April 24, 2019

የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቶችን በማጠናከር የአማራን ሕዝብ መሰረታዊ አጀንዳዎች መሬት ለማስነካት በአንድነት እንረባረብ!
የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የአማራ ክልል ሕዝቦች ትግል ወሳኝ ምዕራፍን የተቆናጠጠ መሆኑን ይገነዘባል፡፡ የአማራን ሕዝብ ትግል ወደ ትክክለኛ አቅጣጫ ለመምራት በተደረገው እንቅስቃሴ የሕዝብ አጀንዳዎች መንግስታዊ ባለቤት አግኝተው ሕዝባችን ጋር በእጅጉ የመቀራረብ ዕድል ከመፈጠሩም በላይ ለጥያቄዎችም ዘላቂ መፍትሄ ለመሻት ጠንካራ መደላድሎችን ተፈጥረዋል፡፡

የአማራ ሕዝብ ትግል ፈር እየያዘ ትላልቅ ውጤቶችን እያስመዘገበ ለዚህ ምዕራፍ የበቃው የኢትዮጵያን የፖለቲካ ቋጠሮ በመለየት ሂደት ከለውጥ ሃይሎች ጋር በተደረገው መናበብ የቋጠሮውን ዋና አካባቢ በዕርግጥም መጨበጥ በመቻሉ ነው፡፡ በአገር ግንባታ ሂደታችን በሕዝቦች መካከል መከፋፈልና መጠራጠር እንዲሰፋ እና እይታን የሚጋርዱ የፈጠራ ግድግዳዎች እንዲበረቱ የተሰራውን ሴራ በማክሸፍ ሂደት የአማራና የኦሮሞ ሕዝቦችን ትስስር እና ግንኙነትን ማጠናከር ከችግሮች ማርከሻ መካከል አንደኛው መድሃኒት ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ ትግሉ ሲጀመር ይህ ግንኙነት ጥሩ መደላድል ሆኖ አገልግሏል፡፡ በዚህ ሳምንትም በአምቦ ከተማ ተገኝተን የአማራና የኦሮሞ ሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትን ይበልጥ ለማጠናከር የተሰራው ስራና የታየው አዎንታዊ ምላሽ ትልቅ ፖለቲካዊና ሕዝባዊ ድል ነው፡፡ ይህን መሰል ግንኙነት ይበልጥ ከሌሎች ሕዝቦች ጋር እየሰፋና እየተጠናከረ መሄድ ይኖርበታል፡፡

በአማራና በኦሮሞ ሕዝቦች ግንኙነት ትልቁ ስዕልና ድል ኢትዮጵያን ለመታደግ እና የሕዝብ ጥያቄዎችን ምላሽ እየሰጡ ወደፊት ፈቅ ለማድረግ እጅግ አስፈላጊ እንደሆነ መግባባት መያዙ ነው፡፡ ግንኙነቱን አስመልክቶ አሁን ላይ አዎንታዊም አሉታዊም በሆነ መልኩ ተፅዕኖ በማሳደር ላይ ያለው የማህበራዊ ሚዲያ መድረክ ውስጥ የተለያዩ ስሜቶች ተስተውለዋል፡፡
የመጀመሪያው ሁላችንም በጋራ ልብ ማለት የሚገባን ጉዳይ የአማራንና የኦሮሞን ሕዝብ በማለያየት የራሳቸውን ፍላጎት ብቻ ለማሳካት የሚፈልጉ አካላት ግንኙነትን ማጠልሸት ላይ መጠመዳቸው የኖረ፤ ያለና የሚኖር መሆኑ ነው፡፡ ይህ ሃይል አሰላለፉ ግልፅ ነው፡፡ በዚህ ሃይል አሰላለፍ ላይ ትግላችን ቀጣይነት የሚኖረውና የጋራ ርብርብን የሚጠይቅ ነው፡፡ እነዚህ ሃይሎች ዕውነተኛ አጀንዳን በማህበራዊ ሚዲያ የማያቋርጥ ዘመቻ ማሳት የሚቻል መስሏቸው የሚደክሙ መሆናቸውም መታወቅ ይኖርበታል፡፡

ሁለተኛው አሰላለፍ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትን በከፊል የሚቀበል መስሎ ነገር ግን በይዘት ደረጃ የተወሰኑ ጉዳዮችን በመምዘዝ ከትልቁ ስዕል እየወጡ ሆን ብለውም ሆነ ሳይረዱት ከዚህ በላይ ለጠቀስናቸው የመጀመሪያ ተሰላፊዎች ዱላ ማቀበል ላይ የሚታትሩ መኖራቸው ነው፡፡

በአምቦ በተካሄደው የአማራና የኦሮሞ የሕዝብ ለሕዝብ መድረክ የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ርዕሠ-መስተዳደር ክቡር ዶክተር አምባቸው መኮንን የአዲስ አበባን ጉዳይ አስመልክቶ ከተሳታፊ ለተነሳላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ የተለያዩ ሃሳቦች እየተንሸራሸሩበት በመሆኑ በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ ማከል ጠቃሚ ነው ብለን እናምናለን፡፡

የአዲስ አበባ ጉዳይ የወቅቱ የፖለቲካ ትኩሳት የሚራመድበት አንድ አጀንዳ መሆኑን እንረዳለን፡፡ የአዲስ አበባ ጉዳይ ከባለቤትነት ጋር በተያያዘ እና ከህገ-መንግስታዊ ድንጋጌዎች ጋር እየተጣመረ የሚቀርብ አጀንዳ ነው፡፡ በሁለቱም ጉዳዮች ላይ የክልላችን መንግስት የያዘው አቋም ግልፅ ነው፡፡ ለምሳሌ፤ የአዲስ አበባ ከተማን ባለቤትነት በተመለከተ ባለቤቶች ነዋሪዎቿና ሁሉም ከተማዋን የገነቡ ኢትዮጵያዊያን (ብሔር፤ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች) ናቸው የሚል ግልፅ አቋም ማራመዳችን የሚታወቅ ነው፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ዛሬም የተለወጠ አቋም የለንም፡፡ በሌላ በኩል ህገ-መንግስቱን በሚመለከት፤ መሻሻል በሚገባቸው መሰረታዊ ጉዳዮች ላይ ህገ-መንግስቱን መፈተሽ፤ ማሻሻል እና ማስተካከል የሚገባ መሆኑን፤ ነገር ግን መሻሻል የሚገባቸው ህገ-መንግስታዊ ድንጋጌዎች ሕዝባችንን ባሳተፈ እና በዴሞክራሲያዊ አግባብ እስኪሻሻሉ ድረስ የምንመራበት ሰነድ መሆኑን ጭምር እናምናለን፡፡ ሕዝባችንም ይህን አቋማችንን ይገነዘበዋል፡፡ ከዚህ አንፃር የአማራና የኦሮሞ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት መድረክ በአምቦ ከተማ ሲካሄድ አንድ የመድረክ ተሳታፊ “የኦሮሚያ ክልል በኢፌዲሪ ህገ-መንግስት አንቀፅ 49(5) መሰረት የሚኖረን ልዩ ጥቅም እንዲከበር በምናደርገው ትግል አቋማችሁ ምንድን ነው” በሚል ምላሽ እንዲሰጧቸው ክቡር ዶክተር አምባቸውን በቀጥታ ጠይቀዋቸዋል፡፡ ርዕሰ መስተዳድሩም ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ በተሰጠው ምላሽ ላይም ብዥታዎች አሉ እና ምን ማለት እንደሆነ እንዲብራራ ጭምር ጥያቄዎች ያሉ መሆኑን ተገንዝበናል፡፡

በእርግጥ በህገ-መንግስቱ መሰረት ልዩ ጥቅም ማለት ምን ማለት እንደሆነ በግልፅ የተቀመጠ ባለመሆኑ ምክንያት ሁላችንም የራሳችንን ፍላጎት በላዩ ላይ ጭነንበት በየአቅጣጫው የምንጓተተው ጉዳይ ሆኗል፡፡ ነገር ግን በተጨባጭ መሬት ላይ ካሉ ችግሮች አንፃር ሲፈተሸ ለምሳሌ፤ በአዲስ አበባ ዙሪያ የሚኖረው የኦሮሞ አርሶ አደር ከተማው ሲያድግና ሲሰፋ የአርሶ አደሩን መብት በመዋጥ ላይ የሚመሰረት ከሆነ ትክክል ስለማይሆን ከዚህ ጋር በተያያዘ የአርሶ አደሮች መብት እንዲከበር በሚደረገው ትግል ጥያቄውን ደግፎ ለመታገል የግድ ኦሮሞ መሆንን አይጠይቅም፡፡ ጥያቄው ፍትሃዊ እስከሆነ ድረስ ከአርሶ አደሩ ጎን ተሰልፎ መታገል ልባዊ ወንድማማችነትን የሚያጎለብት ከመሆኑም በላይ ሰብዓዊነት ጭምር ነው፡፡ በሌላ በኩል የአዲስ አበባ ከተማ በሁሉም አቅጣጫ ዙሪያውን ከኦሮሚያ ክልል ጋር የሚዋሰን በመሆኑ የተፈጥሮ ሃብት አስተዳደር ጉዳይን አስመልክቶ፤ አስተዳደራዊ ጉዳዮችን በህግ አግባብ ለመምራት በሚደረገው ጥረት ከኦሮሚያ ክልል ጎን ተሰልፎ የመታገልን ጉዳይ ከመርህ ውጭ በሆነ አግባብ ጭምር መንቀፍ በጋራ የምንገነባውን አገር ወደ ጎን ትቶ በየራስ ምህዋር የገመድ ጉተታ አዞሪት ውስጥ ከመግባት ውጭ ሌላ ትርፍ የሌለው መሆኑን ልብ ማለት ይገባል፡፡

በመሆኑም ትልቁ ስዕል መሆን ያለበት በሁለቱ ተያያዥ አጀንዳዎች ላይ መሆኑን ለአፍታም ቢሆን መዘንጋት የለብንም፡፡ የአማራን ሕዝብ ጥቅም በዘላቂነት ለማስጠበቅ መታገል፤ ለጠንካራ ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ ግንባታ የማይተካ ሚናችን መጫዎት ይኖርብናል፡፡ ለዚህ ተልዕኮ መሳካት በሕዝባችን ትግል እየታገዝን እየወጣን እየወረድን ነው፡፡ በዚህ ሂደት የአማራን ሕዝብ ጥቅም ለማስከበር ከሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ሃይሎች እና የሕዝብ አንቂዎች (Activists) ጋር ተናቦ እና በመተጋገዝ መስራት የአማራን ሕዝብ ፖለቲካ ወደፊት እንዲራመድ ያደርገዋል፡፡ በዚህ ወቅት የአማራ ሕዝብ አጀንዳዎችን ሊያስጥሉን ያሰፈሰፉ ዕኩይ ሃይሎች ብዙ ናቸው፡፡ የአማራ ሕዝብ በመደራጀት እና በአዲስ የትግል ምዕራፍ ውስጥም ሆኖ በየአካባቢው የተለያዩ ጥቃቶች ሰለባ በመሆን ላይ ነው፡፡ በምዕራብ እና ማዕከላዊ ጎንደር ዞኖች አካባቢዎች የማንነት ጥያቄን ሽፋን በማድረግ የገጠመን አስከፊ ጥፋት ሰሞኑን በምስራቁ የአማራ ክልል ተመሳሳይ መልክን ተላብሶ ተፈፅሟል፡፡ ይህን ችግር ለመቅረፍም መጠነ-ሰፊ ተግባራትን እያከናወንን የምንገኝ ሲሆን ችግሮቹም ቀስ በቀስ በመፈታት ላይ ናቸው፡፡ በመሆኑም ለአማራ ሕዝብ ዘላቂ ጥቅም ይህን ወቅት በአሸናፊነት ለመሻገር እርስ በእርሳችን ተጠላልፈን ከመውደቅ አጉል በሽታ ወጥተን በጋራ ክንዳችን ለሕዝባችን አጀንዳዎች መሬት መንካት በትላልቅ ስዕሎች ላይ ተመስርተን ዴሞክራሲያዊ ትግል፤ ትብብር እና አብሮነትን እንድናዳብር ለመላው ባለድርሻ አካላት ሁሉ የከበረ ጥሪያችንን እናቀርባለን!

ሚያዚያ 16 ቀን 2011 ዓ.ም

ባህር ዳር
► መረጃ ፎረም – JOIN US