀል የመሰረተ ትምህት አብዮት የማይድን በሽታ በመሆኑ ነው።ገጠሬው “ጥራዝ ነጣቂ” ይለዋል።ወይ በቅጡ ተምሮና የእውቀት ከፍታ ላይ ደርሶ እንደ ታሪክ ወደሁዋላ ሽዎች አመታትን ተጉዞ ጥንታዊ መዛግብትን አላገላበጠ፣ ወይ ወደ መሬት ጠልቆ የማንነትን የሉሲን ምስጢር ከመሬት ከርስ ቆፍሮ አልተማረ፣ወይ እንድነ ሄኖክ በመንፈስ ነጥቆ የጸሃይን መስኮቶች አልሰፈረ….የእርሱ “እውቀት” ተጀምሮ የቆመው የነብርሃኑ ዘሪሁንና የበዓሉ ግርማ ልቦለድ ድርሰቶች ላይ ነው።አለቀ። ልቦለድ አንብበህ ደግሞ ጥሩ ፊክሺኒስት ሊወጣህ ይችላል እንጅ በፍጹም ጥሩ አዋቂ ልትሆን አትችልም። ማንበብና መጻፍ ስለቻልክ፣አማርኛን ወዲያና ወዲህ ስላገለባበጥክ ታውቃለህ ማለትም አይደለም።

ከላይ እንደተባለው በተፈጥሮው ትምህርት ቤት ያልደረሰ ሰው ትህትና ስላለው “የተማረ ይገደለኝ” ይላል። በቅጡ ፊደል የጠገበ ሰው ደግሞ የህሊናው ሚዛን በጽኑ መሰረት ላይ ስለሚቆም መቸ፣ ምን፣ ለማንና እንዴት መናገር እንዳለበት ያውቃልና ስጋት አይሆንም። እንደ ተስፋዬ ገብረ አብ ያለው በጠዋቱ ጨንግፎ ከትምህርት የጎደለ ሰው ግን ያው ያገረሸ ሳንባ ነቀርሳ ማለት ነው። የሳንባ ነቀርሳ ኮካይና ባሲላይ ከሚባሉ በጣም አቅመ ደካማ ከሆኑ ባክቴሪያዎች የሚመጣ በሽታ ነው። ይኽ በሽታ የሚያጠቃኽ ሰውነትህ በሆነ አጋጣሚ በደከመ ግዜ ነው። ቢሆንም ግን በወቅቱ የሚሰጡህን መድሃኒቶች በትክክል ወስደህ ከጨረስክ እስከመጨረሻው የምትፈወስ ሲሆን በሆነ አጋጣሚ “ተሻለኝ” ብለህ መድሃኒቱን ብታቋርጥ ግን ቀን ጠብቆ ማገርሸቱ አይቀርም። ያን ግዜ ግን መድሃኒቱን ዳግመኛ ልውስውድ ብትል አንድ ግዜ ተለማምዶታልና የመዳን እድልህ ምንም ነው። የተስፋዬ ገብረ አብ በጠዋቱ ከትምህርት ጨንግፎ ወደ በረሃ መውረድ ወደላይኛው ከፍታም እንዳይወጣ መሰረቱን እያጣው፣ ተመልሶ ወደ ትምህርት ቤት እዳይገባ እድሜው ገፍቶና አይምሮው ዝጎበት ቅርቃር ውስጥ የገባ ነገር አርፎም እንዳይቀመጥም ጀምሮ የተዋት የፊደል ገበታ እንደ ፋፎ ቆሎ እዚህም እዛም እያሰከረችው አቅመ ደካሞችን እረፍት የሚነሳ ሆኗል።

አስገራሚው ነገር “የሁሉ ነገር ባለቤት እኛ ነን” በሚል የኬኛ ሲንድረም የሰከረና በሚሊዮን የሚቆጠር መንጋ ተከታይ አለኝ የሚል “ማህበራዊ” ንቅናቄ በዚህ ዘመን ታሪኩን የሚያጣቅስበት አንድ የተጻፈ ማኑስክሪፕት አጥቶ በተስፋዬ ገብረ አብ ተረት ላይ ተንተርሶ እራሱን ለመግለጥ ደፋ ቀና ማለቱ ነው።” ኦሮሚያ” የሚባልን አገር ከዚህ አድ አይነት ባዶ ቅርፊት ለመፍጠር እችለሁ ብሎ መንገድ መግባት የድንቁርና ጥግ ነው።

ኢትዮጵያ ስትባል እኮ ወደኋላ አንድ ስንዝር እድሜ ተራምደው ማንነታቸው ሊገልጹ የማይቻላቸውና ከባርነት ፍንገላ ተቆርጠው እንደቀሩት ኮንጎ ኪንሻ፣ ማላዊ ወይም ሞዛንቢክ ወዘተ አይደለችም።ከደገኛ ታሪኳም የተቀዳው ህዝቧም ቢሆን ከፔርሺያ ቀደምት ታሪክ ያለው፣ ማንነቱን ከፈርዖን የሚጋራ ወርቃማ ታሪኩን በዲንጋይ ላይ ሳይቀር ጽፎ ያስቀመጠና ይኽንንም ማንነቱን አፍ አውጥተው የሚናገሩለትም መዛግብት ያሉት ብቻ ሳይሆን ትናንት የሰው ልጅ ጥንታዊ ማንነቱን ፍለጋ ሲመጣ ሄዋንን ቆፍሮ ያገኘው እዚህ ምድር ላይ መሆኑን፤ አዳምንም ለማግኘት ቁፋሮው በቀጠለበት አገር እንደ አባባ ተስፋዬ ሳህሉ ስራዎች እንኳን “ተረቴን መልሱ አፌን በዳቦ አብሱ” ተብሎ ለልጆች ማዝናኛ ተረት ለመሆን አቅም በሌለው የተስፋዬ ገብረ አብ የቃላት ድሪቶ ይፈተሻል ብሎ ማሰብ መድሃኒት ቀርቶ አይነትና ስም ያለው እብደት አይደለም።

የቄሮ ንቅናቄ አዲሱን የኦሮሞ ትርክት እራሱ አይጽፍ ቁቤ የተጀመረው በወያኔ እድሜ በመሆኑ የነገውን ትውልድ ለማጭበርበር ካልሆነ ቢያንስ ለዚህ ዘመን ፕሮፓጋንዳ እንደማይሆን ግልጽ ነው። በግእዝና በአማርኛ ሲዘልቅም በሳባውያን ቋንቋ የተጻፈን ታሪክ አይመዝ በዚያ ውስጥ ያለው ባለ ከባድ ሚዛን እውነት እነርሱ ለሚፈልጉት የዘመነ ወያኔ ትርክት የሚመች አይደለም። ስለዚህ ለዚህ ችግር የተስፋዬ ገብረ አብን አይነት ከማንነት ቀውስ የተወለዱ ተረቶችን ሰብስበው “ታሪካችን” ለማለት መገደዳቸው ያሳዝናልም፤ ያሳፍራልም።

በዚሁ አጋጣሚ አሁን ባለው ነባራዊ እውነት በሻቢያ ደረጃ እንኩዋን ለፕሮፓጋንዳ ተብለው ለግማሽ ምእተ አመት ያህል የተፈበረኩ ጸረ አማራና ጸረ ኢትዮጵያዊ ትርክቶች ምን ያህል መሰረተ ቢስ ብቻ ሳይሆኑ ምን ያህል ዋጋ እንዳስከፈሉትም ጭምር ተረድቶ የፊልምና የጽሁፍ ክምቺቶቹን ለማውደምና ከእውነታው ጋር ለመታረቅ አቋም በያዘበት በዚህ ዘመን “አገሬ” በሚላት ኤርትራ ላይ አንዲት ነገር ለመጸፍ መብት የሌለው ተስፋዬ ገብረ አብ ድንበር ተሻግሮ ከኦነጋውያን ጋር የሚያደርገው ግልሙትና በራሱ በሻቢያ በኩል ሳይቀር ሃይ ሊባል ይገባዋል።